ኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ የአዋቂ ወንዶች ቴኒስ ውድድር እንደምታስተናግድ የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን ከትናንት በስቲያ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። ውድድሩ ከግንቦት 6-20/2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቴኒስ ክለብ እንደሚካሄድም ተገልጿል።
ባለፈው የካቲት ወር ኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ የዓለም ታዳጊዎች ቻምፒዮናን አስተናግዳ በስኬት ማጠናቀቋ ይታወሳል። በውድድሩም 14 ኢትዮጵያውያን ስፖርተኞች ተሳትፈው ሦስቱ የዓለምአቀፍ ደረጃ ማግኘት ችለዋል። ኢትዮጵያ በዚያ ውድድር ባሳየችው የመስተንግዶ ጥራት አሁን ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ አዋቂ ስፖርተኞች የሚሳተፉበት ዓለምአቀፍ ውድድርን ለማዘጋጀት በድጋሚ ተመርጣለች።
ውድድሩ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚዘጋጅ ሲሆን ወንዶች ብቻ የሚሳተፉበት ውድድር ነው:: ፌዴሬሽኑ በቀጣይ የሴቶች ውድድርንም ለማዘጋጀት እንደሚሠራ ጠቁሟል። ውድድሩ የፊታችን እሁድ በ5ቱም የአዲስ አበባ ቴኒስ ክለብ ሜዳዎች ይጀመራል።
ውድድሩ በሥልጠና ለቆዩ ስፖርተኞች የውድድር ዕድልን ከመፍጠር ባሻገር ስፖርቱ በዓለምአቀፍ ደረጃ ያለበትን ደረጃ ለመገምገም አላማ አድርጎ እንደሚካሄድም ተነግሯል። ውድድሩ በአገራችን በመዘጋጀቱ የውጭ ምንዛሬን ከማምጣቱም በተጨማሪ ለገጽታ ግንባታ የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል። እስከ አሁን 4 ኢትዮጵያውያን ቴኒስ ተጫዋቾች ለውድድሩ የተመዘገቡ ሲሆን፤ ቁጥራቸው ከዚህም ሊልቅ እንደሚችል ይጠበቃል።
በውድድሩ ከ27 አገራት የተውጣጡ 60 የቴኒስ ስፖርተኞች ፋለማሉ። ለውድድሩ መሳለጥ በአጠቃላይ በውድድሩ ላይ ስፖርተኞችን ጨምሮ ከመቶ በላይ ሰዎች ተሳታፊ ይሆናሉ:: በዓለምአቀፍ ደረጃ 300 እና በላይ ውጤት ያላቸው ስፖርተኞች የሚሳተፉበት ዓለምአቀፍ ውድድር በመሆኑ ከፍተኛ ፉክክርን ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል:: ዝግጅቱ የተሳለጠ እንዲሆን ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ እንቅስቃሴ እንደገባም ታውቋል:: በሕዝብ ግንኙነት፣ በጤና፣ ጸጥታ እና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የተዋቀረው ኮሚቴ ሥራዎችን እንደሚሠራም ተገልጿል::
በሁለት ዙሮች የሚካሄደው ይህ ውድድር በእያንዳንዱ ዙር ለሽልማት 15ሺ ዶላር በአጠቃላይ 30ሺ ዶላር መዘጋጀቱ ተጠቁሟል። ዓለምአቀፍ ደረጃ የተሰጠው ውድድር በመሆኑም አሸናፊዎቹ ዓለምአቀፍ ደረጃን የሚያገኙ ይሆናል። በአብደላ ነዲቭ ኢቨንት ኦርጋናይዘር አዘጋጅነት የሚደረገው ውድድር ስፖርተኞች የውድድር ዕድልን እንዲያገኙና ዓለምአቀፍ ውድድሮችን ወደ አገራችን ለመሳብ ታስቦ እንደሚካሄድ ተነግሯል። ውድድሩ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ የሚካሄድና ለዚህም በቂ ዝግጅት መደረጉን ተጠቅሷል።
ከኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ውድድሩን የሚያዘጋጀው አብደላ ነዲ ሁነት ስለ ቴክኒካዊ ጉዳች በሰጠው ማብራሪያ፤ ካለፈው የወጣቶች ቻምፒዮና ጠቃሚ ልምዶች ስለተገኘ የአሁኑ ውድድር በተሻለ ሁኔታ ለማዘጋጀት ሥራዎች በመሠራት ላይ እንደሚገኙ ጠቅሷል:: ከማዘውተሪያ ስፍራ፣ ከሆቴል፣ ከሚዲያ ጋር ከሚደረግ ግንኙነት፣ ስፖንሰር ከመፈለግ፣ ለውድድር ስለሚያስፈልጉ ግብዓቶች እና በአጠቃላይ ለውድድር ስለሚያስፈልጉ ነገሮች ልምድ በመወሰዱ የተሻለ ዝግጅት እንደሚሆንም ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታምራት በቀለ ኢትዮጵያውያን ስፖርተኞች ጠንክረው ከሠሩ ከሽልማቱ ተቋዳሽ መሆን የማይችሉበት ሁኔታ እንደማይኖር ገልፀዋል። እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፣ የውድድሩ አላማ ሽልማት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ቴኒስ ስፖርተኞች ዓለምአቀፍ ውድድር በማድረግ ውጤት እንዲያገኙ ማስቻል ነው:: መገናኛ ብዙኃን ውድድሩ ትኩረት እንዲያገኝና የተሳካ እንዲሆን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል::
ዓለምአቀፉ የቴኒስ ፌዴሬሽን የተለያዩ ድጋፎችን የሚያደርግ ሲሆን ለተወዳዳሪዎች ነጥብ መስጠትን ጨምሮ 5 ዳኞችንም እንደሚመድብ ተጠቅሷል። ለውድድሩ መሳካት ስፖርት አፍቃሪውና ድርጅቶች ድጋፍ በማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ ተላልፏል። ውድድሩ ዓለምአቀፍ እንደመሆኑ ለስፖርተኞች የዶፒንግ እና የኮቪድ-19 ምርመራ ይደረግላቸዋል::
የአየር ንብረቱ ውድድሩ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመቋቋም እንደሚሠራ የተጠቆመ ሲሆን ለዚህም የተለያዩ መፍትሄ አማራጮችን በመውሰድ ዝግጅት ይደረጋል:: ለዚህም ውድድሩን ከሚዳኙት ዳኞች ጋር ውይይት ይደረጋል:: የመጫወቻ ሜዳው በዝናብ ወቅት እንዳይጨቀይና ምቹ እንዲሆን የሜዳ ንጣፍን በመጠቀም ውድድሩ የተሳካ እንዲሆን ጥረት ይደረጋል::
ኢትዮጵያ በቀጣይ እአአ ሰኔ 5/2023 በሴቶች በሩዋንዳ ኪጋሊ እና ሰኔ 20/2023 በወንዶች ዴቪስ ካፕ በአህጉር አቀፍ ውድድሮች የምትሳተፍ ይሆናል። የሴቶች ቡድን ምርጫ የተጠናቀቀ ሲሆን የወንዶች ማጣሪያ ተደርጎ ምርጫው ይከናወናል:: ለውድድሮቹ ዝግጅት ከ1ወር በላይ ጊዜ የሚቀር ሲሆን ውድድሮቹ ሲቀርቡ በካምፕ በመሰባሰብ እና አሰልጣኝ በመመደብ ልምምዳቸውን እንደሚያደርጉም ፌዴሬሽኑ ጠቁሟል:: በዚህም መሠረት የአሁኑ ውድድር በአገራችን መዘጋጀቱ ብሔራዊ ብድኑ ዓለም አቀፍ ልምድ እንዲያገኝ ይረዳዋል ተብሎ ይጠበቃል::
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2015