በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አዘጋጅነት ‹‹ክህሎት ለተወዳዳሪነት›› በሚል መሪ ሐሳብ 3ኛው አገር አቀፍ የክህሎት ውድድር የማጠቃለያ መርሃግብር ሰሞኑን ተካሂዷል፡፡ ውድድሩ ቴክኖሎጂ ማፍራትና ማሳደግን በትልቁ ትኩረት ያደረገ ሲሆን፤ በቀጣይ እንደ አገር ምን መሠራት አለበት? በሚለው ላይ መንግሥት ትኩረት ሰጥቷል፡፡ በተለይም ደግሞ ሥራ ክህሎት ሚኒስቴር ጉዳዩ አንገብጋቢ ስለመሆኑም ይጠቁማል፡፡ በዛሬው ዕትማችን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍን ከሚመሩት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ ጋር በሚኒስቴሩ ሥራ እንቅስቃሴ በተለይም ደግሞ የክህሎት ውድድርን መሠረት አድርጎ አዲስ ዘመን ዘለግ ያለ ቆይታ አድርጓል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ዘመኑ ክህሎትን ማዕከል ያደረገ ትውልድ እንፍጠር የሚል ነው:: ሚኒስቴሩ በዚህ ላይ ምን እየሠራ ነው?
ዶክተር ተሻለ፡– ሚኒስቴሩ ከተቋቋመ ወዲህ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በርካታ የሪፎርም ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል:: ከዚህ ውስጥ አንዱና መሠረታዊ ጉዳይ ተቋማት ራሳቸው የሚመሩበትን እሳቤ መቀየር ነው:: የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የስልጠና ማዕከላት ብቻ ሳይሆኑ፤ ምርት የሚያመርቱ አገልግሎት የሚሰጡና ከዚህም በተጨማሪ ከሚያመርቱት ምርት እና ከሚሰጡት አገልግሎት ገቢ የሚያመነጩ መሆን አለባቸው:: ከሚያመነጩት ገቢ ደግሞ መልሰው ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት እና ራስ ገዝ ወይንም ደግሞ ራሳቸውን በራሳቸው ማገዝ የሚችሉበትን አካሄድ መከተል አንዱ የሪፎርም ሥራችን ነው::
ሁለተኛው ተቋማት በአካባቢያቸው ባለው ፀጋ መሠረት መልሰው እንዲደራጁ የሚያደርግ ነው:: ይህ ተግባር በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የፖሊ ቴክኒክ ምን ላይ ትኩረት አድርገው ማሰልጠን አለባቸው የሚለውን ነው:: ትኩረት ሰጥተው በሚያሰለጥኑት ላይ ደግሞ ምን ውጤት መጣ? የሚለው ታሳቢ የተደረገበት ነው:: የአካባቢን ጸጋ መሠረት አድርገው ካመረቱ እና አገልግሎት ከሰጡ ብሎም የሚጠበቅባቸውን በአግባቡ ከሠሩ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም አላቸው:: በዚህ አሠራር ከሄዱ የስልጠና ጥራትንም ሊያረጋግጡ ይችላሉ የሚለውን መሠረት አድርገን በአገሪቱ ጥናት አካሂደናል:: በጥናቱ መሠረትም ምን ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው የሚለውን ወደ ተግባር እየለወጥነው እንገኛለን::
አዲስ ዘመን፡- ትልቅ ትኩረት የተሰጣቸው ዘርፎች ምንድን ናቸው?
ዶክተር ተሻለ፡- ሁሉም ኮሌጆች በግብርና ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው:: ሁሉም ኮሌጆች በቱሪዝም፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ ኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ እና በኮንስትራክሽን ላይ ማተኮር አለባቸው:: በምን ላይ አተኩረው ማሰልጠን አለባቸው የሚለውን በጥናት ተለይቶ ወደ ሥራ የተገባበት ነው:: ኮሌጆችም ተለይተው ሥምሪት የተሰጣቸው ሲሆን በዚሁ አቅጣጫ መሠረት ወደ ሥራ ገብተዋል:: ይህ አንዱ ስኬታችን ነው ብለን እንወስዳለን::
አዲስ ዘመን፡- በአገር ደረጃ ይህን እንደ አዲስ ለመሥራት ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?
ዶክተር ተሻለ፡- ከሪፎርም ሥራ ውስጥ ጉልህ ብለን የምንወስደው ከዚህ በፊት የነበረውን ሥርዓት ትምህርት ሙሉ ለሙሉ ለመቀየር ነው:: አዲስ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ተቀርፆ ተግባራዊ መደረጉም ይታወቃል:: ይህ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ በዋናነት ዜጎች ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ የሙያ ትምህርት ወይም የሙያ ክህሎትን መላበስ አለባቸው:: አጠቃላይ የኢትዮጵያ ትምህርት ሥርዓቱና ስልጠናው በሙያ የተቃኘ መሆን አለበት በሚል አስተሳሰብ የተገባበት ነው:: ይህን መሠረት በማድረግ ከዚህ ቀደም ሲል 10ኛ ክፍል ይጠናቀቅ የነበረው የአጠቃላይ ትምህርት ሥርዓት አሁን ወደ 12ኛ ክፍል ተቀይሯል::
ስለዚህ ወደ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና የሚመጡት 12ኛ ክፍል ትምህርትን ያጠናቀቁ ናቸው ማለት ነው:: ቀደም ሲል ከ10ኛ ክፍል ወደ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ይገባ የነበረው በአሁኑ ወቅት መቅረቱንም ማወቅ ያስፈልጋል:: ስለዚህ ይህን ማዕከል ያደረገ አሠራርና ሥርዓት ትምህርት እየተተገበረ ነው:: ከ180 በላይ በሚሆኑ ሙያዎች አዘጋጅተን ወደ ተግባር ገብተናል:: ይህንንም በመላ አገሪቱ እና ከተማ መስተዳድሮች ተግባራዊ አድርገናል:: ስለዚሀ በአሁኑ ወቅት ሁሉም ኮሌጆቻችን በአዲስ ሥርዓት ትምህርት ተገቢው ስልጠና በመስጠት ላይ ናቸው::
አዲስ ዘመን፡- የትምህርት አሰጣጥና ስልጠና ጥራት ብዙ ጊዜ ፈተና የሚነሳበት ነው:: ይህን ለመሻገር የተካሔደ እንቅስቃሴ ይኖር ይሆን?
ዶክተር ተሻለ፡- አንዱ ፈተና የነበረው የስልጠና አሰጣጥ ጥራት ጉዳይ ነው:: የትምህርትና ስልጠናን ጥራት ከምናረጋግጥባቸው መሣሪያዎች ውስጥ አንዱ ከተለያዩ ሴክተሮች ጋር በጋራ ማሰልጠን ነው:: ከግል ሴክተር ጋር መሥራት አለብን:: ከኢንዱስትሪዎች ጋርም በተናበበ መንገድ መሥራት ግድ ይላል:: ከኅብረተሰቡ ጋር በትብብር መሥራትም አስፈላጊ ነው:: ሥራዎች በትብብር ሲሠሩ የትምህርት ጥራት በበለጠ እየተሻሻለ ይሄዳል::
አዲስ ዘመን፡- በተደረጉ ሥምምነቶች ምን ውጤት እየተገኘ ነው?
ዶክተር ተሻለ፡- በስምምነታችን መሠረት በርካቶችን እያሳተፍን ነው:: ከዚህ አንፃር ከ15 ሚኒስቴሮች ጋር የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራርመናል:: ከሌሎች የግል ኩባንያዎችና ኢንዱስትሪዎች ጋርም ተስማምተናል:: ከትልልቅ ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ስምምነቶችን ፈጽመናል::
ከበርካቶቹ ጋርም በእቅዱ መሠረት ሥራውን ጀምረናል:: ይህ ጥረት በሂደት ፍሬ እያፈራ ነው:: የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና የተግባር ትምህርት ስለሚበዛበት ተቋሙ ውስጥ የሚሰለጥኑ አሉ:: ከዚህ ውጪ ደግሞ ድርጅቶችና ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ሄደው የሚሰለጥኑ በርካቶች ናቸው:: ከዚህ አንጻር የፈጠርነው ወይንም የተፈራረምናቸው ሥምምነቶች ወደ ተግባር እየተቀየሩ ጥሩ ፍሬም እያፈሩ ነው:: በአሁኑ ወቅት በርካታ ሰልጣኞቻችን ኢንዱስትሪ ውስጥ ገብተው የተግባር ትምህርትና ልምድ እየቀሰሙ ይገኛሉ:: በአጠቃላይ የውድድር ስሜት የሚፈጥሩ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንገኛለን::
ጤነኛ ውድድር በአስተማሪዎች፣ በተማሪዎች እና ተቋማት መካከል እንዲፈጠር እያደረግን ነው:: ከዚህም አልፎ በክልሎች መካከል ጤናማ የሆነ ውድድር እንዲኖር እየሠራን ነው:: የስልጠና ልማት ወይንም የክህሎት ልማት ሥራው በየጊዜው እያደገ የሚመጣ ነው:: ይህም በቀጣይ እያደገ እንዲመጣም ዕድል ይፈጥራል::
ሰሞኑን ያካሄድነው የክህሎት ውድድር ነበር:: ይህን የጀመርነው ከተቋም ነው:: ከዚያም በክላስተር ደረጃ፤ በዞን ደረጃ በመቀጠል ደግሞ በክልል ደረጃ የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ተደርጎ በመቀጠል በአገር ደረጃ ውድድርን እያካሄድን እንገኛለን:: በአገር አቀፍ ደረጃ ካጠናቀቅን በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄድም አለ::
አዲስ ዘመን፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የክህሎት ውድድር ተሳታፊዎች የሚመረጡት እንዴት ነው? ወደ ውጭ አገር ሄደው ለመወዳደር ሁኔታዎችን ማን ያመቻቻል?
ዶክተር ተሻለ፡– በአገር ውስጥ የክህሎት ውድድር ነጥረው ወይንም በተለየ ብቃት ጎልተው የወጡትን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የክህሎት ውድድር ተሳታፊ ይሆናሉ:: እነዚህን በሂደት እናወዳድራለን:: በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ልምድ ይገኛል::
በዓለም አቀፍ ደረጃ የክህሎት ማህበር (World skill competitions society) የሚባል አለ:: የእኛ ሚኒስቴርም የእዚሁ ማህበር አባል ለመሆን ከጫፍ ደርሷል:: ባለፈው ቻይና ላይ ውድድር ተካሂዶ ነበር:: ከሁለት ዓመት በፊት ደግሞ ይህ የክህሎት ውድድር ራሺያ ተካሂዶ ነበር:: ልክ የስፖርት ኦሎምፒክ እንደሚካሄደው በሁለት ዓመቱ ክህሎት ኦሎምፒክ ይካሄዳል:: በዚህ የውድድር መድረክ ላይ የእኛ ሚኒስቴርም፤ ከየክልሉ የአሸናፊዎች አሸናፊ ከሆኑ ተማሪዎች እና አስተማሪዎች ጋር በዚህ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የምናሳትፍበት ሥራ እየተሠራ ነው ማለት ነው::
ይህ የኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ትምህርት ሥርዓት በየጊዜው እየዘመነ እንዲሄድ ያደርገዋል:: በተጨማሪም ከጊዜው ጋር በተናበበ መንገድ እንዲጓዝ ያስችለዋል:: በውድድር ዓለም ውስጥ ሆነን፤ እዚህ እርስ በእርስ ብቻ ተወዳድረን የምንቀር ብቻ ሳንሆን ከዓለም ጋር ተወዳድረን የት ነው ያለነው ብለን ራሳችንን መፈተሽ እና ማወቅ ተገቢ ነው:: ስለዚህ ተወዳዳሪነትን ለማስፈን እና ብቃትን መሠረት ያደረገ ትውልድ እንዲኖር ሰፋፊ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንገኛለን::
በሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ባለቤቶችም የሚሳተፉበት እና እየተሳተፉበት ያለ መሆኑንም መረዳት ያስፈልጋል:: ይህ እያደገ ከሄደ የኢትዮጵያ የትምህርት ስልጠና እና ቴክኒክና ሙያ ዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የማይሆንበት አንዳች ምክንያት የለም ማለት ነው::
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል በርካታ የግል ተቋማት እና ኢንዱስትሪዎች ለልምምድ የሚጠይቋቸውን በሰልጣኞች በኩል ያለመቀበል ችግር ነበር:: ይህን አስሳሰብ መሻገር ተችሏል?
ዶክተር ተሻለ፡– በሥራ ላይ ፈተናዎች ሊኖሩ ይችላሉ:: አንዳንድ ፈተናዎች መነሻቸው ነገሮችን ካለመገንዘብ የሚመነጩ ናቸው:: ወደ አንድ ተቋም ሰልጣኞች ሲሄዱ የሚሰጡት አበርክቶ ይኖራል:: ይህን ካለመገንዘብ አንቀበልም የሚል አካል ወይም ኢንዱስትሪ ሊኖር ይችላል:: አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ዘርፉን በሚገባ ካለመረዳት የሚመጣ በመሆኑ ለምን እንደዚህ ይሆናል? ብሎ በጥልቀት ማየትና ማጤን ብሎም መፍትሄ ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው::
መሰል ችግሮችን በአካል ቀርቦ ማስረዳት ይጠይቃል:: ከዚህም በተጨማሪ ሠርቶ ማሳየት እና ሃሳብን መሸጥንም ይፈልጋል:: በመሆኑም ከቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ምን ይፈለጋል? ከግል ዘርፉስ ምን ይጠበቃል? የሚለውን ማወቅ አስፈላጊ ነው:: የግል ኢንዱስትሪዎች ሰልጣኞች ወደ ድርጅታቸው ሲሄዱ ማሽን ያበላሹብናል፤ በቂ ክህሎት የላቸውም በሚሉ እና ሌሎች ምክንያቶች ሳቢያ ሊጠራጠሩ ይችላሉ:: ስለዚህ ይህን አስተሳሰብ ለማስተካከል በትጋት መሥራት ይጠይቃል::
ሰልጣኞች ከምረቃ በኋላ ወደዚህ ተቋም ተመልሰው የሚሠሩ ወይንም የሚቀጠሩ መሆናቸውንና ለዚህም በቂ እውቀት ከወዲሁ መያዝ እንዳለባቸው ማሳወቅና በአግባቡ ማስረዳት ይገባል:: በመሆኑም ይህ የጋራ ሥራ ነው:: ለተወሰኑ አካላት በቻ የሚተው ወይንም ደግሞ የአንድ አካል ብቸኛ ኃላፊነት አይደለም::
አዲስ ዘመን፡- ልዩ ክህሎት ያላቸው አካላት ወይም ተወዳዳሪዎች ከውድድሩ ምን ይጠበቃሉ?
ዶክተር ተሻለ፡- በውድድሩ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ300 በላይ ተማሪዎች ከ200 የሚልቁ መምህራን ተወዳዳሪዎች ናቸው:: ከእነዚህ ውስጥ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የወጡት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሸለሙ ይሆናሉ:: በቀጣይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ውድድርም የሚመረጡና የሚሳተፉ ይሆናል:: ይህም ብቻ ሳይሆን ተወዳድረው አሸናፊ የሆኑባቸውን ቴክኖሎጂዎች በሚቀጥለው ዓመት ወደ ምርት በማስገባት ወይንም በሰፊው በማምረት ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል:: ዓላማው ቴክኖሎጂ ማሳየት ብቻ ወይንም ጥቂት ቴክሎኖጂን ወደ ተግባር መቀየር ብቻ ሳይሆን ከኮሌጆች ጋር በመተባበር ምርት ወደ ማምረት ሂደት እንዲገቡም ማድረግን ይጨምራል::
አዲስ ዘመን፡- ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን የታሰበው እንደተጠበቀ ሆኖ አገር በቀል ዕውቀቶችን ከመጠቀም አኳያስ ሚኒስቴሩ ምን እየሠራ ይገኛል?
ዶክተር ተሻለ፡– ችግሮች ሀገርኛ መፍትሄ እንዲኖራቸው ምን ዓይነት ሥራ መሠራት አለበት? የሚለው ትክክለኛ ጥያቄ ነው:: የቴክኒክና ሞያ ዘርፉ አሁን እየሠራ ያለው ክህሎት መር እና ገበያ መር የሆነ ሥራ እንዲኖር ነው። ከዚህ አንፃር የእኛ የስልጠና አግባብ ተግባር ተኮር መሆን አለበት።
በተጨማሪም አገር በቀል ክህሎቶችን እውቀቶችን የሚያወጣና ከእነዚህ ጋር የተሳሰረ ሊሆን ይገባል። በአዲሱ ትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ትኩረት የተሰጠው አንዱ ጉዳይ የትምህርትና ስልጠና ሥርዓታችን በአጠቃላይ ለአገር በቀልና ክህሎት ይሰጥ የነበረው ቦታ ዝቅተኛ ስለነበር ይህንን ለመቅረፍ የሚያስችሉ የሪፎርም ሥራዎች በመሥራት ላይ ይገኛሉ።
ከዚህ አንጻር በመላው አገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች ያሉ ኮሌጆች የአካባቢውን ጸጋ መሠረት አድርገው መልሰው እንዲደራጁና መልሰው ስምሪት እንዲወስዱ ተደርጓል። ይህም በእኛ ቋንቋ የምንለው የዞኒንግና የዲፍሬንሺየሺን ሥራ ነው። ይህ ሥራ እያንዳንዱ ተቋም ወይንም እያንዳንዱ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በአካባቢው ያለውን አገር በቀል እውቀት እና ሰው ሰራሽ ወይንም እዚያ አካባቢ የተፈጠረ ልማት መሠረት አደርጎ አዲስ ስምሪት እንዲያደርግ እየተሠራ ይገኛል። ከዚህ አንጻር በቴክኖሎጂ ውድድር ላይ የቀረቡት አብዛኛዎቹ ሥራዎች ሲታዩ አገር በቀል የሆኑ እውቀቶችንና ሥራዎችን የያዙ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- አገር በቀል እውቀቶችን ከማዘመን አኳያ የተሰጠው ትኩረትስ ምን ይመስላል?
ዶክተር ተሻለ፡– እነዚህም በግንባታ፣ በብረታ ብረት በቆዳ ውጤቶችና ሌሎች ምርቶችም በአገር ውስጥ በተለምዶ ሲሠሩ የነበሩ ሥራዎችን ዘመናዊነትን በማላበስና አሁን ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ በማምረት ለገበያ ማቅረብን ጭምር ያካተተ ነው። እንዲሁም አገር በቀል እውቀቶች እዚያው በተፈጠሩበት የሚቆዩ ሳይሆን መሠረታቸውን ሳይለቁ እየተሻሻሉ እንዲሄዱ የማድረግ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።
የአሁኑ ውድድር የአንድ ጊዜ ሁነት ሆኖ የሚቀር አይደለም:: በዚህ የውድድር ሂደት ያለፉ ሰልጣኞችና አሰልጣኞች እንዲሁም እነሱ ያቀረቧቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሥራዎቻቸው ተመርጠው ወደሥራ እንዲገቡ የሚደረግ ይሆናል። ለዚህም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚቋቋም የባለሙያ ቡድን አለ። ይህ ቡድን ቴክኖሎጂዎቹ የሚያስፈልጋቸውን እርማት ወይንም ማስተካከያ ካለ የሚሠራ ሲሆን በቀጣይም እነዚህ ምርቶች እንዴት ወደ ሥራ ይገባሉ? ለሚለውም ፍኖተ ካርታ የሚያስቀምጥ ይሆናል። በዚህ መሠረት የቴክኖሎጂ አቅራቢዎቹ ከግሉ ዘርፍና ከፖሊ ቴክኒክ ኮሚቴ ጋር በመሆን እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ወደማምረት የሚገቡበትን ዕድል ይፈጠራል።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ቴክኖሎጂ ምርት ሲገቡ የፋይናንስ እጥረት እንደሚያጋጥማቸው የሚያወቁ በርካቶች ናቸው:: ለዚህስ የታሰበው መፍትሄ ምንድን ነው?
ዶክተር ተሻለ፡- አንዳንድ ጊዜ እነዚህ የቴክኖሎጂ አቅራቢዎች የቦታና የገንዘብ እጥረትና ሌሎች ተግዳሮቶችም እንደሚገጥማቸው በማንሳት ወደ ማምረት ሳይገቡ ይቀራሉ። እስካሁን የነበረው ልምድ የሚያሳየው ይህንን ነው:: በመሆኑም በዚህ ዓመት ይሻሻላል ተብሎ የታሰበው ቴክኒክና ሞያ ኮሌጆች ሰፋፊ ቦታ እንዳላቸው ይታወቃል። በመሆኑም ከእነዚህ ባለ ቴክኖሎጂዎች ጋር በመጣመር ሥራዎቹን ወደ ምርት እና አገልግሎት ማስገባት ይጠበቅባቸዋል። ይህም በጋራ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕድል የሚፈጥር ይሆናል።
ከዚህም በተጨማሪ በአንድ ወገን ኮሌጆቹ በርካታ ማሽነሪዎች ያሏቸው በመሆኑ በሌላ በኩል አምራቾች ማሽነሪ የሌላቸው በመሆኑና ማሽነሪ ለመግዛትም የገንዘብ እጥረት ያለባቸው በመሆኑ የራሳቸውን እስኪገዙ ድረስ የኮሌጆቹን ማሽነሪዎችና ቦታዎች በመጠቀም መነሻ ጥሪት ማፍራት እንዲችሉ የሚያደርግ ይሆናል። ይህንን ካገኙና ራሳቸውን ከቻሉ ወጥተው ሙሉ ለሙሉ በግላቸው መሥራት የሚችሉበት ዕድልም ይፈጠራል ማለት ነው።
የቴክኒክና ሞያ ኮሌጆች የቴክኖሎጂ እና የኩባንያዎች መፈልፈያ መሆን አለባቸው:: በዚህ ላይ የማያወላዳ የተቀመጠ አቅጣጫ አለ። ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ከዚህ በኋላ የሚቋቋመው ኮሚቴ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች በአግባቡ አደራጅቶ የትኛው ቴክኖሎጂ የትኛው ተቋም ላይ ወደ ምርት ሊገባ ይችላል የሚለውን ጭምር ተከታትለን የምናስፈጽም ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ከቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማት በተጨማሪ በአገሪቱ የሚገኙ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትልልቅ ጥናትና ምርምር ውጤቶች ቢኖሩም ከ‹‹ሼልፍ›› ወርደው ሲተገበሩ አይታዩም:: ይህስ በሚኒስቴሩ በኩል ታስቦባቸዋል?
ዶክተር ተሻለ፡– እንደሚታወቀው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ትምህርት ሚኒስቴርን ጨምሮ ከተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር በጥምረት የሚሠራና የጋራ እቅድ ያለው ሲሆን፤ የመግባቢያ ሰነድም ተፈራርመናል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሠሯቸው በርካታ የምርምር ሥራዎች አሉ። ነገር ግን ወደ መሬት ወርደው ሲተገበሩ አይስተዋልም። በመሆኑም አንደኛው በቅንጅት የምንሠራበት ጉዳይ ይህንን ለመሻገር ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከኢንዱስትሪው እና ከባለ ሀብቱ ጋር በጋራ የምንሠራበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። በዚህም ረገድ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ካሉ ትልልቅ ኩባንያዎች ጋር በጥምረት እየሠራን እንገኛለን።
አሁንም ተሠርተው ኮሌጆች ውስጥ የተቀመጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ከሼልፍ በማውረድ ወደ ተግባር የምናስገባ ሲሆን፤ በቀጣይም የምርምር ውጤቶች በቀጥታ ወደ ትግበራ የሚገቡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የምንሠራ ይሆናል። ይህ ቴክኖሎጂ እና እውቀትን በአግባቡ የማገናኘት ሂደት ነው::
ዘንድሮም በሦስተኛው አገር አቀፍ የክህሎት ውድድር ያመጣነው ለውጥ እዚህ መጥተው የሚያሸንፉ ቴክኖሎጂዎች ወደ አገልግሎትና ምርት መግባት አለባቸው የሚል ነው። ይህንን በመከታተልም በቴክኒክ ያለባቸውን ችግር በባለሙያ የሚፈታ ሲሆን፤ የፋይናንስ እና የቦታ እጥረት ደግሞ ከኮሌጆች ጋር በማስተሳሰር ለውድድር የቀረቡና ያሸነፉ ቴክኖሎጂዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ትግበራ እንዲገቡ የሚያደርግ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡-ከዚህ በፊት በተደረጉ ውድድሮች የተገኙ ውጤቶች በተጨባጭ ምን አስተምረዋል?
ዶክተር ተሻለ፡– ይህ ውድድር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው። በውድድር ወቅት ተማሪዎች እርስ በእርስ ውድድር ሲያደርጉ ነበር። አስተማሪዎችም በተመሳሳይ በእውቀት እና በክህሎት ውድድር ሲያደርጉ ነበር። በዚህ ሂደት የሚገኙ ግብረ መልሶች አሉ። ለምሳሌ የሠሯቸው ቴክኖሎጂዎች ጥራታቸው ምን ይመስላል? ምን ያህል ተተግባሪ ናቸው? የማህበረሰቡን ችግር ሊያቃልሉ ወይንም ሊፈቱ ይችላሉ ወይ? የሚለው ሁሉ በዝርዝር ይታያል።
ሰልጣኞችም ክህሎቱን ሲተገብሩ የሚያገኟቸው ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ግንባታ የሚሠሩ ከሆነ ይህንን በሚያከናውኑበት ወቅት ከሠሩት ነገር በመነሳት ምን ዓይነት ክህሎት ይጎድላቸዋል? የጥራት ክፍተት ያለው ምን ላይ ነው? በማለት ወደኋላ በመመለስ የትምህርት ካሪኩለሙን እስከ መፈተሽና ማስተካከል ድረስ የሚጠቅም ይሆናል። በተጓዳኝ የመምህራኖችን አቅም የሚገነባበትም ብሎም ሌሎች አደረጃጀቶችም ይፈተሻሉ። እዚህ የክህሎት ውድድር ላይ ልጆቹ ሲሠሩ የሚያሳዩት ጥሩ ነገር እንዳለ ሁሉ የየራሳቸው ድክመቶችም ይኖራቸዋል። ይህንን መነሻ በማድረግ ድክመቱ ከየት መጣ የሚለውን በመፈተሽ ከትምህርት ካሪኩለም ወይንም ከመምህሩ አልያም ከተቋሙ አመራር መሆኑ ይለያል። ይህም ችግሩን ከመሠረቱ ለመቅረፍ የሚያስችል ይሆናል።
ያለፉት ሁለት ውድድሮች በቂ ልምድ የተቀሰመባቸው ሲሆን፤ የዘንድሮውም በተመሳሳይ ብዙ ግብዓት የሚሰበሰብበት ይሆናል። በቀጣይም ከዚህ እየተሻሻለ በአገር አቀፍ ደረጃ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የ‹‹ስኪል ኦሎምፒክ›› በመሳተፍ አገራችን የምትወዳደርበትን ዕድል ለመፍጠር እየሠራን እንገኛለን። በዚህም የኢትዮጵያ የቴክኒክና ሞያ ስልጠና ሥርዓት ከዓለም ጋር ተወዳዳሪ እንድትሆን ሰልጣኞች እና መምህራንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ ተማሪዎች ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ እና ሥርዓቱም ዓለም አቀፍ እንዲሆን እንሠራለን።
አዲስ ዘመን፡- ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ስላደረጉት ቆይታ እናመሰግናለን::
ዶክተር ተሻለ፡- እኔም አመሰግናለሁ::
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2015