እነሆ ግንቦት ከገባበት የመጀመሪያው ሳምንት ጀምሮ እስከ መጨረሻው ሳምንት ድረስ ሳምንቱን በታሪክ ስናስታውስ የደርግ እና የኢህአዴግ ታሪክ ሳይለየን ግንቦት ሊያልቅ ነው:: የሚገርመው ደግሞ አንድ ክስተት በተከሰተ ልክ በሳምንቱ(ዓመተ ምህረቱ ቢለይም) ሌላኛው የሚከሰት መሆኑ ነው::
ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም በደርግ ላይ የተደረገው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ፣ ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከአገር የወጡበት ቀን፣ በሳምንቱ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ኢህአዴግ አዲስ አበባን የተቆጣጠረበት፣ አሁንም በሳምንቱ ግንቦት 27 ቀን 1983 ዓ.ም አዲስ አበባ በፍንዳታ የተናወጠችበት ነበር::
ሁሉንም በሳምንታቸው ስላየናቸው ዛሬ የግንቦት 27ቱን የአዲስ አበባውን ፍንዳታ ክስተቶች እናስታውሳለን::
የደርግ መንግሥት ተወግዶ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ ልክ ከአንድ ሳምንት በኋላ አዲስ አበባ ለሰዓታት በዘለቀ ከባድ ፍንዳታ ተናወጠች:: የተለያዩ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ክስተቱን የዘገቡትና የዓይን እማኞችን አስተያየት እየሰበሰቡ ሰፊ ሐተታ ቢሰጡበትም ትክክለኛ ምክንያቱ ግን እስከ አሁን አልታወቀም::
በደርግና በኢህአዴግ ግብግብ ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ የነበረችው አዲስ አበባ፤ ደርግ ተወግዶ ኢህአዴግ አገረ ገዥነቱን ሲቆጣጠር አዲስ አበባ ከጥይት ድምጽ ፋታ አግኝታ ነበር:: ግንቦት 27 ቀን 1983 ዓ.ም ሌሊት 10፡00 አካባቢ ግን ከተማዋን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያደበላለቀ ፍንዳታ ተሰማ:: ከ100 ሰዎች በላይ እንደሞቱ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጭምር ተዘግቧል::
ፍንዳታው የተከሰተው በቅሎ ቤት በሚገኘው የደርግ ወታደራዊ ሎጂስቲክስ ማከማቻ ወይም በተለምዶ ‹‹ጥይት ቤት›› በሚባለው ነው:: እስከ ሰሜን ማዘጋጃ ድረስ ተሰምቶ ግርግርና ድንጋጤ ተፈጥሮ ነበር::
ቢቢሲ እንደዘገበው፤ በዚያ ሰሞን ከሁለት ሳምንት ጀምሮ ትምህርት ተዘግቶ ነበር። ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከአገር ‹‹ኮበለሉ›› ተብሎ ሲነገር ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ከየትምህርት ቤቱ እየሰበሰቡ ወደቤት አስገቡ:: በዚህ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ትምህርት በዚህ ፍንዳታ እንደገና ሌላ ሥጋት ተፈጥሮ ተስተጓጉሎ ነበር::
ለቢቢሲ አስተያየቷን የሰጠች አንዲት የአዲስ አበባ ነዋሪ ክስተቱን እንዲህ ገልጻዋለች:: ‹‹…ፍንዳታው ሲሰማ ሁሉም ሰው ተነሳ፤ ነገር ግን ግራ በገባው ስሜት ውስጥ ነበር። ጦርነት ነው እንዳንል ጦርነቱ አልቋል.:: ምን እንበለው? እየቆየ ሲመጣ የጥይት የሚመስሉ ትንንሽ ፍንዳታዎች መስማት ጀመርን›› ትላለች::
ፍንዳታው እንደተከሰተ ሰዎች እግራቸው ወደመራቸው በአራቱም የከተማዋ አቅጣጫ መትመም ያዙ። ጉዞው በእግር ስለሆነ ለሁለት ሰዓት ያህል የተጓዙ ነበሩ:: ፍንዳታው የተከሰተበት ቦታ ላይ ደግሞ የሚቀጣጠል ነገር እና ከፍተኛ ጭስ ነበር::
በወቅቱ በፍንዳታው ምክንያት ከ100 በላይ ሰዎች መሞታቸው በመገናኛ ብዙኃን ተነገረ። የቆሰሉም በርካታ ነበሩ። ያኔ የነበረው ጊዜያዊ አስተዳደር(ኢህአዴግ) ጣቱን በደርግ ሰዎች ላይ ቀሰረ። ማከማቻውን ሆን ብለው ያፈነዱት የደርግ ርዝራዦች ናቸው አለ። የወቅቱ መንግሥት ኢህአዴግ ይህንን ቢልም ራሱ ኢህአዴግ ነው ያፈነዳው የሚሉ አስተያየቶችም በሰፊው ሲሰራጩ ነበር::
የፍንዳታውን ክስተት ለመዘገብና ፎቶ ለማንሳት በቦታው የነበሩ የውጭ አገር ጋዜጠኞች ከሞት እስከ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል::
በነገራችን ላይ በዚያው ሳምንት (ከበቅሎ ቤቱ ቀደም ብሎ) ሸጎሌ አካባቢም ተመሳሳይ ፍንዳታ ተከስቶ እንደነበር በታሪክ ይታወሳል:: እነዚህ የፍንዳታና የጦርነት ታሪኮች የደርግና የኢህአዴግ የግንቦት ወር ታሪኮቻቸው ናቸው:: ዋና ዋናዎቹ የደርግ እና የኢህአዴግ ታሪካዊ ክስተቶችም በዚህ ያበቃሉ::
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27 ቀን 2015 ዓ.ም