የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በእጅጉ ከሚፈልጋቸው ግብዓቶች መካከል የግንባታ ማጠናቀቂያ በመባል የሚታወቁት ምርቶች ይጠቀሳሉ። የግንባታው ዘርፍ እየተስፋፋ ከመምጣት ጋር ተያይዞ ሀገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው የሴራሚክ ውጤቶች ትፈልጋለች። ለእዚህ ከሚያስፈለጉት ምርቶች በጣም የተወሰነውን በሀገር ውስጥ ብትሸፍንም፣ በአብዛኛውን ግን ከውጭ በማስገባት ስትጠቀም ነው የቆየችው።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ባለፈው ታህሳስ ወር ባካሄደው አንድ አውደ ጥናት ላይ በቀረበው ጥናታዊ ጽሁፍ የተጠቆመውም ይህንን ያመለክታል። በመድረኩ እንደተጠቆመው፤ ከ2006 እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ ሶስት ነጥብ 34 ቢሊዮን ብር የሚገመቱ የተለያዩ አይነት የሴራሚክስ ምርቶች በሀገር ውስጥ ተመርተው ግብይት ተፈጽሞባቸዋል። በአንጻሩ ከ2006 እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ አምስት ነጥብ 79 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የሴራሚክስ ምርት ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቷል። ይህም የሚያመላክተው ሀገሪቱ ሴራሚክ ለማስገባት ብቻ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ታወጣለች።
በኢትዮጵያ የማዕድን ግብዓትን በስፋት በመጠቀም የተለያዩ የሴራሚክ ምርቶችን በማምረት ከሚታወቁት አምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል አንጋፋው የታቦር ሴራሚክ አክሲዮን ማህበር (ኩባንያ) አንዱ ነው። ኩባንያው አራት ዋና ዋና ፋብሪካዎች ያሉት ግዙፍ ኩባንያ እንደሆነም ከኩባንያው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ከምርቶቹ ውስጥም የሸክላ ንጣፍ (ሴራሚክ)፣ የመታጠቢያ (ባኞ ቤት)ና የገበታ እቃዎች፣ ለኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚውሉ ምርቶች ይገኙበታል። ምርትና አገልግሎቶቹንም ለመንግሥታዊ ተቋማት በስፋት በማቅረብ ይታወቃል።
የታቦር ሴራሚክ አክሲዮን ማህበር (ኩባንያ) ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቅሩ ተስፋዬ እንደገለጹልን፤ ኩባንያው በዓመት ከአስር ሺ ቶን በላይ ምርቶችን ለገበያ ያቀርባል። በአሁኑ ጊዜም ከአንድ ሺ በላይ የሰው ኃይል አለው። በከፍተኛ ወጪ ከውጭ በግዥ የሚገቡ የሴራሚክ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት አስተዋጽኦ ከሚያበርክቱ የአምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል። አሁን ካለው አበርክቶ ከፍ ለማድረግም የማስፋፊያ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል።
ከ2016ዓ.ኋም በኃላ ዓመታዊ አስር ሺ ቶን የማምረት አቅሙን ወደ 18ሺ ቶንና ከዚያም በላይ ለማድረስ አቅዶ እየሰራ ይገኛል። ኩባንያው እስካሁን ሲያከናውናቸው የነበሩትንም ሆነ የወደፊት እቅዶቹንም ለማሳካት ለግብዓት ከሚጠቀማቸው የማዕድን አይነቶች መካከል ሲልድ ስፓር፣ካኦሊን፣ ሳልክ የተባሉት ይጠቀሳሉ፤ የማዕድን ግብዓቶቹ ውበትንም ለመጨመር የሚውሉ ናቸው። ለግንባታ ማጠናቀቂያ ለሚውለው ታይልስ ለተባለው ምርት የሚያገለግል የማዕድን ግብዓት ብቻ ወደ 400 ቶን በቀን ይጠቀማል።
የሚጠቀምባቸው ግብዓቶች በሀገር ውስጥ የሚገኙ ቢሆኑም፣ ከእነዚህ ማእድናት ለረጅም ጊዜ ሲጠቀም የቆየው ከ45 በመቶ የበለጠ አይደለም። በግዥ ከውጭ የሚገባውን ግብዓት ነው በስፋት ሲጠቀም የቆየው።
በግብዓት አጠቃቀሙ ላይ በውስጥ አቅም ጥናት በማካሄድ፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ዜጎች ከዘርፉ ምሁራን ጋርም በመምከር፣ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋርም በመሥራት ሀገር ውስጥ የሚገኘውን የማዕድን ተደራሽነት በማጥናት የጥሬ ዕቃ አቅርቦቱ በሀገር ውስጥ የሚሆንበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በኩባንያው በኩል ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል።
ኩባንያው የጥሬ እቃ አቅርቦትን በሀገር ውስጥ ለመተካት በሰራው ሥራ ውጤት ማምጣት መቻሉን አቶ ፍቅሩ ጠቅሰው፣ የሀገር ውስጥ ግብዓትን ይጠቀም ከነበረበት ከ45 በመቶ አሁን ከ83 ከመቶ በላይ ከፍ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል። ግብዓቱን መቶ በመቶ በሀገር ውስጥ ለመጠቀም ጥረቱ እንደሚቀጥልም አረጋግጠው፣ ስኬት ላይ ለማድረስም ኩባንያው በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የኩባንያው የማዕድን ጥሬ እቃ አቅርቦት መዳረሻዎችን በተመለከተም አቶ ፍቅሩ እንዳስረዱት፤ ኦሮሚያና ሲዳማ ክልሎች የኩባንያው የግብዓት መዳረሻዎች ናቸው። በተለይ ደግሞ ለምርት ግብዓት ከሚውሉት መካከል ለግንባታ ማጠናቀቂያ የሚውለው ታይልስ ኩባንያው ከሚያመርታቸው ምርቶች ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ ሲሆን፣ ለምርት የሚሆነውም ግብዓት በስፋት የሚያገኘው ከኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን አሬሮ ወረዳ እንዲሁም ከሲዳማ ክልል ነው።
በሁለተኛ ደረጃ ኩባንያው ለግብዓትነት የሚጠቀመው ማዕድን ሳልክ የሚባለው ነው። ማዕድኑንም ከኦሮሚያ ክልል ያቤሎ አካባቢ ይጠቀማል። ሲዳማ ክልልም በተመሳሳይ የማእድን ሀብቱ በመኖሩ አማራጮች አሉት። ሀዲያ ዞን ውስጥ የሚገኘውን ካኦሊን የተባለውን እንዲሁም ምርቶቹ ከተመረቱ በኋላ ለማስዋቢያነት የሚውሉ የማዕድን አይነቶች ደግሞ ከሲዳማ ክልል አሮሬሳ አካባቢ እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ቦረና መስመር ላይ እስከ ሞያሌ ካለው አካባቢ ይጠቀማል። ኩባንያው ማዕድናቱ ከሚገኙባቸው አካባቢዎች በመጠቀም የኢንዱስትሪውን ሥራ በማጠናከር ላይ ይገኛል።
ኩባንያው የሚጠቀማቸውን የማዕድን ጥሬ ዕቃ ግብዓቶች ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችለውን ተግባር እያከናወነ መሆኑን አቶ ፍቅሩ ጠቅሰው፤ እስከ አሁን መቶ በመቶ ማሳካት ያልተቻለው የጥናት ሥራ ባለመጠናቀቁ መሆኑን ይገልጻሉ። በሂደት የኩባንያው የግብዓት መዳረሻ ሙሉ በሙሉ ከሀገር ውስጥ ይሆናል ሲሉም ጠቁመዋል።
‹‹ግብዓቱ በሀገር ውስጥ እንዲሟላ ማድረግ ፋይዳው ከፍተኛ ነው። በሀገር ውስጥ እንዲተካ ማድረግ ተጠቃሚ የሚያደርገው ኩባንያውን ብቻ ሳይሆን፣ ለሀገር የሚኖረው አስተዋጽኦም ከፍተኛ ነው›› ሲሉ ገልጸዋል። ይህን ለማድረግ ግን የተጠናከረ ሥራ እንደሚጠይቅ ነው የተናገሩት። ስራው በጥናት መደገፍ እንደሚኖርበትና ኩባንያውም በጥናት እንደሚያምን ጠቁመው፣ በዚህ ረገድ ኩባንያውም እንደሚሰራ፣ ከዚሁ አኳያ የሚካ ሄድ ስራንም እንደሚያበረታታ አስታውቀዋል።
ኩባንያው ግብዓቶቹን በሁለት መንገዶች አግኝቶ እንደሚጠቀም አቶ ፍቅሩ ተናግረዋል፤ አንዱ ኩባንያው በራሱ የሚያመርትበት ሁኔታ መሆኑን ይገልጻሉ። ስራው ከፍተኛ ቁፋሮ ማድረግን የሚጠይቅና በሌላ አካል መሠራት የማይቻል ሆኖ ሲገኝ ኩባንያው በራሱ እንደሚያመርትም ነው የተናገሩት። በሌላ በኩል ደግሞ በማህበር ተደራጅተው ከሚያምርቱ የውል ስምምነት በማድረግና የማምረት ሂደቱ ላይ ተግባቦት በመፍጠር በሚደረግ ርክክብ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኩባንያው በዚህ መንገድ እየተጠቀመ እንደ ሀገር የተያዘውን ከውጭ የሚገባውን የማዕድን ውጤት በሀገር ውስጥ የመተካት ግብ ለማሳካት ጥረት እያደረገ ቢሆንም፣ ኩባንያውን ጨምሮ በዘርፉ ላይ የሚገኙ የማዕድን ግብዓት የሚጠቀሙ አምራች ኢንዱስትሪዎች የበለጠ እንዲበረታቱ ለኢንዱስትሪ ግብዓት ማዕድን ልማት የሚሰጠው ትኩረት ከፍ ማለት እንዳለበትም አስገንዝበዋል። መንግሥት አሁን ለማዕድን ዘርፉ የሰጠውን ትኩረት በዘላቂነት ማስቀጠል ይኖርበታል ሲሉም አቶ ፍቅሩ ጠቁመዋል።
በልማቱ ላይ የተሰማሩትን የተወሰኑ አምራች ኩባንያዎችን ታሳቢ ያደረገ ስራ ብቻ መሰራት እንደሌለበት ገልጸው፣ ስራው ተደራሽነትን ያሰፋ ሲሆን የግብዓት አቅርቦቱን ከማስፋት በተጨማሪ የአልሚዎችም ኢኮኖ ሚያዊ ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። አምራች ኢንዱስትሪዎች የማዕድን ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ የመጠቀም ፍላጎትን እያሳደጉ ሲሄዱ ዘርፉን በቅርበት የሚመሩ ተቋማትም ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የሚጠበቅባቸውን ተልእኮ መወጣት ይኖርባቸዋል።
የሲዳማ ክልል ለሴራሚክ ምርት ግብዓት ከሚገኝባቸው ክልሎች አንዱ ነው፤ የታቦር ሴራሚክ ፋብሪካም የሚገኘው በዚሁ ክልል ነው። ፋብሪካው በግብዓትነት የሚጠቀማቸውን ማእድናት ከሚገዛባቸው ክልሎች አንዱ ይሄው ክልል ነው።
የሲዳማ ክልል የማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን መጩካ እንደሚሉት፤ በሲዳማ ክልል ለግንባታው ዘርፍ በግብዓትነት የሚያገለግሉ ድንጋይ፣ አሸዋ፣ ግራናይት፣ እምነበረድ፤ እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ፓልክ፣ ካኦሊን፣ የድንጋይ ከሰል፣ ድሎማይት የመሳሰሉ የማዕድን አይነቶች በስፋት ይገኛሉ።
አቶ መስፍን እንዳሉት፤ የኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ማእድናት በሚመረትባቸው አካባቢዎች ላይ አሁን ትልቅ ማነቆ የሆነው የገበያ ችግር ነው።በአካባቢው ላይ ትልቁ ግብዓት ተቀባይ ታቦር ሴራሚክ ኩባንያ ነው። እርሱም ቢሆን አንዴ በብዛት ከወሰደ በኋላ ድጋሚ ለመግዛት ረጅም ጊዜ ይቆያል። ዳን የሚባል ፋብሪካም ቢሆን ከተወሰነ ግብዓት ውጭ የሚገዛ ባለመሆኑ ግብይቱ ይቀዘቅዛል። ይህን ተከትሎም ሰፊ የገበያ እድል ባለመኖሩ አምራቾች በተደጋጋሚ ቅሬታ ያነሳሉ።
የማዕድን ግብዓት የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች በብዛት አለመኖርና ያሉትም ቢሆኑ ከአካባቢው የራቁ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ የገበያ እድሉ ጠባብ እንደሆነ አቶ መስፍን ይናገራሉ፤ አምራቾች ወደ ፋብሪካዎች ለመሄድ አቅም ማጣት፣ፋብሪካዎችም ግብዓቱን ከአካባቢያቸው የሚያገኙበት ምቹ ሁኔታ መኖር ጋር በተያያዘ ሩቅ ሄደው የማይገዙ መሆናቸውን በምክንያትነት ይጠቅሳሉ። የማዕድን ልማቱ በሚከናወንባቸው ሥፍራዎች የመሠረተ ልማት አለመሟላትም ሌላው ተግዳሮት እንደሆነ ይጠቁማሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የኤጀንሲው ዋና ተግባር በሥራና ክህሎት ተቋም አማካኝነት ተደራጅተው ለሚመጡ ማህበራት የልማት ቦታ ማመቻቸት ቢሆንም፣ ያለውን የገበያ ችግር ለመፍታት በተለያየ መንገድ ከባለድርሻ አካላት ጋር አብሮ ለመሥራት ጥረት እያደረገ ይገኛል። በዚህም በሚፈለገው ልክ ውጤታማ ሊሆን ባይችልም አሁን ባለው ሁኔታ ከአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለግንባታው ዘርፍ የሚቀርበው የማዕድን ግብአት የተሻለ ነው።
ዘርፉ እንደ ስካቫተር ያሉ የመቆፊያ ማሽን፣ ሎደርና ለጭነት አገልግሎት የሚውሉ ትላልቅ ተሽከርካሪዎች እንደሚፈልግ ጠቅሰው፣ ይህም በማህበራት አቅም የማይቻል መሆኑን ነው የተናገሩት። በዚህ ምክንያትም ለስራ የሚሆን መሳሪያ ችግር መኖሩንም ጠቁመዋል።
አቶ መስፍን የአጭር ጊዜ መፍትሄ በኪራይ አገልግሎት መሥራት እንደሆነና ማህበራቱም በዚህ መንገድ እየሰሩ እንደሆነ አመልክተዋል። ኤጀንሲው ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በተለይም ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከማዕድን ሚኒስቴር ጂኦሎጂ ክፍል ጋር በቅርበት በመሆን በአካባቢው ላይ ያለውን የማዕድን ሀብት በጥናት ለመለየት እየሰራ መሆኑም አስረድተዋል።
በመግቢያው አካባቢ በተጠቀሰው የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር መድረክ ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዚህ ዘርፍ ተስፋ ሰጪ ስራዎችን መስራት እንደሚቻል ፍንጭ እየታየ ስለመሆኑ በመድረኩ ተጠቁሟል፤ በዚህ በጀት ዓመት በተካሄደው የማዕድን ኤክስፖ ላይ ሌሎች ሴራሚክ የሚያመርቱ ኩባንያዎች የግንባታ ማጠናቀቂያዎችን ወደ ማምረት እየገቡ መሆናቸውም ተገልጧል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ መሸፈን የሚቻልበት እድል መኖሩም ተመልክቷል።
በኦሮሚያ ክልል ዱከም ከተማ ላይ አንድ ሴራሚክ ማምረቻ ፋብሪካ ወደ ስራ እየገባ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በአማራ ክልል በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በአረርቲ ከተማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኘው የአረርቲ ሴራሚክ ፋብሪካም እንዲሁ ወደ ስራ መግባቱ ተጠቁሟል። አረርቲ ሴራሚክ ፋብሪካ በቀን እስከ 20 ሺህ ሜትር ስኩየር ሴራሚክ የማምረት አቅም እንዳለውም ተገልጿል።
እነዚህ ሁለቱ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ወደ ማምረት ከገቡ የሴራሚክ ችግሩን በማቃለል ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ታምኖባቸዋል፤ በሀገሪቱ ያለውን የሴራሚክ ምርት እጥረት ለመፍታት ሁለቱ ፋብሪካዎች መጨመራቸው ብቻውን ግን በቂ አይደለም። ተጨማሪ ፋብሪካዎችን ማቋቋምና ወደ ስራ ማስገባት እንደሚያስፈልግ በመድረኩ የተጠቆመ ሲሆን፣ ለፋብሪካዎቹ የሚያስፈልገው ሙሉ ጥሬ እቃ ሀገር ውስጥ እንዳለም ተመልክቷል።
እንደሚታወቀው የማእድኑ ዘርፍ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የአስር ዓመት መሪ እቅድ ለምጣኔ ሀብቱ እድገት ፋይዳቸው ከፍተኛ ተብለው ከተመረጡት አምስት የምጣኔ ሀብት ምሰሶዎች መካከል አንዱ ነው። ለዚህም ሲባል ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።
የማእድን ዘርፉ እንደ ወርቅ ባሉት ማእድናት ላይ በሕገወጥ ግብይት የተነሳ ፈተና ውስጥ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከሕገወጥነቱ ጋር በተያያዘም በ2015 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ከዘርፉ መገኘት ያለበት የውጭ ምንዛሬም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ ታይቶበታል። መንግሥት በዚህ በኩል ያለውን ችግር ለመፍታት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው።
የማእድን ዘርፉ ለኮንስትራክሽን እና ለኢንዱስትሪ ዘርፎች የሚውል ግብዓት የሚያቀርብም ነው። ለማእድን ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት እንዳለ ሆኖ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ተከትሎ በኢንዱስትሪዎች ላይ እየታየ ባለው መነቃቃት የማእድን ዘርፉም ተጠቃሚ ሊሆን የሚችልበት እንዳለ ይታመናል። የሴራሚክ ፋብሪካዎችም የኢንዱስትሪ ግብዓት ማእድናት አምራቾችም ይህን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም በትኩረት መስራት ይኖርባቸዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2015