መንግሥት የአገርን ኢኮኖሚ እየጎዳ ያለውን የኮንትሮባንድ ንግድ ለመቆጣጠር እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል:: የጉሙሩክ ኮሚሽን እና የተለያዩ ቅርንጫፎቹን ዋቢ ያደረጉ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ብዙ ሚሊየን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ ሸቀጦች በቁጥጥር ስር ስለመዋላቸው እየዘገቡ ናቸው:: ኮሚሽኑ ባካሄዳቸው የተለያዩ መድረኮችም ችግሩን ለመቆጣጠር በተከናወኑ ተግባሮች ብዙ ቢሊየን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ ሸቀጦች መያዛቸውን ጠቁሟል፤ ተቋሙ በእዚህ በኩል ስኬታማ ተግባር እያከናወነ መሆኑን ገልጾ፣ የችግሩን አሳሳቢነትም እያመለከተ ይገኛል::
ከፍተኛ የፌዴራል መንግስትና የክልል የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በሸራተን አዲስ ባለፈው መጋቢት ወር በኢንቨስትመንትና ኮንትሮባንድ ንግድን አስመልክቶ ባተኮረ መድረክ ላይ እንደተጠቆመው፤ በ2015 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ብቻ ከ52 ቢሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸውን የኮንትሮባንድ ሸቀጦች በጉሙሩክ ኮሚሽን በቁጥጥር ስር ውለዋል:: በመድረኩ ላይ የኮንትሮባንድ ንግድ እየጨመረ መምጣቱን የተገለፀ ሲሆን፣ በስድስት ወራቱ የታየው የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በጣም አስደንጋጭ መሆኑም ተመልክቷል:: በሌላ መረጃ በበጀት ዓመቱ ሰባት ወራት 53 ቢሊየን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ ሸቀጦች በቁጥጥር ስር ውለዋል::
የጉሙሩክ ባለስልጣን የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴውን ለመቆጣጠር ያግዛል ያለውን እርምጃ መውሰዱን ቀጥሏል:: ለእዚህ ስራ ለሶስት ወራት ያሰለጠናቸውን ፖሊሶች በደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሌጅ ማስመረቁን ሰሞኑን የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል::
በአገሪቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለደረሰው የኮንትሮባንድ ንግድ ያነጋገርናቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ሞላ አለማየሁ፤ ችግሩ ስር የሰደደና ፈርጀ ብዙ እንደሆነ ይገልጻሉ፤ የኮንትሮባንድ ንግድ የአገርን ኢኮኖሚ በማቀጨጭ ረገድ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰው፣ ህጋዊነትን በማቀጨጭ ህገወጥነትን እንደሚበረታታም ያስገነዝባሉ::
የኮንትሮባንድ ንግድ አገር ከምታጣው ገቢ ባለፈም በማህበረሰቡ ጤና ላይ የሚያስከትለው ችግር ዘርፈ ብዙ ነው የሚሉት ዶክተር ሞላ፣ በኮንትሮባንድ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት የጎንዮሽ ጉዳታቸው ያልታወቀ ምርቶች በሰዎች ሕይወት ላይ የሚያስከትሉት አደጋ ፈርጀ ብዙና ቀላል ግምት የሚሰጠው አለመሆኑን ይናገራሉ::
በርካታ አገራት የኮንትሮባንድ ንግድን በጽኑ እንደሚታገሉ ዶክተር ሞላ አመለክተው፣ በታዳጊ አገራት ከምርቶች ዋጋ መቀነስ ጋር ተያይዞ በስፋት የሚስተዋለው ጥራታቸው ያልተረጋገጠና መግለጫ የሌላቸው ምርቶች ወደ አገር ውስጥ በብዛት መግባታቸው መሆኑን ያመለክታሉ:: ይህም ፈርጀ ብዙ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ እንደሚያስከትል አስታውቀው፣ ፈርጀ ብዙ መፍትሔ የሚያሻው እንደሆነ ነው ያስታወቁት::
ኮንትሮባንድ ባደጉ አገራት አገርን የመክዳት ያህል ወንጀል ተደርጎ እንደሚወሰድም ዶክተር ሞላ ይጠቁማሉ:: በኮንትሮባንድ ንግድ የተሳተፈ ሰው ህጉ በቀጥታ ተግባራዊ እንደሚደረግበትና ካፒታሉ ሙሉ ለሙሉ እንደሚወረስ ነው ያመለከቱት:: ይህን እያየ ደፍሮ ወደ ኮንትሮባንድ የሚገባ እንደማይኖርም ገልጸዋል::
‹‹እኛ አገርም ጠንካራ ህግ ማውጣትና ህጉን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል›› ያሉት ዶክተር ሞላ፣ በኮንትሮባንድና በህገወጥ ንግድ የሚጠቀመው ጤናማ መንገድን የሚከተለው ሳይሆን፣ ህገወጡ ነው ይላሉ:: ጠንካራ ህግ ማውጣትና ህጉን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ህግ አውጭው ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበትም አመላክተዋል::
እንደ ዶክተር ሞላ ገለጻ፤ በመንግሥት በኩል የሚታየው ወይም የሚወሰደው እርምጃ የዘመቻ አይነት ነው፤ ይህም ውስንነት ያለው አካሄድና ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት የሚችል አይደለም:: ‹‹በአንድ ሰሞን የዘመቻ ሥራ ለተወሰነ ጊዜ ችግሩን መከላከል ይቻል ይሆናል እንጂ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት አይቻልም:: ዘመቻው ሲቆም ችግሩ መልሶ ያብባል:: ችግሩን በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው በቀጥታና መደበኛ በሆነ መንገድ በዕቅድ ሲሠራ ነው::
ችግሩን በተለያየ መንገድ መታገል እንደሚያስፈልግ ዶክተር ሞላ ገልጸው፣ ከመንግሥት መስሪያ ቤቶች በተጨማሪ በማህበረሰቡ ዘንድም ኮንትሮባንድን ለመከላከል ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ይገልጻሉ:: በተለይም ለማህበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር፣ የኮንትሮባንድ ህገወጥ ንግድ በማህበረሰብ ጤና እንዲሁም በአገር ኢኮኖሚ ላይ ምን ጉዳት ያስከትላል የሚለውን እንዲሁም በህግ የበላይነት ረገድ የሚኖረው ድርሻ ምን እንደሆነ ማኅበረሰቡ ማወቅና መረዳት ይገባዋል ሲሉ ያብራራሉ:: ይህንንም በመደበኛ ሥራ በዕቅድ ይዞ ማስፈጸም የሚችል ቁርጠኛ የሆነ የመንግሥት አካል እንደሚያስፈልግ ነው የጠቆሙት:: ‹‹አሁን ላይ እንዲህ አይነት ሥራ የሚሠራ የመንግሥት አካል አለ ማለት አያስደፍርም›› ያሉት ዶክተር ሞላ፤ እዚህ ላይ ሰፊ ሥራ መሥራት የግድ እንደሆነም ገልጸዋል::
በአንድ ሰሞን የዘመቻ ሥራ ብቻ ስር የሰደደውን የኮንትሮባንድ ንግድ መከላከል እንደማይቻልም ነው ያስገነዘቡት:: በተለይም በረጅም ጊዜ ዕቅድ የህብረተሰቡን ንቃተ ህሊና ማሳደግ አንዱ መፍትሔ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ከወንጀል ጋር ተያይዞ ያለውን አንድምታ፣ በገቢ ረገድ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ አጠቃላይ የአገር ኢኮኖሚን በማቀጨጭ ረገድ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ በማስረዳት በኮንትሮባንድ ንግድ መሳተፍ አገርን የመክዳት ያህል እንደሆነ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል::
በመጀመሪያ ደረጃ የማህበረሰቡን ንቃተ ህሊና ለማሳደግ ምንም የተሠራ ሥራ እንደሌለ ጠቅሰው፣ ይህን ታሳቢ በማድረግ ከዜሮ በመነሳት ብዙ ሥራ መሥራት አንዱ የመፍትሔ አቅጣጫ እንደሆነ ያመለክታሉ::
የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት የቻለው መንግሥት የሚወስደው እርምጃ ከችግሩ ስፋት ጋር ተመጣጣኝ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ነው ሲሉ ዶክተር ሞላ ይጠቁማሉ:: የመንግሥት አካላት ራሳቸውን ከችግሩ ነጻ አውጥተው ተመጣጣኝ እርምጃ መውሰድ አልቻሉም ብለው እንደሚያምኑ ነው ዶከተር ሞላ የተናገሩት::
ይህን ማድረግ ቢቻል የኮንትሮባንድ ንግዱ ለህገወጦቹ አዋጭ አይሆንም ነበር፤ አዋጭ ባይሆን ኖሮ ደግሞ ብዙ ሰዎች ተሳታፊ አይሆኑም ነበር፤ ከዚህም ባለፈ ችግሩ በተወሰኑ ጊዜያት ብቻ የሚታይ ይሆን ነበር ሲሉም ያብራራሉ:: አሁን የኮንትሮባንድ ንግዱ ኢኮኖሚውን እየፈተነው መሆኑን ጠቅሰዋል::
ተመጣጣኝ እርምጃ አለመወሰዱ ችግሩ ስር እንዲሰድ ያደረገው መሆኑንም ነው የሚናገሩት:: መንግስት ተመጣጣኝ እርምጃ ካለመውሰዱም ባለፈ ቁርጠኛ አለመሆኑን ያነሱት ዶክተር ሞላ፤ መንግሥት ጥራት ያለው መረጃ ሰብስቦ ትክክለኛ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ያመለክታሉ:: በተለይም በዘመቻም ይሁን በሌሎች መንገዶች ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር የተዘረጉ አሰራሮች ለምን ውጤት ማምጣት እንዳልቻሉ በገለልተኛ አካል አጥንቶ መለየት እንደሚገባ አመልክተው፣ ከዚህ በመነሳት ወደ ሌሎች መፍትሔዎች መግባት እንደሚገባም አስገንዝበዋል::
የኮንትሮባንድ ንግድ በተለይ በታዳጊ አገራት ላይ የበረታ መሆኑን ዶክተር ሞላ ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኮንትሮባንድ ንግድ ካደጉ አገራት የተለየ መሆኑንም ይጠቁማሉ:: ለዚህም አንዱ ምክንያት ህጉ አስቀድሞ በህግ አውጪው መጣሱ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ:: ዘላቂና የማያዳግም መፍትሔ ለማምጣት ከላይ ያለው የመንግሥት አካል ኮንትሮባንድን በመከላከል ላይ ቁርጠኛ ሊሆን እንደሚገባ ያስገነዝባሉ::
ሥራ ላይ የዋሉ ህጎች መመሪያዎችና ደንቦች ለምንድነው ውጤታማ መሆን ያልቻሉት የሚለውን በሚገባ መፈተሽ እንደሚገባም ዶክተር ሞላ ያመለክታሉ:: በዚህም በኩል ግልጽ የሆነ አቋም መውሰድ ከመንግሥት እንደሚጠበቅም ነው ያስታወቁት:: መንግሥት እስከ አሁን እንደሚያደርገው የዘመቻ በሚመስል የአንድ ወቀት እንቅስቃሴ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል መረዳት እንዳለበት አስታውቀው፣ ይህን አይነቱ አሰራር ዘላቂ መፍትሄ እንደማያመጣ ተናግረዋል::
የዶክተር ሞላን ሃሳብ የሚያጠናክር ሀሳብ የሰጡት ሌላው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አቶ ወሰንሰገድ አሰፋ፤ የኮንትሮባንድ ንግድ ዘርፈ ብዙ የሆኑ ችግሮችን ይዞ እንደሚመጣ ይገልጻሉ:: እንደ እሳቸው ገለፃ፤ አንደኛ መንግሥትን የታክስ ገቢ ያሳጣል:: መንግሥትን ታክስ ካሳጣው ደግሞ መሠረታዊ አቅርቦቶችን ለማህበረሰብ ማቅረብ አይችልም፤ ከዚህም ባለፈ መንግሥት እንደ መንግሥት እንዳይቀጥል ሊያደርገው ይችላል:: ሁለተኛው የኮንትሮባንድ ንግድን የሚጠቀሙ ስግብግብ ነጋዴዎች አብዛኛውን ጊዜ ጥራታቸው ያልተረጋገጠ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዲያስገቡ መንገድ ይከፍታል::
በኮንትሮባንድ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ጥራታቸው ያልተረጋገጠ መድኃኒቶችና ምግቦች ከፍተኛ የጤና ቀውስ የሚያስከትሉ መሆናቸውን አቶ ወሰንሰገድ ተናግረው፣ ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢና መንግሥትን ታክስ ከማሳጣትም በላይ እንደሆነ አስረድተዋል::
በኮንትሮባንድ የሚገቡ የህጻናት ወተትና የታሸጉ ምግቦች ጊዜ ያለፈባቸውና በሥነሥርዓት ያልተመረቱ እንደሆኑም ጠቅሰው፣ የሚያስከትሉት የጤና ጉዳት፤ ማህበረሰቡ ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪ ዞሮ ዞሮ ጫናው መንግሥት ላይ እንደሚያርፍና ጉዳዩ ለአገር ራስ ምታት ሆኖ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል::
‹‹ኮንትሮባንዲስቶች የጦር መሳሪያ በማምጣት ሰዎችን የሚጎዱ፣ ጊዜያቸው ያለፈ መድኃኒቶችና የምግቦች ሕገወጥ ነጋዴዎች በርካሽ አምጥተው በማከፋፈል ገንዘብ ለማትረፍ በሚያደርጉት ጥረት የህብረተሰቡ ጤና በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳል›› ያሉት አቶ ወሰንሰገድ፤ ይህ ደግሞ ኮንትሮባንድ የሚያስከትለው አደጋ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ብለዋል::
በኮንትሮባንድ ንግዱ ላይ የሚሳተፉ አካላት ሕገወጥ ነጋዴዎችና ግለሰቦች ብቻ አለመሆናቸውን አቶ ወሰንሰገድ ይጠቁማሉ:: የኮንትሮባንድ ንግድ በአንዳንድ የጉምሩክ ሠራተኞች እና ድንበር ጠባቂዎች ዋና የገቢ ምንጭ ተደርጎ ሊታይ እንደሚችልም ተናግረው፣ ይህ ሁኔታ ለህገወጥ ነጋዴዎች ሕገወጥ ንግዱን እንደሚያቀልላቸው ነው የገለጹት:: የመንግሥት ባለስልጣናት ጭምር በየድንበሩ በኮንትሮባንድ ንግድ ላይ ከህገወጦች ጋር አብረው የሚሰሩበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም ነው ያመለከቱት::
ሁልጊዜ በድንበር አካባቢ የሚሰሩ ሰዎች ተመሳሳይ ከሆኑ የመግባባትና የጥቅም ትስስር ስለሚፈጠር የኮንትሮባንድ ንግዱ እንዲባባስ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ:: ለእዚህም ድንበር ላይ የሚሠሩ ሰራተኞችን ቶሎ ቶሎ መቀያየር እንደሚገባም ያስገነዝባሉ::
‹‹ሌብነትን የሚጠየፍ ባህል መፍጠር ያስፈልጋል›› ያሉት አቶ ወሰንሰገድ፤ ከመንግሥት ባለስልጣናት አንስቶ እስከ ትምህርት ቤት ድረስ ባለው መዋቅር ሌብነትን የሚጠየፍ ትውልድ መፍጠር አስፈላጊና ተገቢ እንደሆነም አመላክተዋል::
የኮንትሮባንድ ንግዱ በ2015 በጀት አመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የወጪ ንግድ አፈጻጸም ላይም አሉታዊ ተጽእኖ ማሳረፉን አንድ መረጃ ጠቁሟል:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡትን የ2015 በጀት አመት የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ተከትሎ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት የተናገሩትም የኮንትሮባንድ ንግዱን አሳሳቢነት ያረጋገጠ ነው::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በወጪ ንግዱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳረፈ እንደሚገኝ ገልጸው፣ የዘንድሮው የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ትንሽ ዝቅ ማለቱን መናገራቸው ይታወሳል:: ዘንድሮ ለውጭ ገበያ ከቀረበው ወርቅና ጫት የተገኘው ገቢ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በጣም ዝቅ ማለቱን ጠቅሰው፣ የዚህ ምክንያቱ አሻጥርና ኮንትሮባንድ መሆናቸውም በወቅቱ ተናግረዋል::
ይህንን በኮንትሮባንድ ንግዱ እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመከላከል አብዛኛው ኃይላችን አሁን ሀብት ባለባቸውና ሽፍታ በበዛባቸው አካባቢዎች እንዲሰፍር ተደርጓል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ፖሊስ ቀዳሚ ተግባር ኮንትሮባንድን መዋጋት በኮንትሮባንድ የሚመዘበረውን የኢትዮጵያን ሀብት መከላከል ይሆናል ሲሉ ማስታወቃቸው ይታወሳል::
የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴውን ለመቆጣጠር በመንግስት በኩል እየተከናወነ ያለው ተግባር ምን ያህል ስለመሆኑ በጉሙሩክ ኮሚሽን በቁጥጥር ስር እየዋለ ያለው ብዙ ቢሊየን ብር የሚያወጣ የኮንትሮባንድ ሸቀጥ ያመለክታል:: ኮሚሽኑ የኮንትሮባንድ ንግዱ ለመቆጣጠር ዘርፈ ብዙ ተግባሮችን እያከናወነም ነው ችግሩ እየተስፋፋ የመጣው:: ችግሩን ለመፍታት መንግስት የጀመራቸው ጥረቶች እንዳሉ ሆነው ባለሙያዎቹ የሰጧቸውን ምክረ ሀሳቦችም መመልከት ለዘርፈ ብዙው የኮንትሮባንድ ችግር ዘርፈ ብዙ ምላሽ መስጠት ያስችላል::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2015