ኢትዮጵያ በኃይል አቅርቦት ቀጣናውን ለማስተሳሰር ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መሆኑ ተገለጸ

– የዓባይ ግድብ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የቀጣናው ሀገራት ሀብት እንደሆነም ተጠቆመ

አዲስ አበባ፡– ኢትዮጵያ በኃይል አቅርቦት ቀጣናውን ለማስተሳሰር ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ። የዓባይ ግድብም የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የቀጣናው ሀገራት ሀብት እንደሆነም ተጠቆመ።

ሚኒስትሩ ‹‹ቀጣናዊ የኃይል ግንኙነት ለአካታች እና ለዘላቂ ልማት›› በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ በሚገኘው አራተኛው የናይል ውሃ ምክንያታዊና ፍትሐዊ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ለዜጎች አለመዳረስ ኢኮኖሚያዊ እድገትንና የኢንዱስትሪ መስፋፋትን ይገድባል፡፡

ኢትዮጵያ በኃይል አቅርቦት ቀጣናውን በማስተሳሰር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ነው። የኃይል ትስስር መፈጠሩ የሥራ ዕድልን ለመፍጠርና ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር ሚናው የጎላ ነው ብለዋል ።

በአፍሪካ ዛሬም ድረስ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዳልሆኑ የጠቆ ሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ አሁን ላይ ለጅቡቲ፣ ደቡብ ሱዳንና ኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበች መሆኑን አስታውሰዋል፤ በቀጣይነትም ለሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ታንዛኒያ ኃይል ለማቅረብ በሂደት ላይ መሆኗን አመልክተዋል፡፡

የታዳሽ ኃይል ልማት ሥራዎች ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ የኃይል ትብብር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የዓባይ ግድብም የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የቀጣናው ሀገራትም ሀብት እንደሆነም አስታውቀዋል። ከግድቡ የሚመነጨው ኃይልም የቀጣናው ሀገራትን የኃይል ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ድንበር ዘለል የመሠረተ ልማት ትብብር የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063 እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 2030 የልማት ግቦችን ለማሳካት እንደሚያግዙ የገለጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ለግቦቹ መሳካት ትርጉም ያለው አስተዋፅዖ እያበረከተች መሆ ኑን አስታውቀዋል። ሥራው ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የመን ግሥታትን እና ተቋማትን ተባብሮ መሥራት የሚጠይቅ  መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና በእምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች የታደለ መሆኑን፤ ሀብቶቹ በአግባቡ ለምተው ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ተጨማሪ ሥራ እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡

ለቀጣናው ሀገራት የጋራ እድገት በውሃ ሀብት ልማት ላይ በትብብር መሥራት ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በኃይል አቅርቦት ላይ ኢንቨስት ማድረግ የቀጣናው ሀገራት ተቀዳሚ ሥራ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዘርፉ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነች ነው ያሉት ሚኒስ ትሩ፤ በውሃ ሀብትም ብሔራዊ ጥቅሟን ከማስ ጠበቅ ባለፈ የቀጣናውን ሀገራት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራች መሆኑን አመልክተዋል። በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቀጣናውን በመሠረተ ልማትና በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም አስታውቀዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ በበኩላቸው፤ አካታች የሆነ እድገት እና ቀጣናዊ ውሕደት እውን የሚሆነው አስተማማኝ የኃይል ምንጮች በዘላቂነት እና ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ላይ ማቅረብ ሲቻል እንደሆነ አመልክተዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካውያን በራስ አቅም ማድረግን ማሳያ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት ልማታዊ ግንኙነት አብሮ የማደግ ፍላጎቷ ማሳያ እንደሆነ ገልጸው፤ ድንበር ዘለል ትብብር ለአካታች ልማትና ለቀጣናዊ ትስስር ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል።

አፍሪካ በተለያዩ የማዕድን ሀብቶች የበለፀገች መሆኗን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ሀብቶች ለምተው ዜጎችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የግጭት ምክንያት ሲሆኑ ይስተዋላል። በመሆኑም ሀገራት የውጭ ግንኙነት፣ የኢንቨስትመንትና የሌሎች ተያያዥ ዘርፍ ፖሊሲዎቻቸው የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ እንዲሆኑ መሥራት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

ጉባኤው ቀጣናዊ የኃይል አቅርቦት ትብብሮችን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም አመልክ ተዋል፡፡

በፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You