የትኛውም ስፖርታዊ ውድድር ተመጋጋቢ በመሆኑ ለቀጣይ ውድድር የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ ነው:: ሥልጠናን ለመገምገም ሆነ ወቅታዊ አቋምን ለማወቅ ምዘናዎችን በየደረጃው ማከናወን ለአንድ ስፖርት አስፈላጊ ነው:: ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ይህ ሁኔታ መቀዛቀዝ እየታየበት ነው:: የዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎን በሚመለከትም ፌዴሬሽኖች ድጋፍ በማጣት ሃገራቸውን መወከል እየተሳናቸው በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚያቀርቡበት ሁኔታ እየተበራከተ ነው::
ይህንን ተከትሎም በኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ በቀለ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት ማብራሪያ፣ ዓለም አቀፍ የውድድር ተሳትፎን በሚመለከትም ድጋፍ የሚደረግላቸው ስፖርቶች በዋናነት በአህጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ ለሆኑ ስፖርቶች ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል:: ቡድን መሪው እንደሚያብራሩት የስፖርት ማኅበራቱ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጥያቄ በሚያቀርቡበት ጊዜ ይሁንታ ሊያገኙ የሚችሉት፤ ውጤታማነታቸው፣ ለሃገር ገጽታ ግንባታ የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ እንዲሁም የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ማስፋት መቻላቸው ተመዝኖ ነው::
በዚህ መንገድ ካልሆነ ግን በሃገሪቷ ላሉት ከ31 በላይ የስፖርት ማኅበራት፤ ለውድድር ከሚመደበው 22 ሚሊዮን ብር ላይ መደገፍ አዳጋች ነው:: በመሆኑም ማኅበራቱን በመስፈርቱ መሠረት በመለየት የገንዘብ ድጋፍ አሊያም የትብብር ደብዳቤ በማዘጋጀት ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል:: ያም ሆኖ እንደ እግር ኳስ ያሉ የስፖርት ማኅበራት በሚሰጣቸው ድጋፍ መሠረት ውጤታማ ሲሆኑ አይስተዋልም:: በመሆኑም ከዚህ በኋላ ድጋፍ ለማድረግም ሆነ ድጋፉን ለማስቀረት መነሻ የሚሆን ጥናት በመካሄድ ላይ ይገኛል:: ይኸውም ውጤት ላለመመዝገቡ ትክክለኛው ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን ለመለየት ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ በሚያካሂደው ጥናት ነው::
ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመቅረፍም አማራጭ መፈለግ አስፈላጊ በመሆኑ ሚኒስትሩ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል:: በዚህም የተለያዩ ሃገራት ኤምባሲዎችን ድጋፍ እንዲያደርጉለት በማነጋገር በመረጡት ሁኔታ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችላቸው የምክክር መድረክ ይዘጋጃል:: ይህም ከሌሎች ሃገራት ልምዶች በመነሳት መሆኑንም ሥራ አስፈጻሚው አመላክተዋል:: የስፖርት ማኅበራቱም ይህንን በመመልከት ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ እንዲችሉ መንገድ ከፋች መፍትሔ ነው ተብሎ ታምኖበታል:: ከዚህ ባሻገር በአንዳንድ የስፖርት ማኅበራት የሚታዩና ለሌሎችም ተምሳሌት መሆን ከሚችሉ የማኅበራት ሥራ አስፈጻሚዎች ልምድ መውሰድ አስፈላጊ ነው::
ሃገር አቀፍ ውድድሮችን በሚመለከትም በተያዘው ዓመት የተሠራው ስኬታማ አለመሆኑን ሥራ አስፈጻሚው አልሸሸጉም:: በሚኒስትሩ አዘጋጅነት የሚደረጉ ሃገር አቀፍ ውድድሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቋርጠዋል:: ለዚህም ምክንያት የሆነውም የሃገሪቷ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ሲሆን፤ ለሰላም መሣሪያ የሆነው ስፖርት በተቃራኒው የጠብ መሣሪያ ሲሆን የሚስተዋልበት አጋጣሚ ስጋት ሆናል:: ነገር ግን በመጪው ዓመት የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎችን ለማስጀመር ዕቅድ ተይዟል፤ በዚህም ከስፖርታዊ ውድድርነት ባለፈ የዲፕሎማሲ መሣሪያ እንዲሆንም ይሠራል ተብሏል:: ውድድሩ ከቀድሞ በተለየ መልክ እንዲካሄድም የተለያዩ ዘዴዎች ተግባራዊ ይሆናሉ:: በተጨማሪም የተማሪዎች ውድድርን ከትምህርት ሚኒስትር ጋር በመሆን እንዲሁም የሴቶችና የአርሶ አደር ውድድሮችንም ለማካሄድ ታቅዶ እየተሠራ ነው::
በሌላ በኩል የስፖርት ማኅበራትም ውድድሮችን እንደቀድሞ እያዘጋጁ አለመሆኑ ይስተዋላል:: አቅም ያላቸው ፌዴሬሽኖች በበኩላቸው ውድድር እያዘጋጁ ሲሆን፤ አቅሙ የሌላቸው ግን ማካሄድ አልቻሉም:: ለዚህም ፌዴሬሽኖች በገቢ ራሳቸውን ለመቻል የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ እንደሆነ ሥራ አስፈጻሚው ይናገራሉ:: ሚኒስትሩ የሚያደርግላቸውን የበጀት ድጋፍ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ ከማዋል ይልቅ እያባከኑ መሆኑ ስለደረሰበትም ኦዲት መደረግ እንደሚገባቸው ተወስኗል:: ከዚህ ጋር በተያያዘ ፌዴሬሽኖች ሕጋዊ እውቅና እና ፈቃድ በየጊዜው ማግኘት እንዳለባቸው ቢወሰንም አብዛኛዎቹ ጋር የሚስተዋለው ሽሽት ነው:: ይህ ሁሉ ሲሆን ፈቃደኛ ያልነበሩት እነዚህ ፌዴሬሽኖች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሲኖሩባቸው ደግሞ ድጋፍ ፍለጋ ወደ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ያቀናሉ::
ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ በቅርቡ ተግባራዊ ባደረገው መዋቅር መሠረት ፌዴሬሽኖች ራሳቸውን እንዲችሉ፣ የማይችሉ ደግሞ በተዘጋጀው አማራጭ እንዲንቀሳቀሱ ተደርጓል:: ይኸው ከአደረጃጀት ጋር ተያይዞ የመጣው አለመረጋጋትም በዓመቱ ውድድሮች አስፈላጊ በሆነ መልክ እንዳይካሄዱ ምክንያት ሆኗል:: ተከታታይና ተመጋጋቢ የሆኑ ውድድሮችን ማካሄድ አለመቻል በዓለም አቀፍ ደረጃ ሃገርን ውጤታማ እንዳትሆን ያደርጋል:: ይኸው የበጀት እጥረት እና የአመለካከት ችግርም በተፈለገው መልክ ለመራመድ አዳጋች እንዳደረገውም አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2015