የካቲት 28 ቀን 2010 ዓ.ም በዋለው ችሎት በአበዳሪ እና ተበዳሪ መካከል ያለውን የችሎት ክርክር ማየት ቀዳሚ የዕለቱ ጉዳይ አድርጎ ዳኞች ተሰይመዋል።ግራ ቀኝ ባለጉዳዮችም እንዲሁ በቦታው ላይ ጠበቆቻቸውን ይዘው ቀርበዋል።ፍርድ ቤቱም በተዋረድ የመጣውን የፍርድ ሂደት የሚመለከት ሲሆን፣ የመጨረሻ የተባለውን ብይን ይሰጣል።በዚህ መዝገብ መሠረታዊ የሚባል የሕግ ክፍተት ባይኖርም፤ የሥር ፍርድ ቤት እና ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ አግባብነት የጎደለው ስለመሆኑ የሰበር ውሳኔ ያሳያል፡፡
በዚህ መዝገብ አመልካች ወይዘሮ ብርክቲ ግደይ ሲሆኑ፣ ተጠሪዎቹ አቶ ሸምሱ ኑሪ እና ወይዘሮ ፈዲላ እስማኤል ናቸው።በሁለቱም ወገን ጠበቃቸውን ይዘው ቀርበዋል።ይህ መዝገብ በዛሬው ቀን የተቀጠረው ሰፊ ምርመራ ተካሂዶ የመጨረሻውን ፍርድ ሊሰጥበት ነው።ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ይህን የክስ ሂደትና ውጤቱን በ2011 ዓ.ም ለህትመት ማብቃቱም ይታወሳል፡፡
የክርክሩ ምንጭ
ይህ የሰበር ጉዳይ የብድር ውል የሚመለከት ሲሆን፣ ለዚህ ችሎት ሊቀርብ የቻለው የአሁን አመልካች የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመለያ ቁጥር 85781 በ23/05/2009 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበችውን የሰበር አቤቱታ መርምሮ ለመወሰን ነው።
የጉዳዩ መነሻ ሲታይ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአሁን አመልካች (ከሳሽ)፣ የአሁን ተጠሪዎች ደግሞ ተከሳሾች ሆነው ሲከራከሩ ነበር።ቀደም ሲል ተከሳሽ አሁን ከሳሽ ባቀረበችው ክስ ተከሳሾች በ16/11/1999 ዓ.ም በተደረገው የብድር ውል 300 ሺ ብር የተበደሩ ሲሆን፣ በ10/2/2000 ዓ.ም ይህን የብድር ገንዘብ ካልከፈሉ በመያዣነት ያስያዙትን ቤት ስም ሐብት ወደ ከሳሽ ለማስተላለፍ ግዴታ መግባታቸውን ያትታል፡፡
ከሳሽ የቤቱን ዕዳ ለመንግሥት ብር 37 ሺ 80 ብር በተከሳሽ ስም የተከፈለ በመሆኑ፤ የውስጥ ሁለት በሮችን ለማሠራት 10 ሺ ብር፣ የቤቱ የመከላከያ ብረት ለማሠራት 2 ሺ 500 ብር እና ለባለሙያ 1 ሺ 500 ብር ከፍያለሁ የሚል ነው።በመሆኑም ተከሳሾች ይህን ቤት ሥመ ሀብት ወይም ባለቤትነት ስም እንዲያዝልኝ ይህ ካልሆነ ደግሞ ያወጣሁት ገንዘብ ከሕጋዊ ወለድ ጋር እንዲከፍሉኝ የሚል ነው።በተጨማሪም በውሉ መሠረት ውል ተዋዋዮቹ ግዴታቸውን በአግባቡና በወቅቱ ባለመፈጸማቸው በገደብ ውል መሠረት 20 ሺ ብር እንዲከፍሉኝ በማለት ነው ክስ ያቀረቡት፡፡
ታዲያ ተከሳሾች ባቀረቡት መልስ፤ የብድር ውሉን በተመለከተ ተገቢ ነው ያሉትን ክርክር አድርገዋል።ከሳሽ ለባንክ ከፍያለሁ በማለት እንዲከፈላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ በሚመለከት ለባንክ የተከፈለውን ቀሪ ዕዳ 37 ሺ 080 እና ለሁለት በሮች ለመከላከያ ብረት የወጣው ወጪ በጊዜው የነበረውን ተመጣጣኝ ዋጋ ብንከፍል ተቃውሞ የሌለን በመሆኑ በዚህ መሠረት ቢወሰን እንስማማለን በማለት ነበር ምላሽ የሰጡት፡፡
ከዚህ በኋላ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በመመርመር በሰጠው ውሳኔ ተከሳሾች የተበደሩትን 300 ሺ ብር ለከሳሽ እንዲከፍሉ፤ ከሳሽ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ሚኪሊላንድ ሳይት የሕንፃ የቤት ቁጥር 22 የቤት ቁጥር 843 ለተከሳሾች ሊያስረክቡ ይገባል ሲል ይወስናል።ነገር ግን ለቤቱ አወጣሁት ያሉትን ወጪ ወይንም ለበር መከለያ እና በር ማሰሪያ ያወጡትን ወጪ በክስ ውስጥ ያልተካተተ እና ዳኝነት ውስጥ ስላልጠየቀ ውሳኔ አልተሰጠበትም፤ ታልፏል በማለት ይወስናል።ይህ ፍርድ ግን ወይዘሮ ብርክቲ ግደይ አሳዘናቸው፡፡
ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት
ብርክቲ ግደይ ወደ ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያመሩም፤ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረበውን የከሳሽ ገንዘቤ ሊከፈለኝ ይገባል ብለው ያቀረቡትን ብር ባለመቀበል እና ይግባኙን ውድቅ በማድረግ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ትክክል ነው ሲል ይወስናል።ይህ ጉዳይ ያልተዋጠላቸው እና በሥር ፍርድ ቤትም ሆነ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር የተሰኙት አቤቱታ አቅራቢዋ ወይዘሮ ብርክቲ ግደይ ውሳኔው አግባብ አይደለም በማለት ይከራከራሉ።ታዲያ ጉዳዩ ወደ ሰበር አቤቱታም ቀረበ።የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመቃወም ሃሳቡን ለማስለወጥ ነበር ወደ ሰበር ያመሩት።
ወይዘሮ ብርክቲ ግደይ መጋቢት 4 ቀን 2009 ዓ.ም በተጻፈ የሰበር አቤቱታ አመልካችም በመያዣነት የተያዘውን ቤት በተመለከተ የመንግሥት ዕዳ 37ሺ080 ብር እና ቤቱም ወጪ ለበር ብር 10ሺ000 ለመከላከያ ብረት ብር 2ሺ500 ለባለሙያ ብር 1ሺ500 ያወጣሁት ወጪ እንዲከፈለኝ ጠይቄያለሁ።ተጠሪዎቹ አቶ ሸምሱ ኑሪ እና ወይዘሮ ፈዲላ እስማኤል ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት መልስ ይህን ዕዳ እና ወጪዎችን ሳይክዱ አምነዋል።ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ይህን የታመነውን ጉዳይ በፍትሃ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ቁጥር 242 መሠረት ወዲያውኑ ውሳኔ መስጠት ሲገባው ወይም ከዋናው ፍርድ ጋር ሊወስንልኝ ሲገባው ዳኝነት አልተጠየቀበትም በማለት በማለፍ የሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው።ስለሆነም ይህ እንዲታረምልኝ፤ ያወጣሁት ገንዘብም ከወለድ ጋር ታስቦ እንዲከፈለኝ በማለት ከፍተኛ ክርክር አደረጉ።
የሰበር አጣሪ
የሰበር አጣሪም ጉዳዩን ማየት ጀመረ።አመልካች ወይዘሮ ብርክቲ ግደይ ለባንክ የከፈሉትን ዕዳ እና ለቤቱ ያወጡትን ወጪዎች ተከሳሾቹ አቶ ሸምሱ ኑሪ እና ወይዘሮ ፈዲላ እስማኤል የቤቱን ሰነዶች ሲያስረክቡ እንደሚከፍሉ ማመናቸውን አስረገጠ።ነገር ግን ወጪዎችን በተመለከተ ግምቱ የተጋነነ ስለሆነ በነበረው የገበያ ዋጋ ተገምቶ ብንከፍል አንቃወምም ብለው እያለ በክስ የዳኝነት ክፍል ስላልተጠቀሰ ብቻ ዳኝነት ሳይሰጥበት ውድቅ የመደረጉን አግባብነት መመርመር እና አቤቱታ ማስቀረቡ አግባብ መሆኑ ታመነበት።ዳሩ ግን ተከሳሾቹ (አቶ ሸምሱ ኑሪ እና ወይዘሮ ፈዲላ እስማኤል) በዚህ ጉዳይ የሥር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያልተፈፀመበት ስለሆነ የቀረበው አቤቱታ ውድቅ እንዲሆንልን በማለት ተከራከሩ፡፡
የምርመራው ሂደት
የጉዳዩን አመጣጥ የተመለከተው ችሎት፤ የግራ ቀኛቸውን ክርክር አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ እንዲሁም ከአቤቱታው ጭብጥ አንጻር ጥልቅ ምርመራ አካሄደ።በዚህም ምርመራ አመልካች (ወይዘሮ ብርክቲ ግደይ) ባቀረቡት ክስ በብድር ውል መነሻነት የያዙትን ቤት በተመለከተ ለባንክ የተከፈለ ዕዳ 37 ሺ ብር እና ለቤቱ ያወጡት ወጪ 4 ሺ ብር እንደከፈሉ በክሱ ዝርዝር ውስጥ የገለጹ ቢሆንም፤ በዳኝነት ክፍል ሳይጠቅሱ መቅረታቸውን መገንዘብ ምርመራው ያትታል።
በሌላ ጎን ደግሞ የአሁን ተጠሪዎች (ተከሳሾች) ይህን ክሱን በተመለከተ ባቀረቡት መልስ ለባንክ ተከፍሏል የተባለውን ገንዘብ አልካዱም።እንዲሁም ቤቱ ላይ ለተሠሩት ሥራዎች የወጣውን ወጪ በተመለከተ በወቅቱ የገበያ ዋጋ ተገምቶ ቢከፍሉ የማይቃወሙ መሆኑን ገልፀዋል።ተጠሪዎቹ ለባንክ የተከፈለውን ገንዘብ እና ቤቱ ላይ የወጣውን ወጪ አምነዋል።ይህን የግራ ቀኛቸውን ክርክር በሕግ አግባብ ማየቱም አስፈላጊ መሆኑን ምርመራ ውጤት አቅጣጫ አስቀመጠ፡፡
ሕጉ ምን ይላል?
መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ የፍትሐብሔር ሕጉ የተለያዩ ድንጋጌዎች አሉት።የመጀመሪያው ነጥብ ‹‹ከሳሽ በሚያቀርበው የክስ ማመልከቻ ላይ በተለይ ወይም በምትክ ወይም በተለዋዋጭ የሚጠይቀውን ዳኝነት በግልጽ መጥቀስ እንዳለበት የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ቁጥር 224 ተመልክቷል።እንዲሁም ከሳሽ የሚጠይቀው ዳኝነት ጠቅላላ እንደሆነ የክሱን ጭብጥና የማስረጃውን አካባቢ ሁኔታ መሠረት በማድረግ ትክክለኛ መስሎ የታየውን ፍርድ መስጠት እንደሚችል›› በዚህ ድንጋጌ ሥር ተደንግጓል የሚል ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ፤ ‹‹አንድ ተከራካሪ ወገን በመከላከያ መልስ ወይም በማናቸውም በሌላ መንገድ የተከሰሰበትን ነገር በሙሉ ወይም በከፊል ያመነ እንደሆነ ወይም በቃል ክርክር ወቅት የዕምነት ቃሉን የሰጠ እንደሆነ፣ ሌላኛው ተከራካሪ ወገን በዚህ እምነት መሠረት ውሳኔ እንዲሰጠው መጠየቅ እንደሚችል እና ፍርድ ቤትም ሌላ በማስረጃ የሚረጋገጥ ነገር ቢኖርም እንኳን በታመነውና ውሳኔ እንዲሰጥበት በተጠየቀው ጉዳይ ብቻ ፍርድ መስጠት እንደሚገባው የፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ቁጥር 242 ሥር ተመልክቷል›› ይላል፡፡
በእነዚህ የሕግ አግባቦች መሠረት፤ ከላይ ያለው ጉዳይ ሲታይ፤ የአሁን አመልካች (ወይዘሮ ብርክቲ ግደይ) በብድር ውል ምክንያት የያዙትን ቤት በተመለከተ ለባንክ የከፈሉትን ገንዘብ እና ከቤቱ ጋር በተያያዘ ለተሠሩት ሥራዎች ያወጡትን ወጪዎች በክሳቸው ዝርዝር ውስጥ ገልፀዋል።ይህ ከሆነ ዘንድ የሥር ፍርድ ቤት አመልካች ቤቱን ለተጠሪዎች የሚመልሱበት ሁኔታ መኖሩን እስከተገነዘበ ድረስ አመልካች ከቤቱ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ገንዘብ አውጥቻለሁ ወይንም ከፍያለሁ በማለት በክስ ማመልከቻ ላይ እስከጠየቁ ድረስ የሥር ፍርድ ቤት አመልካች ይህ ገንዘብ እንዲከፈላቸው በዳኝነት ክፍል ውስጥ አልጠየቁም የሚል ከሆነ ስለጉዳይ በሕግ አግባብ ግልጽ እንዲያደርጉ ማድረግ የሚከለክለው ነገር አልነበረም፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ፤ ተጠሪዎቹ አቶ ሸምሱ ኑሪ እና ወይዘሮ ፈዲላ እስማኤል ባቀረቡት መልስና የቃል ክርክር አመልካች የጠየቀችውን ይህን ገንዘብ አልካዱም።ተጠሪዎቹ ከዚህ ቤት ጋር በተያያዘ ለባንክ የተከፈለውን ዕዳ እና ለቤቱ የወጣውን ወጪ አምነው ለመክፈልም ፈቃደኛ ናቸው።የሥር ፍርድ ቤትም ከፍ ሲል በተጠቀሰው የሕግ ድንጋጌ መሠረት አግባብነት ያለው ውሳኔ መስጠት ይገባው የነበረ ቢሆንም አልተገበረውም።
ይህም በመሆኑ ጉዳዩ ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ ችሏል።ሲጠቃለል የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በተጠሪዎች እምነት መሠረት ይህን ገንዘብ ለአመልካች እንዲከፍሉ ውሳኔ መስጠት ይገባው ነበር።ነገር ግን ወይዘሮ ብርክቲ በክሳቸው ክፍል ውስጥ ይህን ገንዘብ እንዲከፈላቸው አልጠየቁም፤ በሚል ምክንያት ውድቅ በማድረግ ውሳኔ መስጠቱ እና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ይህን ማረም ሲገባው ሳያርመው የሥር ውሳኔ በማጽናት መወሰኑ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመ መሆኑን በመጠቆም፤ ሰበር ችሎት ጉዳዩን በአንክሮ በመመርመርና በማጣራት የሚከተለውን የመጨረሻ ውሳኔ ወስኗል፡፡
ውሳኔ
1. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመለያ ቁጥር 61912 በ3/2/2009 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ እና ይህን ውሳኔ በማጽናት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመለያ ቁጥር 185781 በ23/5/2009 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመባቸው ስለሆኑ በፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ቁጥር 348 /1/ መሠረት ተሻሽሏል፡፡
2. የአሁን አመልካች በብድር ውል ምክንያት የያዙትን ቤት በተመለከተ ለባንክ የከፈሉትን እና ለቤቱ ያወጡትን ወጪ በድምሩ ብር 41 ሺ ብር እስካልተረጋገጠ ድረስ፣ የአሁን ተጠሪዎች ይህን ገንዘብ ለአመልካች ሊከፍሉ ይገባል፡፡ ነገር ግን የአሁን አመልካች በዚህ ገንዘብ መጠን የዳኝነት ክፍያ ያልከፈሉ እንደሆነ ባለው የዳኝነት ክፍያ ታሪፍ ደንብ መሠረት ሊከፍሉ ይገባል፡፡
3. የሥር ፍርድ ቤቶች አመልካች በብድር ውል ምክንያት የያዙትን ቤት ለተጠሪዎች እንዲያስረክቡ እና ተጠሪዎች ደግሞ በብድር ውሉ መሠረት የተበደሩትን ገንዘብ ለአመልካች እንዲከፍሏቸው በማለት የሰጡት የውሳኔ ክፍል አልተነካም፤ ጸንቷል፡፡
4. የዚህ ውሳኔ ግልባጭ ለሥር ፍርድ ቤቶች ይድረስ፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2015