
አትዮጵያ ዛፍ ናት። ለብዙዎች መኖሪያ፣ መጠጊያና መጠለያ የሆነች! ለአብራኳ ክፋዮች ብቻ ሳይሆን ቀን ለከፋባቸውና ተቸግረው በአገራቸው መኖር ላልቻሉም አስተማማኝ መጠለያ! በውስጧ የሰፈሩ ህዝቦቿም የህብረ ቀለማዊ ውበት ነጸብራቅ ናቸው። የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባህሎችና ሃይማኖቶች ያሏቸው ህዝቦች ናቸውና። ስለሆነም ኢትዮጵያን ብዙ ዓይነት ቀለማት ባላቸውና ውበታቸው የሚስብ ወፎች በሰፈሩበት ዛፍ መመሰል እንችላለን።
እኒህ ህብረ ብሄር ህዝቦቿ ጌጦቿ ስለሆኑና አቃፊነት ባህሪዋ ስለሆነም ጠበበኝ ተቸገርኩ ሳትል ሁሉን በፍቅር አቅፋ ትገኛለች። አንተ እንዲህ አንተ ደግሞ እንዲያ ሳትል ልዩነታችሁ ውበቴ ነው። ደምቄ የምታየውም በእናንተ ህብረ ብሄራዊነት ነው ብላ ሁሉን በፍቅር እያስተናገደች ነው።ከተፋቀራችሁና በሚገባ ከተጠቀማችሁበት በማህጸኔ ያለው ሀብት እንኳን ለእናንተ ለዓለምም ይተርፋልም በምትል እናትም ትመሰላላች – አገራችን ኢትዮጵያ!
ህብረ ብሄራዊ ልጆቿም በተለያየ ቋንቋ፣ ባህልና እምነት ደምቀው አንዳቸው ለአንዳቸው መጠጊያና ከለላ እየሆኑና ሉዓላዊነቷን የሚጋፋ ወራሪ በመጣም ጊዜ ደማቸውን በጋራ እያፈሰሱ ብሎም መተኪያ የሌለው ህይወታቸውን እየገበሩ ነጻነቷን አስጠብቀው በፍቅር እየኖሩባት ይገኛሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የህዝቦቿ ፍቅርና የአገሪቱ ሰላም መሆን እንቅልፍ የነሳቸው የእኩይ ተግባራት ፈጻሚዎች የተለያዩ የሀሰት አጀንዳዎችን እየፈበረኩ ብሄርን ከብሄርና ህዘብን ከህዝብ ለማጋጨት ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም ማለት ይቻላል። አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉትም በኢትዮጵያውያኑ ጨዋነትና አብሮነት ከሸፈ እንጂ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲፈጸም ያልተሞከረ ዘዴ የለም። ይሁንና በክፉውም በደጉም ለሺህ ዓመታት ተዛምዶና ተዋዶ የኖረውን ጨዋውን የአገራችን ህዘብ ለዚህ እኩይ ዓላማቸው ሊያሰልፉት አልቻሉም።
ይሁንና በሀሰት በተፈበረኩ መረጃዎች ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት ሙከራዎች ተደርገው በርካቶች ህይወታቸውን እንዲያጡ ንብረት እንዲወድምና ዜጎች እንዲፈናቀሉ ሆኗል። ዓላማ ለሌለው ጉዳይ በዜጎች ላይ ይህን መሰሉ ሰቆቃ መድረሱ በጣም ከማመሙም በላይ ዳግም ተከስቶ ልናየውና ልንሰማው የማይገባ ጉዳይ ነው።
የተደገሰው የጥፋት ድግስ በህዝባችን አርቆ አስተዋይነትና ጨዋነት በዚሁ ከሸፈ እንጂ የተደገሰው የጥፋት ድግስ ጦስ ቀላል አልነበረም። ህዝባችን በችግሩ ወቅትም ተጠቂ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋሻና ከለላ በመሆን የአጥፊዎችን ሴራ አክሽፏል። ይህንን በማድረግም ኢትዮጵያውያን የተጋመዱበት የአንድነት ገመድ በቀላሉ የማይላላና የማይበጠስ መሆኑን ለማስመስከር ችሏል።
ህዝባችንን እርስ በእርስ ለማባላት የጥፋት ሃይሎች እንቅልፍ አጥተው በሚሰሩበት በዚህ ወቅት በተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መካከል መተማመን ለመፍጠርና አብሮነትን ለማጽናት ታስበው እየተካሄዱ ያሉ የህዝብ ለህዝብ መድረኮች ተስፋን የሚያጭሩና ይበል የሚሰኙ ናቸው።
በአማራና ኦሮሞ፣ በአማራና ትግራይ፣ በኦሮሞና ቤኒሻንጉል፣ በኦሮሞና ሶማሌ እንዲሁም በአፋርና በአማራ ወዘተ የተካሄዱ ህዝብ ለህዝብ መድረኮች ህዝባችን ምን ያህል አርቆ አሳቢ እንደሆነ፣ በእኩይ ዓላማ አስፈጻሚዎች እንጂ በህዝቡ መካከል ቅራኔና ቂም እንደሌለና አንዱ ህዝብ ለሌላኛው ከለላው እንጂ አጥፊው እንዳልሆነ በግልጽ ታይቷል።
በእንባ ጭምር ታጅበው በየመድረኩ ከህዝብ የሚሰነዘሩ አስተያየቶች አጅግ የሚያኮሩና ህዝባችን ያስተሳሰረው የአንድነት ገመድ በቀላሉ የማይበጠስ መሆኑን ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ ናቸው።
በእነዚህ መድረኮች ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የተፈበረኩ የውሸት ትርክቶችን ማጋለጥ እየተቻለ ነው። አንዱ ህዝብ ለሌላው ህዝብ ያለውን ፍቅርና አክብሮት እንዲገልጽም ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።
መድረኮቹ በስብሰባ ብቻ ሳይታጠሩ በቀጣይ የሚተገበሩ አቅጣጫዎች እየተቀመጡላቸው መሆኑም ፍሬያማነታቸውን ያተልቀዋል። ከመድረኮቹ በኋላም የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው በመመለስ የታዩ ተጨባጭ ተግባራት ለአገራችን መረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
እስካሁን የተካሄዱት መድረኮች ፍሬያማ ቢሆኑም በአገራችን አሁን ካለው ተጨባጭ ችግር አንጻር ሲመዘኑ ግን ገና ብዙ ስራ እንደሚቀር መረሳት የለበትም። ትልቋ ስዕል ኢትዮጵያ ናትና መድረኮቹ መላውን የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚያዳርሱና በመጨረሻም የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ መድረክ እስከማዘጋጀት ድረስ የሚዘልቁ መሆን ይኖርባቸዋል። ይህን ማድረጉ ደግሞ ጥፋታችንን ለሚሹ አካላት ክስረት የሀገራችንን ሰላም፣ ዕድገትና ብልጽግና ለምንናፍቅ ለእኛ ደግሞ ትልቅ ድል ይሆናል!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 26/2011