የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የ10ሺ ሜትር የሰዓት ማሟያ(ሚኒማ) ውድድሩን ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገር ውስጥ እንደሚያካሄድ አስታወቀ:: ማጣሪያው ከአንድ ወር በኋላ በሀዋሳ ስታዲየም የሚከናወን ይሆናል::
19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በሃንጋሪ ቡዳፔስት ሊካሄድ የሶስት ወራት ዕድሜ ብቻ ቀርቶታል:: በዚህ ቻምፒዮና ላይ ተሳታፊ የሆነችው ኢትዮጵያም ለረጅም አመታት ስኬታማ በሆነችበት የ10ሺ ሜትር ርቀት የሚወክሏት አትሌቶች ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገር ውስጥ ማጣሪያ ይለያሉ:: በዓለም አቀፍ ደረጃ በዚህ ርቀት በግል የሚደረጉ ውድድሮች ቁጥር በእጅጉ መቀነሱ ይታወቃል:: ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በርቀቱ የሰዓት ማሟያና የአትሌቶች መምረጫ ውድድሩን በሆላንድ ሄንግሎ ሲያከናውን መቆየቱ የሚታወቅ ነው:: ከዚህ ዓመት አንስቶ ግን በራሱ አቅም በሀገር ውስጥ እንደሚያካሄድ እና ለዚህም በቂ ዝግጅት ያደረገ መሆኑን አስታውቋል::
ፌዴሬሽኑ የብሔራዊ ቡድን የሰዓት ማሟያ ውድድሩን በመጪው ሰኔ 11/2015 ዓ.ም፤ በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ስታዲየም ለማድረግ ማቀዱንም አስታውቋል:: የሰዓት ማሟያው ሀዋሳ የሆነበት ምክንያትም አዲስ አበባ በአንጻራዊነት በከፍታ ቦታ(high altitude) ላይ የምትገኝ እንደመሆኗ አትሌቶች አስፈላጊውን ሰዓት ለማስመዝገብ ከባድ ስለሚሆንባቸው ነው:: በሰዓት ማሟያ ውድድሩ ላይ ተካፋይ የሚሆኑ አትሌቶች በፌዴሬሽኑ መስፈርት መሰረት የሚመረጡ ሲሆን፤ በሁለቱም ጾታ በጥቅሉ 32 አትሌቶች እንደሚመዘኑም ታውቋል:: 16 ወንድ እንዲሁም 16ሴት አትሌቶች በሚካፈሉበት ማጣሪያ በሁለቱም ጾታ 16 የሚሆኑት አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ባላቸው ምርጥ ሰዓት የሚመረጡ ናቸው::
የተቀሩት አትሌቶች ደግሞ ከተጀመረ ዛሬ 4ኛ ቀኑን ከያዘው 52ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በርቀቱ በሁለቱም ጾታ ከ1-8 ያለውን ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁት ናቸው:: በዚህ ቻምፒዮና ላይ አዳዲስ እና ልምድ ያላቸው አትሌቶች በእኩል የሚካፈሉ እንደመሆኑ ለማጣሪያው ለማለፍም አትሌቶች እኩል ዕድል የሚኖራቸው ይሆናል:: በዚህም መሰረት በቻምፒዮናው መክፈቻ በተከናወነው የሴቶች 10ሺ ሜትር ውድድር ለማጣሪያው ያለፉ አትሌቶች ተለይተዋል:: እነርሱም ለምለም ኃይሉ፣ ዘይነባ ይመር እና መስታወት ፍቅሩ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ቦሰና ሙላቴ ከአማራ ማረሚያ፣ ውዴ ከፋለ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ትዕግስት ከተማ ከኦሮሚያ ክልል፣ አይናዲስ ተሾመ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ እንዲሁም ገበያነሽ አየለ ከመቻል ናቸው::
በሁለተኛው ቀን የቻምፒዮናው ውሎም በወንዶች ለማጣሪያው ያለፉ ስምንቱ አትሌቶች ተለይተዋል:: በዚህም ቦኪ ድሪባ ከኦሮሚያ ክልል፣ ይስማው ድሉ ከአማራ ክልል፣ ኃይለማርያም አማረ ከፌዴራል ማረሚያ፣ ወርቅነህ ታደሰ ከኦሮሚያ ክልል፣ ለታ አበበ ከኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ፣ ዘነበ አየለ ከፌዴራል ማረሚያ፣ አቤል በቀለ ከአማራ ክልል እንዲሁም ድንቅዓለም አየለ ከአማራ ፖሊስ ሀገራቸውን ለመወከል የሚያስችላቸው የማጣሪያ ውድድር ላይ ይካፈላሉ:: ቻምፒዮናው በመጪው እሁድ ግንቦት 13/2015 ዓ.ም የሚጠናቀቅ ሲሆን፤ የሰዓት ማሟያ ውድድሩ እስከሚካሄድበት ሰኔ አጋማሽም አትሌቶች በቂ የዝግጅት ጊዜ ይኖራቸዋል::
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ተሳትፎ የስራ ሂደት መሪ አቶ አስፋው ዳኜ፤ ቀድሞ በሄንግሎ ይካሄድ የነበረው የማጣሪያ ውድድር በተለያዩ አካላት እገዛ እንዲሁም በፌዴሬሽኑ ወጪ ቢሆንም አሁን ግን ችግሮች የገጠሙት መሆኑን ተናግረዋል። እንደ ኬንያ ያሉ ጎረቤት ሀገራት መሰል ውድድሮችን በሀገራቸው የሚያከናውኑ መሆኑን ተከትሎ፤ ኢትዮጵያም በሀገሯ ማድረግ እንደምትችል ከውሳኔ ተደርሷል:: ደረጃውን የጠበቀና በዓለም አትሌቲክስ የተመዘገበ መም እንዲሁም ምቹ የአየር ሁኔታ ካለ ማጣሪያውን ማከናወን የሚቻል ሲሆን፤ በፌዴሬሽኑ በኩልም ዝግጅት ተደርጓል:: በቀጣይም በሀገሪቷ ደረጃቸውን የጠበቁ መሞች ካሉ በተለያዩ ክልሎች ማጣሪያው የሚደረግ ይሆናል:: ይህም መልካም ልምድ በመሆኑ መበረታታት እንደሚገባው አቶ አስፋው አስረድተዋል።
ለቻምፒዮናው የሚሆኑ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የጠቆሙት የስራ ሂደት መሪው፤ እንደየርቀቱ ሳይንሱ በሚያስቀምጠው ጊዜ መሰረት ምርጫና ዝግጅት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል። በዚህም መሰረት የማራቶን አትሌቶች ውድድር እየተዘጋጀ ሲሆን፤ በሌሎች ውድድሮችም በቀጣይ በሚካሄዱ የአህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሚኒማ የሚያሟሉ አትሌቶች ይመረጣሉ:: እንደ 800 እና 1ሺ500 ሜትር ባሉ ርቀቶች ቻምፒዮናው አንድ ወር እስኪቀረው የአትሌቶች ምርጫው የሚጠበቅም ይሆናል:: በቀጣይ በሚኖሩት ከ46-60 ቀናት ድረስም የብሔራዊ ቡድኑ ምርጫ ተጠናቆ አትሌቶች ለቻምፒዮናው የሚሆን ዝግጅታቸውን የሚጀምሩም መሆኑንም አቶ አስፋው አስገንዝበዋል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2015