ሰሞኑን አንኳር ጉዳይ ሆነው በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ እየተነሱ ካሉ ጉዳዮች መካከል አንደኛው የግል ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ክፍያ ጭማሪን የተመለከተ ነው። ጭማሪው ላይ ከሚመለከታቸው ተቋማት አንዱ የአዲስ አበባ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ነው። በመሆኑም ጭማሪውን እና በአጠቃላይ የትምህርት ጥራትን እንዲሁም በሌሎችም ከተቋሙ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ ከባለስልጣኑ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጇ ወይዘሮ ፍቅርተ አበራ ጋር ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- የአዲስ አበባ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን እያከናወነ ያለው ስራ ምን ምንድን ነው?
ወይዘሮ ፍቅርተ፡- ባለስልጣኑ በአዋጅ 74/2007 ዓ.ም ሲቋቋም ዓላማው በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ያለውን ትምህርት እና ስልጠና ጥራት ለመቆጣጠር ነው። ይህ ማለት አጠቃላይ ትምህርትም የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማትም በአጠቃላይ የሚሰጡት ትምህርት ጥራቱን የጠበቀ ስለመሆኑ መቆጣጠር የባለስልጣኑ ሥራ ነው። በትምህርት እና በስልጠና ዙሪያ በፍትሃዊ መልኩ መዳረስን በተመለከተ የአጠቃላይ ትምህርቱ የሚመለከተው አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮን ነው። የቴክኒክና ሙያዎችን ደግሞ የቴክኒክና ሙያ ቢሮ የሚሠራው ነው። የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ግን በአጠቃላይ ሁሉም የሚሠጡት ትምህርትም ሆነ ስልጠና ጥራቱን የጠበቀ መሆኑን የሚለውን ያያል። የሚሰጡት ስልጠና ጥራቱን የጠበቀ መሆኑን ደግሞ የምናረጋግጥበት የራሱ መለኪያ አለው።
ጥራቱን የምንለካው የመንግስቶቹን ብቻ ሳይሆን የግል የትምህርት እና ስልጠና ተቋማትን ጭምር ያካተተ ነው። ለግል ተቋማት ሲሆን ደግሞ በአጠቃላይ ትምህርት የዕውቅና ፈቃድ ይሰጣል። ለቴክኒክና ሙያው ደግሞ ለመንግስትም ለግልም የዕውቅና ፍቃድ ይሰጣል። ስለዚህ አንዱ ጥራትን የምንቆጣጠረው በዕውቅና ፈቃድ ነው። ስለዚህ አንዱ ጥራትን የምንቆጣጠረው በዚህ መንገድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የጥራት ቁጥጥሩ አጠቃላይ ትምህርት ላይ ሲሉ ምን ማለት ነው? ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ ማለት ነው ወይስ ከ1ኛ ክፍል ጀምሮ?
ወይዘሮ ፍቅርተ፡- ከቅድመ መደበኛ እስከ ደረጃ አምስት (ሌቭል 5) ድረስ የግልም የመንግስትንም ጨምሮ ነው። አጠቃላይ ትምህርት የምንለው ቅድመ መደበኛ፣ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን አጠቃልሎ ነው። በቴክኒክና ሙያ ደግሞ በየአንዳንዷ የሙያ ብቃት አሃድ እስከ ደረጃ አምስት ድረስ ያሉትን ዕውቅና ፍቃድ ይሰጣል። ዕውቅና ፍቃድ ሲሰራ አንደኛ የሚታየው ግብአት ነው። የተቋም ግብአት ሲባል ቁሳቁስ ሳይሆን የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ መሠረተ ልማት እና ተቋሙ ለመማር ማስተማር እንዲሁም ለስልጠና ምን ያህል ዝግጁ ነው? የሚለውም ጭምር ይታያል።
አንድ ተቋም ዕውቅና ከተሰጠው በኋላም በቂ አይደለም። ተቋሙ ዕውቅና ከተሰጠው በኋላም በደንብ አሰለጠነ ማለት ስላልሆነ ከሁለት ዓመት በኋላ የቁጥጥር ሥራ ይከናወናል። አጠቃላይ የጥራት ደረጃ ፍረጃ ይደረጋል። በአጠቃላይ በፌዴራል ደረጃ የቁጥጥር ማዕቀፍ አለ። በቁጥጥር ማዕቀፉ መሠረት መለኪያ አለ፤ በመለኪያው መሠረት የማረጋገጥ ሥራ ይከናወናል። ይህ በየትኛውም ከቅድመ አንደኛ እስከ ኮሌጅ ድረስ ያለውን የሚይዝ ነው።
የጥራት ደረጃው ከላይ በገለፅኳቸው ግብአቶች የሰውም የቁሳቁስም ያንን ተጠቅሞ ደግሞ የሚያከናውነው ስልጠና እና ከስልጠና በኋላ የተማሪው እና የሰልጣኙ ውጤታማነት ይታያል። ስለዚህ የቁጥጥር ሥራ እናከናውናለን። አንዱ ጥራትን የምንለካበት በደረጃ ነው። አንድ ተቋም ደረጃ አንድ ከሆነ ከደረጃ በታች ነው። ማሰልጠንም ሆነ ማስተማር የማይችል፤ በቂ ግብአት የሌለው እና በተገቢው መንገድ የማያስተምር እና ውጤታማ ዜጋን የማያፈራ ማለት ነው። ደረጃ ሁለት የሚባለው ደግሞ በመሻሻል ላይ ያለ፤ ነገር ግን ክፍተቶች ያሉበት ሊስተካከል የሚችል ማለት ነው።
ደረጃ ሶስት ደረጃውን ያሟላ ሲሆን፤ ደረጃ አራት ደግሞ በአገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃ በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል ማለት ነው። ስለዚህ አዲስ አበባ ላይ በአራቱም ደረጃዎች ተቋሞች አሉን። አዲስ አበባ ላይ ደረጃ አንድ የሚባሉ ኤቢኢ ሴንተር የሚባሉ፤ አማራጭ መሠረታዊ ትምህርት አለ። ቀንም ማታም መማር የማይችሉ በቀን ውስጥ ሁለት እና ሶስት ሰዓት ብቻ የሚማሩ በተለያዩ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ሰዎች የሚማሩበት ነው። እነዚህ መሠረታዊውን ትምህርት የሚማሩ ሲሆን፤ በመደበኛው ፕሮግራም ላይ ተለጥፈው የሚማሩ ናቸው።
‹‹ኦ ክላስ›› ወይም 0 ክፍል የሚባሉ አሉ። ‹‹ኦ ክላስ›› የሚባሉት ደግሞ አንደኛ ክፍል ከመግባታቸው በፊት ኬጂ ወይም ቅድመ አንደኛ ላይ ክፍተት ስላለብን እዛ መግባት ያልቻሉ ቢያንስ ስድስት ዓመት የሆነው ልጅ አንደኛ ክፍል ከመግባቱ በፊት መሠረታዊ ዕውቀትን አውቆ እንዲገባ የምናስተምርበት ሞዳሊቲ ነው።
እነዚህ ተቋሞች ከቅድመ አንደኛ ላይ እንዳሉት በቂ መጫወቻ እና ማሸለቢያን የመሳሰሉ ግብቶች የሏቸውም። ስለዚህ ብዙዎቹ ‹‹ኦ ክላሶች›› ደረጃ አንድን እንኳ የማያሟሉ ናቸው። ነገር ግን ከምንም ስለሚሻል ሰባት ዓመት የሞላው ልጅ አንደኛ ክፍል ከመግባቱ በፊት በእነኚህ ‹‹ኦ ክላሶች›› አልፎ መሰረታዊ የሆነ ዕውቀት ማንበብን፣ ከጓደኞቹ ጋር ግንኙነት መፍጠርን ይዞ የሚገባበት ሲሆን ደረጃ አንድ ይህ ደረጃ ነው።
ብዙዎቹ አዲስ አበባ ላይ ያሉት ደረጃ ሁለት የሚባሉት 60 በመቶ አካባቢ ናቸው። ጥሩ እና መሻሻል የሚታይባቸው ናቸው። ነገር ግን የሚቀራቸው ነገር አለ። ሌላ የጥራት ደረጃ የሚረጋገጥባቸው አንዱ የመማር ብቃት ምዘና ነው። አንድ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ምን ያህል ዕውቀት አለው? ምን ያህል ያነባል? ምን ያህል ይፅፋል? ምን ያህል ያሰላል? ለሚለው መለኪያ መስፈርት አለን። የሶስተኛ ክፍል ተማሪም በተመሳሳይ መልኩ ይለካል።
የአራተኛ ክፍል ተማሪም የአማርኛ፣ የእንግሊዝኛም ሆነ የሒሳብ እንዲሁም የአካባቢ ሳይንስ ትምህርት ዕውቀቱ በምን ደረጃ ላይ ነው? የሚለውን የምናጠናበት መንገድ አለ። ስምንተኛ ክፍል አለ፤ በተመሳሳይ መልኩ 12ኛ ክፍልም አለ፤ አጠቃላይ አገር አቀፍ የጥራት መለኪያ አለ። ከጥራት መለኪያው ግኝት በመነሳት ዕቅድ እናዘጋጃለን። ግኝቱንም ለሚመለከተው አካል ለትምህርት ቤት ማህበረሰብ፣ ለወላጆች፣ ለትምህርት ቢሮ፣ ለሱፐርቫይዘሮች፣ ለርዕሳነ መምህራን እና ለሁሉም ይቀርባል። ከዚህ በመነሳት ማሳተካከያ እንዲያደርጉ ስለሚፈለግ አጠቃላይ ጥራትን የምንለካው በዚህ መልኩ ነው።
ሌላው የመምህራን የሙያ ብቃት ነው። መምህሩ የሚያስተምረውን ትምህርት ያውቀዋል ወይ? በትምህርቱ ምን ያህል ብቁ ነው? ዲፕሎማ አለው? የመጀመሪያ ዲግሪ አለው? ወይስ ሁለተኛ ዲግሪ አለው? የሚያስተምረውን ትምህርት በተገቢው ያውቀዋል? እንዴት እንደሚያስተምር የማስተማሪያ መንገዱን ያውቀዋል? የሚለውን ደግሞ እንዲሁ የምንለካበት አገር አቀፍ መስፈርት አለ። በዛ መሠረት እንዲሁ የመምህሩን የሙያ ብቃት እንለካለን። በእነኚህ ነገሮች የትምህርት እና የስልጠና ጥራትን እናረጋግጣለን ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በተደጋጋሚ የትምህርት ጥራት ወርዷል የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ። ለዚህ ተጨባጭ ጥናት ያስፈልገዋል። እናንተ ግን በምትሰሩት የጥራት ቁጥጥር ምን ዓይነት ውጤት አመጣን ትላላችሁ?
ወይዘሮ ፍቅርተ፡- በእኛ እምነት የትምህርት ጥራት በከተማ ደረጃ እያደገ ነው የሚል እምነት አለን። እኛ ቁጥጥር ማድረግ በጀመርንበት ወቅት የነበሩ ተቋሞች አሁን ደረጃቸውን አሻሽለዋል። በዛ ጊዜ በጣም ብዙ ተቋም ደረጃ አንድ ነበር። ከደረጃ አንድ ወደ ደረጃ ሁለት፣ ከሁለተኛ ደረጃ ወደ ሶስተኛ ደረጃ ብዙ መሻሻሎች አሉ። እናም የትምህርት የጥራት ደረጃ ወርዷል ማለት ትክክል አይደለም። አንዱ የጥራት ደረጃ የመምህራን የሙያ ብቃት ነው። በተለይ በመንግስት ወደ ሥራ የሚገቡ የትምህርት ተቋማት ትንሹን የትምህርት ደረጃ መስፈርት አሟልተው የሚገቡ ናቸው።
በሌላ በኩል ጥራት ስንል የተቋማት ደረጃ ነው። ጥራት ስንል የስምንተኛ ክፍል ውጤት ነው። ለምሳሌ መለኪያ በሆነው የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ባለፉት አምስት ዓመታት አዲስ አበባ በጣም አስተማማኝ በሆነ መልኩ እየተሻሻለ ነው። የጥራት መለኪያ አንዱ ይህ ነው። ተጨማሪው 12ኛ ክፍል ነው። የ12ኛ ክፍል ፈተናም ሲታይ ምንም እንኳ ቀጣይ ሥራ ቢፈልግም የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እየተቻለ ነው። ስለዚህ የጥራት ደረጃ ወርዷል ለማለት አስቸጋሪ ነው።
ጥራት ማለት አንዱ መለኪያው የሚወድቁ፣ ተማሪዎችን፣ የሚያረፍዱ ተማሪዎችን እና የሚቀሩ ተማሪዎችን መቀነስ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደግሞ በተለይ መመገብ የማይችሉ፣ የግብዓት እጥረት ያለባቸውን ልጆች መግቦም ግብአት አሟልቶም እያስተማረ ነው። ስለዚህ የትምህርት ውስጣዊ ብቃት (ኢንተርናል ኤፍሸንሲ) የምንለውን ነገርም ጭምር መንግስት ለማሟላት ጥረት እያደረገ ነው። ከጥራት አንፃር በጣም እያደጉ ያሉ ውጤቶች አሉ። ነገር ግን እንደከተማ አስተዳደር ከምንጠብቀው አንፃር ይቀራል። በሁለተኛ እና በሶስተኛ ክፍል የመማር ብቃት ምዘና በስምንተኛ ክፍልም ሆነ ከ12ኛ ክፍል ፈተና የምናያቸው ለውጦች አሉ። ከምንጠብቀው አንፃር ግን በቀጣይ ሥራ ያስፈልጋል የሚል ግምገማ አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- የዩኒቨርስቲ ተማሪው ከታች ሲመጣ በጥራት ተመዝኖ አልመጣም የሚል አስተያየት ይሰማል። ዩኒቨርስቲ ተምሮ ለስራ የሚሰማራውም ተመራቂ ለሥራው ብቁ አይደለም ሲባል ይደመጣል። የጥራት መለኪያው በራሱ ጥራትን ማረጋገጥ ይችላል? መለኪያችሁ ጥራትን ለማረጋገጥ ብቁ ነው?
ወይዘሮ ፍቅርተ፡- የጥራት መለኪያው ላይ ችግር የለም። አንድ ትምህርት ጥራት አለው ለመባል የራሱ መለኪያ መስፈርቶች አሉት። ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት አንደኛው የመምህሩ ብቃት ነው። እርሱንም በሙያ ብቃት ምዘና እያረጋገጥን ነው። በሙያ ብቃት ምዘና ከማረጋገጥ በፊት ደግሞ በትምህርት ቤት የተለያዩ ምዘናዎች አሉ። በስልጠናው በተከታይ ሙያ እድገት ማሻሻያ (ሲፒዲ) እና የመሳሰሉት መምህሩ ራሱ ራሱን የሚያበቃበት ትምህርት የሚያሻሽልበት ዲፕሎማ ከነበረ ዲግሪ እያለ ራሱን የሚያሻሽልበት መንገድ አለ።
ከተቋማት አንፃርም ደረጃ አንድ፣ ደረጃ ሁለት፣ ደረጃ ሶስት እያልን የምንመዝንበት አለ። ከተማሪዎች አንፃር የመማር ብቃት መለኪያ አለ። ችግሩ መስፈርት አይደለም። ችግሩ አንድ ዩኒቨርሲቲ ተምሮ ያጠናቀቀ ልጅ ወደ ሥራ ሲገባ ብዙ ውጤታማ አይሆንምም የሚል አስተያየት ይሰነዘራል። ይህ የሥርዓተ ትምህርት ችግር ነው። የነበረው ሥርዓተ ትምህርት በይዘት የታጨቀ እና ዕውቀት ላይ የሚያተኩር፤ ለተግባር እና ለግብረገብ ትምህርት ትኩረት ያልሰጠ፣ ለአገር በቀል ዕውቀት ትኩረት ያልሰጠ ሰፊ የሥርዓተ ትምህርት ችግሮች ነበሩብን። ስለዚህ አሁን እንደአገርም በአዲሱ የትምህርት እና ስልጠና ፖሊሲ መሠረት የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ ተደርጓል።
አዲስ አበባም አዲስ ሥርዓተ ትምህርት አዘጋጅቶ ተግባራዊ ተደርጓል። ይህ የተዘጋጀው ስርዓተ ትምህርት ልጆችን የሙያ እና ቴክኒክ ብቃት እንዲኖራቸው ያደረገ፤ ዕውቀት ላይ ብቻ ሳይሆን የተግባር ትምህርትንም እየተለማመዱ የሚመጡበት አሠራር፣ አገር በቀል ዕውቀትን እና የግብረገብ ትምህርትን እንዲሁ ታሳቢ ያደረገ፤ አገር ወዳድነትንም በተመሳሳይ ታሳቢ ያደረገ ስርዓተ ትምህርት ስላልነበረ፤ ከዛ አንፃር እንደአገር ሪፎርም ተደርጎ ስርዓተ ትምህርትም እየተስተካከለ ነው። ከዛ አንፃር መታየት ያለበት እንጂ የትምህርት ጥራት መለኪያው ችግር ያለበት አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- መምህር እና የተማሪ ጥምርታ፤ ማለትም በአንድ ትምህርት ቤት የተማሪ እና የመምህራን ቁጥር ሲተያይ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ይገለፃል። በግል ትምህርት ቤት ሳይቀር በክፍል ውስጥ የተማሪው ቁጥር እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ መምህሩ በበቂ መጠን ለማስተማር እንደሚቸገር ይነገራል። የከተማዋ የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ነው። የትምህርት ቤት ግንባታ ምን ያህል በቂ ነው?
ወይዘሮ ፍቅርተ፡- ተማሪ ክፍል ጥምርታው ላይ ችግር አለ። የተማሪ መምህር ጥምርታ ግን ብዙ ችግር የለውም። መስፈርት አለ። በተለይ በመንግስት ትምህርት ቤቶች አንድ መምህር በአማካኝ በጣም ጫና አለበት ከተባለ ከ20 እስከ 25 ክፍለ ጊዜ ይዞ ያስተምራል። በእርግጥ በአንዳንድ የትምህርት ዓይነቶች የመምህር እጥረት ያለበት መምህሩ ከፍ ያለ ክፍለ ጊዜ ሊይዝ ይችላል። በተረፈ ግን ከ20 እስከ 25 ክፍለ ጊዜን ብቻ የሚያስተምር በመሆኑ ያን ያህል ብዙ አይደለም። እንዲያውም ትርፍ ጊዜ ይኖረዋል። በዛ ትርፍ ጊዜው ደግሞ ለቀጣዩ ቀን በደንብ ይዘጋጅበታል የሚል እምነት አለኝ።
የግል ትምህርት ቤቶች አካባቢ እስከ 30 ክፍለ ጊዜ ይሔዳል። ስለዚህ የመምህር እና የተማሪ ጥምርታ ላይ ሳይሆን የተማሪ እና የክፍል ጥምርታው ላይ የተቀመጠ መለኪያ አለ። ችግሩ ይህ ነው። በመለኪያው መሰረት እየሠራን አይደለም። መለኪያው ጥራትን የሚያረጋግጥ ነው። ነገር ግን ከጥራት በፊት ተደራሽነት የሚባል ነገር አለ። ዕድሜው ለትምህርት ደርሶ ከትምህርት ቤት ውጭ የሆነ ልጅ እያለ በክፍል ውስጥ ጥምርታው 50 ነው ብለን አንገድብም። ምክንያቱ ልጆች ቅድሚያ ትምህርት ማግኘት አለባቸው። ዞሮ ዞሮ እያልን ያለነው ስለጥራት ስለሆነ እና በዚህ ዘመን ጥራት የግድ በመሆኑ እንዲሁም አዲስ አበባ ደግሞ አዲስ አበባ ከመሆኗም አንፃር ትምህርትን በጥራት ለመስጠት ብዙ የተሻሉ ሁኔታዎች አሉ።
በዋናነት ችግሩ ማስፋፊያ ክፍለ ከተማ ላይ ነው። አዲስ አበባ ከተማ ላይ ሁሉም ከመሃል ከተማ ወደ ዳር እየወጣ ነው። ያ በመሆኑ የክፍል ተማሪ ጥምርታው በአንድ ክፍል 80 እና 90 ተማሪ እየተማረ በፈረቃ እስከመማር የተደረሰበት ሁኔታ አለ። አጠቃላይ ትምህርት ደግሞ የመንግስት ግዴታም ነው። ሞላ ተብሎ የሚቆም አይደለም። መንግስት ለዜጎች ትምህርት የማዳረስ ኃላፊነት አለበት። ስለዚህ ማስፋፊያ ከተሞች ላይ የከተማ አስተዳደሩ በትኩረት ማስፋፊያ ክፍለ ከተሞች ላይ በየዓመቱ እየገነባ ነው። እንደዛም ሆኖ መልስ መስጠት አልተቻለም።
አሁን አዲስ አበባ ላይ ወደ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ተማሪ አለ። ባለፉት አምስት ዓመታት ከሶስት መቶ ሺህ በላይ ጨምሯል። ከግል ወደ መንግስትም የመዘዋወር ሁኔታ አለ። ስለዚህ የሕዝብ ቁጥሩ ስናነሳ ዕድሜው አራት ዓመት የሆነ በአዲሱ ፖሊሲ ደግሞ ዕድሜው አምስት ዓመት የሆነ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ያለው ትምህርት የሚያስፈልገው እና የተማሪው ቁጥር አይመጣጠንም። ለእዚህም ባለስልጣን ቢሮ ብቻ ሳይሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየዓመቱ የትምህርት ቤት ግንባታ ያካሂዳል።
የከተማ አስተዳደሩ ዘንድሮ ራሱ ባለአራት ወለል 24 ህንፃዎችን ማስገንባት ጀምሯል። በግልም ባለሃብቱ ወደ ትምህርት ሥራ እንዲመጣ ይጋበዛል። ነገር ግን የቦታ ችግርም በመኖሩ ባለሀብት ብዙ አይመጣም እንጂ በዓመት ወደ ሃምሳ እና ስልሳ ባለሀብት ትምህርት ቤት ለመገንባት ይመጣል። ስለዚህ ከዛ አንፃር የተማሪ እና የክፍል ጥምርታውን ወደ ስታንዳርዱ ለማምጣት በመንግስት ተቋሞቻችንም እየተሠራ፤ ለውጦችም እየመጡ ስለሆነ የግል ባለሀብቱም ወደዚህ ስርዓት እንዲመጣ ማድረግ ያስፈልጋል። የትምህርት ፈላጊው ቁጥር በተለይ አዲስ አበባ ላይ ከሁሉም አቅጣጫ የሚገባ በመሆኑ ወደ አዲስ አበባ የሚገቡትም የመማር መብት ስላላቸው ጥምርታውን በተለይ በማስፋፊያ ክፍለ ከተማ በስታንዳርዱ መሠረት ማድረግ አልተቻለም። ለሁሉም ግን ታቅዶ እየተሠራበት ነው።
አዲስ ዘመን፡- የግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ ጭማሪ ላይ ባለስልጣኑ ኃላፊነቱ እስከምን ድረስ ነው?
ወይዘሮ ፍቅርተ፡– የግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ ጭማሪን በተመለከተ የእኛ ተግባር የትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሪ የወላጆችን አቅም ያገናዘበ እንዲሆን ከተቋማት ጋር መምከር ነው። አገሪቱ የምትመራበት የኢኮኖሚ ሥርዓት አለ፤ የተቋማቱ ችግር አለ፤ የህብረተሰቡ የመክፈል አቅም ችግር አለ። እርሱን ሚዛን ጠብቀን እየሔድን ነው። በዚህ መሠረት ተቋማት የክፍያ ጭማሪ ማድረግ ሲፈልጉ ተቋማት ፕሮፖዛል ያስገባሉ። በፕሮፖዛሉ መሠረት ከወላጅ ጋር ይመክራሉ፤ ከተስማሙ ጥሩ ነው። ካልተስማሙ ደግሞ መልሰው ጉዳዩን እንዲያዩ እንዲሁም እኛ ጣልቃ እንድንገባና እንዲስተካከል እያደረግን ነው።
በዚህ ሰሞን በነበረው የክፍያ ጭማሪ አንድ ሺህ 31 የሚሆኑ ተቋማት ተስማምተዋል። 226 ተቋማት አልተግባቡም። ባለፈው ሳምንት እስከ እሁድ ድረስ በትምህርት ቤት ደረጃ አይተዋል። በቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ደረጃ አሁን ማወያየት ተጀምሯል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን እኛ ጀምረናል። እያወያየን ነው። ሁለቱም ጋር ችግር አለ። ተቋማቱ ከዋጋ ንረት አንፃር የሚነካቸው ነገር ያለ ሲሆን፤ መምህሩንም በተሻለ ደመወዝ ይዘው ማቆየት ስላለባቸው የክፍያ ማስጨመር ይፈልጋሉ። ህብረተሰቡ የመክፈል አቅሙ እየተፈተነ ቢሆንም፤ ተቋማቱም ከዋጋ ንረት አንፃር የክፍያ ጭማሪ ጥያቄ አላቸው። ይህንን ሁለቱንም ሚዛኑን ጠብቃችሁ ጨርሱ ብለናል። አልስማማ ሲሉ እኛ እየገባን እያወያየን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከ35 በመቶ ጀምሮ 130 እና 140 በመቶ የጨመሩ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ሲገለፅ ነበር፤ ጭማሪውን በልክ መወሰን አይቻልም?
ወይዘሮ ፍቅርተ፡- ትልቁ ጭማሪ 135 በመቶ ነው። እርሱም እየተነጋገሩ እየቀነሱ ነው። ባለስልጣኑም ሆነ ከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቤትን ያወያያል እንጂ የሚያዋጣህ ይህ ነው ብሎ ዋጋ አይወስንም። ነገር ግን አገልግሎት የሚሰጠው ትምህርት ቤቱ ነው። አገልግሎት የሚቀበሉት ወላጆች ናቸው። ማድረግ የሚቻለው ወላጆች እና ትምህርት ቤቱ ቁጭ ብለው እንዲወያዩ ማመቻቸት ነው። ይህ የሚደረገው ለሁሉም ሲባል ነው። ትምህርት ቤቱም ያለ አግባብ ክፍያ ጠይቆ ከሔዱበት ተቋም አይሆንም። ወላጅ ልጆቹን ይዞ ከወጣ ባዶ ይሆናል፤ አይጠቀምም። ወላጅም በተመሳሳይ ልጁን ሌላ ትምህርት ቤት ካመጣ ፈተና ስለሚሆን ተወያዩ ተግባብታችሁ ቀጥሉ እያልን ነው። በዛ ላይ አብዛኛው ተስማምቷል። ባልተስማሙት ላይ ደግሞ እኛ እየገባን ቢሆንም ዋጋ ትመና ውስጥ ግን አንገባም። ከምንከተለው ስርዓት ጋርም የሚሔድ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንዴ በመንግስትም ሆነ በግል የተለዩ ከሕዝቡ ባህል የወጡ ነገሮች በየትምህርት ቤቱ ያጋጥማሉ። የትምህርት ጥራት ቁጥጥር ሥራውን ስታከናውኑ በግልም ሆነ በመንግስት ትምህርት ቤቶች ያለውን የስነ ምግባር ሁኔታ የምትከታተሉት እንዴት ነው?
ወይዘሮ ፍቅርተ፡- የቁጥጥር ሥራው ሲሰራ አጠቃላይ የትምህርት ስርዓቱን እናረጋግጣለን። የትምህርት ተቋም ለመማር ማስተማር ምቹ ከመሆኑ አንፃር፣ መምህሩን፣ ግብአቱን፣ አደረጃጀቱን የመማር ማስተማር ሂደቱን፣ ውጤቱን እና ስነ ምግባሩንም ጭምር እናያለን። በዚያች ቁጥጥር በምናካሂድበት ወቅት የምናየው የተማሪን ስነ ምግባር የምንለካባቸው መስፈርቶች አሉ። ነገር ግን በዝርዝር ከባህል አንፃር እጅግ የወጡ ተግባራት ከተባለ የትምህርት ቢሮ የሚያየው ነው። ትምህርት ቢሮዎች ለሱፐርቪዥን ሲወጡ የሚያጋጥማቸው ነገር፣ በክፍለ ውስጥ ምልከታ የሚጋጥማቸው ነገር፣ የተማሪ ማርፈድ እና የሥነ ምግባር ብልሽቶች ሊኖሩ ይችላሉ። የተሠራው ሥራ እና ያገኙት ውጤት ይኖራል። ለዚህ ትምህርት ቢሮዎች ቢጠየቁ ይሻላል።
አዲስ ዘመን፡- በእናንተ በኩል ቁጥጥር ካደረጋችሁ በኋላ ክፍተት ስታገኙ እና ሲደጋገም ርምጃ የመውሰድ ስልጣን አላችሁ? በመጨረሻ ምን ታደርጋላችሁ?
ወይዘሮ ፍቅርተ፡– በቅድሚያ ቁጥጥር ስናደርግ ዓላማው ተቋማት እንዲሻሻሉ በመሆኑ ግኝቱ የሚሰጠው ለተቋማት ነው። በኢንስፔክሽን ወቅት በቃል ከምንሰጠው ግብረ መልስ ውጭ የተፃፈ ግብረ መልስ በእያንዳንዱ መለኪያ ተቋሙ የነበረው ጥንካሬ እና የነበረው ድክመት እንዲሁም የባለሙያ ምክረ ሃሳብ ታክሎበት ይሰጣል። መስጠት ብቻ አይደለም፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ትንተና ተካሂዶ ይቀርባል። ትንተናውን (አናሊስሱን) ተከትሎ ለከተማ አስተዳደሩ፣ ለክፍለ ከተሞች እና ለወረዳዎች ይሰጣል። ምክንያቱም የእኛ ተቋም የሚያደርገው ቁጥጥር ነው። ለምሳሌ የመምህራን ዕቅድ አስተቃቀድ ክፍተት አለበት የሚል ውጤት ከተገኘ፤ ይህንን የሚሞላው ትምህርት ቢሮ ነው።
ለትምህርት ቢሮ ግኝቱ ይገለፃል። በዛ መሠረት ያንን የዕቅዱ አካል አድርጎ እየሠራ ነው። እኛ አምና ቁጥጥር አድርገን የደረጃ ፍረጃ ካወጣን በኋላ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ይህን ያህል ተቋም ከነበረበት በዚህ ያህል አሻሽላለሁ ብሎ አቅዷል። ሌላው ክትትል እና ቁጥጥር የሚል የኢንስፔክሽን ሞዳለሊቲ አለን። አንድ ተቋም ደረጃ ከተፈረጀ በኋላ ዝም አይባልም። የተሠጠው ግብረ መልስ ዕቅድ ውስጥ ተካቷል ወይ የሚለው ይታያል። እንደሚታወቀው ክፍተቶች ሊስተካከሉ የሚችሉት ተቋሙ ክፍተቶቹን የዕቅዱ አካል አድርጎ ሲሰራበት ነው። ባለድርሻ አካላት ያንን ወስደው ከሰሩ ነው። ለምሳሌ በትምህርት ቤት አካባቢ አዋኪ ነገር ሊያጋጥም ይችላል። ማህበረሰቡ ባለድርሻ አካል ከሆነ ያንን አዋኪ ነገር ማስወገድ አለበት። ስለዚህ ሥራው የሚሠራው በአንድ ርዕሰ መምህር ብቻ አይደለም። የክትትል እና ቁጥጥር የምንለው የሚያሳየው የባለፈው ግኝት በዕቅዳቸው ውስጥ ማካተት አለማካተታቸውን የምንጠይቅበት ሥርዓት ስላለ ተቋማት ለውጥ እያመጡ ያሉት ለዚህ ነው። ነገር ግን በሚፈለገው ደረጃ ላይ አይደሉም። አሁንም ሥራ ይፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- የትምህርት ቢሮ በአግባቡ ያግዛችኋል? አብራችሁ እየሠራችሁ ነው?
ወ/ሮ ፍቅርተ፡– የጋራ የስምምነት ሰነድ አለን። በጋራ መስራት ባለብን ጉዳዮች ላይ በጋራ እንሠራለን። ለምሳሌ እኛ ደረጃ ስንፈርጅ፤ እነርሱ ደግሞ ተቋማቱ ደረጃቸውን እንዲያሳድጉ ይሠራሉ። እስከ አሁን ተናበን እየሠራን ነው። ለውጦች እየመጡ ያሉት ለዚህ ነው። ለምሳሌ አንዱ ክፍተታችን ሥርዓተ ትምህርት መተግበር ላይ ክፍተት ነበረብን። እኛም ትምህርት ቢሮም በጋራ በጥምር ኮሚቴም እየወረድን እናያለን።
አዲስ ዘመን፡- የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የኢትዮጵያ ተማሪዎች በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ምን ያህል አቅዳችሁ እየሠራችሁ ነው ?
ወይዘሮ ፍቅርተ፡– የጥራት መለኪያዎቻችን በዓለም አቀፍ ደረጃም ተቀባይነት ያላቸው እና ከፌዴራል ትምህርት ሚኒስቴር የተወሰዱ ናቸው። እንደ አገር ጥራት ተብለው የተቀመጡት ነገሮች የትም ሔደው ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸው ነው። ለምሳሌ አንድ ተቋም አለን። ሶስት ቅርንጫፎች አሉት። ዳይመንድ የሚባል ተቋም ከየትኛውም ዓለም ካለ የትምህርት ተቋም ጋር መወዳደር የሚችል ነው። ደረጃ ሶስት የምንላቸው 30 በመቶ አካባቢ ተቋማት ወደ ደረጃ አራት በማደግ የልህቀት ማዕከል እንዲሆኑ እንሰራለን። ለሌሎችም የሥልጠና ማዕከል ይሆናሉ። ሕዝባዊ ሠራዊት የሚባል ትምህርት ቤት የማንጠብቀውን ሰርተው አግኝተናል። ሥርዓተ ትምህርቱ ሲዘጋጅ ተቋሞቻችን ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ።
ወይዘሮ ፍቅርተ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2015