ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2015 23ኛ ሳምንት መርሃግብር ጨዋታዎች ባለፉት ቀናት ተከናውነዋል። በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስቴድየም በሳምንቱ መርሃግብር በተደረጉ ጨዋታዎች አምስት ፍልሚያዎች በመሸናነፍ ሲጠናቀቁ፣ ሶስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተፈፅመዋል። በአጠቃላይም 17 ግቦች ተቆጥረዋል። ግቦቹ የተቆጠሩት 15ቱ በጨዋታ ሁለቱ ደግሞ በፍፁም ቅጣት ምት ነው። በሳምንቱ 46 ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች ቢጫ ካርድ የተመዘዘባቸው ሲሆን አምስት ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች ቀይ ካርድ ተመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር አመራርና ሥነ-ሥርዓት ኮሚቴ ቅዳሜ ግንቦት 05 /2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያዎች ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በተጫዋችና ቡድን አመራሮች ደረጃ በተላለፉ ውሳኔዎች 7 ተጫዋቾች ላይ ቅጣት ተላልፏል። ሱራፌል አወል (ለገጣፎ ለገዳዲ)፣ ደጉ ደበበ (ወላይታ ድቻ) እና ሙሉቀን አዲሱ (ሲዳማ ቡና) ሁለተኛ ቢጫ ካርድ የሚያሰጥ ጥፋት በመፈፀማቸው ቀይ ካርድ ተመልክተው ከጨዋታ ሜዳ የተወገዱ ሲሆን ለፈፀሙት ጥፋት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት አንድ ጨዋታ
እንዲታገዱ ተወስኗል። አበበ ጥላሁን (አርባምንጭ ከተማ) እና ማታይ ሉል(ኢትዮ ኤሌክትሪክ) በተለያዩ 5 ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቅቂያ ካርድ በመመልከታቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት አንድ ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 1500 /አንድ ሺ አምስት መቶ/ እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል። አለልኝ አዘነ (ባህር ዳር ከተማ) በሳምንቱ ጨዋታ ሃይማኖታዊ መልእክት የሚያስተላልፍ ምስል በውስጥ ልብሱ ደርቦ ስለመልበሱ ሪፖርት የተደረገበት ሲሆን በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ደንብ መሰረት ተጫዋቹ የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 /ሶስት ሺህ ብር/ እንዲሁም ክለቡ የገንዘብ ቅጣት ብር 10,000 /አስር ሺህ ብር/ ቅጣት ተላልፎባቸዋል።
ዉሀብ አዳምስ/ ወልቂጤ ከተማ/ በሳምንቱ ጨዋታ ወቅት ከዳኛ እይታ ውጭ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋችን በክርን ስለ መምታቱ ሪፖርት የተደረበት ሲሆን ተጫዋቹ በፈጸመው ጥፋት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት አራት ጨዋታ እንዲታገድና ብር 3000 /ሶስት ሺህ/ እንዲከፍል ተወስኗል።
በክለቦች ደረጃ በታዩ ሪፖርቶችም የተለያዩ ውሳኔዎች ተላልፈዋል። ለገጣፎ ለገዳዲ በሳምንቱ ጨዋታ የክለቡ ከአራት በላይ ተጫዋቾች በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ክለቡ የገንዘብ ቅጣት ብር 5000 /አምስት ሺ/ እንዲከፍል ተወስኖበታል። ወላይታ ድቻ በ22ኛ ሳምንት ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች የእለቱን ዳኛ አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት በመቅረቡ የክለቡ ደጋፊዎች ለፈፀሙት ጥፋት ክለቡ የ50,000/ ሃምሳ ሺህ/ ብር ቅጣት ተላልፎበታል። ኢትዮጵያ ቡና በሳምንቱ ጨዋታ የክለቡ ተጫዋቾች የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታድየም መልበሻ ክፍል ሁለት በሮች ስለመስበራቸው ሪፖርት የተደረገ ሲሆን ክለቡ የተሰበሩትን በሮች እንዲያሰሩ ወይም የዩኒቨርስቲው አሰተዳደር የሚያቀርበውን የንብረትን ዋጋ እንዲከፍል ተወስኗል፡፡
በተጨማሪም በፕሪምየር ሊጉ አ.ማ. የተቋቋመው ቴክኒካል ኮሚቴ የ23ኛ ሳምንት እግር ኳስ ጨዋታ አንዱ በሆነው የኢትዮጵያ መድንና ሲዳማ ቡና ግጥሚያ ዙሪያ ምርመራ እያደረገበት በመሆኑ የኮሚቴው የቅድመ ምርመራ ውጤት እስኪታወቅ ድረስ የጨዋታው ውጤት እንዳይጸድቅ እና ከጨዋታው ጋር የተያያዙ የዲሲፕሊን ውሳኔዎች ውጤቱ ከታወቀ በኋላ እንዲታዩ የውድድርና ሥነሥርዓት ኮሚቴ ወስኗል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2015