እሴቶቻችን ለኢትዮጵያ ከፍታ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን ይናገራሉ። የማህበረሰብ መሪዎች፣ ተፅእኖ ፈጣሪዎች፣ ቤተ ዕምነቶች፣ የመንግስት አካላትና የግል አስተዋጽኦ በትውልድ ውስጥ ያለና የነበረን አደራ ለማስቀጠል እንደሚረዳም ይገልፃሉ። በማህበረሰብ ውስጥ በሚፈጠሩ ለውጦች እሴቶቻችን ለትውልድ ማስቀጠል የአብሮነትንና የመቻቻል ባህልን እየፈጠሩና ትናንት የነበሩትን እያስቀጠሉ መጓዝ አስፈላጊ መሆኑን ነው ምሁራኑ በምክረ ሃሳባቸው የሚያመለክቱት።
ይሁን እንጂ እነዚህን እሴቶች የሚሸረሽሩ ጉዳዮች በየጊዜው እየተደቀኑብንና ፈተና እየሆኑብን ይገኛሉ። ይህንን አስመልክቶ የማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ምሁራን “የቀደሙት ትውልዶች ያስቀመጠልን በጎ ተግባሮች ለምን እየተሸረሸሩና እየጠፉ መጡ?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት ይሞክራሉ። በተለያዩ የውይይትና የምክክር መድረኮችም ለፈተናዎቹ መነሻ የሆኑ መንስኤዎችና መፍትሄዎችን ይሰነዝራሉ። ከነዚህ አንዱ “የማህበራዊ እሴት ምሰሶ የሆኑት ጉዳዮቻችንን በአስተማሪ መንገድ ማሳደግ የቤተሰብ የአስተዳደግ ባህልና የትምህርት ቤቶችን ድርሻ ማላቅ” የሚለው ምክር ሃሳብ ይገኝበታል።
እነዚህ ምሁራን ኢትዮጵያዊ የጋራ እሴቶችንና ባህሎችን አስጠብቆ ለመጓዝና ትውልድን በመልካም ስነምግባር ለማነፅ ሁሉም የራሱን አሻራ ማስቀመጥ እንዳለበትም ይሞግታሉ። በተጨማሪም እየተቀባበልን ያመጣናቸውን እሴቶች ለማስቀጠል እንዲበጅ በፍኖተ ትምህርት እና ስርዓተ ተግባቦት ዙሪያ አፅንኦት መሰጠት እንዳለበት ምክረ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ።
በእነዚህ ሀገራዊ እሴቶች ላይ ያነጋገርናቸው የፎክሎር ባለሙያው ዶክተር ሙሀመድ አሊ እሴቶች በብዙ መልኩ እንደሚገለጹ ይናገራሉ:: ባህላዊ፣ ስነ ልቦናዊ፣ ፖለቲካዊ እየተባሉ እንደሚገለጹም ያመለክታሉ። እርሳቸው ባህላዊ እሴት ላይ ትኩረት ያደረገ ጥናት ማድረጋቸውን ጠቅሰው፣ በጥቅሉ ግን “እሴት” ለሚባለው ቃል አንድ ብያኔ ለመስጠት እንደሚቸግሩ ነው የሚገልጹት።
በጥቅሉ ግን እሴቶች በአንድ ማህበረሰብ፣ ቡድን ወይም ግለሰብ ተቀባይነት ያገኙ መርሆች መገለጫና መለኪያዎች መሆናቸውን ይናገራሉ። በምሳሌነት አንድ አካባቢ ላይ ግጭት ቢፈጠር፣ አንድ ባለጉዳይ ቢጉላላ፣ ወጣቶች የአባቶችን ተግሳፅና ምክር መስማት ቢያቆሙ ይህንን ችግር በሀገረኛ እሴቶች መፍታት የሚያስችል ባህል አሊያም ስርዓት “እሴት” እንደሚባል አብራርተዋል።
“በሀገራችን በአጋጣሚ ሰብዓዊነት በጎደለው መልኩ ሰዎች ሲገደሉ፣ ህፃናትና ሴቶች ሲደፈሩ፣ ከስነምግባር ያፈነገጡ ድርጊቶች ሲፈፀሙ፣ ባህላዊ ስርዓቶች ሲጣሱ ብዙዎች ‘ስምንተኛው ሺ ደረሰ’ በማለት የተጣሱት ስርዓቶች እንዲከበሩ ይሞግታሉ” የሚሉት የፎክሎር ባለሙያው፤ ይህ የሚያሳየው ቀድሞውንም የስነ ምግባር፣ የሰብዓዊነት፣ ታላላቆችን የመስማት እንዲሁም በህግና ስርዓት የመገዛት እሴቶች መኖራቸውንና እነርሱ እንዳይሸረሸሩ ብሎም እንዲጠበቁ የሚደረግ ጥረት በኢትዮጵያዊያን ዘንድ እንዳለ ይናገራሉ።
ዶክተር ሙሀመድ ሰዎች ሲጋጩ ማስታረቅ፣ በመስሪያ ቤቶች የአገልጋይነት ስሜት መላበስ፣ መልክና ስርዓት ያለው ግብረ ገብነትን ማክበር የኢትዮጵያውያን እሴት መሆኑን ይገልፃሉ። እነዚህ ሲጣሱና ስጋት ሲኖር ቀድሞ የነበረው ስርዓት መጣሱን ስለሚያመለክት ለዚያ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚበጅ ይገልፃሉ። እሴትን ከባህል አንፃር ስንመለከተው እሴቶች ሰዎች በግልም ሆነ በቡድን የእለት ተእለት ኑሯቸውን በሚፈልጉት መንገድ ለመምራት ያስችላቸው ዘንድ የሚያበጇቸው ስነምግባራዊ ጉዳዮች እንደሆኑም ይናገራሉ።
“እሴቶች ሰናይና እኩይ ሆነው ይቀመጣሉ” የሚሉት የፎክሎር ባለሙያው፤ ደግነትና ክፋት፣ ሰላምና ጦርነት፣ ፍቅርና ጥላቻ፣ አብሮነትና ግለኝነት፣ ታማኝነትና ክህደት፣ ፍትሃዊነትና አድሏዊነት የማህበረሰቡ የእሴት መለኪያዎች ወይም መገለጫዎች መሆናቸውን ያብራራሉ:: ኢትዮጵያዊነትን ሰናይ መልካም ነገር በትውልዱ ላይ እንዲሰርጽ እና የማንነቱ መገንቢያ ስሪት አድርጎ እንዲቀበለው ለዘመናት የተቀመጠ መሆኑን ይገልፃሉ። በተቃራኒው እኩይ መለኪያዎችን ደግሞ ማህበረሰቡ የሚጸየፋቸውና ትውልዱ ውስጥ እንዳይሰርጹ የሚያደረግበት ስርዓት እንደሆነም ያመለክታሉ።
ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ፣ ባህላዊ ስርዓቶች እንዳይበረዙና በመጤ ባህል እንዳይወረሩ፣ ግጭት ማስወገጃ ባህላዊ ስርዓቶች ተጠብቀው ለትውልዱ እንዲተላለፉ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሚገልፁት የፎክሎር ባለሙያው፣ ምንም እንኳን ዓለማቀፋዊ ይዘት ቢኖራቸውም እንግዳ መቀበል፣ ታላላቆችን ማክበር፣ ግጭት ሲፈጠር በሽማግሌዎች ጣልቃ ገብነት መታረቅና ባህላዊ ስርዓቶችን ማክበር፣ አብሮ መብላት እና ሌሎችም ኢትዮጵያዊ እሴቶች መሆናቸውን ይናገራሉ።
የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆኑት እሴቶች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያየ መልኩ ፈተና እየገጠማቸው፣ አብሮነትን የሚሸረሽሩ፣ ስነ ምግባርን ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ አሊያም ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ወደጎን የሚሉ ድርጊቶች እየተስተዋሉ መሆኑን የፎክሎር ባለሙያው ዶክተር ሙሀመድ ይናገራሉ:: ይህንን እየፈጠረ ያለው በዘመኑ ቁሳዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ርእዮተ ዓለም መከተላችን መሆኑን ይገልጻሉ:: ይህ ሁኔታ በእሴቶቻችን ላይ ተፅእኖ እያሳደረ ይገኛል ነው የሚሉት:: በተለይ ሀብትን፣ ዝናን፣ ስልጣንን እንዲሁም መሰል ቁሳዊ ፍላጎታችንን በሚያሟሉልን ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረጋችን ለእሴቶቻችን መሸርሸር፣ ለባህሎቻችን ወደ ጎን እየተገፉ መምጣት ስጋት እየሆነ መምጣቱንም በምሳሌነት ያነሳሉ።
“እሴቶች በባህሪያቸው መንፈሳዊነትን የተላበሱ ናቸው” የሚሉት የፎክሎር ባለሙያው፤ አንድ ሰው ቢሰርቅ በፍርድ ቤት ቀርቦ ጥፋተኛ እስካልተባለ ወንጀለኛ አይደለም ይላሉ። ይሁን እንጂ ቀደምት አባቶች ትተውልን ባለፉት ከባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና እንዲሁም በወል ስምምነት ከተቀመጡ እሴቶች አንፃር ‘መስረቅ’ ሃጢያት ከመሆኑም ባሻገር ማህበራዊ ውግዘትን የሚያመጣ፣ መገለልን የሚያደርስና ፍፁም አፈንጋጭ በመሆኑ የተነሳም ድርጊቱን ፈፃሚው ከድርጊቱ እንዲቆጠብ እንደሚረዳ ይናገራሉ።
አሁን አሁን ስርቆትን አሊያም ማህበረሰባዊ ቀውስን የሚያመጡ ድርጊቶችን ከህግና ሳይንሳዊ መንገድ ባሻገር በባህላዊ እሴቶች ማረቅ በማቆማችን ቀስ በቀስ ትውልዱ ላይ ክፍተት እንዲመጣና የእሴት ሀብቶቻችንም እንዲሸረሸሩና የመጥፋት ስጋት እንዲገጥማቸው መንስኤ እየሆነ እንደመጣ ይገልፃሉ።
“ለእሴቶቻችን ያለን አመለካከት ሌላኛው ችግሩን እያባባሰው ያለ ጉዳይ ነው” የሚሉት የፎክሎር ባለሙያው፤ ‘እሴቶቻችን ኋላ ቀር ናቸው’ የሚል አመለካከት በትውልዱ ውስጥ እየሰረፀ መምጣቱ ቁልፍ ችግር መሆኑን ይናገራሉ። ይህ አይነቱ አመለካከት በፖለቲካ አመለካከትም ይሁን በሌሎች ልዩ ልዩ ምክንያቶች ግጭት በቡድኖችና ግለሰቦች መካከል ሲፈጠር ግጭቱ በባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴና በአገር ሽማግሌዎች መፍታት አይቻልም የሚል እሳቤ ላይ እያደረሰን ሲሉም ይናገራሉ።
እነዚህን እሴቶች ጠብቀው ያቆዩ አካባቢዎች በሚገባ እየተጠቀሙባቸውና ችግሮቻቸውን እየፈቱባቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አዲሱ ትውልድ እሴቶቹን ኋላቀር ከሚል እሳቤ ወጥቶ ጥቅማቸውን በሚገባ በማጤን ሊጠብቃቸው ይገባል የሚል ምክረ ሃሳብ ዶክተር ሙሀመድ ይሰጣሉ።
“ሽማግሌ ከረገመው እንኳን ሰው ዛፍ ይደርቃል” የሚል አባባል በማህበረሰቡ ዘንድ ለዘመናት የሰረፀ እንደሆነ የሚናገሩት የፎክሎር ባለሙያው፣ ትውልዱ ችግሮቹን ለመፍታት፣ መፍትሄ ለማግኘት ታላላቆቹና ከሕይወትና ከጥበብ ልምድ የቀሰሙ አባቶቹ የዘረጉለትን ስርዓት ሊያከብርና እሴቶቹን ሊጠብቅ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ። አሁን በተለያየ ምክንያት የባህላዊ ሀብቶቻችንን አቅም የሚያሳጡ ነገሮች እያስተዋልን ነው የሚሉት የፎክሎር ባለሙያው፣ ይሄም በማህበረሰቡም ሆነ በአገር መሪዎች ዘንድ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያሳስባሉ።
የፎክሎር ባለሙያው ዶክተር ሙሀመድ፤ የትምህርት ስርዓታችን ለእሴቶቻችን መሸርሸር ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ነው ብለው ያምናሉ። በተለይ የሐገሪቱ ስርአተ ትምህርት እሴቶቹ ላይ ትኩረት ያደረገ አለመሆኑን ገልጸው፣ ይህ በጥቅሉ እንደ አገር እየጎዳን ስለመሆኑም ነው ያሳሰቡት።
በተጨማሪም የመገናኛ ብዙሃን እሴቶችን የሚረሱ፣ የሚንቁና የሚያጣጥሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ መገናኛ ብዙሃኑ በእሴቶቻችን ላይ ቀጥተኛ አሉታዊ ተጽእኖ እያደረሱ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። ለእዚህ እንደ ምሳሌ የሚያነሱትም ከአለባበስ፣ ከባህል ወረራና መጤ ባህል እና ከመሳሰሉት ገዳዮች ጋር ተያይዞ በመገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ አግባብነት የጎደላቸው ዝግጅቶች እሳቱ ላይ ተጨማሪ ጋዝ የሚያርከፈክፉና በጊዜ ሊገደቡ የሚገባቸው እንደሆነ ያሳስባሉ። በመሆኑም የትምህርት ስርዓቱም ሆነ መገናኛ ብዙሃን በአገራዊ እሴቶች፣ መልካም የስነ ምግባር፣ አብሮነትና አንድነትን ሊያጠናክሩ በሚችሉ ሀብቶች ሊገነቡ እንደሚገባና ትውልዱም በዚህ መንገድ መቀረጽ እንዳለበት ይናገራሉ።
“እሴቶቻችን ደካማ ስለሆኑና ስለማይጠቅሙ አይደለም እየተውናቸው ያለነው” የሚሉት ዶክተር ሙሀመድ፤ የሽምግልና ስርዓትን እንደ ምሳሌ መውሰድ ቢቻል በአጥፊና ተበዳይ ዘንድ ዳኝነት የሚሰጥ ሳይሆን ድርድር እንዲደረግ የሚገፋፋ፤ እውነቱ ወጥቶ ካሳና እርቅ እንዲፈፀም የሚያደርግ ነው ሲሉ ያብራራሉ:: በተጨማሪም ‘እውነትና ፍትህን’ የሚያስታርቅ፣ ከዘመናዊው የዳኝነት ስርዓት በተሻለ ቂምና ጥላቻን አስወግዶ ሰላምን የሚያሰፍን መሆኑን ያስረዳሉ። ይህ ስርዓት እየተሸረሸረና ትኩረት እየተነፈገው መምጣቱን አመልክተዋል።
እንደ መውጫ
ኢትዮጵያ የሺህ ዘመናት የአገረ መንግስት ታሪክ፣ ውብ ባህልና ማንነት ያላቸው ብሔረሰቦች በጋራ ተዋደውና በአንድነት ተጋምደው የሚኖሩባት አገር ናት። ሕዝቦቿ ለአይን ማራኪ፣ ጆሮ ገብና ተወዳጅ እሴቶች ባለቤት፤ ባህልና ወጋቸው ለባዳው የሚያስቀና ለወዳጅ ሃሴትን የሚፈጥር ጭምር ነው። ዜጎቿ ጠላትን በአንድነት መክተው ድባቅ የሚመቱ ለሉዓላዊነታቸው መከበር በጋራ ዘብ የሚቆሙም ናቸው። ሁሉም ዜጎች ኢትዮጵያዊነትን ሳይለቁና የመጡበትን ማህበረሰብ ባህልና ማንነት ሳይሸራርፉ አብረው የመኖር የሺህ ዓመታት ታሪክም አላቸው። በተለያዩ ጊዜያት የነዚህን ሕዝቦች አንድነት የሚፈታተኑ አያሌ አጋጣሚዎች የነበሩ ቢሆንም፣ በጠንካራው አብሮነትና የተጋድሎ ወኔ ችግሮቹን በጣጥሰው በማለፍ ዛሬ ላይ ደርሰዋል።
ቀደም ባሉት ዘመናት ስነ ምግባር፣ መልካም አለባበስና ውበት አጠባበቅ፣ ትህትና፣ ታላላቆችን ማክበርና በፍቅርና በአንድነት መኖርን የሚያጎለብቱና የሚጠብቁ ባህሎች የኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊነት መገለጫ ተደርገው ይወሰዱ ነበር። አሁን አሁን የሉዓላዊነት (globalization)፣ የመገናኛ ብዙሃን፣ መጤ ባህሎችና ልዩ ልዩ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ተፅእኖ እነዚህን አገር በቀል ጥበብና እውቀቶች ቀስ በቀስ እንዲረሱና የመጥፋት አደጋ እንዲጋረጥባቸው አድርገዋል::
ይህ ብቻም አይደለም፤ አብሮነት እንዲሸረሸር፣ ጭካኔና ግለኝነት እንዲበረታ፣ ማናለብኝነትና እብሪት እንዲስፋፋ ምክንያት እየሆኑ ስለመምጣታቸው በእንግድነት አስተያየት እንዲሰጡን የጋበዝናቸው ባለሙያን ጨምሮ መሰል የማህበራዊ ዘርፍ ምሁራን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሲሞግቱ እየተደመጡ ነው። የዚህ አምድ አዘጋጅም የባህል ዘርፉን ከሚመራው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጀምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ የጋራ እሴቶቻችንን ለመጠበቅ ሊረባረቡና ትውልዱን ከጥፋት ሊታደጉ ይገባል ሲል መልእክቱን ለማድረስ ይወድዳል። ሰላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2015