መስከረም 28 ቀን 1935 ዓ.ም አዲስ አበባ ‹‹ቀበና›› ከተባለ አካባቢ የተወለደችው ህጻን ልጅነቷን ባሳለፈችበት ዕድሜ የተለየ ተሰጥኦ እንዳላት የነገራት አልነበረም። እሷም ብትሆን ውስጧ የቆየውን ድብቅ ችሎታ በወጉ ሳታውቀው አመታትን አብራው ዘልቃለች።
ሂሩት በቀለ አንዳንዴ ለራሷ በሚመስል ድምጸት ታንጎራጉራች፣ በዘመኑ የነበሩ ድምጻውያንን አስመስላም ትዘፍናለች። ይህን ባደረገች ጊዜ ውስጧን ደስ ይለዋል። መልሳ መላልሳ የምትዘፍናቸው ዘፈኖች ፈጽሞ አይሰለቿትም። ይህን የሚያስተውለው ሲሳይ የተባለ ወታደር ጎረቤቷ ሁሌም ከሌሎች በተለየ ያደምጣታል።
አንድ ቀን ወታደሩ ሂሩትን እንደ ቤተሰብ ቀረብ ብሎ ያጫውታት ያዘ። ሂሩት በየቀኑ ዘፈን እንጉርጉሮዋን እንደሚሰማ ሲነግራት ደንገጥ አለች። ሲሳይ ሸጋ የሆነ ድምጽ እንዳላት ደጋግሞ አረጋገጠላት። እንዲህ ይበላት እንጂ እሱ በሚላት ልክ የሚደመጥ ጆሮ ገብ ድምጽ እንዳላት አታውቅም ነበር። ሲሳይ በአድናቆት ብቻ አላቆመም። ይህን ድምጽ ትጠቀምበት ዘንድ በምድር ጦር ሰራዊት የሙዚቃ ክፍል እንድትቀጠር ሀሳብ ሰጣት። ሂሩት ቃሉን ስትሰማ ቤተሰቦቿን አሰበች። እነሱን ስለምትፈራም እንደማታደርገው መለሰችለት። ሲሳይ ግን ፍራቻዋን አስወግዶ ወደ ስፍራው እንድትሄድ በእጅጉ ገፋፋት። ሂሩት ሀሳቡን እንደዋዛ ማለፍ አልፈለገችም።
በማግስቱ እሷና ሶስት ባልንጀሮቿ ተያይዘው ወደስፍራው አመሩ። የክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ባለሙያዎች ሁሉንም ተቀብለው ለፈተና አቀረቧቸው። ሂሩት ብትፈራም መረዋ የሆነው ድምጽዋ መደበቅ አልቻለም። ዳኞቹን አፍ አስይዛ ውድድሩን በድል አጠናቀቀች።
ዘመን መለወጫን በሀር ሸረሪት
አሁን ሂሩት በሙዚቃ የፈተኗትን ባለሙያዎች አስደንቃ በሙያው ለመቀጠር በቅታለች። በዕለቱ የተጫወተችው ‹‹የሀር ሸረሪት›› የተሰኘውን ዜማ ነበር። የሀር ሸረሪት በእሷ አንደበት ሲዜም ውበት አለው። ጆሮ ገብ የሆነ ድምጽዋ ብዙዎችን ማርኳል። ሂሩትና የሀር ሸረሪት በፈተና አጋጣሚ ብቻ አልተለያዩም። ዜማውን በወጉ አጥንታ በዘመን መለወጫ በዓል የአዲስ አመት መድረክ ላይ እንድታቀርበው ተወሰነ። እንደተባለው ሆኖ ሂሩት የሀር ሸረሪትን በምድር ጦር ኦርኬስትራ ታጅባ በብሔራዊ ቲያትር መድረክ ለሕዝብ አቀረበች።
ለመጀመሪያ ጊዜ ታዳሚ ፊት የቀረበችው ሂሩት ገና ሙዚቃውን ስትጀምር ብርክ ያዛት። እንግዶችን ቀና ብላ ለማየት ድፍረቱን ብታጣ በሀፍረት ተሸማቀቀች። ድንቅ ድምጽዋ እንደጅምሩ አልቀጠለም። ፍርሀቷ ብሶ መድረኩን ትታ ወደኋላ ሮጠች። ሂሩት ተመልሳ አልመጣችም። ሙዚቃውን ሌላዋ ድምጻዊት አሰገደች ካሳ እንድትጨርሰው ተደረገ። ታዳሚውም አዲስ አቀራረብ መስሎት በአድናቆት አጨበጨበ።
ሂሩትን ይህን በማድረጋ ከአለቆቿ ምክርና ተግሳጽ ተለግሷት ወደስራው ልትመለስ ግድ ሆነ። አይናፋሯ ድምጻዊት ሁለት ወዶ እንደማይሆን ታውቃለች። እያደር ግን ሙያውን ከባህርይዋ ለማስታረቅ ታገለችና ተሳካላት። ደርባባዋ ሂሩት ማራኪ በሆነ ድምጽዋ በየመድረኩ እየቀረበች ታዳሚውን ማዝናናቱን ያዘች። በአጭር ጊዜም ክብርና አድናቆት ተከተሏት።
ያኔ በዘመኑ አንዲት ሴት ልጅ እንደዋዛ ከወላጆች ዓይን እንድትርቅ አይፈቀድላትም። የት ወጣሽ የት ገባሽ ማለት የማይቀር ነው። ሂሩት ይህን እውነታ ለማለፍ የታይፕ ትምህርትን ስታሳብብ ቆየች።
ሂሩትና የቤተሰብ ፍጥጫ..
ሂሩት ከቤት ወጥታ፣ ፈተናውን አልፋ ሙዚቀኛ ስለመሆኗ ቤተሰቦቿ አላወቁም። ይህን ምስጥር የግሏ ያደረገችው ወጣት ሁሉን በዝምታ ደብቃ አብራቸው መኖር ይዛለች። አንድ ቀን የሂሩት ቤተሰቦች ለመዝናናት ቢያስቡ ምርጫቸው ብሔራዊ ቲያትር ሆነ። በዕለቱ የነበረው ዝግጅት የሙዚቃ ትዕይንት ነበር።
እንግዶቹ ጥቂት ዘፈኖችን እንዳዩ ልጃቸው ሂሩት በቀለ ወደ መድረኩ ተጋብዛ ሙዚቃዋን ማቅረብ ትጀምራለች። ያዩትን ማመን የተሳናቸው ቤተሰቦቿ ዘፈኑን ሳይጨርሱት አቋርጠው ይወጣሉ። ይህን ያላየች ያልሰማችው ሂሩት ‹‹አገር አማን›› ብላ ወደቤት ስትገባ መላው ቤተሰብ ፊት ነሳት። በተለይ ወንድ አያቷ የሰሙትን ባለማመን ከውርስና ኑዛዜ ሳይቅር አገለሏት። ሂሩት በሆነው ሁሉ ብትደነግጥም የምትወደውን ሙያ መተው አልፈለገችም።
ከጊዜ በኋላ ከቤተሰብ ጋር እርቅ ወረደ። እሷም በነጻነት ከሙያዋ ውላ የጥበብ ስራዋን ማቅረብ ቀጠለች። በተለየ እርጋታ መድረኩን በመያዝ የምትታወቀው ሂሩት የተሰጣትን ዜማ ከግጥሙ አስማምታ ማቅረቧ በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን አስገኘላት። ለስላሳ ዘፈኖቿም ጆሮ ገብ ሆነው በተወዳጅነታቸው ቀጠሉ።
አሁን ሂሩት በክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ በቋሚ ቅጥር እየሰራች ነው። ቦታው ታላቅ ክብር ያለው ነውና በአጭር ጊዜ የእሷም ዝና ጨምሯል። ይህ ዝነኝነቷ ከአድናቆት አልፎ ከሌሎች ዓይን ጥሏታል። አንድ ቀን በአትኩሮት ከሚያይዋት በርካቶች መካከል አንድ ሰው ቀረብ ብሎ አዋያት። ይህ ሰው በፖሊስ ሰራዊት የሙዚቃ ክፍል የግጥምና ዜማ ደራሲው ተስፋዬ አበበ ነበር።
የተስፋዬ ንግግር ዝነኛዋን ሂሩት በማወደስ ብቻ አልተወሰነም። ወደእሷ ያቀረበው ዋንኛ ምክንያት ከነበረችበት ክፍል ወደ ራሱ የፖሊስ ሰራዊት ለመውሰድ ማግባባት ነበር። በዘመኑ የምድር ጦርና የፖሊስ ሰራዊት የሙዚቃ ክፍሎች በዘመኑ በስራዎቻቸው የሚፎካከሩ ዝነኞች ነበሩ። ሂሩት የተስፋዬ ዓላማ ሲገባት በይሁንታ ለመወሰን ተቸገረች። ተስፋዬ ግን የችግሩን መላ በእጁ ይዞት ነበር። እሷን በማሳመን በመልካም ቃልና አንደበት አግባብቶ እሺታዋን ተቀበለ።
ማራኪዋ- ምርኮኛ
1953 ዓ.ም። በብሔራዊ ቲያትር የሚደረገው የአዲሱ አመት የጥበብ ፉክክር ተቃርቧል። የሙዚቃ ክፍሎች ከሌሎች በልጠው ለመታየት ጠንካራ ልምምድ ይዘዋል። ሂሩትና ተስፋዬ በቃል ተማምነው ለመጨረሻው ቀን ቀጠሮ ይዘዋል።
አሁን ሂሩት በፖሊስ የምትፈለግ ተጠርጣሪ ሆና ተፈርጃለች። ይህ ሚስጥርም ለወላጅ እናቷ ተነግሯቸው ተሰማምተዋል። ለሊቱን ሂሩት በፖሊስ ልዩ ፓትሮል፣ መሳሪያ ባነገቱ ወታደሮች ታጅባ አራተኛ ክፍለ ጦር ተወሰደች። ቀልጣፋው የዕለት ሁኔታ መዝጋቢ ሚስጥረኛዋን ምርኮኛ ‹‹ባልታወቀ ወንጀል›› በሚል መዝገብ ስሟን አድምቆ አሰፈረ። ይህ ቅድመ ሁኔታ እንዳበቃ ተስፋዬና አጋሮች አልዘገዩም። ወደቀጣዩ ርምጃ ፈጠኑ።
ኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ የደረሰችው ተጠላፊዋ ቀድሞ የተዘጋጀላት የመኮንኖች ክበብ መዋያ ማደሪያዋ ሆነ። ይህ ስፍራ ከእሷ በኋላ ኒልሰን ማንዴላ በእንግድነት ያረፉበት ታሪካዊ ቦታ ነው። ሂሩት በልዩ ኮማንዶዎች ቀን ከሌት እየተጠበቀች ቆየች። ቀናቶቿ በዋዛ አልባከኑም። በሚስጥር ቤቱ በኦርኬስትራ ታጅባ አዲስ ግጥምና ዜማዎችን ማጥናት ያዘች።
የአዲስ ዓመት ዋዜማ
እነሆ ! አይቀሬዋ ተናፋቂ ቀን ደርሳለች። በዕለተ ጳጉሜ አምስት ተፎካካሪዎቹ የሙዚቃ ክፍሎች በአዳዲስ ስራዎቻቸው ይታያሉ። አሁን የለችም፣ ጠፍታለች የተባለችው ሂሩት በቀለ በመድረክ ተከስታ ለአድናቂዎቿ ልትገለጥ ነው።
ጊዜው ሲደርስ ይህን እውነት ማስተናገዱ ቀላል አልሆነም። እሷ እንደሌሎች ሙዚቀኞች ነጻነቱ የላትም። ሂሩት በግልጽ ከምትታይ ከታዳሚው ጋር በአጃቢዎች እንድትገባ ተወሰነ። ከቆይታ በኋላ በጉጉት የሚጠበቀው የአዲሱ ዓመት ሙዚቃ ተጀመረ። ሂሩት ከሕዝቡ መሀል ተቀምጣ ተራዋ እስኪደርስ ትጠብቃለች።
በድንገት አስተዋዋቂው ሻለቃ ወርቅነህ ስሟን ጠርቶ፣ ዝናዋን አወድሶ ወደመድረኩ ጋበዛት። ተጋባዥ እንግዳው ድንጋጤ በሚመስል ስሜት በዝምታ ተዋጠ። ሂሩት ከመድረኩ ተገኝታ ‹‹ፍቅር የሰላም አክሊል ነች›› የሚለውን ዜማ አንጎራጎረች። ቀጥሎ ሌላውን ሙዚቃ አከለች። መድረኩ በጋለ ጭብጨባና አድናቆት አስተጋባ።
ሂሩት ለፖሊስ ሰራዊት መጫወቷን ያረጋገጡ የምድር ጦር አባላት ቁጣ ነደደ። ይህ ስሜት ተቀጣጥሎም ለሌላ ርምጃ አነሳሳ። የታጠቁት ሀይሎች ከመደረኩ ጀርባ አድፍጠው ይጠብቋት ያዙ። ይህ እውነታ ሲረጋገጥ የቲያትር ቤቱ መብራት እንዲጠፋ ተደረገ። በዚህ መሀል ሂሩት በታዳሚውና በፖሊሶች ታጅባ ከአካባቢው ተሰወረች።
ደማቅ እውቅና በፖሊስ የሙዚቃ ክፍል
ሂሩት ከቀድሞ የሙያ ቤቷ ከምድር ጦር የሙዚቃ ክፍል ወጥታ የፖሊስ ሰራዊትን ከተቀላቀለች በኋላ ስሟን የሚያደምቅ፣ እውቅና ከእሷ ሆነ። ከ1958 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አብዮቱ ፍንዳታ የምትጫወታቸው ዜማዎች የማግኘት ማጣትን፣ የፍቅር ክህደትን፣ የሀገር ፍቅርና የጀግንነት ወኔን የሚያንጸባርቁ ነበሩ። እንዲህ መሆኑ ለብዙዎች ስሜት የቀረበ ሆኖ እውቅናዋን አሳደገው።
ሂሩት በቀለ ከለውጡ በፊትና በኋላ ወደ ውጭ አገራት በመሄድ ስራዎቿን አቀረበች። ኮንጎ ከሰራዊቱ ጋር በመዝመትም ድንቅ ችሎታዋን አሳየች። በሱዳን ግብጽና በሶሻሊስት ሀገራት የነበራት የመድረክ ቆይታ ዝናዋን አጉልቶ ክብርን አጎናጸፋት። ሂሩት በአገራዊ ሙዚቃዎቿ አይረሴ የሆኑ ጠንካራ መልዕክቶችን ማስተላለፍ ችላለች። በተለይ በአድናቂዎቿ ዘንድ እንደ ሕዝብ መዝሙር በጎ ተጽዕኖ ያሳደረው ‹‹ኢትዮጵያ›› የተሰኘው ዜማ የብዙዎችን ስሜት ሰቅዞ እንደያዘ ዓመታትን አስቆጥሯል። ሌሎች ዘመኑን የዋጁ ዘፈኖችም ከአይረሴ ትዝታዎቻቸው ጋር እስከዛሬ ዘልቀዋል። ሂሩት ተደምጠውና ተመዘው በማያልቁ ማህበራዊና አገራዊ ዜማዎቿ አድናቂዎቿን አዝናንታለች አስተምራለች።
ከአገራዊ ሙዚቃዎች
ኢትዮጵያ ሀገሬ …
ኢትዮጵያ… ሀገሬ !
ኢትዮጵያ… ሀገሬ !
መመኪያዬ … ነሽ ክብሬ ።
በጣም ያኮራኛል- ኢትዮጵያዊነቴ ፣
የሐገሬ ፍቅር – ጠልቆ በስሜቴ።
አንች የነጻነት ጎህ -የታሪክ አውድማ፣
በዓለም ተሰራጭቶ -ዝናሽ የተሰማ።
ዘሟል ጎራዴው…
ስጡት ለዛ ጀግና – ጎራዴ ስላችሁ፣
ደጋግሞ ድል ማድረግ – ልምዱንም አውቃችሁ፣
ውርደት አከናንቦ- ጠላቱን የሸኘው፣
የሀገሬ ጀግና አልበገር ባይ ነው።
ዘሟል ጎራዴው!
ጉሮ ወሸባ …
ወሸባዬ ጉሮ ወሸባ ወሸባ ፣
ታጋይ ድል አርጎ ሲገባ።
በምሥራቅ በሰሜን፣
ጉሮ ወሻባ
ድልን ተጎናጽፎ ፣
ጉሮ ወሸባ
የገሩን ጠላት፣
ጉሮ ወሸባ
በወኔ አርግፎ ።
በደሙ ጠብታ አኩሪ ታሪክ ጽፏል
ጉሮ ወሸባ
ጀግናው በጠላት ላይ።
ከማህበራዊ ዜማዎች
ወዳጅ ዘመዶቼ…
ወዳጅ ዘመዶቼ የምትወለዱኝ፣
ስሞት ብቻ አይደለም በቁሜ ሳትረዱኝ።
ከዘመዶቼ ቤት ሲበላ ስጠጣ፣
እኔ ተቸግሬ የሚያስበኝ ሳጣ።
በሕይወት መተያያት ነበር በቁመና፣
አሁን በመሞቴ ባታለቅሱ ምነው፡
ባታውቁት ነው እንጂ የሞትኩት ቆሜ ነው።
ሕይወት እንደሸክላ..
ዕድሜ መገስገሱን ከንቱ ሰው ዘንግቶት፣
ነገ አልፎልኝ ይላል ማለፉን ዘንግቶት።
አይቀር መንፈራገጥ ያ ሆድ እስኪሞላ፣
ወድቃ እስክትሰበር ሕይወት እንደ ሸክላ።
ጣራና ግድግዳው በወርቅ ቢሰራ፣
ገንዘብ ተቆልሎ ቢመስል ተራራ።
በከፋው ጨለማ በዛ በሞት መንገድ፣
ተከትሎ አይሄድም ሀብት ሥጋ ዘመድ ።
ከፍቅር ዘፈኖች
እንደገበቴ ውሀ…
እንደ ገበቴ ውሀ- ዓይኔ ይዋልላል፣
አንተን ያጣሁኝለት ሆዴ ይሸበራል።
መንፈሴ ይረካል አብረኸኝ ስትውል፣
እንደማልሰለችህ አድርጎኛል አድርጎኛል ፍቅርህ።
ያ. ማለፊያው ዓይንህ…
ያ ማለፊያው ዓይንህ- እንዴት ሆኖ ይሆን፣
ሄጄም እንዳላየው እንዳሰብኩት አይሆን።
አውድማው ይለቅለቅ ይሰጣበት ነዶ፣
ታየኝ ያ ጉብል ልጅ ብቅ ሲል ከማዶ።
ዓይን አይችልም…
ዓይን አይችልም- አትዩት፣
ጸባዩ ነው- አትንኩት፣
እሱ ከኔ በቀር- የለውም መድኃኒት።
እንግዲህ ጀመረ ሆዴ መላ ሊያጣ፣
ጀንበሯ ስትጠልቅ ጨረቃ ስትወጣ።
ይመጣል ፈገግታህ ምሽቱን ተላብሶ፣
ዕንቅልፍ ሊያሳጣኝ ሀሳብ አንተርሶ።
እሱ ልጅ የኔ ነው…
ቤቱ ቤቴ በላይ- ቅርብ ለቅርብ ነው፣
መልኩ ዳማ መሳይ ዓይኑ የሚስበው፣
ዘለግላጋ ሀረግ ቀንበጥ አካል ያለው፣
አሳ መሳይ ጉብል እሱ ልጅ የኔ ነው።
ሂሩት በቀለ ከተለያዩ ወንድ ድምጻውያን ጋር በጥምረት በማዜም ጭምር ትታወቃለች። ከ1949 ዓ.ም ጀምሮ በፖሊስ ሰራዊት የሙዚቃ ክፍል ስራዋን የጀመረችው ሂሩት ከ1950ዎቹ አንስቶ እስከ 1980ዎቹ መጀመሪያ ድረስ በሙያዋ እንደተወደደች ዘልቃለች።
ከነዚህ ዓመታት በኋላ ሂሩት የሙዚቃውን ዓለም በመተው መንፈሳዊው ሕይወትን ተቀበለች። በዕምነቷ ዘማሪና አገልጋይ በመሆንም ቀጠለች። ከሰላሳ ዓመታት በላይ ሙዚቃውን ሙሉ በሙሉ አርግፍ አድርጋ ብትተውም መልካም አንደበቷ ተወዳጅ መዝሙሮችን ከማፍለቅ አልታቀቡም። የተለያዩ ሶስት የዝማሬ አልበሞችን ለማውጣት ችላለች።
አንጋፋዋ ድምጻዊት ሂሩት በቀለ በሀገራችን ከሚታወቁት ሴት ድምፃውያን መካከል በዋንኛነት ትጠቀሳለች። ሂሩት በሰላሳ አምስት ዓመታት የሙያ ቆይታዋ ከ200 በላይ ሙዚቃዎችን ተጫውታለች። ከእነዚህ መካከልም ሰላሳ ስምንቱ በሸክላ፣ አስራ አራቱ ደግሞ በካሴት የታተሙ ናቸው።
የድምፃዊትና ዘማሪቷ የሕይወት ታሪክ እንደሚያስረዳው ሂሩት የሰባት ልጆች እናት፣ የአስር ልጆች አያት፣ የሰባት ልጆች ቅድመ አያት ሆናለች። አንጋፋዋ፣ ተወዳጇ፣ ታዋቂዋ ሂሩት በቀለ ከሙዚቃው ዓለም ለዓመታት ብትርቅም ከአድናቂዎቿ ልቦና ፈጽሞ ያልተፋቀች ተጽዕኖ ፈጣሪ ከያኔ ሆና ዘልቃለች።
ስንብት
ሂሩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባደረባት ህመም በህክምና ስትረዳ ቆይታ ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም በተወለደች በ80 ዓመቷ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች። የአንጋፋዋ ድምፃዊት አስከሬን በሀገር ፍቅር ቲያትር የክብር ሽኝት ከተደረገላት በኋላ የቀብር ሥነ ስርአቷ ወዳጅ ዘመዶቿ፣ አድናቂዎቿ፣ የሙያ አጋሮቿ በተገኙበት ግንቦት 7 ቀን 2015 ዓ.ም በጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር ተፈጽሟል።
ሂሩት በቀለ በዘመን አይሽሬ ድንቅና ወርቃማ ሙዚቃዎቿ ትውልድ ሲዘክራትና ሲያስታውሳት ይኖራል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2015