
የኢትዮጵያን ስፖርት በሁሉም ረገድ በሚገባው ልክ እንዳያድግ እግር ከወርች ያሰሩት ችግሮች ብዙ ናቸው። ከነዚህ ችግሮች አንዱ በ1990 ዓ.ም ፀድቆ ተግባር ላይ የዋለው ብሔራዊ የስፖርት ፖሊሲ ይገኝበታል። ይህም ለሀገሪቱ ስፖርት ስብራት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይታመናል።
የስፖርት ፖሊሲው በራሱ የተለያዩ ችግሮች እንዳሉበት በተደጋጋሚ ትችቶች ሲሰነዘሩ የቆየ ሲሆን፣ አተገባበሩም ብዙ ውስብስብ ችግሮች እንዳሉበት ዘርፉን በሚመራው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጭምር የታመነበት ነው። ለዚህም የስፖርት ፖሊሲ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ በባለድርሻ አካላት ውይይት ሲደረግበት ቆይቷል።
ባለፈው ቅዳሜ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዘጋጅነት በባሕርዳር ስታድየም “ስፖርት ለአሸናፊ ሀገር” በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ “የስፖርት ስብራቶችን ለማከም ምን እየተሠራ ነው?” በሚል ሃሳብ ላይ ባቀረቡት ሰነድ የዘርፉ ምሑራን፣ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ጥናት መደረጉን ገልጸዋል። በጥናቱም መሠረት የስፖርቱ መሠረታዊ ችግሮች ተብለው ከተለዩ ሦስት ዓበይት ጉዳዮች አንዱ ከፖሊሲ ጋር የተያያዘ ጉዳይ መሆኑ ጠቁመዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ፣ ባለፉት ሦስት አስርተ ዓመታት ገደማ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲሠራበት የቆየው ብሔራዊ የስፖርት ፖሊሲ ከወቅቱ ጋር አይሄድም። አተገባበሩ ላይም ተናቦ የመሥራት ችግር አለ። ስለዚህም አሁን ላይ ፖሊሲውን ማሻሻል ወይም መቀየር ግድ ይላል። ለዚህም ፖሊሲውን ለመቀየር ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ውስጥም የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ከፀደቀ በኋላ ወደ ተግባር የሚገባ ይሆናል።
ከፖሊሲ ማሻሻያው በተጨማሪ የስፖርቱን ስብራቶች ለመጠገን በመጀመሪያ የገጠመውን የእይታ ችግር ለመፍታት ሰፊ ሥራ በመሥራት ከለውጡ ወዲህ ትልቅ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ሚኒስትር ዴኤታው ያስረዳሉ። ስፖርቱን የልማት መሣሪያ ለማድረግ ሰፊ ጥረት በማድረግ፣ በዘርፉ ገቢን ለማሳደግ፣ የተለያዩ ሥልጠናዎች እየተሰጡ እንደሆነና ከፖሊሲ ጋር የተያያዙ ስብራቶችን ለመጠገን የሚደረገው ዝግጅትም የለውጡ አንድ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዚሁ ከፖሊሲው ጋር ተያያዥነት ያለው የአሠራር ሥርዓት ችግር ለስፖርቱ ስብራት አንዱ ምክንያት መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በተለይም ከላይ እስከ ታችኛው መዋቅር ባሉ መንግሥታዊና ሕዝባዊ አደረጃጀቶች መሠረታዊ ችግሮች እንዳሉ አስረድተዋል። ለዚህም ብዙ የስፖርት አካዳሚና የሥልጠና ማዕከል ቢኖርም በጋራ አሸናፊ ሀገር ለመገንባት ተቀናጅተው የመሥራት ችግር መኖሩ አንዱ ማሳያ አድርገው አቅርበዋል።
መዋቅራዊ ጉዳዮች የስፖርቱ ስብራት ምክንያት ተብለው በጥናት ከተለዩ ነጥቦች አንዱ ሲሆን፣ ይህም ስፖርቱን የምንመለከትበት አስተያየት ሲሆን፣ ስፖርትን ውድድር ብቻ አድርጎ የመቁጠር ችግር እንዳለ ያረጋገጠ ነው። ሚኒስትር ዴኤታው ይህን በዝርዝር ሲያስረዱ ስፖርት ለሰላም፣ ለአንድነት ወዘተ ብሎ ከውድድር ባሻገር ከፍ አድርጎ የመመልከት ብሎም የመሥራት ችግር መኖሩን አመልክተዋል። ይህን ችግር ለመፍታትም ከኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጀምሮ በካቢኔ ደረጃ ለስፖርት ትልቅ ትኩረት እንዲሰጥ አጀንዳ እስከማድረግ ድረስ እየተሠራ እንደሚገኝና ስፖርት ከውድድር ባሻገር የወንድማማችነትና አብሮነትን ትርክት እንዲያሰርፅ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ገልፀዋል።
ማሻሻያ እየተደረገበት የሚገኘው ብሔራዊ የስፖርት ፖሊሲ በዚህ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ በፖሊሲው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና ከተጠሪ ተቋማቱ ስፖርት ባለሙያዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል። በዚህም የሚሻሻለው የስፖርት ፖሊሲና ረቂቅ አዋጅ የሀገሪቱን ስፖርት አሁን ካለበት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ በማድረግ የኅብረተሰቡን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ማዘመን እንደሚገባው አቅጣጫ ሰጥተዋል። በሚሻሻለው የስፖርት ፖሊሲና ረቂቅ አዋጅ ላይ በስፖርት ባለሙያዎች የተነሱ ሃሳቦች ለፖሊሲው ፅናት መሠረት በመሆናቸው በግብዓትነት ተወስደው የስፖርት ፖሊሲው አካል ሆነው እንደሚፀድቁም አክለው ገልፀው ነበር።
በቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 3 ቀን 2017 ዓ.ም