የዚህ ዓመት የዳይመንድ ሊግ ውድድር በኳታሯ ዶሃ ተጀምሯል። ውድድሩን ተከትሎም የአትሌቲክስ ቤተሰቡ ትኩረቱን በተለይ ያደረገው በ3ሺ ሜትር ርቀት መሆኑ ይታወቃል። ምክንያቱ ደግሞ በርቀቱ ባለ ድንቅ ብቃት ባለቤት አትሌቶች በዶሃ በመሰባሰባቸው ሲሆን፤ ቅድመ ግምት አግኝተው የነበሩት ሦስቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እንደተጠበቁትም ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ በመያዝ ዳይመንድ ሊ ጉን በድል ጀምረዋል።
ይህ ሩጫ ከውድድርነቱ ባለፈ የርቀቱ ምርጥ አትሌት ማን ሊሆን ይችላል የሚለውን የመለየት እድል የሰጠም ሆኗል። ከሁለት ወር በፊት በሌቪን የ3ሺ ሜትር ርቀት የዓለም ክብረወሰንን የግሉ ያደረገው ወጣቱ አትሌት ለሜቻ ግርማ ዳይመንድ ሊጉን በበላይነት ሊፈጽም እንደሚችል ተገምቶ ነበር። ከአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ተነስቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልልቅ የውድድር መድረኮች ላይ ብቃቱን ማስመስከሩ ደግሞ የአሸናፊነት ሚዛኑ ወደ እርሱ እንዲያጋድል አድርጎታል። በእርግጥ በርቀቱ ከሚካፈሉት ጠንካራ አትሌቶች አንጻር ፈታኝ ሊሆንበት እንደሚችልም ይጠበቅ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ለዓመታት የርቀቱን የበላይነት ተቆጣጥሮት የቆየው ሞሮኳዊው አትሌት ሶፊያን ኤል ባካሊ በኳታሯ መዲና ዶሃ ወደ ውድድር እንደሚመለስ በማረጋገጡ ነበር።
በቶኪዮ ኦሊምፒክ እንዲሁም በዩጂኑ የዓለም ሻምፒዮና ለሜቻን የረታው ኤል ባካሊ ይህ ውድድር ለቡዳፔስቱ የዓለም ሻምፒዮና አቋሙን የሚመዝንበት እንደሚሆን አስቀድሞ አሳውቆ ነበር። በአንጻሩ የሁለት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮኑ እና የቶኪዮ ኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያባለቤቱ ለሜቻ፤ ባለፈው ዓመት በተካሄደው የቤልግሬድ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮናም የብር ሜዳሊያ ማጥለቁ የሚታወስ ነው። በተያዘው የውድድር ዓመት ደግሞ በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ተሳትፎው ሌቪን ላይ 3ሺ ሜትር ርቀትን 7:23.81 በሆነ ሰዓት በመሸፈኑ የክብረወሰን ባለቤት መሆን ችሏል።
ይህም የ22 ዓመቱን አትሌት በርቀቱ ቅድሚያ ተጠባቂ ሲያደርገው ዶሃ ላይም እንደተለመደው ብቃቱን በማስመስከር አሸናፊ ሊሆን ችሏል። ባለ ድንቅ ተሰጥዖው አትሌት ውድድሩ 500 ሜትር ሲቀረው የሃገሩን ልጆች አስከትሎ ተስፈንጥሮ የወጣ ሲሆን፤ 7:26.18 በሆነ ሰዓትም አሸናፊነቱን መረጋገጥ ችሏል። በቶኪዮ ኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር ሻምፒዮን የሆነው ሌላኛው አትሌት ሰለሞን ባረጋ ደግሞ 7:27.16 የሆነ የግሉን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ሁለተኛ ደረጃ ሊይዝ ችሏል። በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ርቀቶች የሚታወቀው አትሌቱ፤ እአአ 2018 ላይ በበርሚንግሃም እንዲሁም ያለፈው ዓመት የቤልግሬድ የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የብር እና የወርቅ ሜዳሊያዎችን በዚህ ርቀት አግኝቷል።
በ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ የዓለም ክብረወሰን ባለቤቱ እንዲሁም በቅርቡ በተካሄደው የዓለም ሃገር አቋራጭ ሻምፒዮና የብር ሜዳሊያ አሸናፊው አትሌት በሪሁ አረጋዊ ደግሞ የነሐስ ሜዳሊያውን የግሉ ማድረግ ችሏል። ወጣቱ አትሌት እአአ 2021 ዳይመንድ ሊግ የ5ሺ ሜትር አሸናፊ ሲሆን፤ በ3ሺ ሜትር ደግሞ በወጣቶች ሻምፒዮን ነው። በዶሃም 7:27.61 በሆነ ሰዓት መሮጥ ችሏል። ይህም በዚህ ውድድር ሦስቱ አትሌቶች 7 ደቂቃ ከ28 ሰከንድ በታች በመግባት በታሪክ ሁለተኛው አድርጓቸዋል። ሞሮኳዊው አትሌት ደግሞ ኢትዮጵያውያኑን ተከትሎ በአራተኝነት ውድድሩን አጠናቋል።
በሴቶች በኩል በተካሄዱ ውድድሮችም በተመሳሳይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አስደሳች ውጤቶችን ማስመዝገብ ችለዋል። በ1ሺ500 ሜትር ውድድር የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮናዋ ፌይዝ ኪፕዬጎን አሸናፊ ስትሆን፤ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ደግሞ ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነዋል። እጅግ ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረችው ድርቤ ወልተጂ በአንድ ሰከንድ ብቻ ተበልጣ 3:59.34 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ ሁለተኛ ሆናለች። ሌላኛዋ አትሌት ፍሬወይኒ ሃይሉ በበኩሏ 4:00.29 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ በመሆን ገብታለች። ጠንካራ ፉክክር የታየበት ሌላኛው ውድድር በ3ሺ ሜትር የተደረገ ሲሆን፤ ባሕሬናዊቷ ዊንፍሬድ ሙትሌ ያቪ አሸናፊ ሆናለች። ለአሸናፊነት ብርቱ ፉክክር ያደረገችው ኢትዮጵያዊቷ ወጣት አትሌት ሲምቦ አለማየሁ በ1 ሰከንድ ብቻ ተቀድማ ሁለተኛ ልትሆን ችላለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 29 ቀን 2015 ዓ.ም