የዛሬው የባለውለታ አምዳችን እንግዳ የኢትዮጵያ ወዳጅ እና ባለውለታ ስዊድናዊው ኮሎኔል ካርል ጉስታፍ ቮን ሮዘን ናቸው:: ኮሎኔል ካርል ጉስታፍ ከለጋ ወጣነት እድሜያቸው ጀምሮ እስከ ጡረታ መዳረሻ እድሜቸው ድረስ ለኢትዮጵያ ጉልበታቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውን እንዲሁም በመጨረሻ ህይወታቸውን ሰውተዋል። ይሁንና ይህ ታሪክ የቅርብ ጊዜ ቢሆንም እንኳን እኚህ ስዊዲናዊ ግለሰብ ለኢትዮጵያ የከፈሉት ዋጋም ሆነ ስላበረከቱት አስተዋፅኦ በብዙ ሰዎች እንደማይታወቅ ነው የሚነገረው::
ይህንን የተረዳው ደራሲ ሚካኤል ሽፈራው የኢትዮጵያ የክፉ ቀን ወዳጅ የሆነውን የካርል ጉስታቭ ቮን ሮዘን እውነተኛ የህይወት ታሪክና የኢትዮጵያ ቆይታ የሚያስቃኘውን “An Air Borne Knight Errant” የተሰኘ መጽሐፍ ‹‹ከማይጨው እስከ ኦጋዴን›› በሚል ወደ አማርኛ በመመለስ፣ በተወሰነ ደረጃ እንኳን ቢሆን ያለመታወቃቸውን ክፍተት ለመሙላት የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል::
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በተለያዩ ውጥረቶች ውስጥ በገባችበት ዘመናት ወደ እዚህ በመምጣት በቅንነት እና በፍቅር ያገለገሉን፣ በረሀብ በተፈተንባቸው፣ በጦርነት በተጠቃንባቸው ዓመታት ያልተለዩን በርካታ ባለውለታ የውጭ ሀገር ዜጎችን በታሪኳ አስተናግዳለች:: የውጪ ሀገር ዜጋ ሆኖ ራሱን ለከፍተኛ አደጋ አጋልጦ ኢትዮጵያን በሙሉ ልቡና በቆራጥነት በማገልገል ረገድ ካርል ጉስታቭን የሚስተካከል እንደሌለ ይጠቀሳል::
ለመጀመሪያ ጊዜ በ1928 ዓ.ም ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ የከፈተችው ወረራ በስዊድን በተሰማ ጊዜ ከፍተኛ ቁጣ ተቀሰቀሰ:: ምክንያቱም ደግሞ ስዊድን በወቅቱ በሚሲዮናውያን አማካኝነት ከኢትዮጵያ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ፈጥራ ስለነበር ነው:: ጋዜጦቿም የኢጣሊያንን ወረራ በብርቱ አወገዙ:: ጦርነቱ ከተጀመረበት ዕለት ጀምሮ የስዊድን ቀይ መስቀል ኮሚቴ ስዊድናውያን የህክምና ባለሙያዎችን ያካተተ የጦር ሜዳ ሆስፒታል ወደ ጦር ግንባር ለመላክ ውሳኔ አሳለፈ:: የጦርነቱን ሰለባዎች ለመርዳት የሚውል ገንዘብ መሰብሰብ ሲጀመር ህዝቡ ከልብ በመነጨ ስሜት ገንዘቡን ለነዚሁ ለቀይ መስቀል ኮሚቴ አባላት መለገስ ጀመረ:: ይህ ገንዘብ የጦር ሜዳ ሆስፒታሉን የአራት ወር ወጪ ሙሉ ለሙሉ መሸፈን የሚያስችል ነበር::
በጊዜው የ26 ዓመት ወጣት አብራሪ የነበሩት ባለታሪካችን ካርል ጉስታቭ ቮን ሮዘን ከነበሩበት የሰርከስ ትርኢት በረራ ስራቸውን በመልቀቅ ያለ አላማ በዛለ መንፈስ በስዊድን ጎዳናዎች እየተዘዋወሩ ሳለ ድንገት እግር ጥሏቸው፤ እርሳቸው በስፍራው ሲደርሱ በቅርብ ከኢትዮጵያ የተመለሱ እና የሚያቋቸው ዶክተር ጉናር የተባሉ ሀኪም ትምህርታዊ ንግግር ለማድረግ እየተዘጋጁ ነበር:: ካርል በኢትዮጵያ በወቅቱ ድንገት ስለተከፈተው የኢጣሊያ የግፍ ጥቃት የሚተርከውን የዶክተሩን አሳዛኝ ንግግር አዳመጡ:: በሰሙት ታሪክ ስሜታቸው የተነካው ካርል ጉስታቭ ለአፍታም ሳያመነቱ ወዲያውኑ ለስዊድን ቀይ መስቀል ኮሚቴ ፕሬዚዳንት በጻፈው ደብዳቤ፣ የአምቡላንስ አውሮፕላን አብራሪ ሆነው ወደ ጦርነቱ ለመዝመት ፍቃደኝነታቸውን አረጋገጡ ::
በዚህም ሳያበቃ ካርል የግል አውሮፕላናቸውን ለቀይ መስቀል አገልግሎት እንድትውል በስጦታ ማበርከታቸውንም ጨምሮ አሳወቁ:: ከአራት መቶ በጎ ፍቃደኛ አመልካቾች መካከል መመዘኛውን ካርል የግል አውሮፕላኑን ጨምሮ በስጦታ ማቅረባቸውን ቦርዱ ከግምት በማስገባት እርሳቸውን መምረጥ ይችል ዘንድ አሳማኝ ምክንያት ሆኖ በማግኘቱ መርጦ ወደ ኢትዮጵያ እንደላካቸው በመጽሐፉ ላይ ተጠቅሷል::
ካርል ኢትዮጵያ ሲደርሱም በጊዜው በጦርነቱ የነበሩት ሁለት ፓይለቶች ብቻ ነበሩ:: አንዱ ኢትዮጵያዊ ካፒቴን ሚሽካ ባቢ ሼፍ እና ሉድዊግ ዌበር የሚባል በአንደኛ የአለም ጦርነት የተዋጋ አውሮፕላን አብራሪም ነበር:: ዌበር ንጉሱ የራሳቸው የግል አውሮፕላን አብራሪ አድርገው ቀጥረውት በዚህ ስራ ላይ ነበር:: በኋላ ካርል ከንጉሱ በቀጥታ የተለያዩ ትዕዛዝ በመቀበል በመሳሪያ እና በመርዝ ጋዝ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በማንሳት እና እርዳታ በማድረግ መቆየታቸው ይነገራል:: በዚህም በጎ ሥራው ከንጉሱ እና ከባለሟሎቻቸው ጋር እራት እንዲቀርቡ ግብዣ ተደርጎላቸው እንደነበር ይኸው መጽሐፍ ያወሳል::
እኚህ ስዊድናዊ አብራሪ ታዲያ ከሀገራቸው ይዘዋት የመጡት አውሮፕላን በተራራማ ስፍራዎች እና አስከፊ በሆነ የአየር ጠባይ ሳቢያ የማታገለግል ሆና መገኘቷ እጅግ የሚያሳዝን ነበር:: ይሁንና በተመደቡላቸው ሥፍራ ሁሉ በማንኛውም መጓጓዣ በማምራት፣ ከጦር ሜዳ አቅራቢያ ተጠምዶ የነበረ ፈንጂ በማምከን ፣ የተጎዱ ሰዎችን ወደ ቀይ መስቀል ሆስፒታል በማመላለስ ኃላፊነታቸውን በቁርጠኝነት ከመወጣት አልቦዘኑም:: ስዊድናዊው የጦር ሜዳ ሆስፒታል በቦምብ በተደበደበ ጊዜ ግዳጃቸውን እየተወጡ ሳለ ከሞት ለጥቂት መትረፋቸውም ይጠቀሳል::
እንዲህ መሰል በርካታ የሞት አደጋዎች እንደገጠሙት የሚነገርላቸው ቮን ሮዘን በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ በወቅቱ ቢሾፍቱ የተባለችውን ትንሽ መንደር የጎበኙ ሲሆን የበረራ ትምህርት ቤትና ለስራው የሚያስፈልገውን አውሮፕላን ማረፊያ መስራት የሚቻልበትን መንገድ ጥናት ማድረጋቸውን ይጠቀሳል:: እንዲሁም ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያገለግሉ ሲቪል አውሮፕላን አብራሪዎች ይሰለጥኑበታል በሚል ግምት አየር ኃይል ማቋቋማቸውን ግለ-ታሪካቸው ያስረዳል:: ካርል በወቅቱ አየር ሃይሉን የማቋቋም ሃሳብ ሲያቀርቡ ከንጉሱ ተቋውሞ አልገጠማቸውም ነበር::
ምክንያቱም ደግሞ ንጉሱ አገሪቱ ከአየር የሚደርስባትን ጥቃት ለመከላከል በማትችልበት ሁኔታ ተጋላጭ ሆና ላለመገኘት ቁርጥ አቋም ስለነበራቸው እንደሆነ ይነሳል:: በመሆኑም ውጤታማ የሆነ አየር ኃይል መመስረት እና ለዚሁ የሚሆኑትን አብራሪዎች ማሰልጠን ለነገ የማይባል አቢይ ጉዳይ እንደሆነ ታምኖበት ፍቃዳቸውን አገኙ:: እንዲያውም ከዚያ በኋላ ንጉሱ የአየር ኃይላቸውን ዕድገት የሚከታተሉት በከፍተኛ ንቃት እንደነበርም ይጠቀሳል::
ለዚህ ሲሉም በቢሾፍቱ ላይ የእረፍት ጊዜ ማረፊያ ቪላ ሰርተው እንደነበር እንዲሁም ከሰገነት ላይ ሆነው ወደ አየር ኃይሉ እያነጣጠሩ ካዴቶቹ ሲነሱ እና ሲያርፉ እየተመለከቱ እንደሚውሉ ተዘግቧል:: የመጀመሪያዎቹ የአብራሪዎች ቡድን ሲመረቁ በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው የአብራሪዎች አርማ የሆነውን ክንፍ በደረቶቻቸው ላይ ያኖሩላቸው ንጉሱ ራሳቸው መሆናቸውንም ታሪክ ያወሳል:: ካርል ጉስታቭ አጥጋቢ አገልግሎት መስጠት የሚችል የአየር ኃይል ከስዊድኑ አየር ኃይል ጋር በመወያየት በአጭር ጊዜ ውስጥ በመስራት ለንጉሱ ማስረከብ ችለዋል::
እንደሚታወቀው በወቅቱ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሹመት እጅግ ወሳኝ ነገር ነበር:: ነገር ግን ሹመት ሁልጊዜ በውርስ የሚገኝ ነገር አልነበረም:: ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የፈቀዱትን ሹመት ለፈቀዱት ሰው በራሳቸው ፈቃድ ይሰጣሉ:: ከእነዚህም ሹመት እና ሽልማት ውስጥ ንጉሱ ለካርል ጉስታቭ የሰጡት ተጠቃሽ ነው:: ይህ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ወዳጅ ሱዊዲናዊ ለሀገሪቱ ላበረከቱት አስተዋፅኦ በ1960 ዓ.ም በንጉሱ ቤተ- መንግስት በቀዩ ሳሎን የክብር ኒሻን የተሸለሙ መሆኑን ይኸው መፅሐፍ ያስረዳል:: ኢትዮጵያ ውስጥ ለነጻነት ተዋጊዎች እና ለአርበኞች ፣ በድርቅ ለተጎዱ ፣ በረሀብና በወረርሽኝ ለተጠቁ ፈጥኖ ምግብ በማቅረብ፣ ለህክምና እርዳታ ፣ ለአርብቶ አደሮች መሠረታዊ ፍጆታ የምርት እጥረት ሲያጋጥም የአየር በረራ አገልግሎት ለሚፈልጉት ሁሉ ፈጥኖ በመድረስ አቅማቸውን እና ዘመናቸውን ሙሉ ኢትዮጵያን ሲያገለግሉ ስለመኖራቸው መጽሐፉ ምስክርነቱን ሰጥቷል::
ከጀርባው የሚፈፀምበትን ሴራ ተቋቁሞ መስራት እንጂ ፈጽሞ አማርሮ እንደማያውቁ የሚነገርላቸው ካርል ፤ በተለይም ቀይ መስቀል ውስጥ በህክምና አብራቸው በቅርበት የሰራች ነርስ ስለ እርሳቸው ባሰፈረችው ማስታወሻ ‹‹ቮን ሮዘን ከብዙ ረጅምና አድካሚ ጉዞ በኋላ ወደ ቤተሰቡ ሲመለስ ዘወትር የተሸበሸበ ፊቱ ቁልቁል ተንጠልጥሎ መቆም ተስኖት እስኪወድቅ ድረስ በድካም ዝሎ ነበር የሚደርሰው:: ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ ሳገኘው እንዲህ ያለ ገፅታ ነበረው:: ነገር ግን በጣም የሚገርመኝ ከአንድ ሌሊት ዕረፍት በኋላ የተሸበሸበ ፊቱ ተመልሶ ይዘረጋ እና ወደ ወጣትነት ሲመለስ ዘወትር ፈገግታ ከፊቱ የማይለየው “ህይወት እጅግ መልካም ነገር ነው” ወይም ደግሞ “ማግባት እኮ ደስ ይላል” ወ.ዘ.ተ ከሚሉ መልካም ቃላት በቀር ክፉ ነገር የማይወጣው ከትናንቱ ፈጽሞ የተለየ ሌላ ሰው መሆኑ ነበር›› ብላለች::
በሌላ በኩል የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ “በአየር በረራ” ሲሉ የሰየሟት አነስተኛ መጽሐፍ ፅፈው ማሳተማቸውን “ድሮና ዘንድሮ” በተሰኘ ግለ-ታሪካቸው ተጠቅሷል:: የዚያን ጊዜው ወጣቱ መቶ አለቃ ግርማ፣ የካርል ጉስታቭ የልብ ወዳጅ እና የሚቀራረቡትም የቤተሰብ ያህል ነበር:: ትስስራቸውም ብዙ ምዕራፎች ውስጥ ይወሳል:: በፎቶ የተደገፈ ሰፊ ሽፋን ሰጥቶት ካርል ወዝ ባለው አግባብ ተርኮታል:: በካርል ኃላፊነት መረከብ የሚችሉ በቂ አብራሪ ኢትዮጵያውያን ሰልጥነዋል ፤ ከእነዚህ መሀል ግርማ አንዱ ነበሩ::
ከአየር ኃይል በኋላም በስዊድን እና በካናዳ የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ትምህርት ተምረው መመለሳቸውን የህይወት ታሪካቸው ላይ ተዘግቧል:: ካርል ልባዊ ጓደኝነታቸውን በሚመለከት በዚሁ መጻሐፍ ላይ ‹‹ከብዙ ኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ጋር ያስተዋወቀን እርሱ ነበር:: በኢትዮጵያ ውስጥ በሠራነው ስራ ሁሉ እጅግ ትልቅ ድርሻ ነበረው::
በብዙ ረገድ ይረዳን ነበር:: ከስራ ሰዓት ውጪ የሚያዝናናን መልካም ወዳጃችን ነበር:: ብዙ ጊዜም ግብዣዎች ሰርጎችና ፓርቲዎች ላይ ይጋብዘን ነበር:: ትከሻ እያንቀጠቀጡ የሚደነሰውን የኢትዮጵያን እስክስታ ያስተማረኝም እርሱ ነው:: በኢትዮጵያ ውስጥ ያሳለፍናቸው መልካም ጊዜያት ሁሉ ከእርሱ ጋር ያሳለፍናቸው ነበሩ›› በሚል ተጠቅሷል::
ይኸው የተርጓሚ እና ደራሲ ሚካኤል ሺፈራው መጽሐፍ የባለታሪኩ የካርል ጉስታቭ ቮን ሮዘን ታሪክ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን የቅርብ ጊዜ የትዝታ ማህደር ጭምር ነው:: ባለታሪካችን በማይጨው ዘመቻ መጀመሪያ ምዕራፍ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡበት 1928 ዓ.ም ይጀምርና ሶማሊያ በዚያድ ባሬ እየተመራች ኢትዮጵያን ለማጥቃት በተለይ ኦጋዴንን ስትወር 1969 ዓ.ም ላይ የሚጠናቀቅ የአርባ አንድ አመት ሰነድ ነው::
የጠፋውን የታሪካችንን ዱካ በካርል በኩል በምልሰት የሚያስቃኝ የአባቶቻችንም ታሪክ ነው:: ዛሬ እናፈርሳታለን በሚል የሚናቆሩባት አገራችን፤ እንዴት ያለ የላብ እና የደም ዋጋ ተከፍሎባት ከኛ ትውልድ እንደደረሰች የሚነግረን የዘመን ታማኝ ምስክር ነው:: ካርል ሊኖርባትና ሊኖርላት ብቻ ሳይሆን ሊሞትላትም ለተዘጋጀላት ኢትዮጵያን፣ የነበረው ብርቱ ፍቅር ከምንም በላይ ልብ ይነካል:: እኛም የእኚህን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያን አፍቃሪ ሱዊዲናዊ አብራሪን በእንዲህ መልኩ ልንዘክራቸው ወድደናል::
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2015