መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ችግሮችን ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሔ እርምጃዎች መካከል ከአንድ ዓመት በፊት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም ይፋ የተደረገው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው። ንቅናቄው በሀገር አቀፍ ደረጃ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እድገት ተስፋ ሰጪ የሆኑ ውጤቶች እንደተመዘገቡበት ተገልጿል። የአምራች ዘርፉ ዋና ተዋናይ የሆነው የግሉ ዘርፍ በንቅናቄው ቀዳሚ ተጠቃሚ ሆኗል። በንቅናቄው የአንድ ዓመት ሀገር አቀፍ ጉዞ ከ352 በላይ ሥራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማድረግ ተችሏል። 635 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ማምረት ጀምረዋል። አዳዲስ አምራቾችም በዘርፉ ለመሠማራት ፍላጎት ማሳየታቸው የንቅናቄው ውጤት ነው። በንቅናቄው የአንድ ዓመት ቆይታ በዘርፉ ለመሠማራት ፈቃድ ከወሰዱ አራት ሺ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች በተጨማሪ፣ ለአምስት ቀናት በተካሄደው ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ኤክስፖ ላይ 68 አዳዲስ ኢንቨስተሮች ወደ ዘርፉ ለመግባት ፍላጎታቸውን አሳይተዋል።
ንቅናቄው አምራቾች ምርቶችን በሀገር ውስጥ እንዲያመርቱ ትልቅ አቅም ፈጥሯል። ለአብነት ያህልም ከሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት 2 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ፣ ሚሊኒየም አዳራሽ፣ በተካሄደው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ኤክስፖ የተሳተፉ 124 መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ይዘው የቀረቡት ንቅናቄው የፈጠረላቸውን እድል ተጠቅመው በሀገር ውስጥ ያመረቷቸውን ምርቶቻቸውን ነው።
ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ ያመርቱ የነበሩ ፋብሪካዎች ምን ዓይነት ምርቶችን ያመርቱ እንደነበርና ለሌሎች ፋብሪካዎች ምን ያህል ግብዓት ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያመለክት መረጃ አልነበረም። ንቅናቄው ይህ መረጃ እንዲታወቅ በማስቻሉ በአምራቾችና በገዢዎች መካከል ብቻ ሳይሆን በኢንዱስትሪዎች መካከል የተሻለ ትስስር እንዲፈጠር አግዟል።
ከዚህ በተጨማሪም የግሉ ዘርፍ በአምራች ኢንዱስትሪው እንቅስቃሴ ውስጥ ለሚኖረው ውጤታማ ነት ትልቅ ግብዓት ሆነው የሚያገለግሉትና ቀልጣፋ አሠራርን ለማስፈን የሚረዱት የአንድ መስኮት አገልግሎት እና የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር በክልሎችና በየተቋማቱ እየተሻሻለ መጥቷል።
በሀገሪቱ በአምራች ዘርፍ የተሠማሩ በርካታ ተቋማት በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ እቅዶች ላይ ተመሥርተው ሥራዎቻቸውን እያከናወኑ ሲሆን፣ አምራቾችም ንቅናቄው ቀደም ሲል ጀምሮ የነበሩባቸውን ችግሮች ለመፍታት እገዛ እያደረገላቸው እንደሚገኝና በትግበራውም አበረታች ውጤቶችን እያገኙ እንደሆነ ይገልፃሉ።
የአርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሙስጠፋ ሱልጣን ፋብሪካው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የፈጠራቸውን መልካም ዕድሎች ለመጠቀም ቀዳሚ ተሰላፊ ሆኖ እየሠራ መሆኑን ይናገራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፣ በንቅናቄው አቅጣጫ መሠረት በተከናወኑ የምርት ተግባራት ከ50 በመቶ የበለጠ የውጭ ምንዛሪ ማዳን ተችሏል።
‹‹የፀጥታ ኃይሎች አልባሳት በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ለአምራቾች እድል መሰጠቱ ተስፋ ሰጪና ተገቢ እርምጃ ነው።›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይህን ተግባር ሲያስጀምር ‹ይህ ሥራ አሁን ካልተጀመረ ወደፊትም ሊጀመር አይችልም። አምራቾቹ ሥራውን መሥራት ይችላሉ። ክፍተቶች ሲኖሩ ድጋፍ እናደርጋለን› ብሎ ዕድል ሰጥቶናል ሲሉ ይገልጻሉ። ‹‹መንግሥት የሀገር ውስጥ አምራቾች ከዚህ ቀደም ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ እንዲያመርቱ ዕድል መስጠት እንደሚያስፈልግ አምኖ አምራቾችን በዚህ ተግባር ውስጥ ማሳተፉ ተገቢ ነው›› በማለት በንቅናቄው ስላከናወኗቸው ተግባራት ያስረዳሉ።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው አምራች ዘርፉ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳለበትና ሀገሪቱ ብዙ ሥራ ፈላጊ ዜጎች እንዳሏት ጠቁመው፣ ንቅናቄውን በመጠቀም ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚያስከትላቸውን ጫናዎች ለመቀነስና ለሥራ ፈላጊ ዜጎች የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚያግዝ ይገልፃሉ።
‹‹ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢንዱስትሪውን የሚያነሳሳ ትልቅ ሥራ ነው›› የሚሉት አቶ ሙስጠፋ፤ ‹‹ንቅናቄውን አጠናክረን ማስቀጠል ከቻልን ከዚህ የበለጠ የውጭ ምንዛሪ ማዳን እንችላለን። ሠራተኞቻችን አሁን ካላቸው የተሻለ ልምድና እውቀት እያገኙ በሥራቸው የተሻለ ውጤታማ ሆነው ይቀጥላሉ። በሂደትም ብዙ ኢንቨስተሮች እንዲፈጠሩ ሁኔታዎችን ያመቻቻል›› ብለዋል። ንቅናቄውን በሙሉ አቅም በመተግበር በውጭ ምንዛሪ እና የተሳለጠ አገልግሎት አቅርቦት ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ማስተካከልና ለበለጠ ውጤት መትጋት እንደሚገባም ተናግረዋል።
‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የኢንዱስትሪ ምርቶችን አምርቶ ለመሸጥ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ለመተካትና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የሚያሻግር ተግባር እንደሆነ ተስፋ ተጥሎበታል። ይህን ለማሳካት ከሚያስችሉ ግብዓቶች መካከል አንዱ ለአምራቾች የገበያ ት ስስር መፍጠር ነው።
የ‹‹ሳሙኤልና ኢዮብ የብረታ ብረትና እንጨት ሥራ ማኅበር›› የገበያ ጥናት ባለሙያ ሽመልስ ወንድሙ ንቅናቄው ለአምራቾች የገበያ ትስስር እንደሚፈጥር ይናገራል። ‹‹በንቅናቄው የሚፈጠረው ግንኙነት ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን የተሻለ ሥራ ለመሥራት ያግዛል። በርካታ ጥራት ያላቸው ምርቶች በሀገር ውስጥ እንደሚመረቱ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ ይፈጥራል›› ይላል። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ጥሬ እቃዎችና ኢንዱስትሪዎችን ተጠቅሞ ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚሆኑ ምርቶችን በማምረት ገበያውን ማረጋጋት እንደሚቻል ጠቅሶ፣ ይህም የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድግና የገበያ ትስስር እንደሚፈጥር ይናገራል። ድርጅቱ ከቻይናና ከሌሎች ሀገራት በውጭ ምንዛሪ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት እያመረተ እንደሆነ ጠቁሞ፣ ንቅናቄው ተኪ ምርቶችን ለማምረት ፋይዳው ትልቅ እንደሆነ አስታውቋል።
የ‹‹ተድላና ጓደኞቹ ብረታ ብረት ሥራ ድርጅት›› ዋና ሥራ አስኪያጅ አማረ አዳነ በበኩሉ፣ ድርጅቱ የንቅናቄውን ዕድሎች በመጠቀም የግብርና ማሽነሪዎችንና ሌሎች መሣሪያዎችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ መተካት እንደተቻለ ይናገራል። ‹‹ጥራት ያላቸውን ምርቶች በብዛት እናመርታለን፤ነገር ግን የገበያ ትስስር ችግር አለብን። ከመሥሪያ ቦታ በተጨማሪ የመሸጫ ቦታ በሚፈለገው ልክ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ንቅናቄው ምርቶቻችንን በማስተዋወቅ የገበያ ትስስር እንድናገኝ ዕድል ይፈጥራል። በኤክስፖው ምርቶቻችንን ለመግዛት ፍላጎት ካሳዩ ከሃምሳ በላይ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ፈጥረናል›› በማለት ንቅናቄው ስላስገኘላቸው ጥቅም ይገልፃል።
‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ በተለያዩ ዘርፎች የተሠማሩ አምራቾች የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዲፈጥሩ እንደሚያስችል የምትናገረው የኢትዮጵያ ማሽነሪ እና መለዋወጫ አምራቾች ማኅበር የገበያ ጥናት ባለሙያ የአብፀጋ አበራ፤ ንቅናቄው በማሽንና መለዋወጫ ምርት የተሰማሩ ሌሎች አምራቾች ማኅበሩን ተቀላቅለው በጋራ እንዲሠሩ፣ የገበያ ትስስር ዕድል እንዲያገኙ እና አዳዲስ ሃሳቦችን እንዲለዋወጡ ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር ገልፃለች።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አቶ ውቤ መንግሥቱ ንቅናቄው ለግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው በጎ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት ይናገራሉ። ዋና ፀሐፊው እንደሚሉት፣ በንቅናቄው የአምራች ዘርፉ ችግሮች በመንግሥት ትኩረት ማግኘታቸው ትልቅ እርምጃ ነው። ይህን ተከትሎ ችግሮችን የመፍታት ሥራም ተጀምሯል። ሥራ አቁመው የነበሩ ትልልቅ አምራቾች ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ሥራ እንዲመለሱ ተደርጓል። መንግሥት ያሉበትን ክፍተቶች ተመልክቶ የማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመሩ ንቅናቄው ያመጣው ለውጥ ነው።
‹‹የግብዓት አቅርቦትና የውጭ ምንዛሪን ጨምሮ ሌሎች የዘርፉ ችግሮች በመንግሥት ትኩረት አግኝተዋል። ይህ ትልቅ የአስተሳሰብ ለውጥ ነው። ከዚህ ቀደም የግሉ ዘርፍ ያቀርባቸው የነበሩ ችግሮች አሁን በመንግሥትም እየቀረቡ ይገኛሉ። እኛ ጥናት አስጠንተን ለመንግሥት ያቀረብናቸው ችግሮች አሁን መንግሥት ትኩረት ሰጥቷቸዋል›› ይላሉ።
ንቅናቄው የአምራቾችን የማምረት አቅም ለማሳደግ የሚያግዝ ወሳኝ እርምጃ ቢሆንም፣ ገበያ ተኮር የሆነ አካሄድ በመከተል ንቅናቄውን ከግብይት ጋር ማገናኘት ይገባል ሲሉም አቶ ውቤ ይጠቁማሉ። ከማምረት በተጨማሪ ምርቶችንና ገበያን የማገናኘት ተግባር ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ይመክራሉ። ከዚህ በተጨማሪም በተቋማት ዘንድ የሚስተዋለውን የቅንጅት ክፍተት ማስተካከል እንደሚገባም አቶ ውቤ ያስረዳሉ።
ከ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ዋና ዋና ዓላማዎች መካከል አንዱ የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በጋራ በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋፅዖ እንዲወጣ ማስቻል ነው። የዚህ ዓላማ ስኬት በግሉና በመንግሥት ዘርፍ ቅንጅት ላይ የሚወሰን ይሆናል። የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋ፣ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ትብብር መተኪያ የሌለው የዘርፉ ውጤታማነት ግብዓት እንደሆነ በአፅንዖት ያስረዳሉ።
ሚኒስትሯ እንደሚሉት፣ የግሉ ዘርፍና መንግሥት በቅንጅት የማይሠሩ ከሆነ ውጤት መጠበቅ አይቻልም። የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ቅንጅት በየደረጃው አስፈላጊ ነው። መንግሥት ስትራቴጂካዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የፕሮጀክት አመራርና አስተዳደር ሥራዎችን ከግሉ ዘርፍ ጋር በሚገባ ተቀናጅቶ መሥራት አለበት። ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ተግዳሮቶች በመለየት በትብብር መሥራት፣ ትኩረት የተሰጣቸውን ሀገራዊ እቅዶች ለማሳካት ወሳኝ ግብዓት ነው።
በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የተከናወኑ ተግባራት በአገልግሎት ዘርፍ ከታየው መነቃቃት ጋር ተደምረው ሰባት ነጥብ አምስት በመቶ ኢኮኖ ሚያዊ ዕድገት ለማስመዝገብ የተቀመጠውን እቅድ ለማሳካት እንደሚያግዙም ነው ዶክተር ፍፁም የተናገሩት። መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በቅንጅት ሠርተው በአንድ ዓመት ንቅናቄ ያስመዘገቡት ውጤት ቀላል እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ ትብብሩ ዘላቂ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።
‹‹የግሉ ዘርፍ የሌለበትን የአምራች ዘርፍ ማሰብ አይቻልም›› የሚሉት ሚኒስትሯ፤ የግሉ ዘርፍ የአምራች ኢንዱስትሪው ዋና ተዋናይ በመሆኑ መንግሥት ለግሉ ዘርፍ የሚያደርገው ድጋፍና ክትትል ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጠው ይናገራሉ። ‹‹አስተማማኝ በሆነ ደረጃ ‹የሥራ ዕድል የሚፈጥር፣ ምርትን የሚጨምርና የገበያ ችግርን የሚፈታ ኢንቨስትመንት መጣልኝ› ብሎ የሚያስብ ኅብረተሰብና አመራር መፍጠር ያስፈልጋል›› ይላሉ።
የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሃገራዊ ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስ ትሪው ተዋንያን በሆኑ በበርካታ ባለድርሻ አካላት ቅንጅት የሚተገበር ቢሆንም ንቅናቄውን በዋናነት የሚያስተባብረው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው። የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ንቅናቄው የግሉን ዘርፍ በማነቃቃት ረገድ ያስገኛቸው ውጤቶች በአምራች ዘርፉ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ትልቅ እገዛ እንደሚያደርጉ ያስረዳሉ። ‹‹ሰፊ ግንዛቤ ተፈጥሯል፤ ባለሀብቶችን የመደገፍ እና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን የመሳብ ተግባራት ተከናውነዋል። ሥራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ፣ የመሬትና የሼድ አቅርቦቶች እንዲሻሻሉ ተደርጓል። እነዚህ ተግባራት የግሉ ዘርፍ ችግሮች እንዲቃለሉ እገዛ አድርገዋል›› ብለዋል።
አቶ መላኩ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰሞኑን የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት አፈፃፀምን ሲገመግም፣ ባቀረቡት ሪፖርት ከ2015 በጀት ዓመት በፊት 46 በመቶ የነበረውን ሀገራዊ የማኑፋክቸሪንግ ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተደረገ ርብርብ ምርታማነቱን ወደ 53 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ገልፀዋል። የሀገር ውስጥ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች በገበያ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ ለማሳደግ የተደረጉ እንቅስቃሴዎች የገበያ ድርሻውን ወደ 37 በመቶ ለማሳደግ ማስቻላቸውንም አብራርተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ከውጪ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን ከመተካት አንፃር ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን የገለፁት አቶ መላኩ፣ በዚህም በዘጠኝ ወራት አንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸውን ምርቶች በሀገር ውስጥ በማምረት መተካት እንደተቻለ ተናግረዋል። በዚህ አፈፃፀም ውስጥ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ ትልቅ አስተዋፅዖ እንደነበረውም ጠቁመዋል።
የአገሪቱን የምጣኔ ሀብት መዋቅር ከእርሻ መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያግዙ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችና ዕድሎች እንዳሉ አይካድም። ይሁን እንጂ እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት ሀገሪቱ ካላት አቅምና ፍላጎት በብዙ ርቀት ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ለወቅቱ የሚመጥን ተግባራዊ ምላሽ መስጠት እጅግ አስፈላጊ ነው።
ለዚህ ደግሞ ሀገራዊ የማምረት አቅምን በማጎልበት የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ፣ ተጨማሪ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለማቃለልና ተወዳዳሪ አገራዊ ምጣኔ ሀብት ለመገንባት ያስችላል ተብሎ የታመነበት የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ አማራጭ የመፍትሔ አቅጣጫ ነው።
የአምራች ዘርፉን ችግሮች በመፍታት ረገድ አዎንታዊ አስተዋፅዖ የሚኖረውን ይህን ንቅናቄው ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ደግሞ ዘመቻው ምን ለውጥ እንዳስገኘ በየጊዜው ክትትል እያደረጉ መገምገምና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ መንግሥት አሁንም ንቅናቄውን እንዲሁም ዘርፉን ውጤታማ የሚያደርጉ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በማዘጋጀት ምቹ የኢንዱስትሪ ከባቢን መፍጠር ይጠበቅበታል።
ኢንዱስትሪዎች ንቅናቄው የፈጠረላቸውን ዕድል በመጠቀም በሀገር ውስጥ ያመረቷቸውን ምርቶች በንቅናቄው ኤክስፖ ይዘው ቀርበዋል፤
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2015