ወፈፌው ይልቃል አዲሴ፣ ዛሬም በሌሊት ተነስቶ ሰፈራችን ከሚገኘው ዋርካ ስር ቆሞ ይጮሃል:: የዛሬው ጩኸት በውዝዋዜ የታጀበ በመሆኑ ግራ የገባቸው የሰፈራችን ሰዎች ከመቅጽበት ወደዋርካው ተሰብስበው በዋርካው ስር ባሉ ድንጋዮች ተኮለኮሉ::
የሰፈራችን ሰዎች በመሰብሰብ ላይ እያሉ ይልቃል አዲሴም… ‹‹ጥሩ የሰሩ ሰዎች ቢሞቱም ቢኖሩም አይጨነቁም! አለ ሶቅራጥስ እያለ›› ይጮህ ነበር::
የሰፈራችን ሰዎች ወደ ዋርካው ተሰባስበው ቦታቸውን መያዛቸውን ከተመለከተ በኋላ ይልቃል አዲሴ፣ ራሱን ለንግግር እያዘጋጀ ‹እህ..እህ…› ብሎ ጉሮሮውን ጠራረገ። ንግግሩንም እንዲህ ሲል ጀመረ፤ ጦርነት የሚያስከትለውን ጉዳት በምስራቅ በምትገኘው የታላቋ አገር ነዋሪ ለሆኑት ለእኛ ሰፈር ሰዎች መናገር ለክርስቶስ ክርስትናን ወይም ለነብዩ መሐመድ እስልምናን እንደመስበክ እቆጥረዋለሁ:: ስለጦርነት አስከፊነት ለማስተማር በምስራቅ በምትገኘው የታላቋ አገር ታሪክ የመሰለ የመርጃ መሳሪያ ሊኖር አይችልም::
በምስራቅ የምትገኘው ታላቋ አገር ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በጦርነት ስትፈተን ቆይታለች:: በቅርቡም የዚህ ዓይነት ፈተና ገጥሟት የነበረ ቢሆንም በመንግሥቷ ብርታት እና በሕዝቧ ትብብር ተከስቶ የነበረው ጦርነት ወደሰላም ፊቱን እንዲያዞር ተደርጓል:: ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ምስራቅ የምትገኘው ታላቋ አገር ያለችበት አህጉር የራሱንም ሚና በመጫወቱ ነው::
እርግጥ ነው ይህች በምስራቅ በምትገኘው ታላቋ አገር፣ በርካታ አሰቃቂ እና አውዳሚ ጦርነቶች ተካሂደዋል። ይሁንና ሲነኳቸው የማይወዱት ልጆቿ የመጣውን ጠብ አጫሪ ሁሉ በመጣበት አኳኋን ብቻ ሳይሆን ድባቅ መትቶ የመመለሱንም የአባቱን ብልሃት እየተገበረ ልኩን አሳይቷል:: ነገር ግን ጦርነት መቼም ጦርነት ነውና ካሳለፍነው ፈተና ልንማር የተገባ ነው:: እኛ የምስራቋ ኮከብ ልጆች እነዚያ ጦርነቶች ካስከተሏቸው ጉዳቶች ተምረን የወደፊት ያማረች፣ የበለጸገች እና ከጦርነት የጸዳች አገር ከመፍጠር ይልቅ ቀደም ብሎ በተደረጉ ጦርነቶች የነበሩ ጀብዱዎችን እንደጥሩ ተሞክሮ እንደ ጥዑም ዜማ መላልሰን እያወራን ለሌላ ጦርነት ለመዘጋጀት ስንታትር እንታያለን::
ሌሎች አገራት ግን አስተናግደዋቸው ከነበሩ ጦርነቶች ከቀሰሟቸው ልምዶች ተነስተው በርካታ ሳይንሳዊ ፈጠራዎችን ፈጥረዋል:: አሁን ላይ በዓለማችን የሚታዩ በርካታ ሳይንሳዊ ፈጠራዎች እና አሠራሮች ከጦርነት ማግስት የተፈጠሩ ስለመሆናቸው ምሁራን ያስረዳሉ::
ለምሳሌ የዓለማችን በርካታ ሳይንሳዊ ግኝቶች እና አሠራሮች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተፈጠሩ ሲሆኑ፣ በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት የተፈጠሩ ሳይንሳዊ ግኝቶችም በርካታ ከመሆናቸውም ባሻገር የዓለማችንን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች የቀየሩ መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው::
እኛ ግን ከጦርነቶች ብዛት የተማርናቸውን እውቀቶች ለጥሩ ነገር ከመዋል ይልቅ ዛሬም ራሳችንን ብቻ ጀግና እያደረገን በመሳል እና ሌላውን ደግሞ በማንኳሰስ መመጻደቁ ይቀናናል:: የዚህ ችግር ምንጩ በርካታ ነው:: የመጀመሪያው ዋና ምክንያት የጀብደኝነት አባዜ ነው:: ይህ የጀብደኝነት አባዜ ደግሞ የክህሎት ክፍተት እንዳለ የሚያሳይ ነው::
ሌላው ምክንያት ደግሞ በእርግጥ ይህች የምስራቋ ኮከብ ፈላጊዋ ብዙ ነው፤ ምክንያት ብትሉኝ ደግሞ የምስራቋ ኮከብ ጂኦፖለቲካዊ መገኛዋ ጋር ተያይዞ የመጣ ጉዳይ ነው:: በተለይ ካለችበት መልካምድራዊ አቀማመጥ የተነሳ የውጭ ኃይሎች ጫና የሚበረታባት አገር ናት:: ይህ የውጭ ኃይሎች የሚፈጥሩት ያልተገባ ጫና የምስራቋን ኮከብ ለአሰቃቂ ጦርነት ሲዳርጋትም ተመልክተናል::
በእርግጥ የምስራቋ ኮከብ በምስራቅ አፍሪካ መገኘቷን እንደ ትልቅ አጋጣሚ ተጠቅማ ከበርካታ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ማሳደግ እና ለጥሩ ነገርም ማዋል ትችል ነበር:: ከዚህ ጋር ተያይዞ ምስርን እንደጥሩ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል::
ምስር በብድር እና በእርዳታ ያገኘቻቸውን መዋዕለ ንዋዮች ተጠቅማ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ አፍሪካን እና አውሮፓን እንዲሁም ምዕራብ አውሮፓን ከመካከለኛው እና ከሩቅ ምስራቅ አገራት ጋር የሚያገናኛቸውን የስዊዝ ካናልን ገነባች:: ይህ ካናል የዓለማችን ሁነኛ የንግድ መስመር ነው::
ይህን ተከትሎ በርካታ የዓለም አገራት የምስርን ወዳጅነት ለማግኘት በእግር በፈረስ ላይ ታች አሉ:: የዓለም ኃያላን አገራት ሳይቀሩ ምስርን ‹እንነጠፍልሽ› አሏት:: ምስር ራሴን አመመኝ ካለች ኃያላኑ በሙሉ ምስርን ለመምሰል ከሚያደርጉት ጥረት የተነሳ ‹ፀጉራችንን ቁርጥማት አመመን› ለማለት ሁሉ ይዳዳቸዋል:: በአጠቃላይ ምስር ስትነካ ጠጉራቸው እንደ ተበሳጨ ድመት ወደላይ ይቆማል::
በነገራችን ላይ የዓለም አገራት ሁሉ ለምስር የሚያሸረግዱላት ስዊዝ ካናል ስላላት ብቻ አይደለም:: የምስር ሰዎች ባላቸው ትብብር መናበብ ሳቢያ የአገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ስለሚችሉ ነው:: ምስራቃውያን ያላቸውን አንድነት እና የስዊዝ ካናል ስትራቴጂካዊ ተፈላጊነት ተጠቅመው በዓለማችን ፖለቲካል ኢኮኖሚ ሁነቶች ላይ የሚያሳድሩት ጫና ቀላል የሚባል አይደለም::
የእኛ አገር የምስራቋ ኮከብም የምትገኝበት ቦታ የዓለምን ፖለቲካል ኢኮኖሚ መቀየር የሚያስችል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በርካታ የዓለም አገራት በቀጣናው ላይ ዓይናቸውን ጥለውበታል:: ዓይናቸውን ጥለውባት ብቻ አልቀሩም! በተለይም ኃያላኑ የወታደራዊ ቤዝ ለመገንባትም ሲራኮቱ እየተመለከትን ነው:: ነገር ግን የእኛ አንድነት ከመላላት ይልቅ ጠበቅ ሊል ይገባዋል:: ያለማበር የሚያስከትለው ዳፋ መኖሩ መቼም ለእናንተ አይነገርም::
ኅብረትን ለመልካም ሥራ እንዲሁም ለአገር ልማት ብናውል ተጠቃሚዎቹ እኛው ነን:: የእኛ ሁኔታ ግን በተገላቢጦሽ እየሆነ መቸገራችን ነው:: ሁሉም በየፊናው አድራጊ ፈጣ ልሁን በማለት ‹‹አሻፈረኝ›› ማለቱን ማቆም አለበት:: ለምን ቢባል ለአገር ሲባል ነው መልሴ:: አገራችን በውስጥም ሆነ በውጭ ኃይሎች ከዚህ በኋላ የማትታለል እንደሆነችም በግልጽ ልንተባበር የተገባ ነው:: የትኛውም ኃይል ጣልቃ ሊገባብንም ሆነ አገር እንደ ጠንካራ አገር እንዳትቀጥል የማድረግ ስልጣን የለውም፤ ይህ የሚሆነው ግን የራሳችን አንድነትና መተሳሰብ ሲኖር ነው::
የምስራቋ ኮከብ ዜጎችን አንድነት መላላት የተመለከቱ ምዕራባውያን በቀጣናው ያላቸውን ፍላጎት ያለማንም ከልካይ ለማስፈጸም እንዲረዳቸው ቀደም ባሉት ጊዜያት ያደረጉትን መናገር ለቀባሪው እንደማርዳት ይቆጠርብኛል:: ስለዚህም አሁንም ቢሆን አንድነታችንን ለማጠናከር ጊዜው አልረፈደም:: የተጀመሩ ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች የመጡትም በመነጋገር እና በመደማመጥ ነው:: ይህን ኅብረት ስንጥል የምናንጠለጥለው ጦርነትን ነው::
ጦርነት ደግሞ እንደምታውቁት እሳት ነው፤ ልክ እንደ እሳት ሁሉ ሁሉንም አግበስብሶ የሚበላ ነው:: መርጦ የሚያቃጥል አለመሆኑም ይታወቃል:: እሳት የሚያቃጥል ብቻ ሳይሆን ሕይወትንም የሚነጥቅ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም:: አለመግባባት በውይይት ይፈታል፤ ባለፉት ጊዜያት ሲያጋጥሙ የነበሩ አለመግባባቶች የፈጠሩት ጦርነት መማሪያችን ሊሆን የግድ ነው::
እርስ በእርስ ከሚያናጭ አባዜ መውጣትና ዘመኑ የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ መታትር አማራጭ ሳይሆን የግድ የሚል ነው:: የምስራቋ ኮከብ ህዝቦች እርስ በእርሳቸው ጤናማ የሆነ ግንኙነትን በማስቀጠሉ በኩል የሚታሙ አይደሉም:: መልካሙንም መንገድ በመጀመር እና ወገናቸውንም በማስጀመር በኩል እያሳዩ ያለው ፍላጎት የሚናቅ እንዳልሆነ ልብ የምትሉ ይመስለኛል:: በየዘመኑ ለዜጎቻችን አርዓያ የሆኑ ምርጦች እንዳሉን ሁሉ አሁንም መኖራቸው የሚካድ አይደለም:: …ብሎ ይልቃል አዲሴ እየተናገረ እያለ፤ ሁሌም ሳይፈቀድለት የሚናገረው አብሿሙ ክንፈ ጉደታ እንደተለመደው ዛሬም የይልቃልን ንግግር አቋረጠው::
አብሿሙ ክንፈ ጉደታ፣ የይልቃልን ንግግር ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፈው ገልጾ፤ ንግግሩን እንዲህ ቀጠለ… እውነት ለመናገር የእኛ ችግር ጦርነት ነው!? አልነበረም:: ግን ምን ዋጋ አለው! አንዳንዱ የጦርነት ጥማት አለው፤ ይሁንና ጦርነትንም ሆነ አለመግባባትን ወዲያ መጣል ከችሎታችን በላይ አይደለም::
ወንድሜ ይልቃል እንደተናገረው፤ ምስር ያላትን ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ተጠቅማ ሁሉን በእጇ ሁሉን በደጇ ማድረግ ችላለች:: እኛም ያለንን ጠቃሚ ጂኦፖለቲካል አቀመማጥ ተጠቅመን በዓለም አቀፉ ፖለቲካ ጨዋታ እንደምስር የራሳችንን ተጽዕኖ መፍጠር እንችል ነበር። ነገር ግን ይህንን ለማድረግ ትብብሩም መግባባቱም ያስፈልጋል:: አንዳንዴ ክፍተታችን ባለመስማማት ብቻ የሚገለጽ እንዳልሆነ ልብ ይሏል:: የእኛ ፖለቲከኞች ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም ብለው ለታሪካዊ ጠላቶቻችን ሎሌ ለመሆን ሲራኮቱ መታየታቸውም የሚታበል አይደለም::
ጥንት ከነበሩ የምስራቋ ኮከብ ፖለቲከኞች መካከል የምስራቋ ኮከብ የምትገኝበትን ጂኦፖለቲካል አቀማመጥ ተጠቅመው ለአገራቸው ጥቅም ከመስራት ይልቅ ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ህዝብን ከህዝብ እያባሉ አገሪቱን በማያባራ ጦርነት ውስጥ በመዝፈቅ ለውጭ ጠላቶቻችን የጥፋት ዱላ ማቀበል የሚቀናቸው መኖራቸው ሐሰት አይደለም::
አንዳንዴ ብቻዬን በተመስጦ ቁጭ ብዬ ዙሪያ ገባውን ስመለከት የምስራቋ ኮከብ ህዝቦች እና የፖለቲካ ሰዎች ከቀደመ ስህተታቸው ለመማር የሚፈልጉ አይመስሉም:: አለመግባባትን እንደ ቁርስ፣ ምሳ፣ እራታቸው የሚመለከቱ ይመስለኛል:: አለመስማማት ከሌለ አትኖሩም የተባሉ ይመስላሉ::
ሌላው ይቅርና የምስራቋ ኮከብ ልጆች አለመግባባትና እርስ በእርስ አለመተማመን አንዱን ነጣቂ ሌላውን ተነጣቂ ሊያደርገው እንደሚችል ስለምን አይገነዘቡም? ስል እጠይቃለሁ:: እሺ መረዳት አልተቻለም? ይባል፤ እንዴት ጉዳቱ ሊታያቸው አይችልም?
እሺ ከዚህ መማር አቃተን እንበል፤ እንዴት በዘመነ መሳፍንት ከነበረው የእርስ በርስ ግጭት እና እልቂት ትምህርት ወስደን አገራችንን ከግጭት በማራቅ ስለልማት እና ሰላም ብቻ ማውራት ስለምን ከበደን? አሁንም ይህ አባዜ እንደክፉ ልክፍት ተጣብቶ አልለቅ ብሎ ተከትሎናልና ልንለየው ግድ ይለናል::
አለመግባባትን በመግባባት መቀየር ወጪ የሚያስወጣ ጉዳይ አይደለም ብሎ አብሿሙ ክንፈ ጉደታ ወደ መቀመጫው ተመለሰ:: ይልቃል አዲሴ እንደገና ንግግሩን የጀመረው ክንፈ ጉደታን በማመስገን ነበር::
‹‹ሁሉንም ነገር ክንፈ ጉደታ ተናግሮታል፤ እኔም አንድ ነገር ልበልና ንግግሬን ላብቃ፤ ንግግር ጀመረ:: ‹‹የምስራቋን ኮከብ ተጣብቶ አልለቅ ያለውን ክፉ ያለመግባባት በሽታ የሚያሽር መድኃኒት በመግባባት ተባብሮ መስራት ነው:: ብሎ ንግግሩን ሲጨርስ የሰፈራችን ሰዎችም ለይልቃል ያላቸውን አድናቆት በጭብጨባ ገልጸው ስብሰባው ተበተነ።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2015