የዛሬው አነሳሳችንም ሆነ ርእሰ ጉዳያችን ስለ “መሳቁን ይስቃል . . .” ልናወራ አይደለም። ስለ “ጥርስ ባዳ ነው . . .”ም አይደለም። እንጨዋወት ዘንድ የተመረጠው ርእሰ-ጉዳይ የጥርስ ጤና ጉዳይ ነው።
እንደሚታወቀው ጥርስ አንዱ አካላችን ነው። ከዛም ባለፈ ጎናዊ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን፣ ንግግር ያለ እሱ ሙሉ አይሆንም፤ አመጋገብ ያለ ጥርስ ማላመጥ ነው የሚሆነው። ጥርስ ከሌለ ውበት ጎዶሎ ይሆናል። ባይሆን ኖሮ ጥላሁን ገሠሠ “ጥርሰ በረዶ ናት” ባላለም ነበር።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ በ“ጥርሰ በረዶ”ነት የሚታወቁ ሰዎች ለጥርሳቸው ልዩ ጥንቃቄን፣ ለየት ባለ መልኩ ቢያንስ በቀን ሁለቴ (ጠዋትና ማታ) ጥርሳቸውን “ፏፏ” የሚያደርጉ (Toothbrushers) ናቸው እንጂ ማንም ከመሬት ተነስቶ ለአቅመ “ጥርሰ በረዶ”ነት አይደርስም። “ደረሰ” ቢባል እንኳን፣ ከላይ እንዳልነው በጥርሱ ሊመገብ፣ ጥሬ ሊቆርጠም . . . ይችል ይሆናል እንጂ በ“ጥርሰ በረዶ . . .”ነት ደረቱ(ቷ)ን ነፍቶ(ታ) ሊ(ልት)ወዛወዝ አይችልም፤ ወይም፣ አትችልም። ለዚህም ነው በአለማችን ጥርሱን የሚያፀዳው ከአጠቃላይ የአለም ህዝብ ቁጥር 53% ብቻ መሆኑ እያሳሰበ የሚገኘው።
ምንም እንኳን በአገራችን፣ በተለይም እዚህ አዲስ አበባ፣ “የጥርስ ሀኪም” ቤት በየፎቁ ላይ ተንጠልጥሎ ይታይ እንጂ፣ ስለ ጥርስና የጤናው ሁኔታ ብዙም የሚታወቅ እውነት አለ ለማለት ጊዜው ገና ይመስላል።
አደጉ በሚባሉት አገራት የጥርስ ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ሲሆን፤ እንደ ማንኛውም የጤና ጉዳይ እኩል አሳሳቢ ነው። በመሆኑም፣ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግ አንፃር ሰፋፊ ስራዎች ይሰራሉ። የጥናትና ምርምር ስራዎች ያለ ማቋረጥ ይከናወናሉ። ማን የቱ ጋ እንዳለ አንድ፣ ሁለት . . . ተብሎ ይቆጠራል። በመቶኛ ይሰፈራል። አገራት ከአገራት ይወዳደራሉ፣ ይነፃፀራሉም። ማን ፊት መሪ፤ መንስ ኋላ ቀር እንደሆነ በደረጃ ይቀመጥበታል። እናም፣ የጥርስ ጉዳይ የዋዛ እያልደለም እያልን ነው።
የጥርስን ጤና ከመጠበቅ አኳያ ያለው ሁኔታ የአፍ ጤንነት (oral health/hygiene)ን ከመጠበቅ ጋር በጥቅል የሚታይ ነው።
በዚሁ መሰረት፣ በ2021 በተደረገና በአስከፊ ሱስነት (worst habit) መስፈርት በታየ ጥናት 5 በመቶ ብቻ የሆነው የታይላንድ ህዝብ በጥርሱ ጤንነት ደስተኛ ሲሆን፤ የተቀረው አደጋ ላይ ነው። እንግሊዝ “ምንም አይነት የጥርስ ችግር የሌለባቸው አገራት” በሚለው ስር 40 በመቶን ይዛ ትገኛለች። 45% ዜጎቿ የጥርስ ሀኪም የመጎብኘት ልምድ ያላት ጀርመን በሲጋራ አጫሽነት ምክንያት ዜጎቿ (27%) ውበታቸውን ጨምሮ አደጋ ላይ ናቸው። ስፔን የጥርስ ንፅህናቸው ካልጠበቁ አገራት ተርታ (41%) ላይ ትገኛለች። ብራዚል፣ ኢንዶኔዥያና ጣሊያን ሰበቡ ቡና የማዘውተራቸው አስከፊ ሱስ መሆኑን ተጠቅሶ 22 በመቶ ላይ ይገኛሉ። ቻይናውያን በጣፋጭ ወዳድነትና አዘውተሪነታቸው ምክንያት 31% ደረጃ ላይ ሊገኙ ችለዋል። ያ ማለት፣ እነዚህና እዚህ ያልጠቀስናቸው አገራት በተለያዩ ሱሶችና በሰአቱ ጥርሶቻቸውን የማፅዳት ልምድን ባለማዳበራቸው ምክንያት “ጥርሰ በረዶ ናት/ነው” የሚለው የሚመለከታቸው ሊሆኑ አልቻሉም።
ጥርሳቸውን ማፅዳት በመርሳት (Most forgetful toothbrushers) ምክንያት ኢንዶኔዥያ አንደኛ (45%)፤ ብራዚል ሁለተኛ (40%)፤ ጣሊያን ሶስተኛ (40%) ላይ መገኘታቸው ከላይ በጠቀስነው አለም አቀፍ ጥናት ተረጋግጧል።
ጥናቱ ጥርስን በሚገባ ከማፅዳት አኳያ (Best for cleaning between teeth) ቻይናዊያን እያንዳንዷን ጥርስ በተናጠል በማፅዳት ከአለም 1ኛ (21%)፤ ጣሊያን 2ኛ (20%)፤ ኢንዶነዥያዊያን መጨረሻ (7%) መሆናቸውንም ይፋ አድርጓል።
“ከላይ የጠቀስናቸውም ሆኑ ሌሎች የጥርስ ጤናን የተመለከቱ ጉዳዮች ምን ምን ግላዊና ማህበራዊ ችግሮችን አስከተሉ?” ብለን ብንጠይቅ፤ ከላይ ከጠቀስነው ጥናት የዜጎች ከፈገግታ የሚገኝ እርካታ (Smile satisfaction)ን ማጣት ሆኖ ነው የምናገኘው።
18% የሚሆኑ ኔዘርላንዳዊያን በጥርሶቻቸው “በረዶ”ነት (ንጣት)ና በሚያሳዩት ፈገግታ ደስተኞች ሲሆኑ ምንም አይነት ኮስሞቲክስ ባለመጠቀምም ተጠቃሾች (5% የሆኑት የታይ (Thai)፣ ስፓኒሽ፣ ጣሊያን እና የብራዚል ዜጎች፤ 7% ያሆኑ አሜሪካዊያን ለጥርሳቸው ምንም አይነት ኮስሞ ተጠቃሚዎች አይደሉም) ናቸው። በመሆኑም ፈገግታና ከእሱ የሚገኘው እርካታ ተጠቃሚዎች ናቸው።
በገዳይነቱ በሚታወቀው የአፍ ጤንነትን በተመለከተ ጥናቱ የሚናገረው ያለው ሲሆን ከጃፓን (34%)፣ ብራዚል (8%) . . . ቀጥሎ መጥፎ የአፍ ጠረን የተመዘገበባቸው አገራት የእሲያ አገራት መሆናቸውን፤ ከአውሮፓ ጣሊያን (15%)፣ እና ዩኬ (10%) እንደሆኑ ተመልክቷል።
ጣሊያኖች (33% የሚሆኑት) ቢረሱ ቢረሱ ከቤት ሲወጡ ጥርሳቸውን መቦረሽ አይረሱም። ፈረንሳዊያን (28%) ምግብ ከተመገቡ በኋላ ጥርሳቸውን ይቦርሻሉ። 45% የሚሆኑ ጀርመኖች ለጥርሳቸው በመጨነቅ ቢያንስ በአመት ሁለቴ የጥርስ ሀኪማቸው ጋ በመሄድ ጥርሳቸው ያለበትን ሁኔታ ይረዳሉ። (27% የሚሆኑት እነዚሁ ጀርመናዊያን ደግሞ ለጥርሳቸው ሲሉ ብቻ ሲጋራ የሚያቆሙ ናቸው።) በጀቾች (18%) ዘንድ ምንም አይነት የጥርስ ማስዋቢያን መጠቀም ነውር ነው። 14% የሆኑት የጥርስ ጤና ከአጠቃላይ የሰው ልጅ ጤና ጋር ያለውን ግንኙነት ጠንቅቀው ያውቃሉ፤ በመሆኑም ይጠነቀቁለታል። 40% እንግሊዛዊያን በጥርሴ ላይ ምንም አይነት ችግር የለም የሚል የራስ መተማመን ላይ የደረሱ ናቸው። ስፓኒሾች (41%) በቋሚነት ጥርሳቸውን በማፅዳት ይታወቃሉ።
ወደ ራሳችን፤ አፍሪካ እንመለስ።
ከ2010 እስከ 2020 ያለውን ጊዜ የሚሸፍነው (ከ10 አመታት በላይ የፈጀ)፤ “Study shows lower level of tooth brushing practice in Ethiopia” (ኤፕሪል 22፣ 2023) በሚል ርእስ ለአደባባይ የበቃው ጥናት አፍሪካ፣ በተለይም ኢትዮጵያ ላይ በማነጣጠር አስቸኳይ መፍትሄ ያስፈልገዋል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል።
ጥናቱ እንደሚነግረን ከሆነ የአፍ ንፅህናን፣ በተለይም የጥርስ ንፅህናን በመጠበቅ በኩል ኬኒያ አንደኛ (77.5%) ስትሆን፤ ማላዊ በሁለተኛነት (76.6%)፣ ታንዛኒያ ሶስተኛ (72.4%) ደረጃ ላይ ትገኛለች። በዚህ መልኩ እየዘረዘረ የሚሄደው ይህ ጥናት ኢትዮጵያን ከመጨረሻዎቹ ተርታ (12.2%) ላይ ያስቀምጣታል (እሱን ራሱ ልብ ይሏል)። የሚመለከታቸው አጥብቀው እንዲያስቡበትም ይመክራል።
ከዚህ የምንረዳው “ጥርሰ በረዶ ናት . . .” በቀላሉ የማይገኝ መሆኑን ነውና ልናስብበት ይገባል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2015