
– አጠቃላይ አፈጻጸሙ 62 በመቶ ደርሷል
– መንገዱን እስከ ሰኔ 30 ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፦ የቃሊቲ – ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ግንባታ አጠቃላይ አፈጻጸም 62 በመቶ እንደደረሰ እና መንገዱን እስከ ሰኔ 30 ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ። የመንገዱ ዘጠኝ ኪሎ ሜትር የሚሆነው የግራ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ የአስፋልት ንጣፍ እንደተደረገለትም ተገልጿል።
አዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ ሰለሞን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ የቃሊቲ – ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ፕሮጀክት የመንገዱን የግራ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ አስፋልት በማልበስ እስከ ሰኔ መጨረሻ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ በሚሰራው ሥራ እስከ አሁን ዘጠኝ ኪሎ ሜትር የሚሆነው የመንገዱ ግራ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ አስፋልት ንጣፍ ማልበስ ተችሏል።
የበልግ የዝናብ ወቅት መራዘሙን ተከትሎ በፕሮጀክቱ የግንባታ ስራ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ቢሆንም፣ በቀሪዎቹ ጊዜያት የመንገዱን የግራ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ አስፋልት በማልበስ እስከ ፊታችን ሰኔ መጨረሻ ድረስ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም አቶ እያሱ ገልጸዋል። ከቃሊቲ ቀለበት አደባባይ – ቱሉ ዲምቱ የሚዘልቀው ይህ የመንገድ ፕሮጀክት 11 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 50 ሜትር የጎን ስፋት ኖሮት እየተገነባ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ እያሱ፤ አሁን ላይ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ የፊዚካል አፈፃፀም 62 ነጥብ አንድ በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።
የመንገድ ፕሮጀክቱ በገጠሙት ሁለት ዋና ዋና ችግሮች ማለትም በወሰን ማስከበር እና ከፋይናንስ ጋር በተያያዙ ችግሮች ምክንያት የመንገድ ፕሮጀክቱ የግራ ክፍል ግንባታ ለሁለት ዓመት ያህል ተጓትቶ ነበር ያሉት ኃላፊው፤ አሁን ላይ የፕሮጀክቱ ማነቆ የነበሩ ችግሮች የከተማ አስተዳደሩ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት መፍትሄ በማግኘታቸው የግንባታው ሥራ እየተፋጠነ ነው ብለዋል። አቶ እያሱ እንዳመለከቱት፤ ፕሮጀክቱ የትራፊክ ማሳለጫ ድልድዮች አሉት። ቃሊቲ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ቀለበት መንገድ አከባቢ የሚገኘውና 140 ሜትር ርዝመት ያለው ተሻጋሪ የትራፊክ ማሳለጫ ድልድይ ግንባታ ቀድሞ ቢገነባም የማጠናቀቂያ ሥራዎች እየተሰራለት ይገኛል።
በአቃቂ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል አካባቢ የሚገኘውና 70 ሜትር ርዝማኔ ያለው የማሳለጫ ድልድይ ግንባታ አብዛኛው ሥራ የተጠናቀቀ መሆኑንም ገልጸው፤ ጋሪ ድልድይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 20 ሜትር የጎን ስፋትና 50 ሜትር ርዝመት ያለው የተገጣጣሚ ድልድይ ግንባታ የተከናወነበት መሆኑን ጠቁመዋል። ፍሰቱን በተሻለ መንገድ ለማሻሻል ታስቦ ሶስት የተለያዩ ማሳለጫዎች እንዲኖሩት ተደርጎ እየተገነባ ያለው ፕሮጀክቱ፤ የግንባታ ስራው በቻይናው ኮሚኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ የሚከናወን ሲሆን፤ የማማከርና የቁጥጥር ስራው ደግሞ በኢንጂነር ዘውዴ እስክንድር አማካሪ ኩባንያ እየተከናወነ ያለ ፕሮጀክት ነው።
የቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ፕሮጀክት በ2009 ዓ.ም በ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ተጀምሮ በ2012 ዓ.ም ተጠናቆ ወደ አገልግሎት እንዲገባ ቢታቀድም፤ ፕሮጀክቱ ለሶስት ዓመት በመጓተቱ የአካባቢው ህብረተሰብ ቅሬታ ሲያቀርብ ነበር። በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅሬታውን ምላሽ እንዲያገኝ በዘንድሮ በጀት ዓመት ተጨማሪ የሁለት ቢሊዮን ብር ድጎማ አድርጎ ፕሮጀክቱ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ አቅጣጫ ማስቀመጡ ይታወሳል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም