ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የአዋቂ ወንዶች የሜዳ ቴኒስ ውድድርን በደማቅ ሁኔታ እያስተናገደች ትገኛለች። ውድድሩ ከግንቦት 6 ጀምሮ በአዲስ አበባ ቴኒስ ክለብ በጠንካራ ፉክክሮችን እየተካሄደ ይገኛል።
ባለፈው የካቲት ወር ኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ የዓለም ታዳጊዎች የሜዳ ቴኒስ ቻምፒዮናን አስተናግዳ በስኬት ማጠናቀቋ ይታወሳል። በውድድሩም 14 ኢትዮጵያውያን ስፖርተኞች ተሳትፈው ሶስቱ የዓለም አቀፍ ደረጃ ማግኘት ችለው ነበር። ኢትዮጵያ በዚያ ውድድር ባሳየችው የመስተንግዶ ጥራት አሁን ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ አዋቂ ስፖርተኞች የሚሳተፉበት ዓለም አቀፍ ውድድርን ለማዘጋጀት በድጋሚ እድሉን አግኝታለች። ውድድሩ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚዘጋጅ የአዋቂዎች ውድድር ሲሆን ወንዶች ብቻ የሚሳተፉበት ነው::
በአዲስ አበባ ከተማ አምስቱም ቴኒስ ክለብ ሜዳዎች ከግንቦት 6/2015 ዓ.ም አንስቶ አንድ ሳምንት ያስቆጠረው ይህ ውድድር፤ በጠንካራ ፉክክር ታጅቦ ሩብ ፍጻሜ ላይ ደርሷል። በቀጣይም በሚኖረው ቆይታም በፉክክር ታጅቦ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ይጠበቃል። ውድድሩ በስልጠና ላይ ለቆዩ ስፖርተኞች የውድድር ዕድልን ከመፍጠር ባሻገር ስፖርቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለበትን ደረጃ መገምገምን ዓላማ አድርጎ በመካሄድ ላይ ነው። ውድድሩ ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬን ከማምጣቱም በተጨማሪ ለገጽታ ግንባታ የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል። አራት ኢትዮጵያዊያን በውድድሩ በቀጥታ በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ፤ በጥንድና ነጠላ ውድድሮች አብዳላ ነዲም፣ ጣዕመ ገብረስላሴ፣ ዜይኑ መሀመድ እና ያቤትስ ከበደ ቡድኑን ወክለዋል።
በውድድሩ ከ23 አገራት የተወጣጡ ከ60 በላይ የቴኒስ ስፖርተኞች ከፍተኛ ፉክክር በማድረግ ላይ ይገኛሉ። 32 የቴኒስ ተጫዋቾች በነጠላ ምድብ እንዲሁም 32 በጥንድ ምድብ በአጠቃላይ 64 የቴኒስ ተጫዋቾች አጓጊ በሆነ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች በማፋለም ጅማሮውን አድርጓል። ውድድሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ 300 እና ከዚያ በላይ ውጤት ያላቸው ስፖርተኞች የሚሳተፉበት በመሆኑ የስፖርት ቤተሰቡን ቀልብ መሳብ ችሏል።
አሸናፊዎች በሁለት ዙሮች በሚካሄደው ውድድር በእያንዳንዱ ዙር 15ሺ ዶላር በአጠቃላይ 30ሺ ዶላር የሚሸለሙም ይሆናል። ውድድሩ ዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰጠው በመሆኑ አሸናፊዎቹ ዓለም አቀፍ ደረጃን የሚያገኙ ይሆናል። በአብደላ ነዲም ኢቨንት ኦርጋናይዘር አዘጋጅነት የሚደረገው ውድድር ስፖርተኞች የውድድር ዕድልን እንዲያገኙና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ ታስቦ የሚካሄድ ውድድር ነው።
ኢትዮጵያ ከ17 ዓመታት ቆይታ በኋላ ዓለም አቀፍ የሜዳ ቴኒስ ውድድርን ስታዘጋጅ ይሄ ሁለተኛው ሲሆን፤ አዝናኝና የስፖርተኞችን አቅም በሚፈታተነው የሜዳ ቴኒስ ውድድር በብቃት በማስተናገድ ላይ ትገኛለች። በመጀመርያ ዙር ነጠላ ምድብ በተደረጉ ፍልሚያዎች ኢትዮጵያዊው አብደላ ነዲም የዚምባብዌውን ቤንጃሚን ሎክን አስተናግዶ 6ለ0 እና 6ለ1 በአጠቃላይ 2ለ0 በሆነ ውጤት ሊሸነፍ ችሏል። በጥንድ በተደረጉ ውድድሮችም ኢትዮጵያዊያኑ አብደላ ነዲም እና ተማም ገብረስላሴ ከህንዳዊያን ተጫዋቾች ጋር ባደረጉት ጨዋታ ተስፋ ሰጪ ፍክክርን ቢያደርጉም ውጤት ሳይቀናቸው ቀርቷል። የተቀሩት ኢትዮጵያዊያን ቴኒስ ተጫዋቾችም ባደረጉት ፍልሚያ ውጤታማ ባይሆኑም ተስፋ ስጪ እንቅስቃሴን ማድረግ ችለዋል።
ከኢትዮጵያዊያን ቴኒስ ተጫዋች አንዱ የሆነው አብደላ ነዲም፤ መሰል ውድድሮችን ጨምሮ በበርካታ ዓለም አቀፍ ቻምፒዮናዎች ተሳትፏል። ይህ ውድድር በኢትዮጵያ መካሄዱ ለተሳትፎና ውጤትን ለማምጣት መልካም አጋጣሚ ነው። በደረጃ ሳይሆን በዝግጅቱ እንደሚተማመን የተናገረው አብደላ ጥሩ ዝግጅት ከተደረገ ማሸነፍ እንደሚቻል ይጠቁማል።
ከተለያዩ አገራት የመጡ ተወዳዳሪዎች እንደገለፁት፣ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የተካሄደው የወጣቶች ውድድር ስኬታማ ነበር። በወጣቶችና አዋቂዎች መካከል የሚደረገው ውድድር በአእምሮና አካላዊ ፍጹም ልዩነት እንዳለውም ገልፀዋል። ውድድሩ ጠንካራ እና መስተንግዶው፣ የሕዝቡ አቀባበል በጣም ጥሩ በመሆኑ ደስተኛ እንደሆኑም ተናግረዋል።
ዓለም አቀፉ የቴኒስ ፌዴሬሽን የገንዘብ ድጋፍን እና ለተወዳዳሪዎች ነጥብ መስጠትን ጨምሮ 5 ዳኞችንም መድቦ ውድድሩ በመካሄድ ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያም 4 ዳኞችን በማሳተፍ ላይ ትገኛለች። ወቅቱ ዝናባማ በመሆኑ ውድድሩ ላይ በተወሰነ መልኩ ተዕጽኖ ቢፈጥርም የተለያዩ የመፍትሄ አማራጮች ተወስደው ውድድሩን ማስቀጠል ተችሏል። በቀጣይም መሰል ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማዘጋጀት እድል ይፈጥራል ተብሎም ይጠበቃል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2015