ከዛሬ አምስት ዓመታት በፊት ግንቦት 20 የመገናኛ ብዙሃን ዜና እና ፕሮግራም ነበር፡፡ እነሆ ዛሬ ግንቦት 20 ታሪክ ሆኗል፡፡ የዛሬ ሰዎች ሰነድ አገላብጠን እና አባቶችን ጠይቀን የምናውቀው ሳይሆን በዓይናችን ያየነው ታሪክ ሆኗል፡፡ ታሪክ ደግሞ የዛሬ ሳይሆን የትናንት ክስተት ነውና ግንቦት 20 ታሪክ ሆኖ ‹‹እንዲህ ሆኖ ነበር›› ልንለው ነው፡፡ ከዛሬ 32 ዓመታት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን ኢህአዴግ የደርግ ሥርዓትን አስወግዶ አዲስ አበባን ተቆጣጠረና ግንቦት 20 ታሪካዊ ቀን ሆነች፡፡
ቀደም ባሉት ሳምንታት እንዳልነው ይህ የግንቦት ወር የደርግ እና የኢህአዴግ ታሪካዊ ወር ይመስላል። ገና ወደፊትም አለን፡፡ ግንቦት 27 ራሱ የኢህአዴግና የደርግ ታሪክ ነው፡፡ እሱን የዛሬ ሳምንት እናየዋለን፡፡ ለዛሬው የምናስታውሰው ከ32 ዓመታት በፊት በዛሬዋ ቀን የሆነውን የግንቦት 20 ክስተቶችን ነው፡፡
ከ32 ዓመታት በፊት ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ኢህአዴግ ወታደራዊውን የደርግ መንግሥት ገርስሶ አዲስ አበባን የተቆጣጠረበት ቀን ነው፡፡ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር የነበሩ የጻፏቸው መጻሕፍት፣ በተለያዩ መድረኮች የተናገሯቸው ንግግሮች፣ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የተሰሩ ዘጋቢ ፊልሞች… እንደሚያሳዩት ኢህአዴግ ደርግን ያስወገደው በሕዝብ ትብብር ነው፡፡
ምንም እንኳን ጦርነቱ የዓመታት ቢሆንም ኢህአዴግ ግንቦት ሃያን በተለየ ያከብረው የነበረው አዲስ አበባን የተቆጣጠረበትና ቤተ መንግሥት የገባበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡
የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት እንደሚያሳዩት ኢህአዴግ ደርግን ለማስወገድ ሕዝባዊ ድጋፍ የሚያስገኙ ዘዴዎችን ተጠቅሟል፡፡ ከእነዚህም አንዱ የጦርነቱን ዘመቻዎች የአካባቢው ሰዎች በሚያከብሯቸውና በሚያደንቋቸው ሰዎች ይሰይም ነበር፡፡ የአካባቢው ሰዎች በሚናገሩት ቋንቋ ይሰይም ነበር፡፡
ለምሳሌ፤ በወለጋ እና በሌሎች የምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የነበረውን ዘመቻ ‹‹ቢሊሱማ ወልቂጡማ›› ብሎ ነበር የሰየመው፡፡ የኦሮምኛ ቃል ሲሆን ነፃነትና እኩልነት ማለት እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል፡፡ በዚህ ስም የሰየመውም የአካባቢው ሰው የኦሮምኛ ተናጋሪ ስለሆነ ነው፡፡
በወሎ በኩል የነበረው ዘመቻ ደግሞ ዘመቻ ዋለልኝ ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ዋለልኝ መኮንን የወሎ ተወላጅ ሲሆን የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኝ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ይህን የተጠቀመው ዋለልኝ መኮንን የወሎ ተወላጅ ስለሆነ ወሎዎች ይወዱታል ብሎ ሳይሆን ምናልባትም የብሔር ፖለቲካ ጀማሪና አቀንቃኝ ስለነበረለት ይሆናል፡፡
በጎንደር በኩል የነበረው ዘመቻ ደግሞ እስከ ጎጃም ድረስ ‹‹ዘመቻ ቴዎድሮስ›› ይባል ነበር፡፡ በዚያ አካባቢ ያለው ማህበረሰብ የአጼ ቴዎድሮስ ነገር ሲነሳ ወኔው ይቀሰቀሳል ብሎ ስላሰበ ይመስላል፡፡
አራተኛውና አዲስ አበባን የተቆጣጠረበት የመጨረሻው ዘመቻ ደግሞ ‹‹ዘመቻ ወጋገን›› ይባላል፡፡ ‹‹የመጨረሻዋ ጥይት የተተኮሰችበት›› ይሉታል የኢህአዴግ ሰዎች፡፡
በ2008 ዓ.ም ግንቦት 20 ሲከበር የኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት ካቀረበው ጽሑፍ፤ የግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ክስተት የሚከተለውን እናስታውስ፡፡
‹‹…. አዲስ አበባ በሦስት አቅጣጫ በኢህአዴግ ሠራዊት ተከባለች፡፡ ከየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚወጣም ሆነ የሚገባ የለም፡፡ የቀለበቱ ማጥበብ ቀጥሏል፡፡ አምቦ የነበረው ሠራዊት ወደ ሆለታና ታጠቅ ተጠጋ፡፡ በጅማ በኩል የነበረው ግልገል ግቤን ተሻግሮ ወሊሶን አልፎ ወደ ዓለም ገና ተጠግቷል፡፡ ደብረ ብርሃን የነበረው ሃይል ገሚሱ ወደ ደቡብ ምስራቅ በመጓዝ ደብረ ዘይትን ከበባት፡፡ ማንኛውም የጦር አውሮፕላን ወደ ሰማይ አልወጣም፤ አልወረደም፡፡
….ግንቦት 19 ቀን 1983 ልክ ከቀኑ 10 ሰዓት ወታደራዊ ዘመቻውን በበላይነት የሚያስተባብረው ቡድን ለመጨረሻ የሰላም ውይይት ሎንደን ከነበረው የበላይ አመራር ‹‹ቀጥል›› የሚል አጭር መልዕክት ደረሰው። ቀድሞ በተደረገው ጥናት አዲስ አበባ በሦስት ግንባር ተከፍላለች፡፡
በአምቦ ግንባር የነበረው በጎጃም በር በኩል ወደ ፒያሳ በመዝለቅ መርካቶን ተቆጣጥሮ ወደ ጅማ መንገድ ያመራል፡፡ ሁለተኛው ግንባር በደብረ ዘይት የሚመጣ በአቃቂ ገብቶ ንፋስ ስልክ፣ ጎተራ፣ ቄራ፣ አራተኛ ክፍለ ጦር፣ ስታዲየም ጨምሮ እስከ ሜክሲኮ ያለውን ይይዛል።
ሦስተኛው በሰንዳፋ የሚመጣ በኮተቤ በመውረድ ብረታ ብረት ፋብሪካ ከደረሰ በኋላ ለሦስት ንኡስ ግንባር ይከፈላል፡፡ አንዱ በመገናኛ በኩል ወደ ኤርፖርት ያመራል፡፡ ሁለተኛ ክፍል በ22 ሰንጥቆ ወደ መስቀል አደባባይ በመሄድ ታችኛው ቤተመንግሥት ይቆጣጠራል፡፡ ሦስተኛው ክፍል በእንግሊዝ ኤምባሲ አቅጣጫ በግንፍሌ አድርጎ ወደ አራት ኪሎ በመግባት ቤተመንግሥትን ይቆጣጠራል፡፡
ኮማንደሮቹ ይህንን ድልድል በማድረግ ሌሊቱን በሙሉ ሲዘጋጁ አደሩ፡፡ እነ ሐየሎም በነበሩበት አቅጣጫ ታጠቅ አካባቢ የነበረው ሃይል ማታ ወደ ከተማ የመፍረስ ምልክት ስለታየ ይህ ሃይል ወደ መሃል ከተማ ከገባ አላስፈላጊ ዋጋ የሚያስከፍል ውጊያ ስለሚያስከትል አስቀድሞ መያዝ አለበት ተብሎ ስለተወሰነ በዋዜማው የተወሰነ ሃይል ቀድሞ ወደ ቦታው እንዲጠጋ በማድረግ በኮልፌ 18 ማዞሪያ በኩል ተዘጋ፡፡ ከከተማው ወደ ውጪ እንዲበተንም ተደረገ፡፡
አስቀድሞ የወጣው ስትራቴጂ በሚገባ የሰራ መሆኑ እየተረጋገጠ መጣ፡፡ የመንግሥት አብዛኛው ወታደር ከአዲስ አበባ ከመግባቱ በፊት እንዲበታተን ተደረገ፡፡ ገሚሱ መሳሪያ የያዘ ገሚሱ መሳሪያ የሌለው እየተንቀረፈፈ ከሚገባ በስተቀር ተደራጅቶ ወደ ከተማዋ የሚያፈገፍግ ሠራዊት አልነበረም፡፡ ይህ ለኢህአዴግ ትልቅ ድልና ስኬት ነበር፡፡ በሕዝቡ ዘንድም ስጋትን የቀነሰ ነበር፡፡
የወጋገን ዘመቻ ዋና ዓላማው የቀረውን ሠራዊት መደምሰስ ሳይሆን ከተማዋን በብልሃት መቆጣጠር ነበር…››
በሕወሓት ጀማሪነትና መሪነት የተደረገው የትጥቅ ትግል በዚህ መልኩ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ተቆጣጥሮ ለ27 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን መራ፡፡ በ2010 ዓ.ም ለውጥ መጣ፤ ከዚህ በኋላ ያለው ታሪክ ሳይሆን ዜና ነው። እነሆ ግንቦት 20 ግን ታሪክ ሆነ!
የኢትዮጵያ መሪዎች የሚሞገሱበት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት
የፖለቲካ ባህላችን ሆነና በማስተዳደር ላይ ያለ መንግሥት ያለፈውን ሥርዓት ሲወቅስ ነው የምንሰማ፡፡ በከፍተኛ ሥልጣን ላይ ያሉ የመንግሥት አመራሮች የሚሉትን በመስማት ከታች ያለውም ያንኑ ያስተጋባል፡፡ የራሳቸውን ጥንካሬ ከመናገር ይልቅ ያለፈውን መውቀስ የተለመደ ነው፡፡
ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን የኢትዮጵያ መሪዎች አንድ የማይደራደሩበት ነገር አለ፡፡ ይሄውም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስከበር፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በተመለከተ እና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማንም መሪ ማንንም አይወቅስም፡፡ በሌላው ጉዳይ ባልተለመደ መንገድ በአፍሪካ ሕብረት ጉዳይ ግን በማስተዳደር ላይ ያሉ መሪዎች ሁሉ ያለፈውን ሲያመሰግኑ እና ሲያደንቁ ነው የሚሰማው፡፡
አቶ መለስ ዜናዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥልሴን እና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምን በአፍሪካ ጉዳይ አመስግነዋል፡፡ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ዓመት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴን እና አቶ መለስ ዜናዊን አመስግነዋል፡፡
መሪዎቻችን እንደሚሞገሱት ሁሉ ወቃሾችም ቢኖሯቸውም በእነዚህ ጉዳዮች ግን እነዚህን የኢትዮጵያ መሪዎች ማንም ያመሰግናቸዋል፡፡ በተለይም በአፍሪካ ጉዳይ ግን የሚመሰገኑት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ መሪዎችም ነው፡፡ ምክንያቱም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሰረተው ኢትዮጵያ ነው፤ የተመሰረተውም በኢትዮጵያ ቅኝ አለመገዛትና የነፃነት ተምሳሌትነት ስለሆነ ነው፡፡
በዛሬው ሳምንቱ በታሪክ ዓምዳችን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (በኋላ የአፍሪካ ሕብረት) የተመሰረተበትን ምክንያት በማድረግ የሕብረቱን አመሰራረትና ጉዞ እናስታውሳለን፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሰረተው ከ60 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም ነበር፡፡
ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛች ነፃ ሀገር በመሆኗ፤ የተባበረች አፍሪካን ለመመሰረት እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረችው ከ1950ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ነበር። በወቅቱ የነበሩትን 30 አካባቢ የሚሆኑ ነፃ የአፍሪካ ሀገራትን በማነሳሳትና የመሪነት ሚና በመጫወት ግንቦት 17 ቀን በ1955 ዓ.ም በአዲስ አበባ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተመሰረተ፡፡
ይህ ድርጅት ሲመሰረት፤ ከሃያ በላይ በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ የአፍሪካ ሀገራትን ነፃ ማውጣትና የጥቂት ነጮች የበላይነት ሥርዓት ያለባቸውን ሀገራትም ከዚህ የዘር መድልዎ ሥርዓት ማላቀቅ ዋነኛ ዓላማው ነበር። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ይህን ዓላማውን አሳክቷል።
በመጨረሻ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የተቀላቀለችው ሀገር ደግሞ ደቡብ አፍሪካ ነበረች። ደቡብ አፍሪካ የጥቂት ነጮች የዘረኝነት ሥርዓትን አስወግዳ በ1986 ዓ.ም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ተቀላቀለች፡፡
የአፍሪካ ሀገራትን ነፃነት ማረጋገጥ ቀዳሚ ዓላማው አድርጎ የተመሰረተውና ዓላማውን ያሳካው አፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረትና ተልዕኮውን እንዲወጣ በማድረግ ረገድ የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው። ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ የመሪነት ሚና እንዲጫወቱ ያደረጋቸው ደግሞ የነፃይቱ ሀገር ኢትዮጵያ መሪ መሆናቸው ነው፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በዚህ ስሙ የቆየው ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ነው፡፡ ድርጅቱ በ1994 ዓ.ም ወደ ሕብረትነት በመለወጥ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የነበረው የአፍሪካ ሕብረት ተብሏል፡፡ የአፍሪካ ሕብረት የተባለው በ1993 ዓ.ም በዋና መቀመጫው አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ቢሆንም ይፋ የተደረገው ግን በ1994 ዓ.ም ደቡብ አፍሪካ ነው፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመስረት ኢትዮጵያ በመሪዋ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴና በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከተማ ይፍሩ ከፍተኛ ጥረት እንዳደረገችው ሁሉ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ አዲስ አበባ እንዲሆንም በወቅቱ መሪዋ አቶ መለስ ዜናዊ ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች፡፡
በ1994 ዓ.ም የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የሴኔጋል መንግሥት ተወካይ የሕብረቱ ማቋቋሚያ ሰነድ ላይ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ አዲስ አበባ ይሁን የሚለውን አንቀጽ (አንቀጽ 24) ተቃወሙ፡፡ ወደ ሌላ አገር መሄድ እንዳለበትም ምክረ ሃሳብ አቀረቡ፡፡ የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ የሴኔጋላዊውን ሃሳብ በመቃወም የሚከተለውን ንግግር አደረጉ፡፡
‹‹የሴኔጋሉ ተወካይ አንቀጽ 24ን በተመለከተ አሁን መወሰን በጣም እንደሚያስቸግር፤ በተቀሩት አንቀጾች ላይ ግን ምንም ችግር እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡ ተወካዩ የአፍሪካ ሕብረት ጽሕፈት ቤት መቀመጫ የት መሆን እንዳለበት ለመወሰን እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡
በእኔ እምነት በጣም ቀላሉ አንቀጽ ይሄኛው አንቀጽ ይመስለኛል፡፡
ይህን ጉዳይ አሁን ለመወሰን እንደእኔ ከሁሉም በጣም የቀለለ ጉዳይ ይመስለኛል፤ ልክ ጁሊየስ ኔሬሬና ከዋሜ ንኩርማህ አዲስ አበባ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቀመጫ እንድትሆን እንደወሰኑት ማለት ነው፡፡
የያኔዋ ኢትዮጵያ በዘውድ ሥርዓት፣ በአፄ ኃይለሥላሴ ነበር የምትተዳደረው፡፡ ኢትዮጵያን የትኛውም ዓይነት መንግሥት ያስተዳድራት ሁሌም ለአፍሪካ ነፃነት በፅናት መቆሟን ማንም ሰው ሊክደው የማይችለው ሐቅ ነው፡፡
የደቡብ አፍሪካውን የነፃነት ታጋይና አርበኛ ማንዴላን ማን አሰለጠናቸው?! … አፄ ኃይለ ሥላሴ አብዮተኛውን ማንዴላ ኢትዮጵያ ውስጥ አሰልጥነዋቸዋል፡፡ የዚምባቡዌው ሙጋቤ ያደረገውን ፀረ ሮዴሽያ ትግል ማን ነው የደገፈው?! መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ነው፡፡ መንግሥቱ በአገር ውስጥ አምባገነንና ጨፍጫፊ ነበር፡፡ በአፍሪካ ጉዳይ ግን መንግሥቱም እንደ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጠንካራ አቋም ነበረው፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ያላት አቋም መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር የማይቀያየር የፀና አቋም ነው …፡፡››
የአፍሪካ ሕብረት የኢትዮጵያ መሪዎች የሚሞገሱበት ነው ያልነው ለዚህ ነው፡፡ ሥርዓትና መሪዎች ቢቀያየሩም የአፍሪካ ሕብረት ግን የኢትዮጵያን የነፃነት ተምሳሌትነት ሲመሰክር ይኖራል፡፡
በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ሌላው ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት ሰው ደግሞ የንጉሡ ዘመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ከተማ ይፍሩ ናቸው። እኚህ ሰው የንጉሡ ዘመን የውጭ ጉዳይ ግንኙነት አድራጊ ፈጣሪ ነበሩ፤ የንጉሡም ዋና ልዩ አማካሪ ነበሩ፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሊመሰረት በነበረባቸው ጊዜያት ካዛብላንካ እና ሞኖሮቪያ የሚባሉ እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡ በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ጊዜ የአፍሪካ አገራት ተዋህደው አንድ መሆን አለባቸው የሚለው የካዛብላንካ እንቅስቃሴ እና መጀመሪያ መተባበር ይቀድማል የሚለው የሞኖሮቪያ ቡድን እሳቤዎች ነበሩ፡፡ በከተማ ይፍሩ የሚመራው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ግንኙነት እነዚህን ሃሳቦች የማስታረቅ ሥራ ነበር የሚሰራው፡፡
ብልህና በሳል የነበሩት ከተማ ይፍሩ ነገሩን በዲፕሎማሲያዊ ዘዴ ሲያግባቡ ቆይተው የካዛብላንካንም ሆነ የሞኖሮቪያ ሰዎችን ከንጉሡ ጋር በማወያየት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት አስደርገዋል፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ፤ በቆራጥና ጀግና አርበኞቿ ነፃነቷን አስጠበቀች፣ በብልህ ዲፕሎማቶቿና መሪዎቿ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መሰረተች፣ መቀመጫውንም አዲስ አበባ አስደረገች፡፡ እነሆ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በኋላም የአፍሪካ ሕብረት 60 ዓመታት ሆነው ፡፡
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2015 ዓ.ም