አገልግሎት ሰጪና ፈላጊዎች በቀላሉ መገናኘት እንዲችሉ ማስታወቂያ ትልቅ ድርሻ አለው:: አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በክልል ከተሞች ጭምር የተለያዩ ማስታወቂያዎች ተሰቃቅለውና ተለጣጥፈው የምንመለከተውም በዚሁ ምክንያት ነው:: ጥሩ ምርትና አገልግሎት ማስታወቂያ አያስፈልገውም የሚሉ ወገኖች ቢኖሩም፣ ማስታወቂያ ምርትና አገልግሎትን በማስተዋወቅ በኩል ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑ አያጠያይቅም::
የማስታወቂያ ሥራ ከዘመኑ ጋር እየዘመነ መጥቷል፤ ከወረቀት ወደ ባነር ከባነር ደግሞ ወደ ዲጅታል ተሸጋግሯል:: ያም ቢሆን ታዲያ ኢትዮጵያ ውስጥ የማስታወቂያ ሥራ ገና ብዙ የሚቀረው የሥራ ዘርፍ እንደሆነ በዘርፉ ባለሙያዎችና አካላት ይገለጻል:: የዕለቱ የስኬት እንግዳችንም የማስታወቂያ ሥራ ኢትዮጵያ ውስጥ ገና ብዙ ሊሠራበት የሚገባ ዘርፍ እንደሆነ በመግለጽ ሃሳቡን ይጋራል::
የማስታወቂያና የህትመት ሥራዎች ባለሙያ አቶ ጆቫኒ ፓራቶሪ የሰን ላይት ዲጅታል ማስታወቂያና ህትመት ሥራ መስራችና ባለቤት ነው:: በማስታወቂያና ህትመት ሥራ ከተሰማራ አስራ ሰባት ዓመታትን አስቆጥሯል:: ወደ ስራው በሰፊው ከመግባቱ በፊት በተለያዩ የሥራ አጋጣሚዎች የማስታወቂያ ሥራን ማወቅና መረዳት የቻለው አቶ ጆቫኒ፤ ሙያውን ከልብ በመነጨ ፍላጎትና በከፍተኛ ተነሳሽነት እንደጀመረው ይናገራል::
ጣልያናዊ ከሆነው አባቱ እና ከኢትዮጵያዊት እናቱ የተወለደው አቶ ጆቫኒ፤ አዲስ አበባ ከተማ ቄራ አካባቢ ልዩ ስሙ አልማዝዬ ሜዳ ነው ተወልዶ ያደገው:: ምንም እንኳን ከጣልያናዊ አባት ቢወለድም ታዲያ በኢትዮጵያዊት እናት ያደገ በመሆኑ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ልጅ ከእኩዮቹ ጋር አፈር ፈጭቶ ጭቃ አቡክቶ ነው ያደገው:: የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በአጼ ዘረ ያዕቆብ ትምህርት ቤት፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በንፋስ ስልክ እና በጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤቶች ተከታትሏል:: የመጀመሪያ ዲግሪውን ከሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ በማርኬቲንግ ትምህርት ክፍል አግኝቷል::
በ1998 ዓ.ም ሰን ላይት ዲጅታል ማስታወቂያና ህትመት ሥራን ከማቋቋሙ አስቀድሞ በተማረው የማርኬቲንግ ትምህርት የሴልስ ሥራዎችን በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ሠርቷል:: በዚሁ የሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ እያለ ከማስታወቂያና የህትመት ሥራዎች ጋር ተቀራርቦ የመሥራት አጋጣሚ የተፈጠረለት ጆቫኒ፤ ከዕለታት በአንዱ ቀን በአንድ ድርጅት ውስጥ የህትመት ሥራዎችን እንዲሠራ የቀረበለትን ጥያቄ ተቀብሎ ማተሚያ ማሽን ካላቸው ሰዎች ጋር ወዳጅነት በመፍጠር ወደ ሥራው እንደገባ ይገልጻል::
በወቅቱ ማተሚያ ማሽን ካላቸው ድርጅቶች ጋር በነበረው ስምምነት መሰረት የተለያዩ የህትመት ሥራዎችን ወደ ማተሚያ ድርጅቶች በማምጣት እንዲታተም ያደርጋል:: ለዚህም የአገልግሎት ክፍያ ነበረው። በወቅቱ የጀመረው ሥራ ብዙ ሰዎችን እያስተዋወቀው ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በርካታ ሥራዎችን መሥራት አስችሎታል:: ከዚህም በላይ በሥራው ውስጣዊ ደስታና የመንፈስ እርካታን ያገኝበት እንደነበር አጫውቶናል:: ይሄኔ ሥራውን አስፍቶ መሥራት እንዳለበትና ለእሱ የተፈጠረ ሥራ እንደሆነ በማመን ለማስታወቂያና ህትመት ሥራ እራሱ ማዘጋጀት ጀመረ:: በመሆኑም ‹‹ይህ ሥራ ለእኔ የተባለ ዕድል ፈንታዬ ነው›› በማለት ሥራውን አጠናክሮ ለመቀጠል ባስቀመጠው ዕቅድ መሰረት በ1998 ዓ.ም የንግድ ፈቃድ በማውጣት ወደ ሥራው ገብቷል::
ወቅቱ የህትመት ሥራዎች የተስፋፉበት በመሆኑ በጉጉት ወደ ሥራው ገብቷል:: የህትመት ሥራዎቹን ለመሥራት የተለያዩ ጨረታዎችን ሲሳተፍ ጨረታዎቹን ማለፍ ያቅተው እንደነበር ስታወሰው አቶ ጆቫኒ፤ ምክንያቱን ለማወቅ ብዙ ጥረት አድርጓል:: ከብዙ ጥረት በኋላ ያገኘው መልስ መንግሥት በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ለሚቀርቡ ድርጅቶች የተለየ ድጋፍና እገዛ ማድረጉን ሰማ:: ይህን የተረዳው አቶ ጆቫኒ፤ ጊዜ ሳያጠፋ ሁለት ሰዎችን ጨምሮ በመደራጀት የመንግሥትን ድጋፍ ማግኘት ችሏል::
በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅቶ ያቋቋመው ሰንላይት ዲጅታል ማስታወቂያና የህትመት ሥራዎች ድርጅት በሁለት እግሩ መቆም እንዲችል የመንግሥት ድርሻ ከፍተኛ እንደነበር ያነሳው አቶ ጆቫኒ፤ የመንግሥት የተለያዩ ድጋፎች ውጤታማ ሥራ መሥራት እንዳስቻሉት ነው የተናገረው:: ለሥራው ከነበረው ጉጉት በተጨማሪ መንግሥት በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ አምራች ኢንደስትሪዎች የሚሰጠው ድጋፍና ክትትል ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ስለመሆኑ ሲናገር ‹‹እኔ ምስክር ነኝ›› በማለት ነው::
መጀመሪያ ላይ ወደ ስራ ሲገባ ከቤተሰብ 50 ሺ ብር ተበድሮ መነሻ ካፒታል ይዞ ወደ ሥራው የገባው አቶ ጆቫኒ፤ ድርጅቱ ያለፉትን 17 ዓመታት የተለያዩ ውጣ ውረዶችን አልፎ ዛሬ ላይ መድረሱን ሲናገር፤ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት እጅግ ከፍ ያለና የላቀ መሆኑን በመግለጽ ነው:: መንግሥት ወጣቱን አደራጅቶ የማምረቻ ቦታዎችን በነጻ ከማቅረብ ጀምሮ በርካታ ድጋፎች ማድረጉ በተለይም አምራች ኢንዱስትሪው ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት እንዲችል ትልቅ ሚና መጫወት እንደቻለ ነው የጠቀሰው::
በተለይም በተደራጀበት አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ትልቅ ድጋፍና ክትትል ያገኝ እንደነበር ያነሳው አቶ ጆቫኒ፤ በወቅቱ ጥሩ ሥራ መሥራት እንዳስቻለው ይናገራል:: ለሥራው ካለው ቅርበትና ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳም በጥራት፣ በፍጥነትና ተመጣጣኝ በሆነ ክፍያ በመሥራት ገበያውን ሰብሮ መግባት እንደቻለና ተፈላጊነቱ በከፍተኛ መጠን እንደጨመረ ያስታውሳል:: በዚህ ወቅትም በጥቃቅንና አነስተኛ መቆየት የሚገባውን ያህል ጊዜ ቆይቶ ወደ ታዳጊ መካከለኛ አምራች ኢንደስትሪ መሸጋገር የቻለው አቶ ጆቫኒ፤ በ2003 ዓ.ም ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ ታዳጊ መካከለኛ ኢንደስትሪ ተሸጋግረው ተሸላሚ ከሆኑት ኢንደስትሪዎች መካከል ሰን ላይት ዲጅታል ማስታወቂያና ህትመት ሥራ ድርጅት አንዱ እንደነበር ነው ያስታወሰው::
የነበረው የሥራ ትጋት፣ መውጣት መውረድና ጉጉት አሁን ለደረሰበት የስኬት መንገድ ትልቅ ድርሻ ያለው ቢሆንም፤ የባለቤቱ እገዛና ድጋፍ ግን ቀላል ግምት የሚሰጠው እንዳልሆነ ጆቫኒ ይናገራል። በእያንዳንዷ የሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ የትዳር አጋሩና የልጆቹ እናት የነበራት ሚና የላቀ ድርሻ ያለውና ለዛሬ ስኬት ያበቃው መሆኑን ተናግሯል:: ወደ ታዳጊ መካከለኛ አምራች ኢንደስትሪ በተሸጋገረ ማግስት ቢሮና የማምረቻ ቦታ ተከራይቶ የማስታወቂያና የህትመት ሥራዎችን በጥራት መስራት በመቻሉ በርካታ ደንበኞችን ማፍራት እንደቻለና ከብዙ ደንበኞቹም ዕውቅናና ምስጋና ማግኘት እንደቻለና ይህም ለበለጠ ሥራ እንዳተጋው አጫውቶናል::
ማንኛውንም ሥራ ለመሥራት ማስታወቂያ የግድና ወሳኝ እንደሆነ የሚናገረው ጆቫኒ፤ ሰዎች የሚሠሩት ሥራ አምሮ፣ ደምቆና ተውቦ ሲመለከቱት እንደሚያስደስተው ሁሉ መተዋወቅ ሲችልና ለዕይታ ሲቀርብም ገበያ እንደሚያገኝ ይናገራል:: ካልሆነ ግን አገልግሎት አቅራቢና አገልግሎት ፈላጊ ሳይተዋወቁ እንደሚተላለፉ ነው የሚገልጸው።
ድርጅቱ ወደ ሥራ በገባበት ወቅት በአገሪቱ የነበረው ዲጅታል ፕሪንቲንግ ወይም የባነር ህትመት እንደነበር ያስታወሰው ጆቫኒ፤ ሥራዎቹን የጀመረው ማተሚያ ማሽኖች ካሏቸው ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን እንደነበር ያስታውሳል:: ይሁንና ብዙም ሳይቆይ ሰን ላይት ዲጅታል ማስታወቂያና ህትመት ሥራ ድርጅትም የራሱን ማተሚያ ማሽን ከውጭ አገር አስመጥቶ ወደ ሥራው በገባ ጊዜ በስፋት ይሠራ የነበረው የባነር ህትመት ሲሆን በአሁን ወቅት ግን የባነር ህትመት እየቀረ ስሪ ዲ የተባሉ የማስታወቂያ ቴክኖሎጂዎች መምጣታቸውን አስረድቷል::
የማስታወቂያ ሥራው እየዘመነ የመጣ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአሁን ወቅት ከተማ ውስጥ የሚታዩት ቢል ቦርዶች ወደፊት እየቀሩ የሚመጡ መሆናቸውን አንስቶ፤ አሁን ላይ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት የዘመኑ ቴክኖሎጂ በደረሰበት ኤል ዲዲ ወይም ተንቀሳቃሽ ምስሎችን የሚያሳዩ የተለያዩ ማስታወቂያዎች እየተተካ መሆኑን ይናገራል::
ሰን ላይት ዲጅታል ማስታወቂያና የህትመት ሥራ ድርጅትም አሁን ላይ ዘመኑ የደረሰበትን የማስታወቂያ ቴክኖሎጂ በመከተል ሁሉንም አይነት ማሽኖች ተጠቅሞ የተለያዩ የማስታወቂያ ሥራዎችን እየሠራ ስለመሆኑ ሲያስረዳ፤ በተለይም በአልሙኒየም ከሚሠሯቸው ሥራዎች መካከል ፓኔል፣ ስሪ ዲ፣ ኤል ኢ ዲ ላይትና ሌተሪንግ ላይቲንግ የሚባሉ እንደሆኑ ነው የተናገረው:: እነዚህ ሥራዎችም በአብዛኛው ትላልቅ በሆኑ ሆቴሎች፣ በተለያዩ ህንጻዎች፣ ኢንዱስትሪዎችና በሌሎች ቦታዎችም እንደሚታዩ ነው ያስረዳው::
“ሰን ላይት ዲጅታል ማስታወቂያና ህትመት ሥራ ድርጅት” በርካታ የማስታወቂያ ሥራዎችን እንደሠራና አሁንም እየሠራ እንደሆነ የጠቀሰው አቶ ጆቫኒ፤ ድርጅቱ በክልል ከተሞች ከሠራቸው ሥራዎች መካከል በሚሊኒየም ጊዜ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተሠሩት ጥራት ያላቸው ሥራዎች ስለመሆናቸው ምስክሮች ናቸው ይላል:: በወቅቱ ጨረታውን አሸንፈው ወደ ሥራ ሲገቡ ‹‹አትችሉትም›› ተብለው እንደነበር በማስታወስ፤ በአማራ ክልል በሁሉም አካባቢዎች የቢል ቦርድ ሥራውን በ18 ቀናት አጠናቀው ማስረከብ እንደቻሉና ሥራውም የተመሰገኑበት እንደነበር አስታውሰዋል:: በወቅቱ ከአማራ ክልል በተጨማሪ በኦሮሚያ፣ በደቡብና በሌሎች ክልሎችም ተዘዋውረው መሥራት እንደቻሉ ነው አቶ ጆቫኒ ያስረዳው::
ሰን ላይት ዲጅታል ማስታወቂያና ህትመት ሥራ ድርጅት በሁለት የንግድ ፈቃዶች የሚሠራ ሲሆን በዋናነት ከሚሠራቸው የማስታወቂያ ሥራዎች በተጨማሪ ኦፍ ሴት ፕሪንቲንግ የተባለውን የወረቀት ሥራም ይሠራል:: በህትመት ሥራውም ከቢዝነስ ካርድ ጀምሮ ያሉትን ማንኛውም የወረቀት ሥራ የሚሠራ ሲሆን ለአብነትም ፖስተር፣ ብሮሸር፣ ካላንደር፣ በራሪ ወረቀት፣ የኬክ፣ የፒዛና የበርገር መያዣ ካርቶኖች ይጠቀሳሉ:: ለእነዚህ ሥራዎችም አስፈላጊዎቹ ግብዓቶች ወረቀትና ቀለም ናቸው፤ ወረቀትና ቀለሙን ገዝቶ በዲጅታል ማተሚያ ማሽን ማተም ነው::
የህትመት ሥራው የተለያዩ ዘርፎች ያሉት መሆኑን የጠቀሰው አቶ ጆቫኒ፤ የተለያዩ የማስታወቂያ ዕቃዎችን እንደ ቲሸርት፣ ኮፍያ፣ ቁልፍ መያዣ፣ እስኪሪብቶ፣ የደረት ፒን፣ ፍላሽ፣ ዲስክና ሌሎችንም በመጠቀም ደንበኛው የፈለገውን ማንኛውንም አይነት የህትመት ሥራዎች ያትማል:: ከዚህ በተጨማሪም የስሪ ዲና ባነር ላይ ለሚሠሩ ማስታወቂያዎች የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ለአብነትም ለባነር ባነር፣ ቀለም፣ ስቲከርና የተለያዩ ግብዓች የሚያስፈልጉ ሲሆን፤ ስሪ ዲ ማስታወቂያዎችን ለመሥራት ደግሞ ማይካ፣ አልሙኒየም፣ ኤል ኢዲ፣ ፕላስቲክ ስትሪፕና ሌሎች ግብዓቶች አስፈላጊ እንደሆኑ አቶ ጆቫኒ አስረድቷል::
ድርጅቱ የማስታወቂያና የህትመት ሥራዎቹን አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችለውን ቦታ ከመንግሥት በሊዝ መግዛት የቻለ ሲሆን፤ በአሁን ወቅትም 1500 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ ግንባታውን ማጠናቀቅ ችሏል:: በቀጣይም ማሽኖቹን አስገብቶ ወደ ምርት በሚገባበት ወቅት ከ150 እስከ 200 ለሚደርሱ ሰዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ይሆናል:: በአሁን ወቅት የፋብሪካው ግንባታ ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀ መሆኑን የጠቀሰው አቶ ጆቫኒ፤ ፈጥኖ ወደ ሥራ ለመግባት ግን የፋይናንስ እጥረት የገጠማቸው መሆኑን አልሸሸጉም:: ፋብሪካው በርካታ ሥራዎችን መሥራት የሚያስችል እና ትልቅ ሃብት የፈሰሰበት መሆኑን አቶ ጆቫኒ ይገልጻል::
በሌላው ዓለም የማስታወቂያ ሥራ ትልቅ ቦታ ያለውና ብዙ ሥራ የሚሠራበት ዘርፍ መሆኑን የገለጸው አቶ ጆቫኒ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ገና እንደሆነና ብዙ የሚቀረው የሥራ ዘርፍ እንደሆነ ይናገራል:: በተለይም ዘርፉ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙ ሊሠራበት እንደሚገባ በመግለጽ መንግሥት ለአምራች ኢንደስትሪዎች የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና በርካቶችም ዕድሉን በመጠቀም ወደ ሥራ መግባት እንዳለባቸው አስገንዝቧል::
የማስታወቂያ ሥራ በህግ መመራት እንዳለበት ያነሳው አቶ ጆቫኒ፤ መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁን ወቅት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ በመሆኑ በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶች እንደሚቀረፉ ያምናል:: በዚህም ከሁለትና ሶስት ዓመታት በኋላ ጉራማይሌ የሆነው የማስታወቂያ ሥራ አንድ ወጥ በመሆን ለከተማ ውበት እንደሚሆኑ ያለውን ዕምነት ሲገልጽ፤ አሁን ላይ የሚታየውና ከህግ ውጭ የሆኑ አንዳንድ አሠራሮች እየቀሩ እንደሚሄዱ ነው እምነቱን የሚገልፀው፡
ሰን ላይት ዲጅታል ማስታወቂያና ህትመት ሥራ ድርጅት ሲመሰረት ሶስት ሆነው እንደጀመሩት የሚናገረው አቶ ጆቫኒ፤ አንድ ሁለት በማለት በአሁን ወቅት ለ33 ቋሚ እና ለሰባት ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ሲሆን፤ የጊዜያዊ ሠራተኞች ቁጥር በየጊዜው የሚለዋወጥ እንደሆነ ነው የተናገረው:: ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም እንዲሁ እንደ ድርጅትም ሆነ በግሉ የተለያዩ በጎ ተግባራትን እንደሚያከናውን የጠቀሰው አቶ ጆቫኒ፤ በተለይም መንግሥታዊ ለሆኑ ማንኛውም ጥሪዎች ፈጣን ምላሽ እየሰጠ እንዳለና ወደፊትም ይህንኑ ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክቷል::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2015