ወይዘሮዋ በእጃቸው የያዙትን የማዳበሪያ ከረጢት ደጋግመው እያዩ በትካዜ ተውጠዋል። የሚያዩትን እውነት ፈጽመው ያመኑት አይመስልም። አንዴ የእጅ ቦርሳቸውን አንዴ ደግሞ ከአጠገባቸው ያለውን ወጣት ደጋግመው እያዩ በሀሳብ ነጎዱ። ከብረት ጋሪው በእኩል የተደረደሩት የከሰል ማዳበሪያዎች አንዳች ልዩነት የላቸውም።
ሴትዬዋ ግን ይህን ሀቅ ፈጽሞ ያመኑት አይመስልም። ሁሉንም መንትያ ማዳበሪያዎች አንድ በአንድ እያነሱ ወፈር፣ ጠንከር ያለውን ለማግኘት በእጅጉ ደከሙ። በመጨረሻ አንዲት የሩዝ ከረጢት የምታክል ሚጢጢ ማዳበሪያ መርጠው እንደዋዛ በአንድ ጣታቸው አንጠልጥለው ያዟት።
ሴትዮዋ ከጊዜያት በፊት የነበረውን ሽያጭ መለስ ብለው እያስታወሱ ነው። የከሰሉ ውስጣዊ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ቢያንስ ማዳበሪያውን ለልጆች ያሸክሙ ነበር። አሁን ግን ከዚህ መሰሉ ወግ ጋር አልተገናኙም ። ዛሬ የከሰል ገበያው ጣራ ነክቷል። ይህ ብቻ አይደለም። ማዳበሪያ ተብዬው ከረጢት ጎኑ አለቅጥ ጠቦ ፣ ቁመቱ ከአናቱ ተቆምጦ ሸንቀጥቀጥ ብሎ መጥቷል።
አላግባብ ኮስምኖ ፣ ለገበያ የቀረበው የከሰል መያዣ ‹‹ የዛሬን አያድርገውና ›› እያልን ልንተርክ ያስገደደን ይመስላል። እንደው ተጋኗል ባይባልብኝ አሁን በገበያው ያለው የከሰል ማዳበሪያ ሴቶች በትከሻቸው አንግበው ከሚውሉት ቦርሳ በመጠኑ የሚበልጥ አይመስልም።
በዘንድሮ ገበያ እንደጥሩ ስፖርተኛ መሸናቀጥ የጀመሩት የከሰል ማዳበሪያዎቹ ብቻ አልሆኑም። ቀድሞ በጥሩ ይዞታ በየመንገዱ የምንገዛቸው የሶፍት ጥቅሎች ጭምር መክሳት፣ መቀነሳቸውን እየታዘብን ነው። ስለ ጥቅሎቹ ማነስ ደግሞ ገና በእጃችን ሲገቡ ጀምሮ የምንለየው ሆኗል።
አስገራሚው ጉዳይ የጥቅሎቹ አካላዊ ቁመና ማነስ ብቻ አይደለም። ከመኮስመናቸው ጋር በዋጋ ልቀው በጥራት ወርደው መገኘታቸው እንጂ።
የማነስ፣ የመኮስመንን ነገር ካነሳን ደግሞ የዳቦውን ጉዳይ ሳንጠቅስ ማለፉ ይከብዳል። መቼም አነሰም በዛም ከዕለት እንጀራችን ጎን የዳቦ ፍጆታችን በእኩል ይደመራል። ቤተሰብ ላለውና ልጆች ለሚያሳድግ ሁሉ የዳቦን ጉዳይ እንደዋዛ አይተወውም። ዳቦ በአንድም በሌላም በእጅጉ አስፈላጊና ተመራጭ ህልውናችን ነው።
የዳቦው ገበያ ምን ቢወደድና አቅም ቢፈትን ‹‹ይብቃን፣ እንተወዉ›› የምንለው አይሆንም። በየቀኑ ከሚጨምረው ዋጋ ጋር ፍላጎትን ቀንሶ፣ ቁጥርን አመጣጥኖም ቢሆን ይዞ መግባቱ ተለምዷል። ወደ ዘንድሮው ጉዳያችን ስንመለስ ግን በተጋነነ ዋጋ የሚገዛው አንድ ዳቦ ሊይዙት፣ ሊበሉት ያደናግር ጀምሯል።
እንዲህ ዓይነቱ ሸንቃጣ ‹‹ሆድአልባ›› ዳቦ እንኳንስ ተበልቶ ካንጀት ጠብ ሊል አቅሙ ለራሱ ሳይተርፍ፣ ፍርፋሪው ከእጅ ሳያልፍ ይቀራል። እንዲያም ሆኖ በየጊዜው ሰበብ ይዞ የሚጨምረው ዋጋ የሚችሉት፣ የሚቋቋሙት አልሆነም።
ዛሬ ወተት ለመጠጣት ከአንድ ካፌ ጎራ የሚል እንግዳ እንደቀድሞው አምሮቱን ላይወጣ ይችላል። ከቡና ስኒ ጥቂት ከፍ ብላ የተዘጋጀችውን ሸንቃጣ ስኒም ከአንድ ጊዜ በላይ አያነሳትም። እሷን ‹‹ፉት›› እያለ የሚያጠፋው ጊዜ አይኖርም። በአናቷ አረፋ ከተሞላችው ሚጢጢዬ ጋር ፈጥኖ ለመለየት አፍታ አይፈጅበትም።
ወዳጆቼ! እንግዲህ አሁን ‹‹የዛሬን አያድርገውና›› ማለት ግድ ይለን ይዟል። አዎ! ‹‹የዛሬን አያድርገውና›› ከጥቂት ጊዜያት በፊት በእስር የምንገዛቸው፣ ጎመን፣ ሰላጣና ቆስጣ ዋጋቸውን የሚሸከሙ፣ አቅምንም የሚመጥኑ ነበሩ። መቼም ‹‹ነበሩ›› ማለቱ እንደጥንት ታሪክ ካልተቆጠረ ዛሬን በነበር የምናወሳው የጎመን ቆስጣው ገበያ እውነታው እንደአሁኑ አልነበረም።
ዘንድሮ አትክልት ቢጤ ከምግቤ ላክል ብለው ቢያስቡ እንደ ቅንጦት ይሆንብዎታል። ወደ ገበያ ቢወጡም ዓይንና እጅዎ የሚያርፈው ከወገበ ቀጭኖቹ የጎመን፣ ቆስጣ እስሮች ላይ ነው። አሁን ላይ እንደፊቱ በአስር በሃያ ብር የሚሉትን ቆስጣ ጎመን በዋዛ አያገኙም። እንዲያም ሆኖ ዋጋ ጨምሮ ለገበያ የሚቀርበው እስር በየቀኑ ‹‹ችቦ አይሞላም›› ወገቧን ያዘፍናል። ይሁን ብለው ቢገዙት ደግሞ ከቤት ገብቶ ከድስቱ ሲወጣ ከአንዲት ማንኪያ አያልፍም።
ሸንቃጦቹ ዘንድሮ በእጅጉ በርክተዋል። ውስጥ አዋቂ ተብዬዎች እንደሚሉት በፕላስቲክ ዕቃዎች ታሸገው ለገበያ የሚቀርቡ አንዳንድ የዘይት ምርቶች ሳይቀሩ በቅሸባ መስመር የሚያልፉ ናቸው። እነሱ እንደሚሉት የዘይት ዕቃው በታወቀ ምርት ስያሜ እስቲከር ተዘጋጅቶለት ፣ የሊትር መጠኑ ተለጥፎበት ይዘጋጃል።
ማንም እንደሚያደርገው ገበያ ላይ ሸማቹ ዓይነቱንና ሊትሩን አይቶ ማረጋገጥ ላይ ብቻ ያተኩራል። ብዙ ጊዜ እንደሚሆነው አብዛኛው ገዢ የሚሸጥለትን በአመኔታ ተቀብሎ የሚከፍል ነው ። በተለይ ተመዝኖና ታሽጎ ለሚቀበለው ዕቃ ጥርጣሬ ይሉት የለውም።
በአንዳንድ የዘይት ዓይነቶች ላይ ያለው ሀቅ ግን እንዲህ እንዳልሆነ ይነገራል። አንዳንዴ አምስት ሊትር ተብሎ የተለጠፈበት ዘይት አራት ሊትርና ከዚያም በታች ሆኖ ይገኛል። ያለማስተዋል ሆኖ እንጂ ከተመሳሳይ ሊትር የዘይት እሽጎች መሀል በይዞታቸው ሸንቀጥ፣ መለል ያሉትን ዕቃዎች ሳናያቸው አንቀርም።
ከሸንቃጦቹ መንደር ገብተን እንቃኝ፣ እንፈትሽ ካልን ብዙ ማውጣት እንችላለን። ከሰሞኑ ከአንድ የሸቀጣሸቀጥ ሱቅ እንደቆምኩ አንድ ወጣት የልብስ ሳሙና ሲጠይቅ ሰማሀት። ባለሱቁ ዓይነቱንና ዋጋውን ነግሮ ሳሙናውን ከእጁ አኖረለት። እየገረመኝ ሳሙና ተብዬዋን ስስ ነገር አፈጠጥኩባት። ክስት ብላለች። የወገቧ መቅጠን ብዙ የተጠቀሙበት ላጲስ አስመስሏታል።
ወጣቱ ሸማች ሸንቃጣዋን ሳሙና ጨምሮ ሌሎች ዕቃዎችን እየጠየቀ ገዛዛ። ባለሱቁ ጠቅላላ ሂሳቡን ደምሮ የተሸጡትን ዕቃዎች በአንድ ስስ ፌስታል አኖረለት። የተገዙት ጥቂት ዕቃዎችና ለክፍያ የተጠየቀው ገንዘብ የሰማይና ምድር ይሉት ዓይነት ርቀት ነበረው። በወጉ አንዲት ፌስታል ያልሞላው ዕቃ ከፍ ያለ ገንዘብ ተከፍሎበታል።
ወጣቱ ሸማች ከባለሱቁ የተሰጠውን ዕቃ አንጠልጥሎ ራመድ ከማለቱ ቋጠሮው ከእጁ አምልጦ ከመሬት ተዘረገፈ። ነጋዴው እንደዋዛ ሸብ አድርጎ የሰጠው ፌስታል ብጭቅጭቅ ብሎ ጣቶቹ ላይ ቀርቶ ነበር። ጉዳዩ ቢያናድድም ስለፌስታሉ በባለሱቁ ማብራሪያ ተደርጎ ሌላ ተደራርቦለት መንገዱን ቀጠለ ።
እንዲህ ዓይነቶቹ ነፍስ ስስ ፌስታሎች አሁን በየገበያው ተንጠልጥለው ለሽያጭ መቅረባቸው ተለምዷል። በዘመኑ የኑሮ ውድነት በእሳት ላይ ቤንዚን የሚጨምሩ በርካቶች አይጠፉም። እንዲህ ዓይነቶቹ ሌላውን ጎድተው ራሳቸውን ለመጥቀም ዘዴ አያጡም። ያለወጉ ድርቡን ነጥለው፣ ወፍራሙን አቅጥነው፣ ነጩን አጥቁረው ገንዘብ የሚሰበስቡ ህሊና ቢሶች ናቸው። ለማንኛውም ልቦና ይስጣቸው።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2015