ከመስከረም 2013 ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት የመሩት ውበቱ አባተ ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጥያቄ አቅርበው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ የአሰልጣኙን የመልቀቂያ ጥያቄ ተቀብሎ በጋራ ስምምነት ከተለያዩ ሰነበቱ።
አሠልጣኝ ውበቱ ዋልያዎቹን በመሩበት ከሁለት ዓመታት የበለጠ ጊዜ በአጠቃላይ 35 ጨዋታዎችን ያደረጉ ሲሆን 10ሩ ጨዋታዎች የአቋም መለኪያ ናቸው። ከእነዚህም 25 የውድድር መርሐ ግብር ጨዋታዎች ሲሆኑ፣ ዋሊያዎቹ ማሸነፍ የቻሉት 6 ጨዋታዎችን ብቻ ነው። በ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ምድብ አራት ከግብጽ፣ ጊኒና ማላዊ ጋር የተደለደሉት ዋሊያዎቹ፣ በ3 ነጥብና በግብ ተበልጠው በአራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ይህም ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማለፍ እድላቸውን ያጠበበው ሲሆን ለአሰልጣኝ ውበቱ ስንብትም ዋነኛ ምክንያት ሆኗል። ያም ሆኖ ብሔራዊ ቡድኑ ከግብጽና ከማላዊ ጋር ቀሪ የምድብ ጨዋታዎች የሚቀሩት ሲሆን በቀጣይ ዋልያዎቹን ሊረከብ የሚችለው አሰልጣኝ ጉዳይ ተጠባቂ ሆኖ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከትናንት በስቲያ ለዚህ ጥያቄ መልስ የሰጠ ውሳኔ ማስተላለፉን ይፋ አድርጓል። ብሔራዊ ቡድኑን ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲመሩ ከቆዩት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር በስምምነት ከተለያየ በኋላ ቀጣዩን አሰልጣኝ ለመምረጥ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባደረገው ውይይት በቴክኒክ ዳይሬክተርነት እየሠሩ የሚገኙት ኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረማርያም በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት ቀጣይ ጨዋታዎችን እንዲመሩ ከውሳኔ ተደርሷል።
ኢንስትራክተር ዳንኤልን እንዲያግዙ በፕሪሚየር ሊጉ በመሥራት ላይ የሚገኙና በወቅታዊ ውጤታማነትም የተሻሉ ሆነው የተገኙት የባህር ዳር ከተማ አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ምክትል አሰልጣኝ ሆነው እንዲሰሩ ከውሳኔ የተደረሰ ሲሆን ፌዴሬሽኑ ለአሰልጣኙ እና ለክለባቸው ባህርዳር ከተማ ጥያቄ አቅርቦ ፈቃደኛ በመሆናቸው ምክትል አሰልጣኝ ሆነው ተሹመዋል። የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ሹመት ደግሞ በቅርቡ ይፋ የሚደረግ ይሆናል።
ኢንስትራክተር ዳንኤል የዋልያዎቹን ኃላፊነት ከተረከቡ በኋላ “ከግብጽ ጋር ተሞክሮ አለኝ ምንም ፍርሃት የለብኝም፣ ካይሮ ላይ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን 3 ለ 1 የረታንበትን ውጤት አንረሳውም አይረሱትምም” ሲሉ ስለቀጣዩ ፍልሚያ ለሃትሪክ ስፖርት አስተያየት ሰጥተዋል።
“በጣም ተደስቻለሁ የማንኛውም ተጨዋች ሆነ አሰልጣኝ ትልቁ ግቡ የሀገሩን ባንዲራ ወክሎ መወዳደር ነው፣ በግሌ እንኳን ሜዳ ውስጥ የሚፋለም ቡድን መምራት ቀርቶ ቡድኑን በመሪነት ይዞ መጓዝ የሚፈጥረው ኩራት ለየት እንደሚል እረዳለሁ፣ በኃላፊነት ታምኖብኝ በመመረጤ ፌዴሬሽኑን አመሰግናለሁ” በማለትም ኢንስትራክተር ዳንኤል ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሰልጣኝ ውበቱ ከተሰናበቱ በኋላ ለሳምንታት በቆየው የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዳይሬክተርነት ፈተና መመዘኛውን አሟልተዋል ያላቸውን አምስት ተወዳዳሪዎች የስራ ልምድ፣ ያላቸውን የአሰልጣኝነት ላይሰንስ፣ ያላቸው የትምህርት ደረጃ፣ ዕቅድና ቃለ መጠይቅ ካየ በኋላ ኢንስትራክተር ዳንኤል ገ/ማርያምን በ81 ነጥብ የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዳይሬክተር እንዲሆኑ መምረጡ ይታወሳል።
ኢንስትራክተር ዳንኤል ከፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዳይሬክተርነት በተጨማሪ ዋልያዎቹን በጊዜያዊነት ሲመሩ የመጀመሪያ ስራቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከማላዊ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ መምራት ይሆናል። ይህ ጨዋታ የዋልያዎቹ የሜዳ ላይ ፍልሚያ ቢሆንም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጨዋታ የሚያስተናግድ በካፍ ፍቃድ ያለው ስቴድየም ስለሌላት አዲሱ ጊዜያዊ አሰልጣኝ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በገለልተኛ ሜዳ ለማድረግ ይገደዳሉ።
ከማላዊ ጋር የሚደረገው አምስተኛ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ በፈረንጆች ሰኔ 13 (June 20) የሚካሄድ ሲሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጨዋታውን ለማከናወን ሞዛምቢክን ምርጫው እንዳደረገ ከሳምንት በፊት ማሳወቁ ይታወሳል።
ፌዴሬሽኑ ይህን ጨዋታ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በሚገኙ ስታዲየሞች ላይ ለማከናወን ጥረት ቢያደርግም ሩዋንዳ ከዚህ በፊት ተፈቅዶላት የነበረ ስታዲየም ጊዜያዊ ፈቃድ በመነሳቱ ፣ ታንዛኒያ የተሰጣት ፍቃድ ደግሞ የብሔራዊ ቡድኗን ጨዋታ ብቻ እንድታከናወን በመሆኑ፣ ሱዳን በወቅታዊ አለመረጋጋት እንዲሁም ዩጋንዳ እና ኬንያ የተፈቀደ ስታዲየም ባለመኖሩ ምክንያት በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ማከናወን የማይቻል በመሆኑ ኢትዮጵያ ከማላዊ የምታደርገውን ጨዋታ ለማከናወን ሞዛምቢክን ምርጫው እንዳደረገ መግለፁ ይታወቃል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2015