የቀድሞው የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በንጉሱ ዘመን በ1948 ዓ.ም ሲመሰረት ከሶስቱ የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት አንዱ ሆኖ ሙሉ በሙሉ ራሱን የቻለ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመ ነው፤ ዋነኛ ተልዕኮውም የቀይ ባህርን የባህር ዳርቻ ለመጠበቅ ነበር፡፡ በንጉሠ ነገስሥቱ ዘመን የተቋቋመው የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ውስጥ በመግባት በወቅቱ ከነበሩ ምርጥ የዓለማችን የባህር ኃይል አባላት ጋር ተወዳዳሪና ብቁ ለመሆን የሚያስችላቸውን ስልጠናም ወስደዋል – የዛሬው የዘመን እንግዳችን።
ለዓመታት የተመሰረተበትን ዓላማ በብቃት ሲወጣ የነበረው ስመጥር የኢትዮጵያ ባህር ኃይል 1983 ዓ.ም በነበረው ለውጥና ኤርትራ ራሷን ችላ ሉዓላዊ አገር ስትሆን የባህር ኃይሉ በዛው ከሰመ፡፡ በወቅቱ ሌፍተናንት ዮሴፍ ሸጋው በቀድሞ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ረዳት ትምህርት መኮንን የነበሩ። እኚህ ሰውም ከባህር ኃይሉ ጋር የነበራቸው ውል የተቋረጠው እዚህ ላይ ነው።
ሌፍተናንት ዮሴፍ ተወልደው ያደጉት በአዲስ አበባ ልደታ አካባቢ ነበር። ሌፍተናንት በወቅቱ በነበረው የልጆች አስተዳደግ ደንብ ልጆች ጎረቤቱም የቤቱም ማህበረሰብ በጋራ ሆኖ በምግባር ስላሳደጋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ይናገራሉ። ሌፍተናንት አንደኛ ደረጃ በተስፋ ኮከብ ትምህርት ቤት፤ ሁለተኛ ደረጃን በአዲስ ከተማ ትምህርት ቤት እየተማሩ ሳለ ነበር የባህር ኃይል የሚያሰለጥናቸው ወጣት የባህር ኃይል ወታደሮች እንደሚፈልግ የሰሙት።
ቀድሞ የባህር ኃይል አባል የነበረ ጓደኛ የነበራቸው ሌፍተናንቱ፣ በወቅቱ የመገናኛ ዘዴ በነበረው በፖስታ ቤት በኩል የተለያዩ ፎቶግራፎች ይልክላቸው ስለነበር ቀድሞ ልባቸው ውስጥ ተጠንሰሶ የነበረው የባህር ኃይል አባል የመሆን ፍላጎት ለማስቀጠል ሄደው ይመዘገባሉ። በ1967 ዓ.ም አብዮት በተቀጣጠለበት ወቅት ወደ ባህር ኃይል የገቡት እኚህ ሰው ወደውና ፈቅደው በገቡበት የባህር ኃይል ለዓመታት ሲያገለገሉ ቆዩ።
በ1948 ዓ.ም በንጉሱ ጊዜ አንድ ብሎ የጀመረው ባህር ኃይል በ1983 ዓ.ም ሲፈርስ ሌፍተናንት ዮሴፍ አብረው እንደነበሩ ይናገራሉ። ሌፍተናንቱ ለአስራ ሰባት ዓመታት ያገለገሉበት የባህር ኃይል አባላትም በውጭ አገራት የተለያዩ መርከቦች ላይ ተበትነው ይሰሩ ጀመር። እኚህ ሰው ከረጅሙ የህይወት ልምዳቸው ያካፈሉንን በዚህ መልኩ አቅርበነዋል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- የቀድሞ የባህር ኃይል አባላት ማህበር ፕሬዚዳንት እንደመሆንዎ የቀደመውን የሰራዊት ሁኔታ እንዴት እንደነበር ቢያብራሩል?
ሌፍተናንት ዮሴፍ፡– በወቅቱ የጦር ኃይል ተብሎ የሚጠራው የአንዲት አገር ሉአላዊነት የሚያስጠበቅ፣ አገር በነፃነት እንድትሄድ ዳር ድንበሯን አስጠብቆ የሚያቆይ አካል ጦር ኃይል ይባላል። የባህር ኃይል ደግሞ በጦር ኃይል ውስጥ ካሉ የተለያዩ ክፍሎች አንዱ ነው። አንድ አገር የአየር ክልል እንዳላት ሁሉ፤ የባህር ክልል ይኖራታል፤ የየብስ ክልል ይኖራታል። ይህንን ቦታ ደግሞ የሚያስጠብቅ ኃይል አሰልጥና ትገነባለች።
በሰዓቱ በቀይ ባህር ላይ ኢትዮጵያ የነበራትን ከአንድ ሺ ኪሎ ሜትር በላይ ቦታ የሚያስጠብቅላትን ኃይል ባህር ኃይል ብላ አደራጅታ ነበር። በምሰራቅ አፍሪካ ያለውን በርካታ ትርምስ የሚቆጣጠር አገሪቱ በባህር በኩል ከሚመጣባት ችግር የሚከላከል እንዲሁም ሙሉ የባህሩን ክልል ሰላም የሚያስጠብቅ የጦር ሰራዊት አካል የባህር ኃይል ይባላል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ባህር ኃይል ለምን ያስፈልጋታል?
ሌፍተናንት ዮሴፍ፡- ኢትዮጵያ አሁን የባህር በር ባይኖራትም የባህር ኃይል ለአንዲት አገር ወሳኝ ጉዳይ ነው። የባህር በር ሳይኖራቸው የባህር ኃይላቸውን ያደራጁ አገሮችን ለመጥቀስ ያህል ፓራጓይ፣ አዘርባጃን እና ቦሊቪያ እንደ ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላቸው አገራት ናቸው:: ነገር ግን በቂ የባህር ኃይል አላቸው:: አሁን ባለው ሁኔታ ዘጠና ከመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ የሚሳለጠው በውሃ ላይ በሚደረግ ጉዞ ነው:: በተለይም እ.ኤ.አ ከ2008 እስከ 2010 በምስራቅ አፍሪካ የነበረውን የባህር ላይ ውንብድና አስቸጋሪነት የባህር ኃይል መኖሩ አስፈላጊ ነው ማለት ነው:: እንደዚህ ዓይነት የአገራትን ጥቅም የሚጎዱ ውንብድናዎችን ለመከላከል የባህር ኃይል ወሳኝ ነው:: ምክንያቱም አሁን ባለው ዓለማቀፍ ሁኔታ በአንድ ቀጣና የሚፈጠር ችግር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አለማቀፋዊ ችግር ይሆናል::
በሌላ ረገድ ኢትዮጵያ ያሏትን የንግድ መርከቦችና ለአገር ያላቸውን ፋይዳ ማየት ነው:: የአስራ አንድ የንግድ መርከቦች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ባንዲራዋን እያውለበለቡ ከአህጉር አህጉር የሚዘዋወሩት መርከቦቿ ደህንነት ተጠብቆ በሰላማዊ ሁኔታ ስራቸውን ለማከናወን አስተማማኝ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፤ ለዚህም በዘርፉ የሰለጠነ የባህር ኃይል መኖር ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል ኢትዮጵያ የነበራት ሰራዊት እንዴት ይገለጻል?
ሌፍተናንት ዮሴፍ፡- በየጊዜው የተለያዩ ስያሜዎች የሚሰጡት የጦር ኃይል፣ የጦር ሰራዊት፣ መከላከያ ሰራዊት ሲባል የሚቋቋምበት ዓላማ አለው። አንድ አገር ህልውናዋን አስጠብቃ እንድትቀጥል መከላከያ ኃይልን መገንባት ግዴታዋ ነው። ይህ መከላከል የሚለው ቃል ለአንድ አገር በተፈጥሮ የተሰጣትን ሀብት ለመጠበቅ እንጂ ሌሎችን ሄዶ መጉዳትን ዓላማው አድርጎ የሚንቀሳቀስ አይደለም። ለመከላከል ደግሞ ጥንካሬ ያስፈልጋል፤ ያንን ጥንካሬ ለማምጣት በስልጠና የታገዘ ሙሉ ሎጀስቲክ ወሳኝ ነው:: እንዲሁም የተሟላለት እና ለአገር ደህንነት ዘብ ለመቆም የሚችል ብሎም ለራሱ ደህንነቱ የተጠበቀ ሰራዊት እንዲኖር ያስፈልጋል።
እንኳን በአንድ አገር በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ከጉዳት የሚከላከል አካል ያስፈልጋል። በአንድ ቤተሰብ ውስጥ አባት ካለ አባት ቤተሰቡን ይጠብቃል። ኢትዮጵያም በዓለም ውስጥ ያለች አንድ አገር እንደመሆኗ የተሰጣትን ክልል ዳር ድንበሯን የማስጠበቅ ግዴታ አለባት። ያንን ለማስጠበቅ ደግሞ መከላካያ ሰራዊት ያስፈልጋል።
ይህ መከላከያ ሰራዊት ሲቋቋም የራሱ የሆነ መስፈርቶች ቢኖሩትም ቀለምና ዘር ሳይቆጥር የተዋቀረ፣ አገሪቱ ውስጥ ያለውን ህብረ ብሄራዊነት በሚያስጠብቅ መልኩ የተውጣጣ እንዲሁም ከምንም ነገር በፊት ኢትዮጵያን ሊያስቀድም የሚችል ሰራዊት መሆን ይገባዋል። ሰራዊት ሲቋቋም ዓላማው አንድና አንድ ነው፤ የኢትዮጵያን ነፃነት ማስቀጠል፣ ዳር ድንበራን ማስጠበቅ እና ያቺን አገር በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ በምትታወቅበት ነፃነት እንድትቀጥል ማድረግ ነው።
መከላከያ ሰራዊት ማለት እንግዲህ ከላይ እንዳስቀመጥነው ሲሆን፣ ይህ ሰራዊት ሴት ወንድ ሳይባል፣ ኃይማኖት ሳይለይ ብሎም ዘር ቀለም ሳይጠይቅ አንድ አገርን ብቻ የያዘ አገር ወዳድ ሰራዊት ነበር። ይህ ሰራዊት ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ ሲገነባ መስፈርቱ ኢትዮጵያዊነት ነው የነበረው። ይህ ሰራዊት ዓላማውም አገር መጠበቅ ነው ካልን በየመንግስታቱ ለውጥ የሚፈርስ ወይም ፈርሶ የሚገነባ ወይም እንደተፈለገ አውጥቶ ሜዳ ላይ የሚጣል ሰራዊት አይደለም ማለት ነው። አገር ሁልጊዜ ትቀጥላለች። ነገስታት ይመጣሉ፤ ይሄዳሉ፤ ስርአት ይለዋወጣል፤ አገር ግን ስለምትቀጥል መሪዎች በተቀያየሩ ቁጥር እያፈረሱ የሚገነቡት ሰራዊት ሊኖር አይገባም።
ለምሳሌ የባህር ኃይልን ስንመለከት ለ35 ዓመታት የተገነባ ኃይል፣ ስንትና ስንት ሀብት የፈሰሰበት ኃይል የደርግ ሰራዊት ተብሎ በአንድ ሌሊት ማፍረስ ምን አይነት እብደት ነው? ያሰኛል። ስለዚህ ሰራዊት ስርአትን እየተከተለ እንዲፈርስ ወይም እንዲገነባ መፈቀድ የለበትም።
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል ሰራዊት ሲገነባ የነበረውን መስፈርቶች ቢያብራሩልን?
ሌፍተናንት ዮሴፍ፡- ማን ያርዳ የቀበረ፤ ማን ይናገር የነበረ ነውና ነገሩ በቀደመ ጊዜ የነበረውን ለመናገር ከሰራዊቱ አባላት የበለጠ እማኝ አይገኝም። እኔ አሁን የስልሳ አምስት ዓመት እድሜ ባለፀጋ ነኝ፤ በእኔ እድሜ ባህር ኃይል ስገባ የነበረው መስፈርት በትምህርት ከአስረኛ ክፍል በላይ፤ ሙሉ ጤንነት ያለው፤ ኢትዮጵያዊ የሆነ፤ እድሜና አቋም ኪሎን የያዘ ብቻ ነው። ቋንቋና ብሄር ለውትድርና መስፈርት ሆኖ አያውቅም ነበር።
አዲስ ዘመን፡- የአንድ አገር መለያ የሆነ ሰራዊት እንዲኖር ከቀደመው ልምድ ተነስተው ምን መሰራት አለበት ይላሉ?
ሌፍተናንት ዮሴፍ፡- ከላይ እንዳልነው አንዲት አገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ ግዛት ያላት፣ በውስጡ በርካታ ሀብቶችን ብሎም የተፈጥሮ ሀብቶችን የያዘች፣ የበርካታ ሰዎች መኖሪያ እንደመሆኗ ይህንን ያላትን ነገር በሙሉ ማስጠበቅ ሉአላዊነት እንለዋለን:: ይህን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ደግሞ የሆነ ኃላፊነት ሊሰጠው የሚገባ ኃይል አለ፤ ይህ ኃይል የመካላከያ ኃይል ይባላል።
ሁሉም አገር የራሱ የመከላከያ ኃይል አለው። በተለያዩ ጊዜያት አገር ውስጥ የሚከሰቱ፣ አገር እንደ አገር እንዳትቀጥል የሚያደርጋት እንደ ስርአት አልበኝነት ያሉ ነገሮችን ለመከላከል የሚያስችል ሰራዊት አንድ አገር አሰልጥና ማስቀመጥ ይኖርባታል። አንዲት አገር አገር ስትባል የራሷ ስርአትና መመሪያ ያላት ናት:: ለአገር የሚያስፈልጋት ለዛ ስርዓት ተገዥ የሆነ በመመሪያ የሚመራ ኃይል ነው:: ከአገሪቱ ጦር ኃይል በተጨማሪ የውስጥ ስርአትን የሚያስከብር የፖሊስ ሰራዊት ደግሞ ለብቻው ሰልጥኖ ይቀመጣል።
ለመከላከያ ሰራዊት ዋንኛው መስፈርት ኢትዮጵያዊነት ነው። ኢትዮጵያዊ ማንነት ከፊት ሲቀድም ነው:: አንዲት አገር ለሁሉም ዜጎቿ እኩል አገልግሎት የሚሰጥ እንጂ በጎጥ ተከፋፍሎ የሚጠብቃት የጦር ኃይል ሊኖራት አይገባም። መከፋፈሉን ወደ ጎን በመተው የአገርን ሉአላዊነት የሚያስከብር ሰራዊት መመስረት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን በየክልሉ ያሉ ልዩ ኃይሎችን ወደ መከላከያ ሰራዊት በማስገባት መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፤ እዚህ ላይ ያልዎን ሀሳብ ቢገልፁልን?
ሌፍተናንት ዮሴፍ፡– ሁልጊዜ አንድ ነገር ሲታሰብ መጀመሪያ መነሻን መመልከት ያስፈልጋል። መነሻውን የማያውቅ የት እንደሚደርስ አያወቅምና። አዲስ ነገር ሲታሰብ አባቶቻችን በምን መልኩ ይህችን አገር ይመሯት እንደነበር፤ እኛንስ ሲያስረክቡን በምን መልኩ እንደነበር ማጤን ያስፈልጋል። የትውልድ ቅብብሎሽን በተስተካከለ ቅኝት ሄዶ የነበረ መሆኑን ማየት ተገቢ ነው።
አንድም ጊዜ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች አገር መሆኗንና ለነፃነት ዋጋ የከፈሉ አባቶች የሰሩትን ገድል መመልከት ተገቢ ነው። የአገርን ዳር ድንበር ለማስከበር የብሔር ስም አልተጠቀሰም ነበር። አገር እስከዚህ ጊዜ ድረስ ሉአላዊነቷን ጠብቃ እንድትኖር ያቆዩን አባቶቻችን አፅምም ይወጋናል። አሁን በየክልሉ ያሉ ልዩ ኃይሎችን ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅር መልሶ የማደራጀቱ እንቅስቃሴ ተገቢ ነው:: ቢዘገይም መቅረት የማይኖርበት ጉዳይ ነው። አሁንም ማደራጀት ብቻ ሳይሆን የሚደራጅበት መንገድ በደንብ የተጠና ሊሆን ይገባዋል።
አንድ ሰራዊት ስርዓት በመጣ ቁጥር የሚገለባበጥ ሳይሆን የአገርን ሉአላዊነት የሚያስከብር፤ በሰላሙ ጊዜ ፊቱን ወደ ልማት አዙሮ ለአገር ግንባታ ክንዱን የሚዘረጋ ብሎም ለአገር ሰላምም ሆነ ኢኮኖሚ ዋልታ የሆነ መከለከያ ሰራዊት እንዲመጣ ቁልጭ ያለ ግልፅ ፖሊሲ ያስፈልጋል። ይህ ፖሊሲ በቋንቋ ያልተበረዘ፤ በብሄር ያልተቃኘ፤ ኃይማኖትን የማይከፋፍል፤ ዓላማው ለአንዲት አገር ሉአላዊነት ዘብ የቆመ ሰራዊት እንዲሆን የኢትዮጵያዊ ስነ ልቦና ያለው ሰራዊትን ለማስቀጠል የሚያስችል ጥናት ያስፈልጋል። በዚህ ጥናት ተመስርቶ የተቃኘ ሰራዊት ያስፈልጋል:: የአባቶቹን የጀግንነት ታሪክ በየፈርጁ እያስጠበቀ የሚኖር እና የአገር ታሪካዊ ጠላቶች የሆኑ ዳግም እንዳያንሰራሩ የሚያደርግም መሆን ይጠበቅበታል:: ምንም አይነት አገር አፍራሽ ሸፍጥ ሳይሰራ ጂኦ ፖለቲካውን አውቆ የሚመራ የኢትዮጵያ ጦር ኃይልን መቅረፅ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን እየተከናወነ ያለው መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴ መከላከያ ሰራዊቱን ምን ያህል ያጠናክረዋል ብለው ያስባሉ?
ሌፍተናንት ዮሴፍ፡– አሁን እየተከናወነ ያለው ሰራዊቱን መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴ መከላከያ ሰራዊቱን ምን ያህል ያጠናክረዋል ለተባለው ከዚህ በላይ ምን አጠናካሪ ነገር ይኖራል? ምንም አይኖርም:: አገር አንድነቷን እንድታስጠብቅና በአፍሪካ ቀንድ ያለች ኃያል አገር ለመፍጠር ትልቅ አቅም ነው።
ኢትዮጵያ ደካማ ሰራዊት እንዳይኖራትም ያደርጋል:: የጸጥታ ኃይል ጎጥ ውስጥ እንዳይገባና የዚህ ብሔር አገልጋይ ነህ በሚል መከፋፈል እንዳይኖርም ያግዛል:: በዚህም አካሄድ አንድ የመሆን ጅማሬው ይበል የሚያሰኝ ነውና መልካም ነው። ይህን ግን በዚህ የማደራጀት ሒደት ብቻ ማብቃት የለበትም:: ህፃናት ከትምህርት ቤት ጀምሮ ኢትዮጵያዊ ማንነት እንዲኖራቸው አበክሮ መስራት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ልዩ ኃይል ለአንድ አገር ምን ጥቅም ምን ጉዳትስ አለው?
ሌፍተናንት ዮሴፍ፡- መጀመሪያ ስለ ልዩ ኃይሉ ጥቅምና ጉዳት ከመነጋገራችን በፊት ምንድነው ልዩ ያሰኘው የሚለውን ጉዳይ ማንሳት እወዳለሁ። በኛ ጊዜ የተለየ ስራ የሚሰሩና የተለየ ተልእኮ የሚሰጣቸው ኃይሎች ‹‹እስፔሻል ፎርስ›› በሚል ይጠሩ ነበር። ከዛም የኢትዮጵያ አወቃቀር ሲቀየርና በክልል ሲከፋፈል ተከትሎ የመጣው ይህ ልክ የራስ ግዛት ያለው ይመስል የእገሌ ልዩ ኃይል በሚል መቋቋም ጀመረ።
መከላከያ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መዋቅር ውስጥ በየትኛውም ክልል ገብቶ የፀጥታ ጉዳይ መስራት ሲችል ለምን ሲባል ነው ልዩ ኃይል ሊቋቋም ያስፈለገው? በየትኛውስ አዋጅ ነው ሊቋቋም የቻለው? የሚል ጥያቄ መጠየቅ እፈልጋለሁ። በክልሉ ለሚከሰቱ የተለያዩ ጉዳዮች ለማርገብ ከሆነ ፖሊስ ምን ያደርጋል? ስራው የክልሉን ፀጥታ ማስከበር ነው። ለምን ይህ ሁሉ ወጪ ወጥቶ መከላከያ ሰራዊት ማቋቋም አስፈለገ? የሚለው ጥያቄ ብጠየቅም አመሰራረቱ ግን ትክክል አለመሆኑን ሳልናገር አላልፍም።
ልዩ ኃይል የክልል ፀጥታን ያስጠብቃል ከተባለ አንዳንድ ቦታ መከላከያን የሚገዳደር አቅም ያለው ሁሉ አለ፤ ይህ መሆኑ ደግሞ የአገር ስጋት ነው። ስለዚህ ይህ ኃይል መኖሩ የአገር መፍረስ ስጋት ነው። ይህ ልዩ ኃይል ግን በስርአት ተጠንቶ በኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ የተመሰረተ ሰራዊት ውስጥ ገብቶ በወጣበት አቅም ልክ ለአገር የሚበቃና የሚያገለግል ሊሆን ይገባዋል።
አዲስ ዘመን፡- አንድ ክልል ሊኖረው የሚገባው የፖሊስ ሰራዊት ብቻ ነው ይባላል፤ እዚህ ላይ ያልዎት አስተያየት ምንድን ነው?
ሌፍተናንት ዮሴፍ፡– በእኛ ጊዜ የባህር ኃይል ነበር ከዛም የአየር ኃይል፤ እግረኛ ሰራዊት በሚባሉ የተለያዩ ክፍሎች የተከፋፈለ ከመሆኑ በስተቀር በየብሔር የተከፋፈለ አልነበረም። ከእነዚህ ውጪ የፖሊስ ሰራዊት የሚባል ራሱን የቻለ ሰራዊት ደግሞ የውስጥ ደህነንት በሚያስጠብቅ መልኩ ተደራጅቶ ይሰራ ነበር።
ይህ ትልቅ ተቋም በወቅቱ አጠራር በየክፍለ አገሩ የውስጥ ሰላምን የሚያስጠብቀው የፖሊስ ሰራዊት ነበር። ይህ የራሱ አደረጃጀት ነበረው። የውስጥ ችግሮች ቢከሰቱም የፖሊስ ሰራዊት በየቦታው ተገኝቶ ነገሮችን ያስተካክል ነበር። ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ሲከሰት ለምሳሌ የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት፣ ከፖሊስ ቁጥጥር ውጪ የሆነ ነገር ሲመጣ መከላከያ ይጠራል። ከመከላከያ አቅም በላይ ከሆነ ደግሞ ህዝባዊ ሰራዊት የሚባል ሰራዊት አለ፤ ይህ ያለውን ችግር ያስተካክላል።
ቀድሞ በነበሩትም ስርአቶች አንድ ክፍለ አገር የከተማ ፖሊስ እንጂ ልዩ ሰራዊት የሚባል አልነበረውም፤ ይህ አለመኖሩ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ገንኖና እና በልጦ እንዲኖር አድርጎታል።
አዲስ ዘመን፡- እንደ አንድ የሰራዊት አባል አገር ሰላሟ ተጠብቆ ትኖር ዘንድ፤ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ለሚነሱ ግጭቶች ሊኖራት የሚገባው የመከላከል አቅም እስከምን ድረስ ነው ይላሉ?
ሌፍተናንት ዮሴፍ፡- ስለሰራዊቱ ሲነሳ በእኛ ጊዜ አሁን እያልኩ ማነፃፀር አልፈልግም። ኢትዮጵያ እስካለች ድረስ አብሯት የሚኖር ዳር ድንበሯን አስከብሮ ሉአላዊነቷን አስጠብቆ የሚሄድ ሰራዊት ያስፈልጋታል። ለዚህም የመከለካያ ሰራዊትን ከሰው እስከ ትጥቅ በበቂ ሁኔታ ማደራጀት ያስፈልጋል።
አሁን ባለው ሁኔታ አገራችን በርካታ ጠላቶች ያላት አገር ናት፤ ይህንን በተገቢው መልኩ ተረድቶ ከአገር የሚቀድም የለም በማለት ደረቱን ለጥይት የሚሰጥ ኃይል ያስፈልጋታል። በአሁኑ ወቅት በግልፅ የሚታዩ ዳር ድንበርን የመድፈር ሁኔታ አለ። ይህንን የሚከላከል ከታሪክ ተጠያቂነት የሚያድን፣ ጠላትን ተቋቁሞ ለማለፍ የሚያስችል፣ ከውስጥ ግጭት የፀዳ ኢትዮጵያዊ መከላከያ ሰራዊት ሲኖር ነው።
እኔ በዘመኔ አራት መንግስታትን ተመልክቻለሁ። ሁሌም መሪዎች ይሄዳሉ፤ ህዝብ ቀሪ ነው:: የዚህ ህዝብ አካል የሆነ ሰራዊት ሊኖረ ያስፈልጋል። ሰው በብሔር መከፋፈሉን ትቶ አንድ አይነት አመለካከት ያለው ማህበረሰብ፤ ማህበረሰቡ የወለደው ጠንካራ አንድነት የሚጠብቅ መከላከያ ሰራዊት ያስፈልጋል።
ወጣቶች ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ለአገር አገልግሎት የሚሰጡ ወታደሮችን በመፍጠር እንደነ እስራኤል ፍፁም አገር ወዳድ የሆነን ህዝብ ማደራጀት ተገቢ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ውድ ጊዜዎን ሰውተው ተቋማችን ድረስ መጥተው ሀሳብዎን ስላካፈሉን በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስም ላቅ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
ሌፍተናንት ዮሴፍ፡– እኔም ሀሳብህ ይጠቅማል ብላችሁ እንደካፍል ስለጋበዛችሁኝ ከልቤ አመሰግናለሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2015