መንግሥት የህዝቡንና የሀገሪቱን ጥያቄዎች መመለስ የሚችለው ከገቢ ግብር በሚሰበስበው ገንዘብ መሆኑ ይታወቃል:: ይህን ታሳቢ በማድረግም የገቢ ግብር የመሰብሰብ አቅሙን እያጠናከረ ይገኛል:: በዚህም በየአመቱ የሚሰበሰበው ግብር እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ በአንዳንድ የበጀት አመታትም ከእቅድ በላይ የተሰበሰበበት ሁኔታም ታይቷል::
እንዲያም ሆኖ ግን ኢኮኖሚው የሚያመነጨው ገቢ እየተሰበሰበ እንዳልሆነ ነው የሚገለጸው:: በእርግጥም ኢኮኖሚው የሚያመነጨው ግብር እየተሰበሰበ አይደለም:: በአሁኑ ወቅት ያለደረሰኝ መሸጥ እንዲሁም ከዋጋ በታች ሽያጭ ማከናወን / በደረሰኝ ላይ ዝቅተኛ የሽያጭ ዋጋ ማስቀመጥ/ የንግዱ ዘርፍ መሰረታዊ ችግሮች እየሆኑ የመጡበት ሁኔታም ይህን ሀቅ በሚገባ ያመለክታሉ:: ሌሎች ተገቢው ግብር እንዳይሰበሰብ የሚያደርጉ ችግሮች እንዳሉ ሆነው ማለት ነው::
ያለደረሰኝ መሸጥ፣ ከዋጋ በታች መሸጥ በንግዱ ማህበረሰብ የሚስተዋሉ የየዕለት ተግባር ሆነው መቀጠላቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ:: እነዚህ ችግሮች የመንግሥትን ገቢ ማስቀረታቸውን ተከትሎ በየአቅጣጫው የሚነሳው የህዝቡ የመልማት ጥያቄ እንዳይመለስ እንቅፋት ይፈጥራሉ::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሰሞኑ በገቢ አሰባሰብ ረገድ ያስመዘገባቸውን ስኬቶች ለማሳደግና ያጋጠሙ ችግሮችን ለይቶ የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያመቸው ዘንድ በከተማዋ ከሚገኙ አምራቾች፣ አስመጪና ላኪዎች ጋር ውይይት አድርጓል:: የውይይቱ ዓላማም በገቢ አሰባሰብ ረገድ የተመዘገቡ በጎ ተሞክሮዎችን ይበልጥ ለማጎልበት እንዲሁም ቀሪ ሥራዎችን ለመሥራት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ነው::
ከተማዋ ከምታመነጨው ኢኮኖሚ ከፍ ያለ ገቢ መሰብሰብ እንዲቻልና በከተማዋ የሚስተዋለውን ከዋጋ በታች ሽያጭ እንዲሁም ምርቶችን ያለ ደረሰኝ መሸጥን ለመከላከል እንዲሁም በገቢ ግብር አሰባሰብ ዙሪያ የሚስተዋሉ የተለያዩ ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ የሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከአምራቾችና አስመጪዎች ጋር ተወያይተዋል:: የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ያለው የንግድ ስርዓት ጤናማ በሆነ መንገድ እንዲመራ እንዲሁም የመንግሥት የገቢ ግብር በአግባቡና በወቅቱ መሰብሰብ እንዲችል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ማድረጉ በዘርፉ ያለውን ችግር ለማቃለል እንደሚረዳ ከመድረኩ ተገልጿል::
በወቅቱም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ፤ የታክስ ህግ ተገዢነትን ተግባራዊ ለማድረግ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ውይይት ማድረግ መቻሉ አስፈላጊ ከመሆኑም ባለፈ በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረው ድርሻ ቀላል ግምት የሚሰጠው እንዳልሆነ አመልክተዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ ምርቶችን ያለደረሰኝ መሸጥ እንዲሁም ከዋጋ በታች መሸጥ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁኑ ወቅት እየተባባሰ መምጣቱን በመስክ ጥናት ማረጋገጥ ተችሏል:: በዚሁ ያለደረሰኝ መሸጥና ከዋጋ በታች በመሸጥ ችግርም የገቢ ሰብሳቢ ቢሮው ብቻ ሳይሆን፣ ባለድርሻ አካላት ጭምር መሰብሰብ የሚገባቸውን ገቢ መሰብሰብ እንዳይችሉ እንቅፋት እንደሆነ የጥናቱ መነሻ እንደሚያሳይ አመላክተዋል::
የችግሩ ምንጭ የተለያየ ቢሆንም በንግድ ሥራ ላይ ከተሰማሩ ግብር ከፋዮች ጋር መወያየትና የጋራ አቋም መያዝ የመጀመሪያው ሥራ ሊሆን ይችላል ያሉት የቢሮ ኃላፊው፤ መድረኩ ታምኖበት የተዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል:: ለታክስ ህግ ተገዢ መሆን ከንግዱ ማህበረሰብ የሚጠበቅ ሲሆን፤ የታክስ ህግ ተገዢነት ማለት፤ ትክክለኛ የታክስ መሰረትን፣ ትክክለኛ የሆነ የታክስ ምጣኔን እንዲሁም ትክክለኛ ስሌትን በወቅቱ ለይቶ ገቢ ማድረግን እንደሚጠይቅ በማስረዳት፤ ለዚህም አስመጪዎችና አምራቾች ከፍተኛ ሚና መጫወት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል::
ቢሮው ‹‹ከየካቲት እስከ የካቲት›› በሚል በጀመረው የግብር መክፈል ንቅናቄ ለተወሰኑ ግብር ከፋዮች ዕውቅና መሰጠቱን ያስታወሱት የቢሮ ኃላፊው፤ መንግሥት ለጥቂት ግብር ከፋዮች ብቻ ዕውቅና በመስጠት ለውጥ ይመጣል ብሎ እንደማያምን እና ብዙዎችን በማሰርና በመቅጣትም ለውጥ ይመጣል ብሎ እንደማያምንም የቢሮ ኃላፊው አስገንዝበዋል:: ከዚህ በበለጠ በንግድ ስርዓቱ እንዲሁም በገቢ አሰባሰብ ሂደት ውስጥ እንቅፋት የሆኑትን ጉዳዮች ለይቶ በማውጣት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መወያየት፣ መግባባትና ተቀራርቦ መሥራት እንደሚገባ አስታውቀዋል::
በመሆኑም በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለይቶ ማውጣት እንዲቻል መድረኮችን በመፍጠርና ተቀራርቦ በመሥራት ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ጠቅሰው፣ ለአብነትም መርካቶ አካባቢ ከሚገኙ ተራ አስጫኞች፣ ጅምላ አከፋፋዮች፣ በየደረጃው ያሉ ቸርቻሪዎችና ከክልል ነጋዴዎች ጋር ቢሮው ሲወያይ መቆየቱን ተናግረዋል:: በእነዚህ መድረኮች የተገኘው ግብዓትም ከአስመጪዎችና ከአምራቾች ጋር ተቀራርቦ መሥራትን እንደሚያመላክት ጠቅሰው፣ በግብር አከፋፈልና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከአምራቾችና አስመጪዎች ጋር በመወያየት ጠቃሚ የመፍትሔ አቅጣጫ እንደሚገኝበት ገልጸዋል::
የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ ዓይናለም ንጉሴ በበኩላቸው፤ የንግዱ ማህበረሰብ በርካታ ችግሮችን እንደሚያነሳ ጠቅሰው፣ በንግድ ስርዓቱ ውስጥ በየጊዜው አይነታቸውን እየቀያየሩ የሚመጡ ችግሮች ስለመኖራቸው አስታውቀዋል:: ችግሮቹ የቱንም ያህል የበረቱ ቢሆኑ በጋራ ውይይትና ምክክር ሊፈቱ እንደሚችሉም አመልክተዋል:: አዲስ አበባ ከተማ የንግድ ማዕከል ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ከአምራችና አስመጪዎች ጋር መወያየትና መመካከር መቻል ጠቀሜታው የጎላ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል::
በንግዱ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በመንግሥት መታየት ያለባቸውን የፖሊሲና የመሳሰሉ ጉዳዮችን በመንግሥት እንዲሁም በታክስ ከፋዩ ማለትም በአስመጪዎችና በአምራቾች በኩል የሚስተዋሉ ችግሮችንም በየደረጃው መፍታት የግድ የሚልበት ወቅት እንደሆነ ነው ሚኒስትሯ ያመላከቱት:: ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ ለማስመጣት የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ትልቅ ማነቆ መሆኑን ጠቅሰው፣ አምራቾች ተኪ ምርቶችን በአገር ውስጥ በማምረት ከአስመጪነት ወደ ላኪነት ለመሸጋገር እየተጉ እንደሆነም ተናግረዋል:: የውጭ ምንዛሪ እጥረት ባጋጠመ ጊዜ የመንግሥትን የፖሊሲ አቅጣጫ አውቆ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት በሚደረገው ሙከራ አምራቾች የሚያስመሰግንና ዕውቅና ሊያሰጥ የሚችል ሥራ እየሠሩ እንደሆነም አስታውቀዋል::
አሁን ያለው የታክስ አስተዳደር በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ማለፉን ነው ሚኒስትሯ የጠቆሙት:: የታክስ አስተዳደሩ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ መሰብሰብ ያለበት መሆኑን አምኖ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግና ህግ ለማስከበር በሚያደርገው ሙከራም የተለያዩ ችግሮች እንደሚገጥሙት ጠቅሰው፣ ይህም የገቢ ግብር በአግባቡ እንዳይሰበሰብ የሚያደርግ አንዱ ችግር ነው በማለት ጠቁመዋል::
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ ለህግና ስርዓት ተገዢ ሆኖ በሚሠራው ዘንድ በተለይም በንግድ ስርዓት ውስጥ ባሉ ያልተገቡ እንቅስቃሴዎች ምክንያት ነጻነት የማጣት ስሜት ይፈጠራል፤ በዚህም ነጻ ሆኖ መሥራት አልቻለም:: የታክስ ህጉ፤ ታክስ ከፋዩ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ታክስ የመክፈል ልምድ እንዲያዳብር የሚፈቅድ ህግ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ህጉን አክብረው ለማይሠሩት ደግሞ ጠንካራና እንዲታረሙ የሚያስችል ህግ ያለው ተቋምም አለ:: በመሆኑም ዜጎች ለራሳቸውና ለአገራቸው ታምነው ለራሳቸው የሚገባቸውን በማስቀረት ለመንግሥትም የድርሻቸውን መስጠት ግዴታቸው ነው::
የመንግሥት የገቢ ግብር አሁን በግልጽ እንደሚታየው አላግባብ እየተመዘበረ እንደሆነ ሚኒስትሯ አስታውቀዋል:: ሰዎች በጊዜያዊ ገደብ ያገኙትን ገቢና ወጪ አስልተው ‹‹ለመንግሥት መክፈል የሚገባኝ ይህን ያህል ነው›› በማለት ያሳውቃሉ:: ይሁንና ግብር ከፋዩ የግብር መጠኑን ካሳወቀ በኋላ ገቢዎች ሚኒስቴር የሚያጣራበት መንገድ ያለው በመሆኑ ያጣራል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ገቢዎች ሚኒስቴር በሚያጣራበት ጊዜ ከተከፈለው ገቢ ተቀራራቢ የሆነ ገቢ እንደገና የሚከፈልበት አጋጣሚ ስለመኖሩ ነው ያስረዱት:: ይህም መንግሥት አምኖ ግብር ከፋዩ በታማኝነት ግብሩን እንዲከፍል ሲያደረግ፤ ግብር ከፋዩ ታምኖ መክፈል አለመቻሉን እንደሚያሳይ ጠቅሰው፣ እንዲህ ያለውን አሰራር በጋራ መግታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል::
ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ እንዲህ አይነቱን አሠራር መግታት ካልተቻለ ልንገነባት የምናስባትን ኢትዮጵያ መገንባትና አስተማማኝ የሆነ ገቢ ማመንጨት እንችልም:: የታክስ ህጉ ነጻነትን ከፈቀደ በኋላ ተጠያቂነትንም አያይዞ የሚሄድ በመሆኑ ህጉ ተግባራዊ ይደረጋል::
በመድረኩ በዋናነት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ከደረሰኝ ጋር ተያይዞ ያለው ችግር መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ ችግሩ እንደ አገር ተመሳሳይ የሆነ መፍትሔ ሊበጅለት እንደሚገባም ገልጸዋል:: ከደረሰኝ ውጪ መሸጥና አሳንሶ ከመሸጥ በተጨማሪ ደረሰኝ አትመው የሚሸጡ ግለሰቦች ስለመፈጠራቸውም አስታውቀው፣ ህገወጥነት ስር እየሰደደ መሄዱን አመላክተዋል:: እነዚህንና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት በየደረጃው ከሚገኙ የመንግሥት አካላት ጋር በመሥራት መፍትሔ ማምጣት እንደሚቻልም ነው የተናገሩት::
በመድረኩ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ በበኩላቸው ለአገር ዕድገትና ለውጥ የንግዱ ማህበረሰብ ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸው፣ በጋራ ችግሮች ላይ በጋራ ተወያይቶ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል:: ‹‹ግብር ከፋይና የግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤት ቤተሰብ ናቸው›› ያሉት ከንቲባዋ፤ ግብር ሰብሳቢው መስሪያ ቤት ያለ ግብር ከፋይ ሊኖር እንደማይችል አስቦ፤ ያለ ግብር ከፋይ መንግሥት እንደሌለና አገር መቆም እንደማትችልም ጭምር በማሰብ ግብር ከፋዩን አክብሮ ማገልገል አለበት ሲሉ አሰገንዝበዋል:: አያይዘውም አሉ የተባሉ ችግሮችንም በጋራ በመወያየትና በመመካከር መፍታት እንደሚቻል አስረድተዋል::
ከንቲባዋ እንዳሉት፤ ግብር መክፈል የውዴታ ግዴታ ነው፤ ውሃ፣ መብራት፣ መንገድ፣ ጤና እና ሌሎች ተጨማሪ አገልግሎቶችን ለማግኘት ግብር መክፈል የግድ ይሆናል:: በግብር አሰባሰብ ሂደት በግብር ከፋዩ በኩል የተነሱ በርካታ ችግሮች ይታያሉ፤ ማንኛውንም ችግር በሩቅ ሳይሆን ተቀራርቦ በመወያየትና በመነጋገር መፍታት ይቻላል:: መንግሥት ከግብር ከፋዮች ጋር ተቀራርቦ መወያየትና መነጋገር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ለውጦችን ማምጣት ተችሏል::
መንግሥት ከግብር ከፋዮች ጋር መወያየትና መነጋገር ከጀመረ ወዲህ በተጨባጭ የታክስ መሰብሰብ አቅም ጨምሯል ያሉት ከንቲባዋ፤ እንደ አገር ከታክስ ለመሰብሰብ በተያዘው እቅድ በብዙ መልኩ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ሲሉ ገልጸዋል:: ያም ቢሆን የአገሪቷ ኢኮኖሚ የሚያመነጨው ሀብት ግብር መሰብሰብ አለመቻሉን አስታውቀዋል:: ለዚህም የመንግሥት የማስፈጸም ብቃት ማነስ አንደኛው ምክንያት መሆኑን ተናግረው፣ ሁለተኛው ግብር የመክፈል ባህል ዝቅተኛ በመሆኑ ነው ብለዋል:: ግብርን በታማኝነት የመክፈል ባህልን ማሳደግም ሆነ ችግሮችን መፍታት የጋራ ጉዳያችን ነው ያሉት ሚኒስትሯ፣ ተቀራርቦ በመነጋገር አበረታች ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለዋል::
ከንቲባዋ እንዳሉት፤ ግብራቸውን በትክክል የማይከፍሉ አካላትን በማጋለጥ እንዲጠየቁና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ግፊት ማድረግ ከእያንዳንዱ አካል ይጠበቃል:: በተመሳሳይ ደግሞ መንግሥት ግብራቸውን በትክክል የሚከፍሉትን በልዩ ሁኔታ የሚያበረታታ፣ የሚያከብርና የሚሸልም ይሆናል::
የንግዱ ማህበረሰብ ካነሳቸው ጥያቄዎች መካከል የሚወጡ ህጎችን የማወቅና ስልጠና ማግኘት የሚሉ ጉዳዮች እንደሚገኙበት አስታውሰው፤ ለጥያቄዎቹ ሁሉ መንግሥት በየደረጃው ምላሽ እንደሚሰጥ ገልጸዋል:: በጋራ መወያየትና ተቀራርቦ መነጋገሩ በቀጣይ ሊዳብር እንደሚገባም አስገንዝበዋል::
በንግድ ስርዓት ውስጥ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል ያለደረሰኝ ሽያጭ እና ከዋጋ በታች መሸጥ እንዲሁም ግብርን በአግባቡና በተገቢው ስሌት አለመክፈል የብልጣብልጥነትና የአዋቂነት ምንጭ ሆነው እንደሚታዩ ከንግዱ ማህበረሰብ በስፋት የተነሱ ጉዳዮች ናቸው:: በመሆኑም እነዚህንና ሌሎች በገቢ ግብር አሰባሰብ ሂደት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን የተለያዩ ስልቶችን ተጠቅሞ መቅረፍ ተገቢ እንደሆነ የጠቀሱት የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ፤ ለእያንዳንዱ ችግር መፍትሔው መሆን የሚችለው ተቀራርቦ መሥራት እንደሆነ አስገንዝበዋል::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2015