‹‹ዛሬ ያጋጠሙን የፖለቲካ ስብራቶች ትናንት የወረስናቸው የትርክት እዳዎች ናቸው›› ምህረቱ ሻንቆ (ዶ/ር) ፡- በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረዳት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔረሰቦች፤ የሃይማኖት ተከታዮች ሀገር መሆንዋ፤ ሕዝቦቿ ወደውና ፈቅደው በጋራ ያፀኗት ሀገር ስለመሆንዋ በተደጋጋሚ የሚነሳ ጉዳይ ነው። ዛሬም ድረስ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ የቆየችውም በዜጎቿ የአንድነት ካስማ መሆኑም እሙን ነው። በሌላ በኩል በተለያዩ ዘመናት ሀገሪቷን የመሩ ነገስታት ሕዝባዊ አንድነትን አስጠብቀው ለመቀጠል ባደረጉት ጥረት ልክ ብዝሃነትን በማክበር ረገድ ውስንነት እንደነበረባቸው ይተቻሉ። ይህም አሁን ላይ በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚታየው አለመረጋጋቶችና ግጭቶች በመንስኤነት ይጠቀሳል። የሚያግባባ ሀገራዊ ትርክት አለመኖሩም ችግሮቻችንን በቀላሉ አልፈን እንዳንሻገር እንቅፋት እንደሆኑብን የሚያስማማን ሀቅ ነው።

በአዲስ መልክ እየተገነባች ባለችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ልሟቷንና የማደግ ተስፋን በሚመጥን ልክ ሕብረ ብሔራዊ አንድነቷን አስቀጥላ ትጓዝ ዘንዳ መንግሥት የበኩሉን እየሠራ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ የሚያነሳው እውነታ ነው። በዋናነትም በታሪክ አጋጣሚም ሆነ በነበሩ ብልሹ የአመራር ስልቶች ጥያቄና ቅሬታ ያላቸው አካላት ተቀራርበው በአንድ የውይይት አውድማ መምከር ያስችላቸው ዘንዳ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሙ የዚሁ ሥራ አንዱ አብነት ነው።

ለመሆኑ ሀገሪቱ ዘመኑን የሚዋጁ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ይኖራት ዘንድ ምን ሊሠራ ይገባል? ለመቃቃራችን ቁልፍ ምክንያት የሚባሉ ተረኮችን አስወግደን የወል ትርክትን እንዴት መፍጠር እንችላለን? የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን ይዘን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረዳት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ምህረቱ ሻንቆ (/) ቢሮ ተገኝተናል። ከእንግዳችን ጋር ያደረግነውን ውይይት እነሆ ብለናል።

 አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ ስለትርክት ምንነትና ለአንድ ሀገር ስላለፈው ፋይዳ ያንሱልንና ውይይታችንን እንጀምር?

ምህረቱ (ዶ/ር)፡– ሀገር ስንል በትልቁ ስዕል ብዙ ነገር በውስጡ የያዘ ነው። ሀገርን ሀገር ከሚያደርጉ ብዙ ነገሮች አንዱና በጣም ወሳኙ ትርክት ነው። ትርክት በመሰረቱ ይፈጠራል፤ ሲፈጠር ደግሞ አንድ የተከናወነ ወይም የሆነ ነገርን መነሻ በማድረግ ይነሳል። ከተነሳ በኋላ ማን ፈጠረው? ለምን ተፈጠረ? እንዴት ተፈጠረ? መቼ ተፈጠረ? የሚሉት ነገሮች ደግሞ ተከትለው ይመጣሉ። ትርክት በአይነቱ አወንታዊ ወይም አሉታዊ ሊሆን ይችላል። ይህም ሲባል ትርክት መፍጠሩ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ የሚነገርበት መንገድ፤ ለሌሎች የምናስተላልፍበት ሁኔታ በጣም ኃይል አለው። በአጠቃላይ ሀገርንም የሚጠቅመውም ሆነ የሚጎዳው በሚነገርበት መንገድ ነው።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ብዙ ነገሥታት ወይም መሪዎች ነበሩ፤ እነዚያ ነገሥታት መልካም ነገር ሰርተዋል፤ በዚያው ልክ ደግሞ በዘመናቸው የተፈጠሩ ክፍተቶች ወይም ውስንነቶች ነበሩ። ስለዚህ ውስንነቱ ብቻ ጎልቶ የሚታይ ከሆነ ትርክቱ የተነገረበት መንገድ ሊሆን ይችላል። ምንም ስህተት አልነበራቸውም ተብሎ የሚነገር ከሆነ ትርክቱ የተወራበት መንገድ ያመጣው ውስንነት ነው። ስለዚህ ትርክቱን የምንገልፅበት ሁኔታ መልካምም ሆነ ሆነ መጥፎ ብለን እንድናምን ያደርጉናል። በመሆኑም ትርክት ለእኔ የሚፈጠር ነገር ነው፤ ከዚያ ከማን? ለማን? መቼ ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች ተከትሎ ይመጣል።

በጥቅሉ ትርክት ሀገርን ይገነባል፤ ሀገርን ያፈርሳል። በመሆኑም ቆም ብለን ማሰብ ያለብ ነገር በትርክት ሀገርን እንዴት እንገንባ? የሚለውን ነገር ነው። የብዙ ሀገራትን ታሪኮችን ብናይ በትርክት ምክንያት የጠፉ፤ የወደሙ፤ ጉዳት የደረሰባቸው በርካቶች እንደሆኑ እንረዳለን። እ.ኤ.አ 2013 ላይ ግብፅን ካጋጠሟት ፈታኝ ሁኔታዎች ዋነኛው ጉዳይ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቀ ትርክት ነው። ያ ትርክት ግብፅን እንድትናወጥ አድርጓታል። ብዙ ሀገራት በአንድ ትርክት ምክንያት የሕዝባቸው ማኅበራዊ ትስስር ሲበላሽ አይተናል፤ የፖለቲካ ትስስር ሲፈርስ ተመልክተናል። ሕልማቸው ሲጨናገፍ፤ እድገታቸው ወደ ኋላ ሲቀር አስተውለናል።

አንዳንዶች ደግሞ መልካም ወይም አወንታዊ ትርክትን በማስቀደምና እሱ ላይ በመሥራት ሀገራቸውን ከፍ አድርገው፤ በዓለም ሀገራት ተርታ እንድትቆም ያደረጉ አሉ። ስለዚህ መልካም ሆነ መጥፎ ትርክት የምንፈጥረው በምርጫችን ነው ማለት ነው። የምንፈጥረውም እኛው ነን፤ የተፈጠረውንም በመልካም መንገድ ትውልድ ጋር እንዲደርስ የምናደርገውም እኛው ነን። የሁላችንም ሚና ተደምሮ ነው የአንድ ሀገር ትርክትን የሚፈጥረው።

ግን ደግሞ መንግሥት የአምበሳ ድርሻ አለው። መንግሥት ትርክትን ማስረፅ፤ ትውልድ ጋር እንዲደርስ የማድረግ አቅም አለው። በተመሳሳይ ተቋማትና ሊሂቃን እንዲሁም ማኅበረሰቡ የየራሳቸውን ድርሻ አላቸው። ስለዚህም ሁሉም አካላት ሚናቸውን በአግባቡ ከተወጡ ሀገራዊ ትርክትን እንፈጥራለን።

ስለዚህ ለሀገረ መንግሥትም ሆነ -ለብሔረ-መንግሥት ግንባታም ወሳኙ ትርክትን መገንባት ነው። የትኛውም አወንታዊ፤ አሰባሳቢ፤ አብረን እንድንቆም የሚያደርገን፤ ልዩነቶች እያሉ መልካም ነገሮች ላይ እንድናተኩር የሚያደርገን ትርክት ልንገነባ ይገባል። በመሰረቱ ልዩነትን የሚያጠፋ ትርክት የለም፤ መንግሥትን የሚቃወሙ ሰዎች በዘመናት መካከል አይጠፉም ወደፊትም ይቀጥላሉ፤ ነገር ግን ምሰሶ የሆኑ፤ በጋራ እንድንቆም የሚያደርጉ ነገሮች ላይ አንድ መሆን መቻል አለብን።

ደቡብ አፍሪካውያን አፓርታይድ ሥርዓትን ገርስሶ ለማጥፋት ”እንደ ደቡብ አፍሪካዊ አንድ ላይ እንቁም” ብለው ነው የተነሱት። እነዚህ ሰዎች በፖለቲካ እሳቤ አይስማሙም ነበር፤ ነገር ግን የጋራ ጠላት አላቸው፤ በዚያ ዙሪያ የጋራ ትርክትን መፍጠር ችለዋል። በአሜሪካም ዲሞክራቶችና ሪፐብሊካን የማይስማሙበት በርካታ ጉዳዮች አሉ፤ ነገር ግን በአሜሪካ ደህንነት ላይ፤ ኢኮኖሚና አንድነት ላይ የጋራ የሆነ አቋም ግን አላቸው።

በእኛ ሀገርም ልዩነት እንደ ልዩነት ተቀብለን የጋራ የሆኑ ጉዳዮች ላይ አብረን የመቆም ትርክትን መፍጠር መቻል አለብን። እስከዛሬ የተከሰቱት ጥፋቶች ይህንን የጋራ ትርክት መገንባት ባለመቻላችን ነው። የጋራ የሚያደርጉን እሴቶችን እሱ ላይ ሥራ መሥራት አለብን።

አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ ለተፈጠሩ ችግሮች የትርክቶች ተፅዕኖ ምን ያህል ነው ማለት ይቻላል?

ምህረቱ (ዶ/ር) ፡– ትርክት በሀገራችን ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል። ዛሬ የገባንበት የፖለቲካ ስብራቶች ትናንት የወረስናቸው የትርክት እዳዎች ናቸው። እነዚያ የትርክት እዳዎች እኛም እንዳንደግመው እሰጋለሁ። እዳን መክፈል እንጂ በእዳ ላይ እዳን መጨመር የለብንም። ትላንት ከነበሩና አብረን እንዳንኖር የሚያደርጉን ነገሮች ማስቀረት ይገባናል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለሀገሩ መቆም አለበት፤ ማሰብና መሥራት ይጠበቅበታል። ከሁሉም በፊት ሰው ሁሉ ኢትዮጵያዊነቱ እንዲሰማው ማድረግ ይገባል። የሚያግባቡን የጋራ የምንላቸው ድሎቻችን ላይ የጋራ ድርሻ እንዳለንም መተማመን ይገባናል።

ለምሳሌ የጋራ የሆነውን ዓድዋን እንውሰድ፤ ዓድዋ የሁላችን ሆኖ ሳለ ዓድዋ ላይ የምንሻማ ከሆነ፤ ዓድዋ ላይ የእኔ ድርሻ ከፍ ያለ ነው፤ ያንተ ያንሳል የምንል ከሆነ፤ እዚህ ላይ የእኛ ትርክት ልዩነትን እንጂ አንድነትን አይፈጥርም። ስላለፉ ነገሥታት አስበን እርስበርሳችን የምንጣላ ከሆነ እሱም እንደ አሉታዊ ትርክት ነው የሚወሰደው። ምክንያቱም ደግሞ ነገሥታት በዘመናቸው ሥራ ሠርተው ሄደዋል፤ እኛ እነሱን ወደ ኋላ ሄደን መመዘንም ሆነ እነሱ ላይ መፍረድና መኮነን አንችልም። ግን ደግሞ እነሱ የሠሩትን ስህተቶች መድገም የለብንም። ይልቁኑ እነሱ የሠሩትን መልካም ነገር ግን ማስቀጠል ነው ያለብን። ስለዚህ ትናንት የነበሩትን ክፍቶች ዛሬ ላይ ላለመድገም ነው መሥራት ያለብን።

የትናንትና አመራሮቻችን የሚያሰባስበንን ነገር ካልሠሩ፤ እነሱ አልሰበሰቡንም፤ አላለሙም፤ አላሳደጉም፤ አልሠሩም ካልን ልክ እንደነሱ እኛም ያልተሠሩ ጉዳዮችን ብቻ በመዘርዘር ነው ጊዜያችንን ነው የምናቃጥለው ። ነጮች እንደሚሉት ታሪክን መማር ሳይሆን የሚጠቅመን ከታሪክ መማር ነው። ይህ ሲባል ታሪክ አይጠቅምም እያልኩኝ አይደለም፤ ነገር ግን ከታሪክ ተምረን፤ ስህተቶችን አርመን፤ መልካም ነገሮችን አስቀጥለን፤ የጋራ የሆኑ ሀገራዊ ስሜቶቻችንን ቀስቅሰን ለሀገር እድገት አብረን ነው መቆም ያለብን።

ለምሳሌ ዓድዋ ኢትዮጵያኖች ድል ነው፤ ዓድዋ ውስጥ የምናየው ብዝሃነትን ነው። አፍሪካውያንን የሚኮሩበትን የድል ታሪክ እኛ ግን ድሉን ለየግላችን እየወሰድን በገዛ ሀገራችን ላይ መከፋፋል እንፈጥራለን።

በጥቅሉ ትናንት የነበሩ የጋራ ትርክቶቻችንም ማስተካከል የምንችል ከሆነ ዛሬያችንንም ሆነ ነጋችን ማስዋብ እንችላለን ብዬ አስባለሁ። ትናንት ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ግን የነበረው መልካም ነገር አንስተን ተስማምተን ልንቀጥል ነው የሚገባው። ይህንን ስል የትናንትናውን ስህተት የክርክር አጀንዳ አድርገን፤ እየተከራከርን ሕይወታችንን ከማባከን ይልቅ እኛም ዛሬ ላይ ከእነሱ ተምረን የተሻለ ነገር ልንሠራ ነው የሚገባን። የተሻለች ኢትዮጵያን ፈጥረን ለልጆቻችን መልካምና ለሁላችንም የምትሆን ሀገር ማስተላለፍ ነው የእኛ የቤት ሥራ መሆን ያለበት። ነገር ግን ይህንን ማድረግ ካልቻልን ለልጆቻችን የምናስተላልፈው እዳ ነው የሚሆነው።

አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ በየክልሉ የሚታዩ አለመረጋጋቶች ፅንፍ የረገጡ ትርክቶች ውጤት ነው የሚሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች አሉ፤ እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?

ምህረቱ (ዶ/ር) ፡- የሰው ልጅ ሕይወትም፤ ሀገርም፤ ጊዜም በሶስት ነገር ይገለፃሉ፤ ይኸውም ያለፈው፤ የአሁኑና የወደፊቱ ተብለው። ሶስቱም እንደበርጩማ እግር አንዷ እግር ከተሰበረች በሁለቱ መቆም አይችልም። ስለዚህ ትናንትን እንደጠላት መቁጠር፣ ዛሬን ብቻ ከፍ አድርጎ ማውራት፤ ነገን መፍራት አይቻልም። ሶስቱንም በሚዛን ማየት ብቻ ነው የሚያዋጣው።

ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ላይ ያጋጠሙን ችግሮች የፖለቲካ ትርክቶች ናቸው። የፖለቲካ ትርክት ደግሞ የሚስተካከለው በፖለቲካ ትርክት ነው። ነጮቹ እንደሚሉት የተበላሸ ስርዓት የሚቃናው በተስተካከለ ሥርዓት ነው። ስለዚህ የፖለቲካ ትርክት ስብራቱ የሚጠገነው በተስተካከለ የፖለቲካ ትርክት ነው። የፅንፈኝነት ምንጭ አንዱ ከትናንትናው ትርክት የመጣ ነው፤ በተለይ አንተን ወይም አንቺን ሊያጠፋ ነው የሚሉ እሳቤዎችን ይዘን አድገን ከሆነ እሱን ነው ተግባራዊ የምናደርገው። ከአብሮነት ይልቅ በመካከላችን የተዘራው ልዩነት፣ መፈራራት፣ መገፋፋት ከሆነ እሱ ነው የሚመራን።

ስለዚህ ዛሬ ላይ ማርቲን ሉተርኪንግ እንደተናገው ጨለማን በጨለማ ማሸነፍ አንችልም፤ ጨለማን በብርሃን ብቻ ነው የምናሸንፈው። ከታች ከሕፃናት ጀምረን መልካምነትን፤ ኢትዮጵያዊነትን ቀርፀን ማሳደግ አለብን። ሕፃናትን ስናሳደግ እነሱ የተገኙበት ብሔረሰብ ከሌላው እንደማይበልጥ፤ ከሌላው ጋር እንዴት መኖር እንደሚቻል፤ ኢትዮጵያዊነት ማለት ሁሉንም ያሰባሰበ ግን አንድ የጋራ ሀገር እንዳለን ማስተማር፤ ትውልድን መልካም ስሜት ማስታጠቅ ግድ ይላል።

በመሰረቱ ይህንን ችግር ካልፈታን ዛሬ ላይ ያውን ፅንፈኝነትን ብናስወግድ እንኳን ነገ ሌላ ፅንፈኝነት ሊፈጠር ይችላል። ስለዚህም አሰባሳቢ ትርክት ላይ ያለመታከት መሥራት አለብን።

ፅንፈኝነት ሀገራችንን በእጅጉ ጎድቷታል፤ ልማቱን፣ የሰው ሕይወትን ዋጋ አስከፍሏል፤ የወደፊቱን የኢትዮጵያ አቅጣጫ ሳይቀር ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ችግር አስከትሏል። ሆኖም መንግሥት በሆደሰፊነት ሁኔታዎችን እየተመለከተ ከጥፋት ሀገሪቱን እየታደጋት ይገኛል።

ለምሳሌ የሰሜኑ ጦርነት በሰላም እንዲጠናቀቅ መንግሥት ያደረገው ጥረት ትልቁ ማሳያ ነው። ያንን መልካም ተሞክሮ በየቦታው መድገም ያስፈልጋል፤ በአማራም ሆነ በኦሮሚያ አልያም በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች መድገም ይገባል። በእርግጥ አንዳንድ ቦታዎች ላይ መንግሥት በልበ ሰፊነት የጀመራቸው ሥራዎች የሚበረታቱ ናቸው። ምክንያቱም ከሰላም ውጪ ሌላ አማራጭ የለውም። በጦርነት ጀምራ በጦርነት የጨረሰች ሀገር የለችም። ብዙ ኪሳራ ከደረሰ በኋላ መቆሙ ስለማይቀር፤ ኪሳራው ከመድረሱ በፊት በውይይት ችግሮች እንዲፈቱ ማድረጉ ጠቃሚ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት አንድ ጥይት ሲተኮስ ዶላር ነው፤ ይህም ሲባል በሌላ በኩል ኢኮኖሚው እየተጎዳ ነው ማለት ነው። ስለዚህ የፖለቲካ ትርክት ኢኮኖሚውንም ይጎዳል፤ ኢኮኖሚው ተጎዳ ማለት ደግሞ ማኅበራዊ ሕይወት ተናጋ ማለት ነው።

ይህንኑ በመረዳት መንግሥት አለመግባባቶች በሰላም እንዲቋጩ ይፈልጋል። ሆኖም የመንግሥት ፍላጎት ብቻ ውጤታማ አይሆንም፤ ሌላኛውም አካል ሊስማማ ይገባል። ሁለቱም የየራሳቸውን ኃላፊነት በሚገባ ሲወጡ ነው ሀገር የምትረጋጋው። መንግሥት ለሰላም ሆደ ሰፊነቱን ማስቀጠል አለበት፤ ግን ደግሞ ተፋላሚው አካል ለሰላም በሩን የማይከፍት ከሆነ መንግሥት ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል።

ከሁሉም በላይ ግን ለግጭት ምክንያት የሆኑ ነገሮችን በሙሉ ወደ ጠረጴዛ ማምጣት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የምክክር ኮሚሽኑ የፅንፈኞችንም ሆነ የገዢ ፓርቲንም ሃሳብ ተቀብሎ ሕዝብ እንዲወስን የማድረግ ሥራ እየሠራ ነው። ይህም የበለጠ ይፈታዋል ተብሎ ይታሳባል፤ እኛም እንደ ሕዝብ ተወካይነታችን፤ ሌላው አካል እንዲሁ ባለበት ኃላፊነታችንን መወጣት ስንችል ነው የኢትዮጵያን ሰላም ማረጋገጥ የሚቻለው። የወል ወይም የጋራ ትርክት የሚፈጠረው ሁሉም ተስማምቶ፤ አንድ ላይ የሚያዋጣ ነገር ላይ ሲደርስ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ሃሳቦችን ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው ከተግባባን ብቻ ነው። አለዚያ ግን እኩል የማንሳተፍ ከሆነ ሰላማችን ላይ እውን ሊሆን አይችልም።

አዲስ ዘመን፡- ታዲያ የወል ትርክትን ለመፍጠር ከማን ምን ይጠበቃል ? በዚህ ረገድ የምሁራኑና የሃይማኖት ተቋማት ሚና ምን ሊሆን ይገባል ይላሉ?

ምህረቱ (ዶ/ር) ፡- በመሰረቱ ይሄ ጉዳይ ለአንድ አካል የሚተው አይደለም። እኔ በተቀመጥኩበት ቦታ ከእኔ የሚጠበቀውን ነገር ከሠራሁ ሚናዬን ተወጥቻለሁ ማለት ነው። የእያንዳንዳችን ጥረት ሲደመር ኢትዮጵያን አፅንቶ ያቆማታል። ሚናን በየአውዱ ካላየን በስተቀር አንዱ ከአንዱ እየጠበቀ በመሃል ሥራው ሳይሠራ ይቀራል። እንዳነሳሽው የምሁራን ሚና ብዙ ጊዜ ይነሳል። ተፅፏል፤ ተዘርዝሯል። ይነገራል፤ ይወራል። አሁን ያለንበት የፖለቲካ አውድ ሕዝበኝነት ወይም ታዋቂነትን የሚከተል ነው። አንድ ሰው ከፈለገ አራትና አምስት ሚሊዮን ሰው ተከታይ ሊኖረው ስለሚችል የሰውዬው ስሜት አራት ሚሊዮንን እንደፈለገ ያደርጋል። በነገራችን ላይ ምሁር ማለት የሆነ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ማለት ብቻ አይደለም፤ የመንግሥት አመራሮችንም እንዲሁ ምሁራን ወይም ሊሂቃን ሊባሉ ይችላሉ። ነገሮችን መቅረፅ፣ ማዛባት፣ ማስተካከል የሚችል አካል ምሁር በመሆኑ ነው።

በተለይ የፖለቲካ ምሁር ሀገሪቱን የሚያይበት ሁኔታ ወሳኝ ነው። ስልጣን ወይም ሃብት የያዘ፤ አጀንዳ መቅረፅ የሚችል ሰው ፖለቲካውን እንደፈለገ ሊያዛባ ይችላል። በቁጥር ደረጃ ትንሽ ቢሆኑም የሀገር ኃላፊነት ተሰምቷቸው የተሰማሩበት ወይም የሚቀርፁት አጀንዳ በጤናማ መንገድ ካልቀረፁ በስተቀር አስቸጋሪ ነው። ተከታይ ያላቸው ሰዎች ተከታዮቻቸው ጤናማ አጀንዳ መስጠት ከቻሉ ሀገርን ማቆም ይችላሉ። መንግሥትን መቃወምና ሀገርን መቃወም የተለየ መሆን አለበት። መንግሥት ይመጣል፤ ይሄዳል።

ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተለዩት መንግሥታዊ አስተዳደርን መቃወምና ሀገርን እንደሀገር መቃወም ነው። ይህንን ነው መለየት መቻል ያለብን።

በጥቅሉ ምሁራን የሚሠሩት ሥራ ሀገርን ማዕከል ያደረገ መሆን አለበት፤ ባለሃብቱ ያለው ሃብት ሀገርን የሚገነባ መሆን አለበት፤ ምክንያቱም ሃብቱ የሚጠበቅለት ሀገር ስትኖር ነው። ሕንፃው ጤናማ የሚሆነው ሀገር ስትኖር ነው። ስለዚህ ባለሃብቱም ሃብቱን መመደብ ያለበት ሀገር በሚገነባ ጉዳይ ላይ ነው እንጂ ጠመንጃ ገዝቶ የሆነ አካልን ለመደገፍ ከሆነ ሃብቱም አይዘልቅም፤ ልማቱም አይሳካም።

በምሁራኑም በኩል እንደዚሁ ነው። ፅንፈኝነትን የሚያበረታታ የምሁራን ሚና ሊኖር አይገባም። አሁን እንደሀገር የገባንበት ሁኔታ ኢትዮጵያ እንደትበተን የሚያደርግ በመሆኑ ከዚህ ተግባር መታቀብ ተገቢ ነው። እነሱ ማሊያ አንድ ወቅት የውስጥ ችግራቸውን መፍታት ባለመቻላቸው ተመልሰው መንግሥት መሆንም ሆነ ጠንካራ ሀገር መሆን አልቻሉም። ስለዚህ ከእነሱ ልንማር ይገባል።

የሃይማኖት ተቋማትም ሚናቸው የጎላ ነው። አሜሪካ በተሠራው አንድ ጥናት ከጠቅላላው የአሜሪካ ሕዝብ የሃይማኖት ተቋማትን የሚያምነው 42 በመቶ ብቻ ነው። ቀሪው 58 በመቶ አያምንም ማለት ነው። የሃይማኖት ተቋማት አመኔታ ካጡ የመጨረሻ መውደቂያ ይጠፋል።

በሌላ አነጋገር የሃይማኖት ተቋማት እንደፈጣሪ ተወካይ ተደርገው የሚቆጠሩ በመሆን እነሱ ላይ እምነት ሲታጣ የሚፈጥረው አደጋ ከባድ ነው። አሁን ላይ እንደሚታየው በሃይማኖት ተቋማት ላይ የአመራር ችግር እየበዛ ነው። አመራር ላይ ክፍተት ካለ አማኙም ላይ ይበዛል፤ ውጤቱ ደግሞ ሀገርን ይረብሻል። የሃይማኖት ተቋም ኃላፊነታቸው አንዳንድ ጊዜ ከመንግሥት በላይ መሆን አለበት። ለፍትህ ዘብ መቆም አለባቸው። የሃይማኖት ተቋማት አሁን ላይ የምንሰማቸው የሚያስደነግጡ ነገሮች ናቸው። አንዳንድ ቦታ ላይ መንግሥት ተሽሎ የሚገኝበት ሁኔታ አለ፤ ያ ግን መሆን አልነበረበትም።

አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር የወል ትርክትን ለመፍጠር የተጀመሩ ሂደቶች በእርሶ እይታ ምን ይመስላል?

ምህረቱ (ዶ/ር) ፡- አስቀድሜ ለመግለፅ እንደገለፅኩት የሀገርም ሆነ የትውልድ ግንባታ በአንድ ጀምበር የሚሳኩ አይደሉም። ዛሬ ላይ የምናያቸው ውጤቶች አሉ፤ ከገጠመን ከፈተና አንፃር እስከዛሬ ተቋቁመን መኖራችንም ትልቅ ነገር ነው። ምክንያቱም ያጋጠሙን ፈተናዎች ውስብስብ እና በርካታ ናቸው። ሕዝቡ አብሮ እንዳይኖር የሚያደርጉ፤ የሃይማኖት አባቶች እርስበርሳቸው እንዲጣሉ የሚያደርጉ፤ አማኞች ወደ ቤተ-እምነት እንዳይሄዱ የሚያደርጉ፤ የሚያጋጩ ትርክቶች ተፈጥረዋል።

ባለፉት ሰባት ዓመታት ሙሉ ለሙሉ ማንም ሰው ማንም እንዳያምን ተደርጎ የተፈጠሩ የውሸት ትርክቶች አሉ። ብሔር የሚሰደብበት፤ ሃይማኖት የሚንቋሸሽበት ሁኔታ አይተናል። ሕዝቡ ግን ከጅምሩም መልካም እሴቶች ስላሉት ከአሁናዊ ነገሮች ይልቅ የነበረውን ትስስር በማክበር ዘልቋል። የተፈጠሩ ብዙ መልካም ነገሮች አብረን እንድንኖር፤ ኢትዮጵያ ማለት ራሷን በዓለም ደረጃ ከፍ ማድረግ እንዳለባት፣ ብዙ የልማትና ፖለቲካ ሥራዎች ፤ የእኛ ድምፅ እንዲሰማ የተደረገበት ብዙ መልካም ትርክቶች ኢትዮጵያን የሚመጥናት ከተማ፤ አመራር እንዲፈጠሩ ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል።

ይሁንና በተሠራው ልክ ማኅበረሰቡ ተረድቷል፤ በዚያ ልክ እየኖረ ነው ማለት ግን አይቻልም። 130 ሚሊዮን ሕዝብ ይዞ በአንድ ጊዜ ሁሉም ነገር ተስተካክሎ መስመር ይዞ መሄድ አይቻልም። ነገር ግን ብዙ ተስፋ ሰጪ ሥራዎች ተሠርተዋል። ተስፋን የሚያጨልሙ ነገሮች ደግሞ ተፈጥረዋል። ግን እስከአሁን መቋቋም ችለናል።

ከዚህ በመነሳት አሁንም ቢሆን ፈተናዎችንን እየቀነስን፤ መልካም ነገሮቻችንን እያጎለበትን መሄድ ብቻ ነው የሚያዋጣው። አለዚያ እንደ ሀገር ሕዝብ እየጨመረ፤ በዚያው ልክ ፍላጎቶች እየጨመሩ፤ ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች እያሉ በቀላሉ መኖር የለብንም። ብዙ ፈተናዎችንም ለመጋፈጥ ዝግጁ መሆን አለብን። ሕዝቡ ከእኛ በሚፈልገው ልክ መዘጋጀት አለብን። ለዛሬውም ሆነ ለመጪው ፈተና ከፍ ብለን ኢትዮጵያን የሚመጥኑ ሥራዎች መሥራት ነው የሚጠበቅብን።

ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ምሳሌ ልንገርሽ፤ አንድ አውሮፕላን መብረር ከጀመረ በኋላ ከስሩ ተጠምጥሞ ዘንዶ ተገኘ፤ የአየር ትራፊኮች ለአብራሪው የመከሩት ዘንዶው እንዲወድቅ ከተለመደው በላይ ፍጥነት እንዲጨምር ነው። እሱም ያንን አደረገ፤ እንደተባለውም ዘንዶው ወደቀ። ስለዚህ እኛ ዛሬ ላይ የገጠመንን ችግር ፊት ለፊት መጋፈጥ ብቻ ሳይሆን በልማቱ ላይ፣ በአብነት ላይ፤ በመስማማቱ ላይ፣ የወል ትርክትን ፍጥነታችንን ስንጨምር ብቻ ነው የዛሬን ፈተና መጣል እና ማለፍ የምንችለው። አለበለዚያ ግን ፈተናውም ከእኛ አቅም እኩል ሲሆን ሕዝብ ተስፋ ይቆርጣል።

አዲስ ዘመን፡- በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ካላት የወጣት ቁጥር አንፃር ወጣቱን ተሳታፊ ማድረግ ያለመቻሉ ለተፈጠሩ ችግሮች እንደ አንድ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል? ከሆነ ምን ሊደረግ ይገባል?

ምህረቱ (ዶ/ር) ፡- ወጣቱ አሁን ላይ ተመልካች ሳይሆን ችግር ፈቺ ማድረግ ብቻ ነው የሚያዋጣው። ወጣት ተመልካች በሆነበት ሀገር ውስጥ ሀገሪቱ የማደግ እድሏ ጠባብ ነው። አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የወጣቱ ቁጥር 70 በመቶ ነው እንላለን፤ በቁጥሩ ልክ ግን ትኩረት ያስፈልገዋል። አስቀድሜ እንዳነሳሁት ከታች ጀምሮ ሥራ ፈጣሪ ትውልድ መቅረፅ ያስፈልጋል። የወጣቱን የልቦና ውቅር ከጅምሩ ማስተካከል ያሻል። ሥራ የለም የሚባለው መንግሥት ቢሮ ውስጥ ቁጭ ብሎ ለመፈረም ከሆነ መቼም ቢሆን ይሄ ችግር አይፈታም።

ስለዚህ የሥራ እድል መፍጠር መንግሥት ለሁሉም ሊፈጥር አይችልም። አሁን ላይ ከአራት ሚሊዮን ያላነሰ የሥራ እድል ውጭ ሀገር ጭምር እየላከ ወጣቱ ተጠቃሚ እንዲሆን እያደረገ ነው። ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በየዓመቱ የሚመረቀው የሚወጣው ወጣት ምን አይነት አዕምሮ ይዞ ወጣ? ወጣቱን ተፈላጊ የሚያደርግ ነው? ሥራ ፈላጊ የሚያደርግ ነው? የሚለውን ነገር መፈተሸ አለብን። ምክንያቱም ደግሞ የሥራ ባሕላችን ካልተቀየረ በስተቀር 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሲቪል ሰርቫንት የያዘች ሀገር ከዚህ የመሸከም አቅም አይኖራትም።

አስተሳሰባችንን መቀየር አለብን። ኢትዮጵያን ሊያስጠራ የሚችል፤ ኢትዮጵያን ሊሸከም የሚችል ወጣት በዓለም አቀፍ ደረጃ ላይ ኢትዮጵያን ሊመጠን የሚችል ነገር ይዞ የሚገኝ ወጣት ያስፈልጋል። እንደ ሀገር ወጣትን የሚወክል ነገር ካልሠራን ውጤታማ ልንሆን አንችልም። በዚህ ረገድ መንግሥት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፤ በአንፃሩ ወጣቱም ቢሆን ሁሉንም ከመንግሥት ሳይጠብቅ ሥራ የመፍጠር ባሕል ሊያዳብር ይገባል።

አዲስ ዘመን፡- ለትውልዱ መበላሸት የትምህርት ሥርዓቱ አንደኛው ተጠያቂ እንደሆነ ይጠቀሳል፤ የትምህርት ሥርዓቱ ክህሎትን ያገለለና ለክህሎት ቦታ የማይሰጥ መሆኑ ወጣቱን ከሥራ ፈጠራ እንዳሰናከለው ይገለጻል፤ እዚህ ላይ ያልዎት ምልከታ ምንድን ነው?

ምህረቱ (ዶ/ር) ፡- ክህሎትን በተመለከተ አንድ ሰው ከማስተርስ ይልቅ ክህሎት ያለው ሰው ነው በዓለም ላይ እየተፈለገ ያለው። አውሮፓ በሰው ልማት በጣም ብዙ እየሠራችና ከአፍሪካ ሳይቀር በርካታ ወጣቶችን እየፈለገች ነው። ኢትዮጵያ በዚህ ላይ ብዙ መሥራት አለባት ብዬ አምናለሁ። ዲግሪ መያዝ ጠቃሚ ነው፤ ሆኖም ሀገር የሚለወጠው ሙያም (ክህሎት) ሲታከልበት ነው።

እያንዳንዱ ባለዲግሪ ሙያ ቢኖረው የሥራ እድል ችግር አይነሳም። እስከአሁን ባለው ሁኔታ በሙያ ደረጃ አልሠራንም። ለዚህ ነው ሁሉንም ነገር ከውጭ የምናስገባው። ሰው በሙያው ሲሠራ ፈጠራዎች ይመጣሉ። ኬንያ በሳምንት ብቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት የሚያገኙት ከ20 ያላነሱ አዳዲስ ፈጠራዎችን ታስተዋውቃለች። ጃፓን የተፈጥሮ ሃብት እምብዛም የላትም፤ የልጆቿን ጭንቅላት ተጠቅማ ነው ማደግ የቻለቸው። እኛም ሀገር ትውልዱ ቢነቃና ክህሎቱን ቢያሳደግ፤ ያንን የሚያበረታታ ሥርዓት ከተዘረጋ ያደጉት ሀገራት የደረሱበት መድረስ የማንችልበት ምክንያት የለም።

አዲስ ዘመን፡- መንግሥት ሙስናን መከላከል ባለመቻሉና በተቋሞቹ ተጠያቂነትን ማስፈን ያለመቻሉ በሕግና በሥርዓት የሚመራ ሀገር ወዳድና ለሕዝብ የቆመ ትውልድ እንዳይፈጠር ምክንያት ነው ብለው የሚያነሱ አካላት አሉ። ይህ ለእርሶ ምን ያህል ኣሳማኝ ነው?

ምህረቱ (ዶ/ር) ፡– በመሰረቱ ሌብነት ወይም ሙስና የግለሰብ፤ ተቋም፤ መንግሥታዊ ወይም ሥርዓታዊ ሊሆን ይችላል። አሁን ባለው ሁኔታ በእኛ ሀገር መንግሥታዊ (ሥርዓታዊ) ሌብነት አለ ብዬ አላምንም። አሁንም ግን ግለሰባዊ ሌብነት አለ። ስለዚህ ሁለቱን መለየት ያስፈልጋል።

ግለሰባዊ ሌብነት መንግሥት ከመከላከልና ተጠያቂ ከማድረግ አንፃር አንዳንድ ጊዜ መንግሥት የሚያስጮኻቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ግን ሳይናገር የሚወስዳቸው ርምጃዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ብዙ ጊዜ ግን እኛ ትላልቅ ሚኒስትሮች ካልታሰሩ በስተቀር ርምጃ እየተወሰደ አይመስለንም። ወይም ደግሞ የማንፈልጋቸውን ሰዎች አዕምሯችን ውስጥ እናደርግና ይሄ ሰው ካልተነቀለ፤ ካልተነሳ እንላለን። ሙስና የሚጸዳው በዚያ ብቻ ነው ብዬ አላስብም። ሙስና (ሌብነትን) የሚጠላ ትውልድ ማፍራት ካልቻልን በስተቀር በዘመናት መካከል የሚሰርቁ ሰዎች አይጠፉም።

በመጀመሪያ ደረጃ የሚሰርቁ ሰዎች ነጋቸውን የሚፈሩ ሰዎች ናቸው። ነገ እድል የለኝም፤ ከዚህ ቦታ ከተነሳው ስለምጠፋ ማከማቸት አለብኝ ብለው የሚያስቡ ሰዎች ናቸው። ማንኛውም ሰው በክህሎቱ ካመነ በብቃቱ ከተመካ፤ በፈጣሪው ካመነ የእናቶችን፣ የአባቶችንና የድሆችን ገንዘብ አይበዘብዝም። በዚያ ልክ የሚሰማራ ሰው አዕምሮው የተበላሸ ሰው ነው። ብዙ ነገሮችን ዘርፎ ስላከማቸ ተጠቃሚ ነው ልንለው አንችልም፤ ዘርፎ በገነባው ቤት ውስጥም በሰላም ላይኖር ይችላል። የቀደሙ ታሪኮችም የሚያሳዩት ይህንኑ ነው። እንዲህ አይነቶችን ተሞክሮች አውጥተን ፊት ለፊት የመነጋገር ባሕል ልናዳብር ይገባል። የሰረቀው ፊት ለፊት ሌባ ልንለው ይገባል፤ የምንሸፋፍነው ነገር ሀገርን አያድንም።

መንግሥታዊ ሌብነት ግን እንደሌለ ላሰምርበት እወዳለሁ። በመሰረቱ የምክር ቤቱ ዋናው ሥራ እነዚህን ተቋማት መቆጣጠር በመሆኑ መንግሥታዊ ሌብነት አለ ካልን ምክር ቤቱ የለም እንደማለት ነው። ይሁንና ተጠያቂነት መስፈን አለበት፤ ምክንያቱም የሚያጠፉ ሰዎች ካልተቀጡ በጣም የሚሠሩ ሰዎች ተስፋ ይቆርጣሉ። ታማኝነትን የምናበረታታው ታማኝ ያልሆነ ሰውን ስንቀጣ ነው። ተቋማት ላይም የሚሠራና የማይሠራ ሰው ተለይተው የሚሠራውን ስንሸልም የማይሠራው ራሱን ያያል።

ሆኖም እኩል የምናስተናግዳቸው ከሆነ የሚሠራውን ሰው ሞራል ይነካና በመሥራትና ባለመሥራት መካከል ልዩነት ስለሚጠፋበት ከማይሠራው ጋር ይቀላቀላል። በመሆኑም ሁለቱን በልኩ ለይቶ ለሚሠራው በሠራው ልክ፤ ያልሠራውን በተቀመጠው አግባብ ልናስተምረው ልንመልሰው ይገባል ባይ ነኝ።

አዲስ ዘመን ፡- ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።

ምህረቱ (ዶ/ር) ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You