በቢሾፍቱ የሚገነባውን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በ18 ወራት ለማጠናቀቅ ታቅዷል

  • በአየር መንገዱ ላይ የሚቀርቡ ክሶች መሠረተ ቢስ መሆናቸውም ተገልጿል

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቢሾፍቱ የሚገነባውን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሚቀጥሉት 18 ወራት ለማጠናቀቅ ማቀዱን አስታወቀ። በአየር መንገዱ ላይ የቀረቡት ክሶች መሠረተ ቢስ መሆናቸውንም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸምን አስመልክተው ትናንት በሰጡት መግለጫ፣ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላለፉት በርካታ ዓመታት ማስፋፊያ እየተደረገለት ቢቆይም እየጨመረ የመጣውን ዓለም አቀፍ መንገደኛ ማስተናገድ ወደማይችልበት ደረጃ እየደረሰ ነው። ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትም አየር መንገዱ በቢሾፍቱ ተጨማሪ አየር ማረፊያ ለመገንባት እየሠራ ነው።

እንደ ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፣ ተጨማሪ አየር ማረፊያው የሚገነባው ቢሾፍቱ አካባቢ ሲሆን አየር ማረፊያውን ዲዛይን የሚያደርግ ዓለም አቀፍ ተቋራጭ ተመርጧል። ዲዛይኑን እና ግንባታውን የሚሠሩት ሥራ ተቋራጮች በሚቀጥሉት 18 ወራት እንዲያጠናቅቁ ስምምነት ላይ ተደርሶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

አየር ማረፊያው የሚገነባበት ቦታ ላይ ያረፉትን አርሶ አደሮች ወደ ሌላ ቦታ ለማዘዋወር የሚያስችል ቦታ በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ተለይቶልናል ያሉት አቶ መስፍን፣ የተለየው ቦታ ላይ ኑሯቸውን የሚመሩበት መኖሪያ ቤት የሚገነባ ሥራ ተቋራጭ በመመረጡ ሰሞኑን እንፈራረማለን ብለዋል።

የሲኤንኤን ናይሮቢ ጋዜጠኛ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሶማሊያ ዜግነት ያላትን መንገደኛ በማስነሳት ወንበሯን ለኢትዮጵያዊ ባለሥልጣን በመስጠት በኃይል አስወርዷታል ሲል በቪዲዮ ጭምር አያይዞ ማሰራጨቱን ያስታወሱት አቶ መስፍን፣ ይህንን ክስ አንቀበለውም ፤ ትክክለኛም አይደለም ብለዋል።

እውነታው መንገደኞቹ ሶስት ሲሆኑ፤ የኢትዮጵያ ባለሥልጣን በቦታው አልነበረም። ከጎረቤት ሀገር የመጡ ቪአይፒ ቢኖሩም የተሳፈሩት በቢዝነስ ክላስ ነው። እነሱ ደግሞ የያዙት የኢኮኖሚ ክላስ ትኬት ነው። አውሮፕላን ውስጥ የገቡትም ያለፈቃድ ነው ሲሉ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሳፋሪዋን ወንበር ለሌላ ተሳፋሪ አሳልፎ የሰጠበት ምንም ምክንያት አለመኖሩን አረጋግጧል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ አየር መንገዱ እውነተኛ መረጃ ለጋዜጠኛው ለመስጠት ጥረት ቢያደርግም ፈቃደኛ ሊሆን አለመቻሉን ጨምረው ገልጸዋል።

አየር መንገዱ ዓለም አቀፋዊ ሕግን ተከትሎ የሚሠራ፣ መንገደኞችን እንደ አመጣጣቸው እና አመዘጋገባቸው የሚያስተናግድ ሲሆን፤ በቀጣይም ይህንኑ ተግባራዊ ያደርጋል ብለዋል።

በሌላ በኩል የኤርትራ ሲቪል አቬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከመስከረም 30 ጀምሮ እንዳይበር የሚል ደብዳቤ መላኩን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመው፤ ደብዳቤው ይህንን አጥፍታችኋል የሚል ምንም ዓይነት ማብራሪያ አልነበረውም ብለዋል። በቀጣይ ቀን ግን በማህበራዊ ሚዲያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትክክለኛ ያልሆነ አሠራር በመከተሉ፣ የሚጠይቀው የትኬት ዋጋ በመወደዱ፣ የመንገደኞች ሻንጣ የሚጠፋ፣ የሚሰበርና የሚሰረቅ በመሆኑ አግደነዋል እና ጉዟችሁን አስተካክሉ የሚል መግለጫ አውጥቷል ሲሉ ጠቁመዋል።

በረራ አቪየሽኑ መቋረጡ ሳያንስ የኢትዮጵያን አየር መንገድ ስም የማጥፋት ሥራ የሠራ በመሆኑ ክሱ በፍጹም ተቀባይነት የለውም ሲሉ ገልጸው፤ መጋቢት ወር ውስጥ የኤርትራ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች ሻንጣ የሚያጉላላ በመሆኑ ለደንበኞቹ ካሳ እንድንከፍል በጻፈልን ደብዳቤ መሠረት ወዲያውኑ የማስተካከያ ርምጃ ወስደናል ብለዋል።

በወሰድነው ርምጃም መንገደኞች ከሻንጣቸው ጋር እኩል እንዲሄዱ እና በየአውሮፕላኑ ያለውን የተሳፋሪ ቁጥር በመቀነስ ችግሩ ተፈትቷል። ይህ እንደመወንጀያ መደረጉ ተገቢነት የለውም ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስህተቶችን ለማረም ዝግጁ በመሆኑ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ጤናማ ግንኙነት፣ ንግድና ቱሪዝም እንዲኖር የሚጥር ተቋም በመሆኑ በረራው እንዳይቋረጥ የኤርትራ የሚመለከታቸው ባለሥልጣናትን ለማነጋገር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።

በሌላ በኩል አየር መንገዱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 7 ነጥብ 02 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ጠቅሰው፤ የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 14 በመቶ አድጓል ብለዋል።

በጀት ዓመቱ 17 ነጥብ አንድ ሚሊዮን መንገደኞችን ማጓጓዙን ገልጸው፤ ከነዚህ ውስጥ 13 ነጥብ 4 ዓለም አቀፍ መንገደኞች ሲሆኑ ቀሪዎቹ የሀገር ውስጥ መንገደኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በጭነት 754 ሺህ 681 ቶን ማጓጓዙን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር ስድስት በመቶ አድጓል ብለዋል። በበጀት ዓመቱ አምስት ዓለም አቀፍ የመንገደኛ መዳረሻዎችን በመጨመር የዓለም አቀፍ በረራ መዳረሻዎችን 139 ማድረስ መቻሉን አስታውቀዋል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ሐምሌ 23/2016 ዓ.ም

Recommended For You