ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ? ሳምንቱ እንዴት ነበር፤ መቼም እንደተለመደው ይህንንም ሳምንት በትምህርት እንዳሳለፋችሁ እርግጠኛ ነኝ:: ጎበዝ ተማሪ የዘወትር ተግባሩ ትምህርቱን በትኩረት መከታተልና የተማረውንም እንዳይደራረብበት ከስር ከስር ማንበብ ነው:: ይህንን በአግባቡ የሚተገብር ልጅ ደግሞ ሁሌ ስኬታማ ነው:: ልጆች እንደሚታወቀው የትምህርት ማጠናቀቂያ ጊዜ ጥቂት ወራት ብቻ ቀርተውታል፤ ስለዚህ ትምህርታችሁን ትኩረት ሰጥታችሁ መማርና ለፈተና መዘጋጀት አለባችሁ:: እናንተም ይህንን ተገንዝባችሁ ቅድመ ዝግጅታችሁን ማጧጧፍ አለባችሁ:: በእርግጠኝነት ሥራችሁን ጀምራችኋል ብዬ አስባለሁ::
ልጆች የዚህ ሳምንት እትማችን ለእናንተ ሳይሆን ለወላጆቻችሁ የተዘጋጀ ነው:: ወላጆቻችሁ ይህንን ፅሁፍ ካነበቡ በኋላ ለእናንተ የሚያደርጉላችሁ በርካታ ነገሮች ይኖራቸዋል:: ስለዚህ ወላጆቻችሁ እንዲያነቡት ጋብዟቸው እሺ?
ልጆች በተፈጥሮ ረጅም ንግግር የማይወዱና በነገሮች መደጋገም የሚሰለቹ ናቸው:: ከመጫወቻ እቃዎቻቸው ጀምሮ ሁሌ አዳዲስ ነገሮችን ይፈልጋሉ:: ብዙ ጊዜ ልጆች ነገሮችን በተግባር ሞክረው ጥቅምና ጉዳቱን ማወቅ ይፈልጋሉ:: በመሆኑም የተከለከሉትን ነክተው የሚያስከትለውን ውጤት ለማወቅ ሲሞክሩ ማስተዋል የተለመደ ነው::
ብዙ ጊዜ ወላጆች ‹‹ልጆቻችን የምንነጋራቸውን ነገር አይሰሙንም፤ እያወራናቸው አያዳምጡንም›› ሲሉ ይሰማሉ:: ለብዙ ወላጆችና አሳዳጊዎች በልጆቻቸው አለመስማትና ትዕዛዛቸውን አለመፈጸም የተለመደና ትልቁ የዕለት ተዕለት ተግዳሮት ነው። ታዲያ ልጆች ለምን አይሰሙንም? ለምን አይታዘዙንም? በምንናገራቸው ጊዜ የመሰላቸት ስሜት ለምን ፊታቸው ላይ ይነበባል? የሚሉ ጥያቄዎች በአዕምሯቸው ማብሰልሰላቸው የማይቀር ነው::
ልጆች በትንሽ ነገር የሚሰለቻቹ እንደመሆኑ መጠን ስንናገራቸው ንግግሮቻችንን በትኩረት እንዳይሰሙ ሊያደርጓቸው የሚችሉ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ:: በዚህ ሳምንት እትማችን እነዚህን ምክንያቶች እንመለከታለን::
የመጀመሪያው ልጆችን በምንናገራቸው ሰዓት ረጅምና አሰልቺ ገለጻ ማድረግ ሲሆን፤ እኛን የማዳመጥ ትግስት ያሳጣቸዋል:: እነሱን እንደማናዳምጥና ረጅም ገለፃ በማድረግ የራሳችን ብቻ ሃሳብ ብቻ የምናንጸባርቅ መሆኑን ካሰቡ ፈጽሞ እኛን አይሰመንም:: በመሆኑም ልጆችን በምናናግርበት ወቅት የራሳችንን ሃሳብና ፍላጎት ከማንፀባረቅ ይልቅ ስለጉዳዩ እነሱም ያላቸውን ሃሳብ ከግምት በማስገባት ሃሳባቸውን እንዲናገሩ ማድረግ ያስፈልጋል::
ልጆችን በምንናገርበት ወቅት ንግግራችንን የምንጀምርባቸው ቃላት እጅግ ወሳኝ ናቸው:: ልጆች የማይወዷቸውን ቃላት መጠቀም ንግግራችን ላይ ፍላጎት እንዲያጡ ያደርጋቸዋል:: አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች አሉታዊ በሆኑ ቃላቶች ፤ ለአብነት “አይሆንም፣ አታድርግ፣ አትችልም” በሚሉ ቃላት መናገር ከጀመሩ ልጆች እነዚህ ቃላት የወቀሳና የክስ ስለሚሆንባቸው ወላጆቻቸውን ከጅምሩ እንዳይሰሙ ያደርጋቸዋል።
ብዙ ጊዜ ልጆችን የምናናግራቸው በጩኸትና የአለቅነት መንፈስ ባለው ስሜት ከሆነ ልጆች ሁልጊዜ ንግግራችንን በጩኸት ካላደረግነው በስተቀር ያለመስማትና ያለመታዘዝ ልምድን ያዳብራሉ:: በመሆኑም ልጆችን በምናናግርበት ወቅት ትግስትና እርጋታ በተሞላበት መንገድ መሆን አለበት::
ልጆችን በምናናግርበት ወቅት ትኩረታቸው ሌላ ነገር ላይ አለመሆኑን ማስተዋል ሌላኛው ምክንያት ነው:: ልጆች ትኩረታቸው ሌሎች ነገሮች ላይ ከሆነ እኛን የማዳመጥ እና ለንግግራችን ቦታ የመስጠት እድላቸው አነስተኛ ነው:: ልጆች እየተጫወቱ ወይም ቴሌቪዥን እያዩ ከሆነ ትኩረታቸውን ማግኘት ስለሚከብድ በዚህ ወቅት ልጆችን ከማናገር ይልቅ ትኩረታቸውን ስቦ ለምንናገረው ነገር ቦታ ሰጥተው እንዲያዳምጡን ማድረግ ይመከራል።
ልጆች አይሰሙንም ብለን በምናስብበት ወቅት መጮህና መቆጣት ሌላኛው እንዳይሰሙን የምናደርግበት ምክንያት ነው:: ስለሆነም ከመናደድና ከመቆጣት ይልቅ ሰከን ብለን በፍቅርና በተረጋጋ መንፈስ ብናናግሯቸው የተሻለ ሊሰሙንና ሊያዳምጡን ይችላሉ። ልጆች ሁሌም ወላጆቻቸውን ይመስላሉ፤ ሁልጊዜም ወላጆቻቸውን አርአያ አድርገው ያድጋሉ:: በሕይወታቸው ውስጥ የሚያውቁትና ትልቁን ቦታ የሚሰጡት ለወላጆቻቸው በመሆኑ ወላጆቻቸው የሚያደርጓቸውን ነገሮች ደግመው ለማድረግ ይሞክራሉ:: ስለዚህ ልጆችን ራሳችን ጥሩ አድማጭ ሆነን ካላስተማርናቸው ንግግሮቻችንን በትኩረት ሊያደምጡ አይችሉም::
ልጆች ላለመስማት ከመረጡ ንግግራችንን ላይሰ ይችላሉ:: ብዙ ጊዜ የወላጆቻቸውን ትኩረት ፈልገው ግን ትኩረት ማግኘት ካልቻሉ፤ ወላጆች ያልተረዱላቸውና በዚህም ምክንያት ሊፈታላቸው ያልቻለ ችግር ካለ፤ እንዲሁም ወላጅን ያለማክበር ችግር ያለባቸው ልጆች ለወላጆቻቸው ንግግር ትኩረት የመስጠትም ሆነ የመስማት ፍላጎት ላይኖራቸው ይችላል:: በመሆኑም ልጆች እንዳይሰሙን ያደረጋቸውና ያልተረዳንላቸው ችግር ምንድነው ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንዲሁም ልጆችን በግልፅ በማወያየት ችግራቸውን መፍታት ተገቢ ነው::
ሌላው ምክንያት ደግሞ ከጤና እክል ጋር ተያያዥነት ያላቸው ችግሮች ሊሆኑ ይችላሉ:: ስለዚህም ከመቆጣትና ወደ እርምጃ ከመግባታችን በፊት መከታተል ይኖርብናል:: አንዳንድ ልጆች በጤና ችግር ምክንያት የመስማት ችግር ሊኖርባቸው ይችላል። ይህን መከታተልና በተለይ በህጻንነት ወቅት የሀኪም እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው::
በለጥሻቸው ልዑልሰገድ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2015