መግቢያ
ነገር ከረር ያለ ይመስላል። ምስክሮች ቢደረደሩም እውነታውን ለመደበቅ አልተቻላቸውም። ፍርድ ቤቱም የሚቀርቡ ማስረጃዎችንና መረጃዎችን ሲመረምርም አንድ ሃቅ ግን መካድ አልተቻለም። እውነታው ጉዳት የደረሰባቸው ተበዳይ ሴት፣ ሁለት ጉዳት አስተናግደዋል። አንድም አካላዊ ጥቃት፤ ሁለትም በሆዳቸው ውስጥ የነበረውን ጽንስ ይችህን ምድር ሳይመለከት በእናቱ ማህፀን ሞት ተፈርዶበታል። በእናቱ ማህፀን ሳለ በክንድ ተመታ። ተጠርጣሪዋ የስምንት ወሯን እርጉዝ በቀጥታ በሆዷ ላይ የመታችው ከመሆኑ አኳያ ድርጊቱ በወንጀል ህግ ቁጥር 581/ለ)፤ 27(1) 540 ስር የተመለከተውን የግድያ ሙከራ የሚያቋቁም ስለመሆኑም የህግ አንቀፆች ያመለክታሉ።
ይህ ጉዳይ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሥር ፍርድ ቤት ጀምሮ እስከ ክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደረሰ። በዚህም አላበቃም፤ አመልካች እና ተጠሪ አንዱን በአንዱ ሲቃወሙ ወደ ፌደራል ደረሰ። ሰበር ችሎትም ቆሙ። በወቅቱ የነበሩት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ተገኔ ጌታነህ እና አራት ዳኞችም ለዚህ የሰበር ውሳኔ በአንድ ላይ ለመወሰን ከችሎት መንበር ላይ ተቀመጡ።
በእርግጥ በዕለቱ የሰበር ውሳኔ በዚህ መዝገብ የተጠቀሱት አመልካችም በአካል አልቀረቡም፤ ፋይሉ ግን አንድ በአንድ ቀርቧል። ተጠሪው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሄራዊ ክልልዊ መንግስት አቃቤ ህግ በሌለበት ጉዳዩ ታይቶ መዝገቡ ተመርምሮ ፍርድ ተሰጠ። ድርጊቱን በፈፀመው ሰው ላይ በግድያ ሙከራ የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል ሲሆን፤ የወንጀል ህግ አንቀጽ 27(1), 581(ለ), 540 ላይ የሚያርፍ ነው። ይህ የወንጀል ምርመራ ታሪክ የሰነድ መለያ ቁጥሩ 90089 ሲሆን፤ ጥቅምት 20 ቀን 2006 ዓ.ም ሰበር ሰሚ ችሎት የመጨረሻ የሚለውን ውሳኔ ያሳርፋል። ይህም ውሳኔ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ውሣኔዎች ቅፅ 15 ላይ የወንጀል ድርጊት ሆነው የሰበር ውሳኔ ከተሰጣቸው መካከል ውሳኔዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሶ ለህትመት አብቅቶታል።
የነገሩ ጅማሮና ሂደቱ
ጉዳዩ ወንጀል ሲሆን፤ የተጀመረውም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት አሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በስር ፍርድ ቤት አመልካች ተከሳሽ ተጠሪ ከሳሽ ሆነው ነበር። የቀረበው ክስም አመልካቿ የወንጀል ህግቁጥር 27/1/ 540 ስር የተመለከተውን በመተላለፍ በባሞባሲ ወረዳ ባሞበስ ከተማ 02 ቀበሌ ጥቅምት 14 ቀን 2004 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 1፡00 ሰዓት አካባቢ የግል ተበዳይ ጠይባ መሐመድ መኖሪያ ቤት አካባቢ የግል ተበዳይ በሆድዋ ላይ በመምታት ሆድዋ ውስጥ የነበረው ፅንስ ቦታውን እንዲለቅ እና የመውለጃ ቀን ያልደረሰ ፅንስ በሆድዋ ውስጥ እንዲሞት በማድረግ፤ የምጥ አመጣጥና ከ4 እስከ 5 ከወሊድ በኋላም የደም መርጋትና የደም መፍሰስ እንዲፈጠር በማድረግ በፈፀመችው የመግደል ሙከራ ወንጀል ፈፅማለች የሚል ነው።
አመልካችም ፍርድ ቤት ቀርባ የዕምነት ክህደት ቃሏን ስትጠየቅ የወንጀሉን ያልፈፀመች መሆኑን ክዳ ቃልዋን ሰጠች። ይህን ድርጊት መፈጸም ቀርቶ ማሰቡ ከባድ ስለመሆኑ ለፍርድ ቤቱ ለማስረዳት ሞክራለች። ፍርደ ቤቱ ግን በዚህም አላበቃም። ቀጥሎም ፍርድ ቤቱ በግራ ቀኙ በኩል የተቆጠሩትን ምስክሮች አስቀርቦ ከሰማ እና ጉዳዩንም ከመረመረ በኋላ ድርጊቱ ተፈፅሟል በተባለበት ጊዜ ማለትም ከጥቅምት 9 አስከ 16 ቀን 2004 ዓ.ም ድረስ አመልካች ዕቃዋን ለመውሰድ ሱዳን ሀገር ልዩ ቦታው ኩርሙክ ተብሎ የሚጠራ ቦታ ሄዳ እዚያ የነበረች እና በቦታው አለመኖሯ በመከላከያ ማስረጃ ተረጋገጠ። በሌላ በኩልም አመልካች እንደተባለው በእርግጥም በወቅቱ በቦታው ብትኖርና ጉዳቱን የፈፀመች ቢሆን ኖሮ ጉዳዩ ወዲያውኑ ለፖሊስ ሪፖርት በተደረገ እና አመልካችም ሳትቆይ ወዲያውኑ ቁጥጥር ስር በዋለች ነበር በማለት አመልካቿ ድርጊቱን አለመፈፀሟን በበቂና አሳማኝ ሁኔታ ተከላከለች። በመሆኑም በወንጀል መቅጫ ህግ ሥነሥርዓት ቁጥር 149(2) መሠረት ከክሱ በነጻ እንድትሰናበት በአብላጫ ድምፅ ውሳኔ ይሰጣል።
የከሳሽ ቅሬታ
በዚህ ውሳኔ ግን ከሳሽ አልተደሰቱም። በደል ስለመኖሩ በጽኑ ለማስረዳት ሞከሩ። ከሳሽ በተሰጠው ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቀረቡ። ፍርድ ቤቱም በበኩሉ ግራ ቀኙን አስቀርቦ በጉዳዩ ላይ እንዲከራከሩ አደረገ። ጉዳዩን በመመርመር አመልካች በክሱ በተጠቀሰው ጊዜና ቦታ የስምንት ወር እርጉዝ የነበሩትን የግል ተበዳይ በክንዷ ሆዷን እንደመታቻት የግል ተበዳይም ወዲያውኑ በዚሁ ምክንያት ህመም እንደተሰማቸውና ፅንሱም መላወሱን እንዳቆመ በኋላም የግል ተበዳይዋ ወደ ሃኪም ቤት ተወስደው ሲታዩ ሽሉ ሞቶ በመገኘቱ በህክምና መሳሪያ እንዲወጣ ተደርጓል የሚል ሃሳብና ማስረጃ ቀረበ።
ሆኖም ግን የግል ተበዳይ በዚሁ ጉዳት ምክንያት የታመቀና የረጋ ደም መፍሰስ ያጋጠማቸው ስለመሆኑ፤ የግል ተበዳይ ጨምሮ በዐቃቤ ህግ በኩል ቀርበው በበታች ፍርድ ቤት በተሰሙት ምስክሮች ቃል እና ህክምና ማስረጃ የተረጋገጠ መሆኑን ገለፀ። በአንፃሩ ግን በአመልካች በኩል የተሰሙት መከላከያ ምስክሮች ቃል በተለይም አመልካቿ በተጠቀሰው ጊዜ ኩርሙክ ቦታ ሄዳ እዚያ የነበረች ስለመሆኑ በምን አግባብ ሊያውቁ እንደተቻሉ በሚመለከት የአንዱ ምስክር ቃል ከሌላው የሚጣረስ በመሆኑና በዚህም ምክንያት ክብደት እንደማይሰጠውና ተዓማኒነት የሌለው መሆኑ እየታወቀ የበታች ፍርድ ቤት ተከሳሸዋ ወንጀሉን ተከላክላለች በማለት በነፃ እንዲሰናበቱ በአብላጫ ድምፅ ውሳኔ መስጠቱ ተገቢነት የሌለውና ስህተት ያለበት ነው በማለት ተከሳሿ ክሱ በቀረበበት የህጉ ድንጋጌ ስር ጥፋተኛ ሊባል ይገባል የሚል መቃሚያና ክርክር ቀረበ።
ነገሩ እየጦዘ መጣ። የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ መሻር አለበት የሚለው ሐሳብ በርታ በማለት የጥፋተኝነትም የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት በመቀበልና ከህጉ ጋርም አገናዝቦ መመልከቱን ከተገለፀ በኋላ በሦስት ዓመት ከሰባት ወር ፅኑ እስራት ሊቀጡ ይገባል በማለት ወስነ። የሰበር አቤቱታ የቀረበለት የክልሉ ሰበር ችሎትም ጉዳዩ መሠረታዊ የህግ ስህተት የለውም በማለት የአመልካችን አቤቱታ ሳይቀበል አለፈ።
ከክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወደ ሰበር
አመልካች የሥር ፍርድ ቤትም ሆነ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያስተላለፈው ውሳኔ ሊዋጥላቸው አልቻለም። ጽንስ የሚያክል ነገር ሞቶ ሳለ፤ ደም ፈሶኝ ስለምን በሦስት ዓመት ከሰባት ወር ፍርድ ብለው ተቃወሙ። ጉዳዩ ሰበር ደረሰ።
ተከሳሽ በበኩላቸው፤ ለሰበር የቀረበው አቤቱታም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ሲሆን፤ መሠረታዊ ይዘቱም በጥቅሉ ጥፋተኛ የተባሉበት ድርጊት አለመፈፀማቸውን ገለጹ። ‹‹እኔ በመከላከያ ማስረጃ በሚገባ በማረጋገጥ የተከላከልኩ ስለመሆኔ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተመርምሮ የተሰጠው ውሳኔ በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ ተሽሮ ጥፋተኛ ተብዬ መቀጣቴና እንዲሁም ይኸውም ክልሉ ሰበር ችሎትም መፅናቱ ስህተት ያለበት በመሆኑ ውሳኔው ሊሻርልኝ ይገባል። ይህ የሚታጠፍ ከሆነም አባት የሌላቸው ልጆች የማሳድግ መሆኔንና የመሳሰሉት ግንዛቤ ውሰጥ ገብቶ ቅጣቱ ሳይፈፀም በገደብ ታግዶ እንዲቆይ አሊያም እንዲቀነስልኝ›› ሲሉም ተማጸኑ። አቤቱታውም በሰበር አጣሪ ችሎቱ ተመርምሮ ለሰበር ክርከር ችሎት ቀርቦ ሊታይ ይገባል በመባሉ ምክንያት ተጠሪም ቀርቦ የበኩሉን መልስ በጽሑፍ እንዲሰጥ መጥሪያ እንዲደርሰው የተደረገ ቢሆንም ባለመቅረቡ ጉዳዩ በሌለበት እንዲታይ ሆነ።
ሰበር ምን አለ?
የሰበር አቤቱታ በቀረበበት ውሳኔ ላይ መሠረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ተፈፅሞበታል ማለት ይቻላል? ወይ ወይስ አይቻልም የሚለውን ነጥብ በጭብጥነት ይዞ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መረመረው።
በምርመራውም መሰረት የአሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የግራ ቀኙን ምስክሮች ሰምቶና ጉዳዩንም መርምሮ የሥር ተከሳሻ ወንጀሉን ተከላክላለች በሚል ምክንያት በነፃ እንዲሰናበት በአብላጫ ድምፅ ውሳኔ የሰጠ ቢሆንም፤ በአሁን ተጠሪ አመልካችነት ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በበኩሉ ግራ ቀኙ እንዲከራከሩ ካደረገ በኋላ ጉዳዩን በመመርመር አመልካች በመካከላቸው የነበረውን ግጭት መነሻ በማድግ የስምንት ወር እርጉዝ የሆነችውን የግል ተበዳይ ጠይባ መሐመድን በሆድዋ ላይ በክንዷ መትታ ጉዳት ያደረሰችባት መሆኑ፤ የግል ተበዳይዋም በዚሁ ምክንያት ከተመታችበት ቦታ ሳትንቀሳቀስ ብርቱ ህመም እንደተሰማት፣ ፅንሱም መላወሱን ማቆሙን፤ ከዚያም ሀኪም ቤት ተወስዳ በባለሙያ ምርም ሲደረግላት ፅንሱን ሞቶ በመገኘቱ ምክንያት በህክምና መሳሪያ እንዲወጣ መደረጉንና ከግል ተበዳይዋም ብዙ የረጋና የታመቀ ደም በመፍሰሱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባት ስለመሆኑ በምስክሮች ቃልና ህክምና ማስረጃ መረጋገጡ ተገለፀ።
በአንፃሩ ደግሞ በስር ተከሳሽ በኩል የተሰሙት የመከላከያ ምስክሮች ቃል አንዱ ከሌላው ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ተአማኒነት የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም በማለት የሥር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመለወጥ በአመልካች የጥፋተኝነት ውሳኔ ካስተላለፈ በኋላ በሦስት ዓመት ከሰባት ወር ፅኑ እስራት ሊቀጡ ይገባል በማለት ቅጣት ጥሏል። የሰበር አቤቱታ የቀረበለት ክስ ሰበር ችሎትም ውሳኔው ስህተት የለውም በማለት ወስነ።
እንግዲህ እኛም ጉዳዩን እንደተመለከትነው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አመልካች ወንጀሉን ሊያስተባሉ አልቻሉም የሚል ድምዳሜ የጥፋተኝነት ውሳኔውን ሊሰጥ የቻለው በህግ የተሰጠውን የማስረጃ ምዘና ተግባሩን መነሻ በማድረግ መሆኑን ከውሳኔው ይዘት የምንገነዘበው ጉዳይ ነው።
ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱም ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ተጠቅሞ ያረጋጠውን ፍሬ ነገር ይህ ችሎትም እንዳለ የሚቀበለው ጉዳይ ይሆናል እንጂ በዚህ ረገድ የሚቀርበውን ክርክር ችሎቱ ለማየት በህግ ስልጣን አልተሰጠውም። በሌላ በኩል እነዚህን በይገባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ የተረጋገጡትን ፍሬ-ነገሮች መነሻ በማድረግ በህግ አተገባበር ረገድ በበታች ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ የተፈጠረ ስህተት መኖር አለመኖሩን በተመለከተ ስንመለከተው ደግሞ አመልካች የስምንት ወር እርጉዝ በቀጥታ በሆዷ ላይ የመታችው ከመሆኑ አኳያ ድርጊቱ በወንጀል ህግ ቁጥር 581/ለ)፤ 27(1) 540 ስር የተመለከተውን የግድያ ሙከራ የሚያቋቁም በመሆኑ በዚህ ረገድ በጥፋተኝቱ ውሳኔ ላይ የተፈጠረ ስህተት አላገኘንም የሚል ነው።
ቅጣትን በሚመለከት የቀረበው የሰበር አቤቱታም ቢሆን ቅጣቱ በወንጀል ህግ ቁር 192 መሠረት ሳይፈፀም ታግዶ እንዲቆይ ለማድረግ የሚያስችል ምክንያቶች ተሟልተው ባልተገኙበት ሁኔታ ቅጣቱን ማገድ የማይችል ሲሆን፤ መጠኑን በተመለከተም ከደረሰው ጉዳትና ወንጀሉ ክብደት አኳያ በስር ፍርድ ቤት የተጣለው ቅጣት ተገቢ ነው ከሚባል በስተቀር መሠረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበት ሆኖ አልተገኘም። በመሆኑም ተከታዩን ውሳኔ ሰጥናል ሲል ሰበር ችሎትም ከስር ፍርድ ቤት ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲተላላፍ የነበረውን ውሳኔ አጸናው። በመሆኑም በወንጀሉ የተጠረጠሩት ግለሰብ ቅጣታቸውን ሊከናነቡ ግድ ሆነ፤ ፍርድ ቤት የቀረበው ማቅለያም ተገቢነት የለውም በሚል ተላልፎ የነበረው የእስር ቅጣት ውሳኔ ፀና።
ውሳኔ
1. የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመዝብ ቁጥር 03748 በ24/7/2005 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ እና እንዲሁም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመለያ ቁጥር 04446 በ17/8/2005 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ በወንጀል መቅጫ ህግ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 195(2)(ለ)(2) መሠረት ፀንቷል።
2. የሰበር አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ ሙሉ በሙሉ የፀና መሆኑን አመልካች በሚገኙበት ማረሚያ ቤት በኩል ይገለፅላቸው ሲል መዝገቡን ዘግቷል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2015