ሰማይ የአህያ ሆድ ሲመስል ከመኝታው እየተነሳ ሲጮክ የከረመው ወፈፌው ይልቃል አዲሴ፣ ዛሬ ላይ ደግሞ ሰዓቱን ቀይሮ የሰፈራችን ሰዎች “ከበተስኪያን” ሲመለሱ ያለውን ሰዓት መርጦ በተለመደው ቦታው ተከስቷል። ዛሬም ላብ ላብ እስከሚለው ይጮሃል። ጩኸቱን የሰማ የሰፈራችንና የእድራችን ሰዎች ከህጻን እስከአዋቂ አንድም ሳይቀር ዋርካው ሰር ተገኙ።
ሰዎች በመሰብሰብ ላይ እያሉ ይልቃል አዲሴም…
‹‹አስበን እንስራ ለነገም እንዲሆን፣
ይሁን ይሁን ብለን የማይሆን እንዳይሆን።
አለ የአንዳርጌ መስፍን»
እያለ በባለፈው ስብሰባ የተናገረውን ግጥም ደጋግሞ ያምቧርቅ ነበር። የሰፈራችን ሰዎች ወደ ዋርካው ተሰባስበው ቦታቸውን መያዛቸውን ከተመለከተ በኋላ ይልቃል አዲሴ፣ ራሱን ለንግግር እያዘጋጀ እህ..እህ… ብሎ ጉሮሮውን ጠራረገ። ንግሩንም እንዲህ ሲል ጀመረ፤ …በሰፈራችንና በእድራችን ለሚስተዋለው ጽንፈኝነት (Extremism) እንዲሁም ትምክህተኝነት (CHAUVINISIM) አብይ ምክንያት ከፈረንጅ ሀገር ያመጣናቸውን የፖለቲካ ቃላትና ጽንሰ ሀሳቦቻቸውን በቅጡ ካለመረዳት የመነጨ ነው።
በነገራችን ላይ የእኛ ሰፈርና እድር ሰዎች የፖለቲካ ቃላትን ጽንሰ ሃሳብ ካለመረዳት ባለፈ በፈረንጅ አፍ የሚጠሩ ቃላትን እንኳን በቅጡ አስተካክለው የመጥራት ችግርም በስፋት ይስተዋልባቸዋል።
ይህንን እንዲሁ በግብዝነት ያልኩ እንዳይመስልብኝ በምሳሌ ላስረዳችሁ። በእኛ ሰፈር እና እድር ተንሻፈው የሚጠሩ የፈረንጅ አፎች በጣም በርካታ ናቸው። በመሆኑም በዚህ ዝግጅት ሁሉንም ተንሻፈው የሚጠሩ ቃላትን ለመጻፍ የማይሞከር “አፍንጫን በምላስ ለመነካት” የሚደረግ ከንቱ ድካም አይነት ነው። ያም ሆነ ይህ በእኛ ሰፈር እና እድር በፈረንጅ አፍ ሚነገሩ ቃላትን እናጣምማለን የሚለው ሀሜት ብቻ እንዳይሆን የተወሰኑትን የተጣመሙ ቃላትን ጠቆም አድርጌ ባልፍ ይመረጣል።
በእኛ ሰፈር እና እድር አጣመን ከምንጠራቸው የፈረንጅ አፎች መካከል ‹‹ትሪንቡሌ›› አንደኛው ነው። የእኛ ሰፈር ሰዎች ‹‹ትሪንቡሌ›› ያሉት እኮ…. በሊቢያ ዋና ከተማ ትሪፖሊ የሰለጠነውን የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ዘመናዊ ፖሊስ ጦር ለመጥራት ነው። ባጭሩ ትሪፖሊ የሚለውን የፈረንጅ አፍ ለመጥራት ነው ትሪንቡሌ ያሉት። እስኪ እናንተ ፍረዱት ትሪፖሊ እና ትሪንቡሌ በምን ይገናኛል።
ሌላው እንደምሳሌ ማንሳት የምፈልገውና በእኛ ሰፈር ሰዎች በትክክል የማይጠራው የፈረንጅ አፍ ደግሞ በቀደሙት ጊዜያት ኢትዮጵያን ለረጅም ዘመናት ሲያገለግል የኖረውን «ኤን ስሪ (N 3)» የሚባል አንድ ተሽከርካሪ ነው። ይህን ኤን ስሪ ተሽከርካሪ የእኛ ሰፈር ሰዎች ‹‹ኤንትሪ›› እያሉ ይጠሩታል። ሁሉንም የተጣመሙ የፈረንጅ ቃላት ዘርዝሮ ለመጨረስ መሞከር ከላይ እንዳልኩት አፍጫን በምላስ ነው የሚሆነው። ስለሆነም የመጨረሻ ማሳያ የሚሆንና በእኛ ሰፈር ሰዎች ተንሻፈው ከሚጠሩ ቃላት መካከል አንዱን ልጨምርና ወደ መነሻ ሀሳቤ ልመለስ። እንደሚታወቀው በእኛ ሰፈር እና እድር ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች አስኳላ እየተባሉ ይጠራሉ። አስኳላ እያሉ የሚጠሩት ‹‹ስኩል›› የሚለውን የእንግሊዘኛ ቃል መሆኑን ስናስብ የእኛ ሰፈር ሰዎች በፈረንጅ አፍ የሚነገሩ ቃላትን በማንሻፈፍ ተወዳዳሪ እንደማይገኝላቸው እንገነዘባለን ።
የእኛ ሰፈር እና እድር ሰዎች ቃላትን አንሻፎ የመጥራት ልምዳቸው በፖለቲካውም ተጋብቶባቸው ከፈረንጅ አፍ የወሰዷቸውን የፖለቲካዊ ጽንሰ ሃሳቦችን ጭምር አንሻፈው ከመረዳት ባለፈም ለተከታዮቻቸውም ሆነ ለተማሪዎቻቸው አንሻፈው በማስተማርም ይታወቃሉ።
አሁን ላይ በሰፈራችንና በእድራችን የምንጠቀማቸው አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ጽንሰ ሐሳቦች ከፈረንጅ ትምህርት የተቀዱ ናቸው። ይሁን እንጂ ጽንሰ ሐሳቦችን ስንቀዳ ሆነ ብለን ወይም ባለማወቅ የምንሰጣቸው ትርጓሜ ጽንሰ ሃሳቦቹን ከተዋስናቸው ፈረንጆች ከሚሰጡት ትርጉም እጅጉን የተራራቀ ነው። ይህም ሰፈራችን እና እድራችን የጽንፈኞች መፈልፈያ እንዲሆን አድርጓል።
የእኛ ሰፈር ጽንፈኞች ከፈረንጅ አፍ የወሰዷቸውን የፖለቲካ ጽነሰ ሃሳቦች በራሳቸን ፍላጎት እና እውቀት ልክ ቀደው ለመስፋት የሚያደርጉት ያልተገባ መግተርተር ሳይ እድራችንን እና ሰፋራችንን ወዴት ይስዱት ይሆን? በማለት አብዝቼ እጨነቃለሁ።
ለምሳሌ በአሃዳዊነት እና በፌደራሊዝም መካከል የሚሰጡት ትርጉም ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ነው። በአሃዳዊነት እና በፌደራሊዝም መካከል የአለም ህዝብ አረዳድ እና እኛ ሰፈር ተጨባጭ ሁኔታ ፈጽሞ የተለያዩ ናቸው።
የእኛ ሰፈር ሰዎች ፌደራሊዝም የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ በራሱ ብሔር፣ ብሄረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ በራስ ቋንቋ የመማር፣ በራስ ቋንቋ የመዳኘት፣ በራስ ቋንቋ የመናገር መብትን እንደሚያጎናጽፍ እና አሃዳዊነት ደግሞ ብሔር፣ ብሄረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ በራስ ቋንቋ የመማር፣ በራስ ቋንቋ የመዳኘት፣ በራስ ቋንቋ የመናገር መብታቸውን የሚደፈጥጥ አድርገው ሲናገሩ ይሰማሉ። ይህ ትክክል አይደለም! ይህን ስል ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር ለሰፈራችን እና እድራችን አይበጅም ማለቴ አይደለም። አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር ለሰፈራችንም ሆነ ለአገራችን ትክክለኛ አማራጭ መሆኑን ዘንግቸው አይደለም። ነገር ግን ዴሞክራሲ እስከሌለ ድረስ የትኛውንም ያህል የፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር (state structure or form of government) ተግባራዊ ብናደርግ የዜጎችን በራስ ቋንቋ የመዳኘት፣ በራስ ቋንቋ የመናገር መብትን ማጎናጽፍ አይቻልም።
ለምሳሌ በአጼ ዮሐንስ አራተኛ ዘመን የነበረችው ኢትዮጵያ የፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀርን ትከተል ነበር። ነገር ግን በዘመኑ የነበረው የመንግስት አይነት (type of government) ንጉሳዊ (monarchical) ስለነበር እና ዴሞክራሲ እና ፍትህ የማይታሰቡበት ወቅት ስለነበር ምንም እንኳም ኢትዮጵያ የፌዴራላዊ የመንግስት አወቀቃር ብትከተል የዜጎችን በራስ ቋንቋ የመዳኘት፣ በራስ ቋንቋ የመናገር መብትን ማጎናፀፍ እንዳልቻሉ የታሪክ ድርሳናት ፍንተው አድርገው ያሳዩናል። ስለዚህ የፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀርን ላልተገባ ጥቅም የምታውሉ የሰፈራችን አፈቀላጤዎች ለሰፈራችን ስጋት ስለሆናችሁ ከድርጊታችሁ ብትቆጠቡ መልካም ነው።
ሌላው በሰፈራችን የሚገኙ አፈቀላጤዎች ከሚያንሻፍፏቸው የፈረንጅ የፖለቲካ ጽንሰ ሃሳቦ መካከል ካድሬ (CADRE) የሚለው አንደኛው ነው። በእኛ ሰፈር ይህንን የፖለቲካ ጽንሰ ሃሳብ ለገዥው ፓርቲ አመራሮች ብቻ በመስጠት እና የገዥውን ፓርቲ አመራሮች ዝቅ አድርጎ ለመመልከት ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። ይህ ትክክል አይደለም!..ካድሬ ማለት የአንድን ፓርቲ አቋም የሚያጠናክሩ፤ ሌሎችን በማስተማርና በመምራት የዜጎችን የፖለቲካል ኢኮኖሚ ንቃተ ህሊናቸውን ከፍ የሚያድርጉ፤ በስራም ሆነ በኃላፊነት ከፍ ያለ ድርሻ የሚወስዱ፤ የፓርቲያቸውን ርእዮተ አለም ጥራት የሚጠብቁ፤ የፓርቲያቸውን አባሎች ርዕዮተ አለም የሚያጠናክሩ፤ ፓርቲው በዴሞከራሲ “መርህ” እንዲደራጅ ትክክለኛውን የአመራር ፈር የሚቀዱ ሰዎች ናቸው።
በእኛ ሰፈር እና እድር ግን ለካድሬ የተሰጠው ትርጉም ፅንሰ ሀሳቡን ካመነጩት ፈረንጆች ትርጉም እጅጉን የተለየ ነው…ብሎ ይልቃል አዲሴ እየተናገረ እያለ፤ ሁሌም ሳይፈቀድለት የሚናገረው አብሿ ክንፈ ጉደታ እንደተለመደው ዛሬም የይልቃልን ንግግር አቋረጠው…
አብሿ ክንፈ ጉደታ የይልቃልን ንግግር ሙሉ በሙሉ እደሚደግፈው ገልጾ፤ ንግግሩን እንዲህ ቀጠለ… ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በእኛ ሰፈር እና እድር ከፈረንጅ የተወሰዱ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አጀንዳ የተሸከሙ ጽንሰ ሃሳቦች የተንሻፈፉ ትርጉም እንዲኖራቸው የተደረገው በሁለት አብይ ምክንያቶች ነው። አንደኛ የነዋይ እና የስልጣን ሴሰኞች ስልጣናቸውን ለማስጠበቅና የነዋይ ጥማቸውን ለማርካታ ካላቸው እኩይ ፍላጎት የመነጨ ነው።
ሁለተኛው ደግሞ የጽንሰ ሀሳቡን ትክክለኛ መልዕክት ካለመረዳት የመነጨ ነው። ይህ ሲባል በርካታ የእኛ ሰፈር እና እድር ፖለቲከኞች ነጮች ሊጠቀሙበት የፈለጉትን ቋንቋ (የፖለቲካ ጽንሰ ሀሳብ) በመሰለኝ እና በደሳለኝ ይተረጉሙታል። ይህ ደግሞ ራሳቸውን ከማጣመም አልፎ ሌሎችንም እያጣመመ ሰፈራችንን እና እድራችንን ወደአልተፈለገ አቅጣጫ እየወሰደው ይገኛል።
በእኛ ሰፈር የሚገኙ የፖለቲካ ጽንሰ ሀሳብን የሚያንሻፍፉ ሰዎች ሁነኛ አቋም የላቸውም። ለራሳቸውም ሆነ ለአገራቸው አይታመኑም። በሁለት ቢላዋ መብላትን የሚመርጡ ናቸው። ይህን ስል አንድ ገጠመኝ ልንገራችሁ… አንድ ሰውዬ ወንዝ እየተሻገረ እያለ በድንገት ደራሽ ውሃ ይመጣና ከድንጋይና ከእንጨት እያላጋ ይዞት ይሄዳል። ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ ሆኖ ጥቂት ሜትሮችን እንደተጓዘ ከወንዙ ዳር ላይ ትልቅ ጉቶ ወይም የዛፍ ስር ያገኛል። ‹‹እድል ከእኔ ጋር ነች›› ይልና የዛፉን ስር ሙጭጭ አድርጎ ይይዛል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እባክህ ፈጣሪ ከዚህ መዓት አውጣኝ እያለ ፈጣሪውን መለመን ገባ። ፈጣሪውም ለተጨነቀው ሰው በአካል ይከሰትና ‹‹አንተ በፈጣሪህ አዳኝነት ታምናለህ?›› ሲል ይጠይቀዋል። ውሃ ውስጥ የተዘፈቀው ሰውዬም ‹‹አዎ ጌታዬ!… እንዴት በፈጣሪ አዳኝነት አለማመን እችላለሁ? በደንብ ነው የማምነው›› ሲል ለፈጣሪው መለሰ። ፈጣሪውም ‹‹እንግዲያውስ በእኔ የምታምን ከሆነ የያዝከውን ጉቶ ልቀቀው›› ሲል ሰውዬውን ጠየቀው። ሰውዬውም ‹‹አይ በአንተም አምናለሁ፤ ነገር ግን ጉቶውን አለቅም›› ሲል መለስ ይባላል።
በእኛ ሰፈር ያሉ ፖለቲከኛችም እንደዚህ ሰውዬ በሁለት ቢላዋ ለመብላት የሚፈልጉ ናቸው። እውቀት ሲያጥራቸው የፖለቲካ ጽንሰ ሃሳብን በማጣመም፤ የፖለቲካ ጽንሰ ኃሳቡን እንደምንም ብለው ሲረዱ ደግሞ ያልተገባ የፖለቲካ ሸቀጥ በመነገድ ትርፍ ለማጋበስ ይሞክራሉ።
‹‹ከፖለቲካ ጽንሰ ሃሳቦችን ለጊዜአዊ ጥቅም መስጠበቂያ የሚለውን አጀንዳ ሲነሳ በደርግ ዘመነ መንግስት የተከናወነ አንድ ኩነት አስታወሰኝ›› አለና ንግግሩን ቀጠለ…
በደርግ ዘመነ መንግስት ድሬዳዋ አካባቢ በሚገኝ አንድ የወታደር ካምፕ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ የደርግ ወታደራዊ መኮንኖች ‹‹የሶሻሊዝም ንድፈ ሃሳብ መሬት ላይ ማዋል ከተፈለገ በአገራችን የሚገኙ ማናቸውም ኃይማኖቶች ዛሬውኑ ሊፈርሱና ሊጠፉ ይገባል። ከዚህ በኋላ ኃይማኖት የሚባል ነገር መኖር የለበትም›› ብለው ይነጋገራሉ። ይህን ተከትሎ የደርግ መኮንኖች መጽሐፍ ቅዱስ እና ቅዱስ ቁራንን እየሰበሰቡ ያቃጥሉ ገቡ።
በዚህ ጊዜ ነገሩ ያልተዋጠለት አንድ የደርግ መኮንን ‹‹ኃይማኖት ላይኖረን ይችላል፤ ነግር ግን ለምን መጽሐፍ ቅዱስን እና ቅዱስ ቁራንን እናቃጥላለን?›› ሲል ይጠይቃል። ይህን ተከትሎ ከወታደሮች መካከል አንድ መኮንን ተነሳና ‹‹ይህ ሰው ጽረ አብዮተኛ ነው። ከመንግስታችን የለውጥ ጎዳና በተቃራኒ የቆመ ነው። ከገንጣይ እና አስገጣይ እንዲሁም ከወንበዴዎች ተለይቶ የሚታይ አይደለም›› ሲል ተናገረ።፡
በአዳራሽ ተሰብስበው መጽሐፍ ቅዱስ እና ቅዱስ ቁራን ሲያቃጥሉ የነበሩ ሰዎች ለምን መጽሐፍ ቅዱስ እና ቅዱስ ቁራን ይቃጠላል ብሎ የሞገተውን ሰው እንዲታሰር አስፈረዱበት። አራት አመትም ታሰረ። አለመገደሉ እድለኛ ነው።
ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሊቆጣጠር ሰሞን ከአራት ዓመት የእስር ቆይታ በኋላ የእስር ፍርዱን አድርሶ ተፈታ። ኢህአዴግ አዲስ አበባን በተቆጣጠረ ጊዜም ለተሃድሶ በሚል የደርግ መኮንኖችን ጃንሜዳ ሰብስበው ወደ ሆለታ፤ በኋላም ወደ ጦላይ ወስዷቸው ነበር። በዚህ ወቅት አራት አመት የታሰረው ስውዬ እና አሳሪዎቹ ለተሃድሶ ጦላይ ተገናኙ። በጦላይም መጽሃፍ ቅዱስ እና ቅዱስ ቁራን ሲያቃጥል እና ሃይማኖት ይጥፋ ብሎ ሲናገር የነበረው ሰው በአንዴ ተገልብጦ መጽሐፍ ቅዱስን ሲሰብክ ተገኘ።
ስለሆነም ለጊዜአዊ ጥቅም ሲባል እውነታውን እያወቅን እውነትን ደፍጥጠን ሰዎችን ብናጋጭም ወደፊት እውነታው በወጣ ጊዜ ግን መሸማቀቃችን አይቀርም።
በነገራችን ላይ እንደእነዚህ አይነት ሰዎች በፖለቲካው አለም አድርባይ (OPPRTUNIST) ተብለው ይታወቃሉ። መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄ እና ፍላጎት በጊዜያዊ ጥቅም በመለወጥ ከዋናው የፖለቲካ መስመር መውጣትና ትግሉን ማጨናገፍ አድርባይ (OPPRTUNIST) ይባላል። የፖለቲካ ልሂቃን እንደሚሉት፤ አድርባዮች የህዝብን ትግል ለማጨናገፍ አንድም ግዜው ከሚፈለገው ነገር እጅጉን ወደኋላ ይቀራሉ። በሌላ በኩልም ደግሞ ህዝብን ለማዋናበድ እንዲመቻው ጊዜው ከሚፈልገው ሁኔታ እጅጉን ቀድመው ይሄዳሉ…ብሎ ንግግሩን ጨርሶ ወደመቀመጫው ሲቀመጥ ወፈፌው ይልቃል አዲሴም ንግግሩን ከአቆመበት ቀጥለ…..
ሁሉም ሰው ዝም የሚለውና የሚታገሰው እስከሚሰለቸው ብቻ ነው። አሁን ላይ በአሻጥረኛ ፖለቲከኞች ላይ ትዕግስታችን አልቋል! መታገስ ከማንችልበት ደረጃ እየደረስን ነው። እናንተ እንወክላችኋለን በምትሉት ህዝብ ላይ አያሌ አሻጥሮችን እየሰራችሁ እያወቅን እንዳላወቅን፤ እየሰማን እንዳልሰማን ዝም ብለን እንድትኖሩ ስንፈቅዳላችሁ ስለምን እንናንተ እኛን በጎሳ አቧድናችሁ እያደባደባችሁ እንዳንኖር ለምን ታደርጋላችሁ? አሁንስ አበዛችሁት። ሁሌ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ህሙማን በሚያስነሱት ችግር የሚጎዱት የሰፈራችን እና የእድራችን ሰዎች ናቸው። እኛ እናንተ አሻጥረኞች በምትፈጥሩት የፖለቲካ አሻጥር ትክሻችን ጎብጧል! ምናልባትም ወደፊት ምንም የፖለቲካ ፓርቲ የማንፈልግበት ደረጃ እንድንደርስ እያደረጋችሁን ይመስለናል። ‹‹በቃ እኛን ተውን!›› አለ በብስጭት።
ወፈፌው ይልቃል አዲሴ፣ ግንባሩን ቁጥር ፈታ እያደረገ ንግሩን ቀጠለ፤ አልፍሬድ ኖቤል መጀመሪያ ደማሚትን ሲሳራ የሰውን ልጅ የሚያጠፋውን ፈንጅ ለመስራት አስቦ አልነበረም። የፈረንጅ ፖለቲከኞች እና ፈላስፎችም የተለያዩ የፖለቲካ ንድፈ ሃሳቦችን ሲያፈልቁ የአለምን ህዝብ ካልተገባ አገዛዝ ለማዳን እንጂ ህዝብን ለመጨቆን አስበው አልነበረም። ነገር ግን የአልፍሬድ ኖቤልን ደማሚት የሰው ልጅ ለማጥፋት በፈንጅነት እንደተጠቀመው ሁሉ የፖለቲካ እና የፍልስፍና ሊቃውንትን አስተሳስብ አጣምማችሁ ለአልተገባ ጥቅም እያዋላች ያላችሁ የስልጣን እና የገንዘብ ሴሰኞች ወይም በሽተኞች ከስራችሁ ብትቆጠቡ ጥሩ ነው።
ለእናንተ ፖለቲካ ማለት ለጊዜያዊ ጥቅም ብሎ ህዝብን ከህዝብ ማናከስ ነው እንዴ? ለእናንተ ፖለቲካ ማለት እንወክለዋለን በምትሉት ህዝብ ደም የራሳችሁን ኪስ ማድለብ ነው እንዴ? አሁን አሁን በእናንተ የተነሳ የፖለቲካን ትርጉም ምን እንደሆነ ለመገንዘብ እየተቸገርን ነው ።
ዳኛ ከሌለ ጠበቃ እና አቃቢ ህግ ኖረ አልኖረ ምን ትርጉም አለው? ሀገር እና ህዝብ ከሌለ ፖለቲከኛ ኖሩ አልኖሩ ምን ትርጉም ይኖረዋል። ስለዚህ ከምትሰሩት እኩይ ስራችሁ ብትመለሱ ጥቅሙ ለእናንተው ነው።
በ1950ዎቹ በሀገረ ሲውዘርላንድ ሁሉም ዜጋ ለ24 ሰዓት የሙቅ ውሃ አገልግሎት ያገኝ ነበር። ያለን የተፈጥሮ ሃብት ከሲውዘርላንድ የትና የት እጥፍ ነበር። ይሁን እንጂ በፖለቲካ ሴሰኞች ሴራ ይኸው መኖር እንዳንችል እየሆን ነው። አሻጥረኛ ፖለቲከኞቻችን ከውጭ አገር የፖለቲካ ንድፈ ሃሳብ በአካፋ እየጋፋችሁ ስታመጡ ምን አለበት ከፈረንጆች ስልጣኔ በማንኪያ ብታቀምሱን? ብሎ ንግግሩን ሲጨርስ የሰፈራችን ሰዎችም ለይልቃል ያላቸውን አድናቆት በጭብጨባ ገልጸው ስብሰባው ተበተነ።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2015