የመንግስት ተቋማት የበጀት አጠቃቀም ሁሌም ከወቀሳ ድኖ አያውቅም። ይህ ወቀሳ ግን በብዛት በጀታቸውን አላግባብ ከመጠቀም ወይም ከማባከን ጋር የተያያዘ ነው። ይህንን በተመለከተ የፌዴራል ኦዲት መስሪያ ቤት ከቅርብ አመታት ወዲህ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉድለቶችን ይፋ በማድረግ አበረታች ስራ እየሰራ ይገኛል። የዛሬው ትዝብታችን ግን ወዲህ ነው፣ የተቋማት አግባብ ያልሆነ ወጪና የበጀት ብክነት እንዳለ ሆኖ በጀትን ያለመጠቀም ጉዳይ ላይ ያጠነጥናል።
የበጀት አመቱ መገባደጃ ሰኔ በመጣ ቁጥር የመንግስት መስሪያ ቤቶች ጥቅም ላይ ያላዋሉትን በጀት ለመጠቀም ከወትሮው በተለየ ሲጣደፉ ይስተዋላል። አዳዲስ ፕሮጀክቶችን መጀመር፣ ያልተከፈሉ ክፍያዎችን መፈፀም፣ ስብሰባና የሆቴል ቤት ስልጠናዎች በዚህ ወቅት ይበረክታሉ። ይህ በብዙ የመንግስት ተቋማት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ልምድ ቢሆንም ብዙ ጊዜ ከብክነት ጋር በተያያዘ እንጂ በተገቢው ቦታና ጊዜ በጀትን ባለመጠቀም ጉዳይ ላይ ጥያቄ ሲነሳ አይስተዋልም።
መንግስት ለተቋማቱ በጀት የሚመድበው ለሕዝብ ተገቢውን አገልግሎት በተገቢው ጊዜና ቦታ እንዲሰጡ መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው። በዚህ ረገድ የተሰጣቸውን በጀት አንጠፍጥፈው በተገቢው ጊዜና ቦታ በማዋል እንዲያውም አንሷቸው ተጨማሪ የሚጠይቁ ብዙ ተቋማት እንዳሉ መካድ አይቻልም።
በተቃራኒው ደግሞ በጀታቸውን ታቅፈው አመቱን ሙሉ ቁጭ ብለው የበጀት መዝጊያው ወር ሰኔ ሲመጣ “ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” የሚሉ ተቋማት ቁጥር ቀላል አይደለም። ከእንዲህ አይነት ተቋማት በተጨማሪ ብዙ መስራት የሚገባቸው ነገር እያለ በጀታቸውን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ተመላሽ ማድረግ የታማኝነት ምልክት አድርገው የሚቆጥሩም አሉ። ሁለቱንም በዝርዝር እንመልከት።
“ሰኔ መጣ በጀት ይውጣ!” የሚሉ ተቋማት አመቱን ሙሉ ተቀምጠው መጨረሻ ላይ የመንግስትን ገንዘብ በየቦታው ለመርጨት የሚገቡበት ጥድፊያ በአንድም በሌላም መልኩ ብክነት ነው። የእንዲህ አይነት ተቋማት አስራ አንደኛ ሰዓት ላይ መፍጨርጨር በብዛት ይህን ሰርተናል ለሚል ሪፖርት ያህል ነው። ከረፈደ ሰኔ ሲደርስም ቢሆን የሚመዙት ገንዘብ አገርና ሕዝብን የሚጠቅም ቢሆን ባልከፋ ነበር። በብዛት በዚህ ወቅት የሚወጣ ገንዘብ በስብሰባ፣ ስልጠናና በእቅድ ውስጥ ለሌለ ግዢ የሚውል መሆኑ ነው የሚያስተዛዝበው።
አመቱን ሙሉ ያልተሰጠ ስልጠናና ያልተካሄደ ስብሰባ በጀቱን ለመጠቀም ሲባል አዲስ አበባ መካሄድ ሲችል አዳማና ቢሾፍቱ ይሄዳል። ተቋሙ የማያስፈልገው ወይም አንገብጋቢ ላልሆነ እቃ ግዢ ይውላል። ይህ የሚሆነው ምናልባትም ተቋሙ በጀቱን ለሕዝብ አመቱን ሙሉ ሊያገለግልበት ሲገባ ሆን ተብሎ ወይም በችልተኝነት ታልፎ ሊሆን ይችላል።
እንዲህ አይነቱ ልምድ በጀትን ቅርጥፍ አድርጎ ከመብላት አይተናነስም። ለትክክለኛው ነገር በትክክለኛ ጊዜ ያልወጣ በጀት እንዲያውም ባይወጣ ሳይሻል አይቀርም። ምክንያቱም በጥድፊያ ላላስፈላጊ ነገር ከሚዘራ በጀት በአንድ ስሙ የሚቀመጠው ወይም የሚመለሰው የተሻለነውና ነገ ሌላው ይጠቀምበታል።
ሌላው አስገራሚ ጉዳይ በጀታቸውን ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል ተመላሽ የሚያደርጉ ተቋማት ጉዳይ ነው። እውነት ለመናገር እንዲህ አይነት ተቋማት በጀት የሚመልሱት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰራ ነገር ጠፍቶ ነው? ወይስ የሚሰሩትን ሰርተው የእውነትም ተርፏቸው ነው? ሁለቱም አሳማኝ መልስ ሊሆን አይችልም። ይህ ማለት በራሳቸው ገንዘብ የሚያመነጩ ተቋማት ገንዘብ ተርፏቸው በጀት መዝጊያ ላይ ለመንግስት ተመላሽ አያደርጉም ማለት አይደለም። የመንግስት በጀት ብቻ ጥገኛ የሆኑ ተቋማት በጀት የሚመደብላቸው በአመት ውስጥ ለመስራት የያዙት እቅድ ግምት ውስጥ ገብቶ
ነው። መንግስት ለነዚህ ተቋማት የሚይዘው የበጀት መጠን ደግሞ የተትረፈረፈ ነው ብሎ የሚምል አለ ተብሎ አይታመንም። ተቋማቱ ከሚያከናውኑት ስራ አንፃር ብዙ በጀት ሊፈልጉ ቢችሉም እንኳን መንግስት አቅሙ በሚፈቅድለት መጠን ነው በጀት የሚፈቅደው። ይህን አንጠፍጥፎ መጠቀም ሲገባ ተመላሽ ማድረግ ግን ገንዘብ እያለ ጦም እንደማደር ነው የሚቆጠረው። አልፎ ተርፎም አገርና ሕዝብን መበደል ነው።
ይህ በብዛት ከተቋማት የስራ ሃላፊዎች የማስፈፀም አቅም ጋር በተያያዘ የሚፈጠር ሊሆን ይችላል። ወይንም ተቋሙ ከእቅዱ በላይ የተለጠጠ በጀት ተለቆለታል ማለት ነው። በዚህ ረገድ ብዙ ተቋማት በጀት ሲመልሱ በቀጣዩ አመት ያነሰ በጀት ይያዝላቸዋል እንጂ እቅዳቸውን ምን ያህል ተግባራዊ አድርገው ነው በጀት የተረፋቸው ተብለው የሚጠየቁበት አሰራር አይስተዋልም።
የ2014ን ረቂቅ በጀት ለማፅደቅ በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመንግስት በጀት እንደሚባክንና በቀጣይም ይህንን ለማስተካከል የሚያስችሉ አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ተናግረው ነበር። ባለቀ ሰዓት በጥድፊያ የሚባክን በጀትን እንዲሁም ተመላሽ የሚደረገውን በጀት ጉዳይም በነካ እጃቸው ቢመለከቱት መልካም ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም