ኢትዮጵያውያን አርበኞች ወራሪውን የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ድል ካደረጉ በኋላ በስደት እንግሊዝ ይገኙ የነበሩት ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አዲስ አበባ የገቡት ከ78 ዓመታት በፊት፣ በዚህ ሳምንት (ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም) ነበር።
ይህን ምክንያት በማድረግም በአርበኝት ትግሉ ወቅት የላቀ ሚናና ተሳትፎ ከነበራቸው አርበኞች መካከል የታላቋ አርበኛ ክብርት ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌን የጀግንነት ተጋድሎ በአጭሩ እናካፍላችሁ።
በ1888 ዓ.ም በጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ድል የሆነው የኢጣሊያ ጦር ቂሙን ሳይረሳ ሽንፈቱን ሳይዘነጋ ከአርባ አመታት በኋላ ዳግመኛ ለብቀላ በተመለሰበት አጋጣሚ በአዲስ አበባ ከተማ በአገር ተቆርቋሪ ዜጎች መስራችነት «የሀገር ፍቅር ማህበር» ተቋቋመ።
በማህበሩ በአባልነት ለመጀመሪያ ጊዜ ከተመዘገቡ ሴቶች መካከልም ጀግናዋ ሸዋረገድ ገድሌ አንዷና ግንባር ቀደም ነበሩ። እኚህ ሴት የቤተ- ክህነት ተማሪ የነበሩና ‹‹ትዳርም አልፈልግም›› ሲሉ ለምናኔ እየሩሳሌም ድረስ የተጓዙ ናቸው።
በአገራችን ታሪክ ከመጀመሪያዎቹ የባንክ ተጠቃሚዎችና የአክሲዮን ገዥዎች መካከልም እርሳቸው አንዷ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል። የሸዋረገድን ስም ይበልጥ እንዲደምቅ ያደረገው ታሪክ ግን የአርበኝነት ተጋድሎአቸው ነበር። ወራሪው የኢጣሊያ ጦር አገራችን እንደገባ የመጀመሪያ ተግባሩ ያደረገው ለዘመናት በድል ሲውለበለብ የቆየውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በማውረድ የራሱን ባንዲራ መተካትን ነበር።
በወቅቱ ይህን ድርጊት በአይናቸው የተመለከቱት ሸዋረገድ ግን ወራሪውን ጦር ሳይፈሩና ሳይሳቀቁ «አገሬ ተወረረች ፣ ተዋረደችም» ሲሉ አምርረውና ጮኸው ማልቀሳቸውን ተያያዙት። ሁኔታቸውን ያዩ የጣሊያን ሹማምንቶችም የእርሳቸውን ድርጊት እንደድፍረት በመቁጠር ለክስ አቀረቧቸው። ሸዋረገድ ግን በተለየ ወኔ ተሞልተው «አዎ አልቅሻለሁ፣ የአገሬን መወረርና መዋረድ ያወቅሁት የኛ ሰንደቅ አላማ ወርዶ የእናንተ ሲወለበለብ በማየቴ ነው ሰው ለእናት አገሩ ቢያለቅስ ነውሩ የቱ ላይ ነው?» ሲሉ እልህ በተሞላ ሁኔታ መለሱላቸው።
ሸዋረገድ አገራቸው በጠላት ጦር ዳግመኛ መወረሯ ከታወቀ ወዲህ «ህይወቴ አገሬ ናት» ሲሉ ለመታገል ቆረጡ። ለአርበኞች ስንቅ በማቀበል፣ መሳሪያ በመግዛትና በማዘዋወር፣ መረጃዎችን በማሰባሰብ፣ መድኃኒቶችን በመላክና ለተዋጊ ወገኖቻቸው የሞራል ድጋፍ በማበርከት የተጋድሎ አመታትን አሳለፉ።
የእሳቸው ድርጊት ግን ለጣሊያኖቹ ሰላም አልሰጠም። ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት በዘለለ ለክስ እንዲቀርቡ ወሰኑባቸው። እርሳቸው ግን ስለፈፀሙት ድርጊት ሁሉ ኩራት እንደሚሰማቸውና ይህንንም ያደረጉት ለአገራቸው ክብር ሲሉ እንደሆነ በድፍረት መናገራቸውን ቀጠሉ።
ሸዋረገድ ከፈፀሙት አኩሪ የጀግንነት ተጋደሎ ባሻገር በጦርነቱ ዋዜማ በ1927 ዓ.ም ለተቋቋመው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ንብረታቸውን ሸጠው በማስረከብ አገር ወዳድነታቸውን አስመስክረዋል።
ይህን በማድረጋቸውም በድጋሚ ከመከሰስ አልዳኑም። እሳቸው ግን ኢትዮጵያውያን ወይዛዝርት ከየቤታቸው እራፊ ጨርቆችን እንዲያሰባስቡ በማድረግ ለቁስለኞች እንዲላክ ያደርጉ ነበር። ከዚሁ ድርጊታቸው ጎን ለጎን የጠላት መረጃዎችን በማሰባሰብና ወደ አርበኞች በምስጢር እንዲደርስ በማድረግ ታላቅ ተግባር ፈፅመዋል።
አርበኛዋ ሸዋረገድ በሚፈፅሟቸው በርካታና አኩሪ ገድሎች ጥርስ የነከሱባቸው ጣሊያኖች ህይወታቸውን በእስር እንዲገፉና ቆይቶም ሞት እንዲፈረድባቸው ወስነው ነበር። ሆኖም አዚናራ ወደምትባልና ሰሜናዊ ምእራብ ወደምትገኝ ደሴት ታስረው እንዲቆዩ ፍርዱ በመቀየሩ የእስር ዘመናቸውን በደሴቲቱ እንዲገፉ ቁርጥ ሆነ።
ጀግናዋ አርበኛ ሸዋረገድ ግን የቦታ ለውጥና ርቀት አልበገራቸውም። ወኔያቸውን አጠናክረው ትግላቸውን ቀጠሉ። በእስር ቤቱ የሚቀርብላቸውን ምግብ በአሳሪዎቻቸው ፊት በመድፋትና ጦማቸውን ውለው በማደርም ተቃውሞ ማድረግ ጀመሩ። የእስር ቆይታቸው ከአንድ አመት በላይ እንደዘለቀ እንዲፈቱ በመወሰኑም አዲስ አበባ የመግባት እድል አገኙ።
አዲስ ዓለም ይገኝ የነበረው የጣሊያን ምሽግ ህዳር 5 ቀን 1933 ዓ.ም ሲሰበር ጠቃሚ መረጃዎችን ለአርበኞች በማሰባሰብና በርካታ እቅዶችን በመንደፍ ታላቁን ድርሻ የሸፈኑት ሸዋረገድ ነበሩ።
ምሽጉ ከተሰበረም በኋላ ደጀን መሆኑን ትተው ወደ ውጊያ ለመግባት በመወሰናቸው ከሻለቃ በቀለ ወያና ከደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ጦር ጋር ተሰልፈው ጠላትን ተፋልመዋል። በጦርነቱ የአራት ሰአታት ውጊያ ላይ ጠላት በጣለው ድንገተኛ አደጋ ከታላቅ ተጋድሎ በኋላ የተማረኩት ሸዋረገድ ዳግመኛ በጣሊያኖች እጅ በመውደቃቸው የፊጥኝ ታስረው ወደእስር ተወረወሩ።
የጀግኖች አርበኞች ትግል ተጠናክሮ የጠላት ጦር በመጣበት እግሩ በታላቅ ውርደትና በአሳፋሪ ሽንፈት በ1933 ዓ.ም ከአገራችን ሲባረር ታላቋ አርበኛ ሸዋረገድ ገድሌም ነፃ ሆነው ተፈቱ። ከዚህ በኋላ ለእኚህ ሴት ህይወትን በነፃነት ማጣጠም ታላቅ ትርጉም ነበረው። ቀድሞ የጀመሩትን አርበኞችን የመርዳት ተግባር አጠናክረው የበጎ አድራጎት ስራን ቀጠሉበት።
በንግዱ ዘርፍ ተሰማርተውም በርካቶችን እንደጠቀሙም ይነገርላቸዋል። ጥቅምት 22 ቀን 1942 ዓ.ም ይህችን አለም የተሰናበቱት ታላቋና አይረሴዋ አርበኛ ሸዋረገድ ገድሌ የመሞታቸው ዜና እንደተሰማ ህዝቡ እንዲህ ብሎ አንጎራጉሮላቸው ነበር።
እናንት ወጥ ቤቶች በርበሬ ቀንጥሱ፣
እናንት ስጋ ቤቶች ሰንጋውን ምረጡ፣
ሸዋረገድ ገድሌ ለገና ሲመጡ።
ቤተሰቧ ሰፊ ገናና ጥምቀት፣
ሸዋረገድ ገድሌ እንደምን ትሙት።
ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ
ለኢትዮጵያ ነፃነት ሰማዕታት !
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25/2011
አንተነህ ቸሬ