የዛሬው የፍረዱኝ ዓምድ ዝግጅታችን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ቀበሌ 04 በተለምዶ አየር ጤና፣ ካራ ተብሎ ወደሚጠራው ሰፈር ይሰደናል፡፡ ዝግጅቱም ወይዘሮ እጅጋየሁ በላይ እና አቶ ዳዊት ተስፋዬ የተባሉ ግለሰቦች ከወንድም እና እህቶቻቸው ጋር በውርስ ይገባኛል ያነሱትን ውዝግብ ይዳስሳል፡፡
«በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወረዳ 02 ቀበሌ 4 የቤት ቁጥር 183 ተመዝግቦ የሚገኝ ቤትን ለስምንት ልጆች በጋራ እንድንካፈል ቤተሰቦቻችን የተናዘዙልን ቢሆንም፤ ምክንያቱን በውል ባልተረዳነው አግባብ የቤት የወራሽነትነት መብታችንን
ተገፈናል፡፡ ስለሆነም በመልካም አስተዳደር ችግር ሳቢያ እየደረሰብን ያለውን ያልተገባ ጫና የኢትዮጵያ ሕዝብ አይቶ ይፍረድ» ሲሉ ወይዘሮ እጅጋየሁ በላይ እና አቶ ዳዊት ተስፋዬ የተባሉ ግለሰቦች ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አቤት ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ግራ ቀኙን አይቶ መፍረድ ይችል ዘንድ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ከሰዎች እና ከሰነድ ያገኛቸውን ማስረጃዎች በጥልቀት በመመርምር የሚከተለውን ዘገባ ሠርቷል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
አቤቱታ አቅራቢዎች
በዚህ ዝግጅት በደል ተፈጽሞብናል ካሉት ግለሰብ መካከል ወይዘሮ እጅጋየሁ በላይ አንደኛዋ ናቸው:: እንደ ወይዘሮ እጅጋየሁ ገለጻ፤ ተወልደው ያደጉት ዛሬ ላይ ውዝግብ በተነሳበት ቤት ውስጥ ነው:: አቶ በላይ በሚባሉ የአባት ስም ይጠሩ እንጂ አሳድገው፣ አስተምረው እና ለወግ ለማዕረግ ያበቋቸው አቶ መኮንን ሲሳይ እና ባለቤታቸው ወይዘሮ ትርንጎ ምሕረቴ ናቸው::
አቶ መኮንን በሕይወት እያሉ ዛሬ ላይ ውዝግብ የተነሳበትን እና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ቀበሌ 04 በቤት ቁጥር 183 ተመዝግቦ የሚገኘውን ቤት በ2001 ዓ.ም ለስምንት ልጆች እና የልጅ ልጆች ማውረሳቸውን ይናገራሉ:: ይህም ውርስ ሕጋዊ ይዘቱን እንዲጠብቅ በማሰብ ሁሉም ነገር የተከናወነው በኢፌዴሪ የሰነዶች ማረጋጋጫ እና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት በኩል ነው::
አቶ መኮንን እና ባለቤታቸው ወይዘሮ ትርንጎን፣ ስምንት የሚሆኑ ልጆቻቸውን እና የልጅ ልጆቻቸውን ያሳደጉት ከአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በያዙት እና በሚያስተዳደሩት 1 ሺህ 700 ካሬ ሜትር ግቢ ውስጥ ነው:: ለስምንቱም ልጆች እና የልጅ ልጆችም ያወረሱት ይህንኑ 1 ሺህ 700 ካሬ ሜትር መሬት እና በውስጡ የሚገኙ ቤቶች መሆኑን ያስረዳሉ::
እንደወይዘሮ እጅጋየሁ ገለጻ፤ ቦታው በጃንሆይ ጊዜ የተያዘ ነው:: ይሁን እንጂ ይህ ቦታ በአየር ካርታ ከመታየቱ እና የአፈር ግብር ከመክፈል ውጭ ሕጋዊ ካርታ አልነበረውም ::
በግቢው ውስጥ በርካታ ቤቶች እንደነበሩ የሚናገሩት ወይዘሮ እጅጋየሁ፤ ሁሉም ቤቶች በአባታቸው በአቶ መኮንን የተሠሩ መሆናቸውን ያስረዳሉ:: እዚህ ግቢ ውስጥ እናት አባቶቻቸው አርጅተው እያለ ሦስት የልጅ ልጅ እና ሁለት ወንድሞቻቸው ከአባቶቻቸው ጋር አብረው ይኖሩ ነበር:: ይሁንና አቤቱታ አቅራቢዎች ትዳር ከመመሥረታቸው ጋር ተያይዞ ከቤተሰቦቻቸው ቤት ወጥተው መኖር ከጀመሩ በርካታ ጊዜያት ተቆጥረዋል:: አቤቱታ ካቀረቡት መካከል አንደኛው ሰው 6 ኪሎ አካባቢ ነዋሪ ሲሆኑ፤ ሌላኛዋ ደግሞ አየር ጤና አካባቢ ነዋሪ ናቸው ::
ይህ በእንዲህ እያለ አቶ መኮንን ሲሳይ በ2007 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ:: ከአቶ መኮንን ሕልፈት በኋላ ብዙም ያልቆዩት ወይዘሮ ትርንጎ በ2012 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ:: የወይዘሮ ትርንጎን ሕልፈት ተከትሎ በኑዛዜ የተካተቱ ልጆች እና የልጅ ልጆች ቤቱ ሕጋዊ እውቅና እንዲኖረው ለማድረግ ካርታ ለማውጣት እንቅስቃሴ ይጀምራሉ:: ካርታ በክፍለ ከተማ ደረጃ እንደሚሠራ ቢታወቅም የካርታ ይሠራልን ጥያቄ በኮልፌ ቀራኒዮ ወረዳ 02 ነበር የጀመሩት::
ይህ ሲሆን በዛሬው ዝግጅት አቤቱታ አቅራቢዎች ስለሁኔታው የሚያውቁት ነገር አልነበረም:: ጉዳዩ የሚመለከታቸው በወረዳው የሚገኙ አካላት በቤቱ ላይ ካርታ ለማውጣት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለማስኬድ በሰነዶች ማረጋጋጫ ቢሮ በውርስ የተካተቱ ሁሉም ልጅች እንደሚያስፈልጉ ካርታ ለማውጣት ለሄዱ ልጆች ይነገራቸዋል:: ይህን ተከትሎ ካርታ የማውጣት ሂደቱን በድብቅ ሲያከናውኑ የነበሩ ወራሾች ዛሬ ላይ ለዝግጅት ክፍላችን አቤቱታ ያቀረቡትን እህት እና ወንድማቸውን ለቤቱ ካርታ ለማውጣት እንቅስቃሴ ላይ በመሆናቸው ወረዳ 02 እንዲመጡ ይነግሯቸዋል::
ነገሩ አዲስ የሆነባቸው አቤቱታ አቅራቢ እህት እና ወንድም ወረዳ 02 እንዲመጡ በጠየቁበት ዕለት መገኘት እንደማይችሉና ካርታ የማውጣት ሂደቱን በሌላ ጊዜ ተገናኝተው ቢጀምሩ የሚሻል መሆኑን መግባባት ላይ ይደርሳሉ:: ወረዳ 02 ለመገናኘትም ቀን ይቆርጣሉ:: በተቆረጠው ቀን መሠረት አቤቱታ አቅራቢዎቹ ወረዳ 02 ተገናኙ:: ይሁንና በድብቅ ካርታ ለማውጣት ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ወንድም እና እህቶቻቸው በቀጠሯቸው ቀን ወረዳ 02 ሳይገኙ ቀሩ::
አቤቱታ አቅራቢዎች ወረዳ በሄዱበት ወቅት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የወረዳ አመራሮች ጋር አጭር ውይይት ማድረጋቸውን ይናገራሉ:: በዚህም ውይይት ለእያንዳንዱ ወራሽ ልጅ ከ1 መቶ 50 ካሬ ሜትር በላይ ሊደርሳቸው እንደሚችል ነግረዋቸው እንደነበር ያስረዳሉ::
ወደነበርንበት እንመለስና አቤቱታ አቅራቢዎች ካርታ ለማውጣት በቀጠሯቸው መሠረት ወረዳ 02 ቢገኙም በድብቅ ካርታ ሊያወጡ የነበሩት ወንድም እና እህቶች ግን በቀጠሯቸው ሳያገኙ ቀሩ:: ይህን ተከትሎ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ለወንድም እና ለእህቶቻቸው ወረዳ 02 አስተዳደር ጽሕፈት ቤት መሆናቸውን እና እነሱን እየተደበቁ መሆናቸውን በስልክ ይገልጻሉ:: ይህ በእንዲህ እንዳለ በቀጠሯቸው ያልተገኙት እህት እና ወንድም ወደ ወረዳ 02 እንደማይመጡ ለአቤቱታ አቅራቢዎች ይገልጻሉ:: አቤቱታ አቅራቢዎችም ለምን እንዳልተገኙ ይጠይቋቸዋል:: ይህን ተከትሎ አቤቱታ አቅራቢዎች ጆሯቸውን እስከመጠራጠር ያስደረሰ መልስ ይሰማሉ፤ ቤቱ አቤቱታ አቅራቢዎችን እንደማይመለከትና በቤቱ ላይ አቤቱታ አቅራቢዎች ሳያካትቱ በራሳቸው ካርታ ለማውጣት ሂደት መጀመራቸውን ይገልጹላቸዋል ::
አቤቱታ አቅራቢዎችም የቤቱ ወራሽ እኛ ጭምር ሆነን ሳለ ግን ተወልደን ካደግነበት ቤታችን በመራቃችን ብቻ እንዴት ቤቱን በእናንተ ስም ብቻ ካርታ ለማውጣት ሂደት ትጀምራላችሁ? ሲሉ መጠየቃቸውን ይናገራሉ:: ይህን ተከትሎ ካርታ ለማውጣት እንቅስቃሴ ውስጥ የገቡት ወንድም እና እህትም በቤቱ የይገባኛል ጥያቄ ካላችሁ ወደ ፍርድ ቤት መውሰድ ትችላላችሁ የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ይገልጻሉ::
በዚህ ምክንያት አቤቱታ አቅራቢዎች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወሰዱት:: ተከሳሽ እህትና ወንድምም አቤቱታ አቅራቢዎችን እህት እና ወንድማችን አይደሉም አሉም:: በውርስ ቤቱ ላይ የይገባኛል ጥያቄ ያነሱት ሰዎች ብር ስለፈለጉ እንጂ ፈጽሞ ተከሳሾች እንደማያውቋቸው ለፍርድ ቤት መግለጻቸውን ይናገራሉ::
ሁኔታው እየተባባሰ ሲሄድ ለፍርድ ቤት ክርክር የሚረዳቸውን ጠበቃ ማቆማቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ እጅጋየሁ፤ በዚህም በፍርድ ቤት ፊት ልጅ አይደላችሁም፤ አናውቃችሁም፤ ተብለው የነበሩት አቤቱታ አቅራቢዎች የሟች አቶ መኮንን ልጆች መሆናቸው ተረጋገጠ:: ይህን ተከትሎ ሕጋዊ ወራሽ ናቸው? አይደሉም? የሚለውም በፍርድ ቤት ለማየት ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ተመራ:: ፍርድ ቤትም በመለያ ኮድ ቁጥር 123515 ከሳሽ እና ተከሳሽን አከራከረ::
ከሳሾችም ለፍርድ ቤት በቀን 28/11/13 በተጻፈ አቤቱታ እንዳመለከቱት፤ ሟች አቶ መኮንን ሲሳይ ነሐሴ 7 ቀን 2007 ዓ.ም በተደረገ ኑዛዜ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 የቤት ቁጥር 183 ከሆነው ቤታቸው ከተከሳሾች ጋር እንዲካፈሉ ኑዛዜ ያደረጉላቸው በመሆኑ እና አቶ መኮንን ሲሳይ ደግሞ በ2007 ዓ.ም በመሞታቸው በኑዛዜው መሠረት ከቤቱ የሚደርሳቸውን ድርሻ ይስጡን ሲሉ ወይዘሮ አበባ መኮንን፣ አቶ አድማሱ መኮንን፣ ወይዘሮ ወይንሸት መኮንን፣ ኃይለሚካኤል መኮንን፣ አብርሃም ታዲዮስ እና ቃሉ ታዲዮስን ከሰሱ:: ተከሳሾች በጽሑፍ ባስገቡት መቃወሚያ እንደገለጹት፤ ከሳሾች ያቀረቡት የውርስ ሃብት ድርሻ ክስ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1000(1) ድንጋጌ መሠረት አውራሻቸው አቶ መኮንን ከሞቱበት ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ባለማቅረባቸው ምክንያት መብታቸው በይርጋ የታገደ ነው ::
ከዚህ በተጨማሪ ከሳሾች ሟች በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 የቤት ቁጥር 183 የሆነውን መኖሪያ ቤት ነሐሴ 07 ቀን 2001 ዓ.ም ከሳሾች እና ተከሳሾች እኩል እንድንካፈል ባደረጉት ኑዛዜ መሠረት ተከሳሾች ከውርስ ንብረቱ ድርሻቸውን ለመካፈል ጥያቄ አቅርበው እንደተከለከለ በማስመሰል ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው መሆኑ ብቻ ሳይሆን በኑዛዜው መሠረት ከውርስ ንብረቱ ድርሻ የማግኘት መብት አላቸው ቢባል እንኳ በኑዛዜ ወራሽነታቸው የሚጠበቅባቸውን ሕጋዊ ግዴታ ያልተወጡና ላለፉት 13 ዓመታት በእጃቸው ባልነበረ የውርስ ንብረት ላይ ያቀረቡት የድርሻ ክፍፍል ጥያቄ በሕግ ፊት ተቀባይነት የለውም::
ከዚህ በተጨማሪም ተከሳሾች በጽሑፍ በሰጡት ምላሽ እንደገለጹት፤ ከሳሾች የሟች አቶ መኮንን ሲሳይ የኑዛዜ ወራሽ መሆናቸውን በመግለጽ ከውርስ ንብረቱ ተከሳሾች ድርሻችን እንዲያካፍለን በማለት ክስ ከማቅረብ ውጪ ከላይ ከተጠቀሰው ጊዜ ጀምሮ የውርስ ሀብቱ በእጃቸው የሚገኝ ስለመሆኑ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ማስረጃ ካለማቅረባቸውም
በላይ ሟች በሕይወት እያሉ ቤቱ በላያቸው ላይ ሊወድቅ በመቃረቡ ምክንያት ለቤቱ እድሳት ሲደረግ ከወረዳው በመልካም አስተዳደር ፕሮግራም በተሰጠን ፈቃድ መሠረት በ2003 እና በ2004 ዓ.ም በድምሩ ብር 250 ሺ /ሁለት መቶ ሃምሳ ሺ ብር/ ተከሳሾች ከኪሳችን ወጪ በማደረግ ቤቱን ከማሳደሳችንም በላይ እንዲሁም አውራሽ አባታችን ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው ምክንያት ለቀብር ሥነ-ሥርዓትና ለሌሎች ወጭዎች በድምሩ ብር 65 ሺ /ስልሳ አምስት ሺ ብር/ በጠቅላላው ብር 315 ሺ /ሦስት መቶ አስራ አምስት ሺ ብር/ ወጪ ያደረግን ቢሆንም ከሳሾች በወራሽነታቸው ያለባቸውን ሕጋዊ ግዴታ ያለመወጣታቸው ብቻ ሳይሆን የት እንዳሉ እንኳ ሳይታወቁ ለ13 ዓመታት አድራሻቸውን ደብቀው ተሰውረው ከከረሙ በኋላ ሟች ያደረጉት ኑዛዜ በፍርድ ቤት ጸድቆ ማስረጃው ተሰጥቶናል በማለት ኑዛዜው በፍርድ ቤት መጽደቁ የውርስ ንብረቱ ባለመብት እንደሚያደርጓቸው በመቁጠር በተከሳሾች ላይ ያቀረቡት የውርስ ሀብት ድርሻ ጥያቄ ሕግን ያልተከተለ ስለሆነ ክሱ ውድቅ መደረግ አለበት የሚል ነው ::
ተከሳሾች እነዚህን እና መሰል መከራከሪያዎችን ቢያቀርቡም በ25/06/2014 በተሰጠ ብይን መሠረት በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 የቤት ቁጥር 183 የሆነው ቤት ሟች አቶ መኮንን ሲሳይ፣ ነሐሴ 7 ቀን 2001 ባደረጉት ኑዛዜ መሠረት 50 በመቶ የኑዛዜ ተጠቃሚ ስለሆኑ ቤቱን ከተቻለ በስምምነት ካልተቻለ ደግሞ ግምቱን አንደኛው ለአንደኛው በድርሻው በመክፈል እንዲያስቀሩ ፤ ይህም ካልተቻለ በሐራጅ ሽጠው ገንዘቡን በየድርሻቸው እንዲካፈሉ በመወሰን ለፍርድ ባለእዳ የይግባኝ መብት ተሰጥቶ ክርክሩ መዘጋቱን አቤቱታ አቅራቢዋ ያስረዳሉ::
የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ ቤቱን መካፈል እንዲቻል ቤቱ እንዲለካ ተወሰነ:: በዚህም ቦታውን ለማስለካት የፍርድ ባለመብቶች መሐንዲስ ይዘው በቦታው ተገኙ:: ነገር ግን ከፍርድ ባለእዳዎች አንዱ ቤቱ አይለካም፤ ከተለካም እናት እና አባታቸው ይኖሩበት የነበረችው ቤት ብቻ ናት መለካት ያለባት ሲል ሁከት ማስነሳቱን ይገልጻሉ:: ይህን ተከትሎ ቦታውን ለመለካት የፍርድ አፈጻጸም የተለካው መሐንዲስ መለካት ያለበት ሁሉም ቦታ እንጂ የውርስ ኑዛዜ የተናዘዙት እናት እና አባት ይኖሩበት የነበረችው ቤት ብቻ አይደለም ማለት ሁከት ያስነሳውን ልጅ እና የፍርድ ባለዳዎች ለማስረዳት ሞከረ:: ነገር ግን የፍርድ በለእዳዎች አሻፈረን በማለታቸው ቦታውን ሊለካ የመጣው መሐንዲስ የመጣበትን ጉዳይ ሳይፈጽም ለመመለስ መገደዱን አቤቱታ አቅራቢዋ ይናገራሉ::
ይህን ተከትሎ ቦታውን እንዲለካ የተላከው መሐንዲስ “የፍርድ ባለእዳዎች ቦታውን ለማስለካት ፈቃደኛ አይደሉም” ሲል ለፍርድ አፈጻጸም በደብዳቤ አመልክቶ እንደነበር አቤቱታ አቅራቢዋ ይገልጻሉ:: በዚህም ቦታውን አላስለካም ያለው ግለሰብ ታስሮ እንዲቀርብ ተወሰነ::
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፍርድ ባለእዳዎች ፍርድ ቤቱን ይግባኝ ጠየቁ:: በዚህ ይግባኝም መጀመሪያ ላይ ይከራከሩበት ከነበረው የመከራከሪያ ርዕስ ወጥተው በጎረቤት ሰዎች የተሳተፉበት ኑዛዜ ሰነድ አመጡ:: የጎረቤት የተሳተፈበት የኑዛዜ ስምምነት ከሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት የተሻለ ማስረጃ መሆን ከቻለ አቤቱታ አቅራቢዋም የጎረቤት ሰዎች የተሳተፉበት የኑዛዜ ሰነድ ማቅረብ እንደሚችሉ ለፍርድ ቤት ገልጸው የጎረቤት ሰዎች የተሳተፉበት የኑዛዜ ሰነድ አቀረቡ:: ይሁን እንጂ ዳኛው የእርሳቸውን ሰነድ አልቀበልም በማለት አቤቱታ አቅራቢዋ ያመጡትን ሰነድ ውድቅ እንደአደረገው ያስረዳሉ::
በይግባኝ በነበረው የፍርድ ቤት ክርክር የፍርድ ባለዕዳዎች ያቀረቡት መከራከሪያ ሟች በሕይወት እያሉ ለአንደኛ ባለእዳ በ12/07/1994፣ ለሁለተኛ የፍርድ ባለእዳ በ07/02/1987 ዓ.ም፣ ለሦስተኛ የፍርድ ባለእዳ በውትድርና ላይ ስለነበረች በሁለተኛ የፍርድ ባለእዳ በኩል ውርሱ እንዲሰጣት፣ ለአምስተኛ የፍርድ ባለእዳ በቀን 12/07/1994 ዓ.ም፣ ለ6ኛ የፍርድ ባለዕዳ በ12/07/1994 ዓ.ም በተደረጉ የስጦታ ውሎች ሟች የሰጧቸውን ቦታ ተከፋፍለው በየአቅማቸው ቤት ሠርተው እየኖሩበት መሆኑን አስረዱ::
ከዚህ በተጨማሪም ይዞታው ሰነድ አልባ በመሆኑም የሟችም ሆነ የፍርድ ባለዕዳዎች የይዞታ ልኬት ተወስዶ ለእያንዳንዱ ይዞታ ፋይል ተሠጥቶት ወደ መሬት አስተዳደር ተልኮ የይዞታ ካርታ እየጠበቁ መሆናቸው ገልጸው፤ በየይዞታቸው ላይም ውሃ እና መብራት አስገብተው እየተጠቀሙ እንደሚገኙ አስረዱ::
ነገር ግን ዋናው ክርክር በየግላቸው የሠሩትን ቤት የማይመለከት የሟች ቤትን ብቻ የሚመለከት ሆኖ እያለ የፍርድ ባለመብቶችም ቤቱን የፍርድ ባለእዳዎች በይዞታው ላይ በየግል የሠሯቸው ቤቶች መሆናቸውን እያመኑ ፍርዱ የቤት ቁጥር 183 ስለተባለ የፍርድ ባለዕዳዎች የሠሯቸው ቤቶችም በዚሁ የቤት ቁጥር የሚታወቁ በመሆኑ ፍርድ እንዲያስፈፅም የታዘዘው የፌደራል ፍርድ ቤቶች ፍርድ አፈፃፀም ዳይሬክቶሬት የፍርድ ባለዕዳዎችን የግል ቤቶችንም በቤት ቁጥር 183 ስር አካቶ ክፍፍል ሊያደርግ በመሆኑ እና የፍርድ አፈፃፀም አጠቃላይ ልኬት ልውሰድ ስላለ የፍርድ ባለዕዳዎች የግል ንብረቶች እና በውርስ ክርክሩ ያልተከራከርንባቸው የፍርድ ባለዕዳዎች የግል ቤቶች ከአፈፃፀም ውጪ እንዲሆኑ እንዲታዘዝልኝ በማለት አቤቱታ አቀረቡ::
በማስረጃነት ሟች ለ1ኛ የፍርድ ባለዕዳ ግንቦት 12/1994 ዓ.ም ያደረጉት የስጦታ ውል፣ ሟች እና ባለቤታቸው ጥቅምት 7 ቀን 2007 ዓ.ም ለ2ኛ የፍርድ ባለዕዳ ቤት ሠርቶ እንዲጠቀም ያደረጉለት የስጦታ ውል፣ ሟች ግንቦት 12 ቀን 1994 ዓ.ም ለ5ኛ የፍርድ ባለእዳ ያደረጉት የስጦታ ውል፣ ሟች ለ6ኛ የፍርድ ባለዕዳ ግንቦት 12 ቀን 1994 ዓ.ም ያደረጉት የስጦታ ውል ፣ 2ኛ የፍርድ ባለዕዳ የቤት እድሳት ፈቃድ የወሰደበት ሰነድ፣ ባለይዞታው 2ኛ የፍርድ ባለእዳ መሆናቸውን የሚያመለክት በ2012 ዓ.ም የተሰጠ ከወረዳው ዋና ሥራ አስፈፃሚ 2ኛ የፍርድ ባለዕዳ ነባር ባለይዞታ እና ካርታ በሂደት ላይ መሆኑ ተገልጾ የመብራት አገልግሎት በግላቸው እንዲያገኙ የተፃፈ ደብዳቤ፣ 5ኛ የፍርድ ባለዕዳ ውሃ በግላቸው ያስገቡት ደረሰኝ አቅርበዋል::
የተሰጠ የፍርድ ባለመብቶች መልስ እንዲሰጡ ታዝዞ የፍርድ ባለመብቶች ነሐሴ 3 ቀን 2014 ዓ.ም በተጻፈ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 418 አቤቱታ የሚያቀርበው አንድን ውሳኔ ለማስፈፅም ንብረት ሲያዝ በንብረቱ ላይ የቀዳሚነት መብት ያለው ሰው ይህ ንብረት እንዳይያዝ ወይም እንዳይከበር የሚል ነው:: ይህ ድንጋጌ የፍርድ ምክንያት የሆነን ንብረት የሚመለከት ሳይሆን ገንዘብ እንዲከፈል የተሰጠን ውሳኔ ለማስፈፅም በተያያዘ ንብረት ላይ ነው::
የፍርድ ባለእዳዎች እንደዚህ አይነት ክርክር ፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 358 መሠረት የሚስተናገድ ሲሆን፣ የፍርድ ባለእዳዎች የዋናው ክርክር ተካፋይ ስለሆኑ እንደዚህ አይነት እድል የለውም:: የፍርድ ባለዕዳዎች ያቀረቡት ክርክር ዋናው ክርክር ላይ ሊቀርብ የሚገባው እንጂ በአፈፃፀም ክርክር ሊቀርብበት አይገባም:: በመሆኑም የፍርድ ባለእዳዎች አቤቱታ በፍ/ብ/ስ/ህ/ቁ 419(2) መሠረት ውድቅ ይደረግልን በማለት በጽሑፍ ተከራክረዋል::
በመጨረሻም የይግባኝ ማመልከቻውን ተቀብሎ የተመለከተው በፌደራል መደበኛ ፍርድ ቤት ኮልፌ ቀራኒዮ ምድብ 3ኛ ውርስ ችሎት የኮ/ቀ/መ/ቁ፡- 128660 በሆነ መለያ ቁጥር ሁለቱን ወገኖች ሲያከራክር ቆይቶ በ25/12/2014 ዓ.ም የሚከተለውን ውሳኔ አስተላለፈ::
የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፍርድ አፈፃፀም ዳይሬክቶሬት ፍርድ ቤቱ በ25/06/2014 በመለያ ቁጥር 123517 በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 የቤት ቁጥር 188 ላይ በግማሹ ወይም በ50 በመቶ ላይ የፍርድ ባለመብቶች የኑዛዜ ተጠቃሚ ስለሆኑ ክፍፍል እንዲፈፀም የሠጠው ውሳኔ የቤት ቁጥር 183 በሚል በሚታወቁት የፍርድ ባለዕዳዎች ይዞታቸውን ከሟች በስጦታ አግኝተው በራሳቸው የሠሯቸውን ቤቶች የማይጨምር እና ፍርዱ እና ውሳኔው የተሠጠው የቤት ቁጥር 183 በሚል ከሚታወቁት ቤቶች መካከል ሟች ይኖሩበት የነበረው ሦስት (3) ክፍል ቤት ላይ ብቻ መሆኑን ተገንዝቦ አፈፃፀሙን በዚህ ሟች የኖሩበት በነበረው ሦስት ክፍል ቤት ላይ ብቻ እንዲያስቀጥል ታዝዟል ::
በዚህም ውሳኔ ፍርድ ቤቱ ቤተሰቦቻቸው ብቻ ይኖሩባት የነበረችውን ቤት ብቻ ተለክታ ለስምንት እንድትከፈል መወሰኑን ያስረዳሉ:: ጉዳዩን በይግባኝ እስከ ሰበር ችሎት ቢያደርሱትም የስር ፍርድ ቤት የወሰነው ይጸናል በማለት ፍርድ ቤቱ ፍትሕ እንደተነፈጋቸው ያስረዳሉ::
ሌላኛው አቤቱታ አቅራቢ አቶ ዳዊት ተስፋዬ ይባላል:: እንደ አቶ ዳዊት ገለጻ፤ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 የቤት ቁጥር 183 ቤት የአያታቸው የአቶ መኮንን ሲሳይ ነበር:: አቶ ዳዊትን ያሳደጉት እና ለወግ ለማዕረግ ያበቁት አቶ መኮንን ሲሳይ ናቸው :: አቶ መኮንን ሲሳይ እድሜያቸው በገፋ ጊዜም የዛሬውን አቤቱታ አቅራቢ እና ሌሎች ሰባት ልጆችን ወራሽ በማድረግ በ2001 ዓ.ም ለኢፌዴሪ የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት የኑዛዜ ሰነድ አስገቡ::
ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ መኮንን በ2007 ዓ.ም አረፉ:: ቀጥሎም ባለቤታቸው ወይዘሮ ትርንጎ በ2012 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ:: ይህን ተከትሎ በኢፌዴሪ የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ሕጋዊ ወራሽነት በተካተቱት ሕጋዊ ወራሾች መካክል ውዝግብ ተፈጠረ:: በዚህም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደውት እንደነበር የሚናገሩት አቶ ዳዊት፣ ከላይ በጎረቤት ሰዎች አማካኝነት የተፈጸመው ኑዛዜ ሲፈጸም እርሳቸው በወትድርና ሀገራቸውን በማገልገል ላይ ስለነበሩ ስለጉዳዩ እንደማያውቁ ይናገራሉ::
ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቱ የኢፌዴሪ ሰነዶች ማረጋጋጫ እና ምዝገባ ሕጋዊ ሰነዶችን ወደ ጎን ትተው በጎረቤት ሰዎች የተፈጸመን የኑዛዜ ውል ማጽናታቸው ተገቢነት የለውም ብለው እንደሚያምኑ ያስረዳሉ::
ከሰነዶች የተገኙ ማስረጃዎች
ሰነድ አንድ፡- በነሐሴ 7 ቀን 2001 ዓ.ም የተጻፈ፤ ለሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ገቢ የተደረገ ሰነድ እንደሚያመላክተው አቶ መኮንን ሲሳይ አስፋው የተባሉ ኢትዮጵያዊ በኮልፌ ቀራኒዮ ወረዳ 02 በቤት ቁጥር 183 ተመዝግቦ የሚገኘውን ቤታቸውን ለስምንት ልጆቻቸው እና የልጅ ልጆቻቸው እንዳወረሱ ይገልጻል::
ሰነድ ሁለት፡- ከአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ኮልፌ ምድብ ችሎት በቁጥር መ/ቁ 55358 እና በ 21/5/2013 ዓ.ም በተጻፈ ሰነድ እንደተረጋገጠው ወይዘሮ እጅጋየሁ በላይ የተባሉ ግለሰብ የአቶ መኮንን ሲሳይ ሕጋዊ ወራሽ ስለመሆናቸው ተመላክቷል::
በተመሳሳይ ከአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ኮልፌ ምድብ ችሎት በቁጥር መ/ቁ 55597 እና በቀን 14/11/2013 ዓ.ም በተጻፈ ሰነድ እንደተረጋገጠው አቶ ዳዊት ተስፋዬ የተባሉ ግለሰብ የአቶ መኮንን ሲሳይ ሕጋዊ ወራሽ ስለመሆናቸው ተመላክቷል::
ዝግጅት ክፍላችን በመጨረሻም ማስተላለፍ የሚፈልገው መልዕክት ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ያገባኛል የሚል አካል ካለ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን ነው::
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2015