“የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ለሀገራዊ ትርክት በቁጭት መሥራት ይጠበቅባቸዋል” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፡የኪነጥበብ ባለሙያዎች ለሀገራዊ ትርክት መሳካት በቁጭት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመለከቱ፡፡ የጥበብ ኢንዱስትሪ እንዲያድግና ባለሙያዎች የሚፈልጉት እንዲሟላ ቀድማ ኢትዮጵያ ማደግ እንዳለባት ጠቆሙ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከመላው ኢትዮጵያ ከተውጣጡ የጥበቡ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ከትናንት በስቲያ በተወያዩበት ወቅት እንደገለጹት፤ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ይሄ ሁሉ ባህል እያለን ለምን ለማኝ ሆንን በሚል ቁጭት ለሀገራዊ ትርክት መሥራት ይጠበቅባ ቸዋል፡፡

መንግሥት ኪነጥበብ ለትውልዱ ጠቃሚ መሆኑን በመገንዘብ በሚሠሩ የልማት ሥራዎች ሁሉ የኪነጥበብ ማሳያዎች ገንብቷል፤ የነበሩትንም አድሷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኪነ ጥበብ ለሀገር ግንባታ ካለው የማይተካ ጉልህ ሚና አኳያ ሀገራዊ የኪነጥበብ ሥራዎች ካልተጠናከሩ ብልፅግና ኢትዮጵያ ውስጥ ሊመጣ አይችልም ብለዋል። መደመር መጽሐፋቸው ለዕሴት ግንባታ ጥበብ ያለውን ሚና ማሳየቱንም ጠቁመዋል።

በሀገሪቱ የትምህርት መስጫ ተቋማት ኪነጥበብ ትኩረት ተሰጥቶት ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል። በተገነቡ 30ሺ መዋዕለ ሕጻናት ዋናው የትምህርት መከወኛ ኪነጥበብ መሆኑን በማንሳት በ10 ዩኒቨርሲቲዎች የኪነጥበብ ትምህርቶች እየተሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል። ከዚህ ባለፈም ጥበብን የሻተ መገደብ ስለሌለበት ኪነጥበብ በአዲስ አበባ በሦስተኛ ዲግሪ እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ከውጭ በመጡ ባለሙያዎች አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ተጠቅሞ ፊልም እንዴት እንደሚሠራ ለባለሙያዎች ሥልጠና ተሰጥቷል። ሥልጠናው ቀጣይነት ያለው፤ የሀገራችንን ፊልም ለማሳደግና በርካታ ቀደምት ታሪኮችን ለመሥራት ያግዛል።

ከዚህ ቀደም ባልነበረ መልኩ የመንግሥት ተቋማት ራሳቸውንና አገልግሎታቸውን ለማስተዋወቅ በጀት መድበው በባለሙያዎች ፊልም ማሠራታቸው መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ማሳያ እንደሆነም ጠቁመዋል ።

ስለሰው ብዙ መናገርና ማድነቅ ይብቃን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከሰው መማር ቢያስፈልግም እኛ ውስጥ ያለው ሀብት የሚራከስና የሚጣጣል መሆን እንደማይገባው አስገንዝበዋል።

ለዚህም የባህል ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ሕዝብ ለሕዝብ በሚል መርሕ ዓለምን እንደተጓዙት የኪነጥበብ ባለሙያዎች፤ የዘመኑ የጥበብ ባለሙያዎች የሁሉንም አካባቢ ቋንቋና ባህል በአርት ለመግለጽ እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መንግሥት በጥበቡ ጥሩ ሥራ እንዲሠራ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አቅም እየጎለበተ ሲሄድ መንግሥት ከሀገር ውጭም ኢንቨስት የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጥበብ በመንግሥት ብቻ ሳይሆን በየትኛውም መስክ መታወስና መዘከር አለበት። የጥበብ ጉዳይ ለባለሙያዎቹና ለመንግሥት ብቻ ሳይሆን ለትውልድም የሚጠቅም በመሆኑ አቅም ያላቸው መክፈልና ማሠራት ቢለማመዱ አብዛኛው ነገር መልክ እየያዘ እንደሚመጣ አመልክተዋል።

በቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You