ሰላም ልጆች ስለቀጭኔ ምን ያህል ታውቃላችሁ ? የእንስሳት መዘክርን ብትጎበኙ ስለ ቀጭኔም ሆነ ስለሌሎቹ እንስሳት ተፈጥሮ በጥልቀት ለማወቅ ትችላላችሁ:: አዲስ አበባ ውስጥ ምትኖሩ ልጆች በተለይ በአገራችን ብቸኛውንና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር ያለውን የእንስሳት የተፈጥሮ ቅርስ መዘክር (ሙዚየም) የመጎብኘት ዕድል አላችሁ:: ዛሬ እኔ ስለቀጭኔ ካነበብኩትና የመዘክሩ ኃላፊ ከሆኑት ከወይዘሮ አልማዝ ለማ ያገኘሁትን ላካፍላችሁ::
ልጆች ኃላፊዋ እንደነገሩኝ ቀጭኔዎች የሚገኙት በአፍሪካ ብቻ ሲሆን ጡት አጥቢ አራዊት ስትሆን ውብ መልክ ያላቸውና ፈጣኖችም ናቸው:: በምድር ከሚገኙ እንስሳት በርዝመት አንደኛ ሲሆኑ ከ 4 ነጥብ 4 እስከ 5 ነጥብ 5 ሜትር ርዝመት፤ እንዲሁም 1 ሺ 360 ኪሎግራም ክብደት አላቸው:: ይህ ክብደት ግን በሰዓት እስከ 60 ኪሎ ሜትር ድረስ በቅልጥፍና ከመሮጥ አያግዳቸውም:: ሴቷም ሆነች ወንዱ ቀጭኔ ቁመታቸውን የሚጠቀሙበት አርቆ ለማየት ሲሆን የትኛውም አደጋ ሲመጣ ገና ከሩቅ ለማወቅ ያስችላቸዋል። ጠባብ ጆሮዎች፣ ሁለት ትናንሽ ቀንዶች እንዲሁም ጠቆር ያለ ለስላሳ ጸጉር አላቸው። ዓይኖቻቸው በጣም ትላልቅና ጥቁር ሲሆኑ ረዣዥም በሆኑ ቅንድቦች የታጠሩም ናቸው::
ልጆች! የቀጭኔ አንገትና ትከሻ የቅጠል ቅርፅ ባላቸውና ቀጫጭን በሆኑ ነጭ መስመሮች ያጌጠ ነው ደስ አይልም:: ሆኖም ቀለማቸው የተለያየ ሲሆን ከወርቃማ ዳለቻ አንስቶ እስከ ቡናማ እንዲያውም ጠቆር እስካለ ቀለም ይደርሳል። ነገር ግን የቀጭኔዎች ዕድሜያቸው እየገፋ በሄደ መጠን ቀለማቸውም እየጠቆረ ይሄዳል። ይሄን ጊዜም አረጁ ይባላል::
ቀጭኔዎች ከዝሆን በስተቀር ማንኛውም ሌላ እንስሳ ሊደርስ በማይችልበት ከፍታ ላይ የሚገኙ ረዣዥም ቀንበጦችን ለመብላት የሚያስችል አስደናቂ አፈጣጠር አላቸው። ልዩ የሆነ የመቆንጠጥ ችሎታ ያለው የላይኛው ከንፈራቸው ሲሆን እንደተፈገለው የመተጣጠፍ ችሎታ ያለው ምላሳቸው ሹል በሆኑ እሾሆች የታጠሩ ቅጠሎችን ለመቀንጠብ ያስችላቸዋል።
ልጆች! ቀጭኔዎች በቀን እስከ 34 ኪሎ ግራም የሚመዝን ዕፅዋት መመገብ ይችላሉ። የተለያዩ ዕፅዋትን የሚበሉ ቢሆኑም ይበልጥ የሚመርጡት ግን በአፍሪካ ሜዳዎች የሚገኙትን እሾሃማ ግራሮች ነው:: ልጆች ሌላው ስለቀጭኔዎች ያለው አስገራሚ ነገር አንድ ወንድ ቀጭኔ ምግብ ለመፈለግ ምላሱን እስከ 42 ሳንቲ ሜትር መዘርጋት መቻሉ ነው:: አያስደንቅም? የቀጭኔዎች አንገት በጣም አስደናቂ የሆነ የመተጣጠፍ ችሎታም አለው:: ይህም ላይኛዎቹን የዛፍ ቅርንጫፎች ለመቀንጠብም ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ረዥሙን ራሳቸውን እንደ ልባቸው ለማዘንበልና ለማዟዟር የሚያስችላቸው ነው::
ለቀጭኔ ወደ ላይ መንጠራራት በጣም ቀላል ነገር ሲሆን ተጎንብሶ ውኃ መጠጣት ግን ይከብዳቸዋል። ወደ ውኃ ጉድጓድ በሚቀርቡበት ጊዜ የፊት እግሮቻቸውን ቀስ በቀስ ከፍተው ካራራቁ በኋላ ወደ ውኃው ለመድረስ እንዲችሉ ሁለት ጉልበቶቻቸውን አጠፍ ያደርጋሉ። ቀጭኔዎች እንዲህ ባለው አመቺ ባልሆነ ሁኔታ እያሉ ረዥም አንገታቸውን እስከ መጨረሻ ይዘረጋሉ። ደግነቱ ግን ከሚመገቧቸው ቅጠላ ቅጠሎች በቂ እርጥበት ስለሚያገኙ ቶሎ ቶሎ ውሃ መጠጣት አያስፈልጋቸውም።
ልጆች ስለ አኗኗራቸው ኃላፊዋ እንደነገሩን ቀጭኔዎች ከ 2 እስከ 50 የሚደርሱ አባላት ባሉት መንጋ ተደራጅተው አንድ ላይ የሚኖሩ ፍጥረታት ናቸው። አንዲት ነፍሰ ጡር ቀጭኔ ልጅዋን ከ 420 እስከ 468 ለሚደርሱ እርግዝና ቀናት ከተሸከመች በኋላ ሁለት ሜትር ቁመት ያለው ግልገል ትወልዳለች። ግልገሏ በምትወለድበት ጊዜ ራስዋን ታስቀድምና በሚያስገርም ሁኔታ ከሁለት ሜትር ከፍታ ላይ ወደ መሬት ትወረወራለች። ይሁን እንጂ በ15 ደቂቃ ውስጥ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስባት እየተውተረተረች ትነሳና ጡት ለመጥባት ዝግጁ ትሆናለች። ከሁለት ወይም ከሦስት ሳምንት በኋላ በደመ ነፍስ ተመርታ የግራር ቀንበጦችን መለቃቀም ስለምትጀምር ብዙም ሳትቆይ ረዥም እርምጃ ያላትን እናትዋን ተከትላ ለመሄድ የሚያስችል ጉልበት ታገኛለች። አንዲት የቀጭኔ ግልገል በጣም ውብ መልክ ሲኖራት የወላጆችዋ አነስተኛ ግልባጭ ነች። ቁመቷ ከቀጭኔ ርዝመት ጋር ሲወዳደር አጭር ብትሆንም ከብዙ ሰዎች ቁመት ግን ትበልጣለች። በእናቷ ጥንቃቄ የተሞላበት ጥበቃ ተማምና አላንዳች መሸበር አካባቢዋን የምትማትረው ግልገል ላያት ሁሉ ልዩ መስህብ እንዳላትም ኃላፊዋ ነግረውናል:: ግልገል ቀጭኔዎች በተወለዱበት ወራት በግልገል መዋያ ተሰባስበው ሙሉውን ቀን ዕረፍት በማድረግ፣ በመጫወትና በአካባቢያቸው የሚሆነውን ነገር በመመልከት ጊዜያቸውን እንደሚያሳልፉም አስረድተውናል:: የቀጭኔ ግልገል ለማመን በሚያዳግት ፍጥነት እንደምታድግና በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ አንድ ሜትር የሚያክል ቁመት ሲጨምር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ደግሞ በእጥፍ እንደሚያድግም ገልፀውልናል:: በአንድ ሳምንት ብቻ 23 ሳንቲ ሜትር ያህል ሊያድግ ይችላል! እናትዬው ለልጅዋ ከፍተኛ ጥበቃ የምታደርግ ሲሆን ልጅዋ የተወሰነ ርቀት እንድትዘዋወር ብትፈቅድላትም ሩቅ የማየት ችሎታ ስላላት በዓይኗ ትከታተላታለች ብለውናል። ልጆች ስለ ቀጭኔ ብዙ የምነግራችሁና ከወይዘሮ አልማዝ የሰማሁትና በቤተ መጽሐፍት ያነበብኩት ቢኖርም ቦታ ስለማይበቃ የቀረውን የቀጭኔንንም ሆነ የሌሎቹን እንስሳ ታሪክ መዘክሩን በመጎብኘት እንዲሁም መጽሐፍትን በማንበብ የበለጠ እንድታውቁ በመጋበዝ ለዛሬ ስለቀጭኔዎች ያካፈልኳችሁን ታሪክ አበቃሁ:: መልካም ሳምንት!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2015