የጦርነትን አስከፊነትና አውዳሚነት ዓለም ላይ ከኢትዮጵያውያን በላይ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በምላሱ ቀምሶ፣ በአይኑ አይቶ፣ በጆሮው ሰምቶ፣ በአፍንጫው አሽትቶ፣ በእጁ ዳሶ በጥቅሉ በአምስቱ የስሜት ሕዋሳት ያረጋገጠ የለም። በተለይ የ1960ዎቹ ትውልድ በተከተሉትና እየተከተሉት ባለው የሴራና የመጠላለፍ ፖለቲካ ሳቢያ ላለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመታት በአገሪቱ በዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት እንደሀገር ወደፊት መጓዝ ተስኖን ባለንበት ቆመናል።
በተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም በማዕድን የበለጸገ ለም መሬት ይዘን ሆዳችን ተርቧል። እኛ ከጦርነት አዙሪት መውጣት ተስኖንን ስንዳክር ብዙዎች ግን ከኋላችን ተነስተው ዛሬ ላይ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢኮኖሚ … ወዘተ ተመንድገው የት እንደደረሱ እያየን ነው። የጦርነትን አስከፊነትና አውዳሚነት ለኢትዮጵያውያን መናገር ለቀባሪ እንደማርዳት ይቆጠራል። የሰላምን ዋጋ ማስገንዘብም እንዲሁ ።
እሩቅ ሳንሄድ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ በሰሜኑ ክፍል በነበረው ጦርነት የአንድ ሀገር ዜጎች እርስ በእርስ ተዋግተው እልፎች ተሰውተዋል። አያሌ ንጹሓን ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከሕጻን እስከ ዓለም በቃኝ ብላ እስከመነነች አዛውንት መነኩሴ ድረስ ብዙዎች ተደፍረዋል። የሀገሪቱን ዓመታዊ በጀት በእጥፍ የሚሸፍን ሀብት በጦርነቱ ደቋል። መሠረተ ልማት ወድሟል። አንዳንድ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ወደነበሩበት ለመመለስ ዓመታትን ጭምር ይወስዳሉ።
ሺህዎች ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለው ከሕይወታቸው ላይ እንደዋዛ ዓመታትን አባክነዋል። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም የሰላም አየር እርቆት ጠዋት ማታ በጦርነት ዜና አዕምሮው ታውኮ ቆይቷል። በጥቅሉ ጦርነቱ ያስከተለውን ዳፋ አይደለም በዚች አጭር መጣጥፍ ቀርቶ በየመስኩ (በማኅበራዊ፣ በታሪክ፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በሥነ-ልቦና ወ.ዘ.ተ ) አንዳንድ መጽሐፍ ቢዘጋጅ እንኳን ጥንቅቅ አድርጎ የሚገልጸው አይመስለኝም።
ታዲያ “ጦርነት ይብቃ፣ ሰላምን እናጽና” በሚል መሪ ቃል በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ሲካሄድ የነበረው ጦርነት “በሰጥቶ መቀበል መርሕ” በፕሪቶሪያ ሲደረግ በነበረው ድርድር በሰላም እንዲያልቅ ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱ ወገኖች እውቅና በተሰጠበት ማግስት ሆን ብየ የጦርነቱን ጠባሳ ማንሳቴ የሰውን ቁስል ለማስታወስ ፈልጌ አይደለም።
ወይም ሰላም ወርዶ በአገሪቱ የሰላም አየር በመንፈሱ ሳልደሰት ቀርቼ አይደለም። ወይም ደግሞ የጦርነት ነጋዴ ሆኜም አይደለም። እንደአንድ ሰላም ወዳድ ዜጋ የሰላም አየር በመንፈሱ እጅግ ደስተኛ ነኝ። ይልቁንም ትናንት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የጥይት ድምፅ ከመሰማቱ በፊት በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ተብሎ ችግሮችን ሰጥቶ በመቀበል መርሕ ተፈትቶ ቢሆን ኖሮ፤ “እንደሀገር የገባንበት ምስቅልቅል ውስጥ ባልገባን፤ ገመናችንም የዓለም አደባባይ ላይ ወጥቶ ባልተሰጣ ነበር” ብሎ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚቆጭ እርግጠኛ ነኝ።
ሌላው ቀርቶ የጦርነቱ ጠንሳሾችና ተዋናዮች እራሱ እንደተቆጩና ሕዝባቸውን ለመካስ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ ከድርድሩ ማግስት ሲናገሩ ተደምጠዋል። ቁጭ ብሎ በጋራ ለመነጋገር “አሻፈረኝ” ሲሉ የነበሩ አካላት ዛሬ ላይ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው ችግራቸውን ፈትተው የሰላም አየር እንዲሰፈን ማድረጋቸው በጣም ያስደስታል። ይህ የሰላም ድርድር ይበልጥ ከአውዳሚው ጦርነት በፊት ቢሆን ኖሮ ደግሞ ምን ያህል አገርን ከውድቀት፤ ሕዝብን ከመለያየት ይታደግ እንደነበር መገመጥ የሚከብድ አይሆንም ።
ነገሩ “የሺህ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ” እንደሚባለው የጦርነት መቋጫው ሰላማዊ ድርድር ነው። በመሆኑም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የነበረው ጦርነት በድርድር ተፈትቶ ሰላም ሰፍኗል። ዘግይቶም ቢሆን ሰላም እንዲመጣ የበኩላቸውን ሚና የተጫወቱ አካላት ምስጋና ይገባቸዋል። ሰላሙ እስከመጨረሻው የጸና እንዲሆን ሁሉም አካላት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል። ማኅበረሰቡም የበኩሉን ሚና መጫወት አለበት። ሰላሙ ይበልጥ እንዲጸና ከበላይ አመራሩ ባሻገር ኅብረተሰቡ ተቀራርቦ የሚወያይበት መድረክ ሊፈጠር ይገባል።
በዚህ ጽሑፌ ላነሳው ወደ ፈለኩት ርዕሰ ጉዳይ ስመለስ ፤ ዛሬስ እንደሀገር እና ሕዝብ አይደለም ከትናንት አዳፋ ታሪካችን ከዛሬ ስድስት ወር በፊት በአገሪቱ በሰሜኑ ክፍል ሲካሄድ ከነበረው ጦርነት ከልብ የጦርነትን አስከፊነት ተምረናል ወይ? የሚለ ው ነው።
ትናንት ችግሮቻችን በሰጥቶ መቀበል መርሕ መፍታት ተስኖን ከገባንበት የጦርነት አዙሪት በቅጡ ሳንወጣ ዛሬም ሌላ የጦርነት ምዕራፍ ለመክፈት እዚህም እዚያም የጦርነት ነጋሪት ሲጎሰም ይሰማል። ትናንት የሰላም አማራጮች ሁሉ ተዘግተው ወደ ጦርነት በመገባቱ ያተረፈ ማነው? ያሸነፈስ ማነው? …? የአንድ ሀገር ልጆች እርስ በእርስ በመገዳደል አሸናፊም፣ አትራፊም … እንደሌለ ከአንዴም ሁለት፣ ሶስት ጊዜ ከኛ ከኢትዮጵያውያን በላይ ያየ ማን አለ።
በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሀሳብን በሀሳብ እንጂ በጠመንጃ ማሸነፍ አይቻልም። ይህን ደግሞ እሩቅ ሳንሄድ በቅርቡ በአገሪቱ በሰሜኑ ክፍል ሲካሄድ በነበረው ጦርነነት ታይቷል። በመሆኑም ልዩነት ያለው ኃይል ሁሉ ከመንግሥት ጋር ቁጭ ብሎ በሰከነ መንፈስ መነጋገር አለበት። ልዩነትን በውይይት እንጂ በመገዳደል መፍታት ያለፈበትና ኃላቀር ፋሽን ነው።
መንግሥት ከሁሉም በላይ በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍንና የዜጎች ደህንነት እንዲጠበቅ ከማድረግ ካለን ኃላፊነት አንጻር ችግሮችን በሆደ ሰፊነት በድርድር ለመፍታት የጀመረውንና ትርጉም ያለው ውጤት እያመጣ ባለው አካሄዱ በበለጠ ቁርጠኝነት ሊቀጥልበት ይገባል ። ኅብረተሰቡ የጦርነቶች ዋነኛ ገፈት ቀመሽ እራሱ መሆኑን ከትናንት የጦርነት ታሪኮች በመማር የጦርነት ነጋሪት ጎሳሚዎችን በቃችሁ ሊል ፤ለሰላም ዘብ መቆምና ጦርነትን ባገኛው አጋጣሚ ሁሉ ማውገዝ ይጠበቅበታል።
በአጠቃላይ የዓለም ታሪክ እንደሚያስረዳን ጦርነት ለሰላም በተዘረጉ እጆች እንጂ በመሣሪያ እጦት አይቆምም። እንዲሁም በሰላማዊ ድርድር እንጂ በአሸናፊና በተሸናፊ መንፈስ የተቋጩ ጦርነቶች ዘላቂ ሰላም አያሰፍኑም። ይህንንም በተጨባጭ እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ላለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመታት እርስ በእርስ ተዋግተን አይተነዋል። በቅርቡም የጦርነትን አስከፊነት አይተነዋል።
ከጦርነቶች ያተረፍነው አንዳች ነገር የለም። ስህተትን በስህተት በመድገም “ታጥቦ ጭቃ” መሆን የለብንም። እንደሀገር ሁለንተናዊ እድገታችን በሰላም እንጂ በጦርነት አይረጋገጥም። ይህንን ተገንዝበን ከትናንት ስህተታችን በመማር በሰጥቶ መቀበል መርሕ የትኛውንም ችግር በድርድር በመፍታት ሰላማችንና አንድነታችን በማጽናት በኅብረት የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን የማድረግ ኃላፊነት ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ነው።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2015