ለብዙ ወራት ተሰውሮ የነበረው ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ከዚህ ቀደም በተለየ መልኩ በተከታተይ ቀናት ሰማይ የአህያ ሆድ ሲመስል እየተነሳ በሰፈራችን ከሚገኘው ዋርካ ስር ቆሞ መጮሁን አብዝቷል። ዛሬም እንደ ወትሮው ሁሉ እየጮኸ ነው። ሰዓቱ የሰፈራችን ሰዎች ወደ «በተስኪያን» የሚሄዱበት ነው። ይሁንና የዛሬው የይልቃል አዲሴ ጩኸት ከዚህ ቀደሙ የተለየ በመሆኑ በሰፈራችን የሚገኝ ማንኛውም ሰው ከህጻን እስከ አዋቂ ‹‹በተስኪያን» መሄዱን ትቶ ይልቃል አዲሴ ወደሚጮህበት ዋርካ ተሰበሰበ። ሰዎች በመሰባሰብ ላይ እያሉ ይልቃል አዲሴም በተደጋጋሚ «ከርሞ ጥጃ፤ ክርሞ ጥጃ፤ ከርሞ ጥጃ» እያለ ይጮህ ነበር።
የሰፈራችን ሰዎች ወደ ዋርካው ተሰባስበው ቦታ ቦታቸውን መያዛቸውን ከተመለከተ በኋላ ይልቃል አዲሴ ራሱን ለንግግር እያዘጋጀ እህ..እህ…ብሎ ጉሮሮውን ጠራረገ። ንግሩንም እንዲህ ሲል ጀመረ፤… ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ዓለማችን ሁሉም ነገሯ በፍጥነት ሲለዋወጡ እየተመለከትን ነው። ዛሬ ላይ አዲስ ሆነው ያየናቸው ኩነቶች ከሳምንት በኋላ ያለፈባቸውና አሮጌ ሆነው እናገኛቸዋለን። ዛሬ ላይ የተሰራ ድንቅ ስራ ከወር በኋላ በአዲስ ተተክቶ ይቀርባል። ይህ አካሄድ የዚህ ዘመን ሁነኛ መገለጫ ነው።
ፖለቲካውም በዚሁ ልክ ሆኗል። ትናንት ላይ የነበሩ ዓለምን ያሳጨበጨቡ አስተሳሰቦችና መላው የዓለም ህዝብ የገዛቸው ሃሳቦች ዛሬ ላይ አርጅተው ተጥለው በአዲስ ሲተኩ እየተመለከትን ነው።
ለምሳሌ ትናንት በወታደራዊ መንግስት ሲተዳደሩ ነበሩ አገራት ዛሬ ላይ ሁሉ ነገራቸውን ጥለው ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግረዋል። ትናንት ላይ በስፋት ሲስተዋል የነበረ የፓርቲ አመሰራረት ዛሬ ካለው ፈጽሞ የተለየ ነው። ዛሬ ላይ ፓርቲዎች የሚታገሉበትና ህዝብን የሚያታግሉበትም ስልት ከትናንትናው ፈጽሞ የተለየ ነው። ትናንት ላይ ሲንጸባረቁ የነበሩ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሞች ዛሬ የሉም፤ በአዲስ ተተክተዋል። በአጠቃላይ ትናንት የነበሩ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኩነቶች ዛሬ ላይ የሉም ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ይሁን እንጂ በእኛ አገር የሚገኙ በርካታ ፖለቲከኛ ነን ባይ ወገኖች ግን የአገራቸውን ነባራዊ ሁኔታ ምኑንም ሳያገናዝቡ ትናንት ከእነ ማርክስ እና ሌኒን እንደወረደ የተዋሱትን ንድፈ ሃሳብ እንደዘወትር ፀሎት እየደጋገሙ በማኘክ እና ራሳቸውን በፖለቲከኛ ማማ ላይ በማስቀመጥ፤ ከእነሱ ውጭ በአገሪቱ አዋቂ እንደሌለ እና ሁሉም የአገሪቱ ችግር የሚፈታው በእነርሱ እና በእነርሱ ብቻ እንደሆነ በማሰብ በ1960ዎቹ በተከፈቱ ዘፈኖች እስከዛሬ ድረስ እየጨፈሩ ይገኛሉ። እነኝህ ወገኖች በቆሙበት ደርቀው ቀርተዋል ቢባል ማጋነን አይደለም።
የእነርሱ ተከታዮች እና ደቀመዛሙርቶቻቸውም ታላላቆቻቸውም የሰሩትን የክፋት ፖለቲካ እንደ ፖለቲካዊ ጥበብ በመቁጠር ዛሬም ላይ የአገራችን ሁለንተናዊ መስተጋብር በከፍተኛ ደረጃ ሲያውኩት ይስተዋላሉ። የአገራችንን ሁለንተናዊ ህግጋት መጠበቅ እና ማክብር የሚባለውን ነገር ፈጽሞ አያውቁትም። የአገራችንን ሁለንተናዊ ህግጋት መጠበቅ እና ማክብር እንደ ኋላቀርነት ይቆጥሩታል።
በእርግጥ የማርክሲስቶችን ሃሳብ ወስደው አገራቸውን በአወንታዊ መልኩ የቀየሩ በርካቶች ናቸው። ይሁን እንጂ በእኛ አገር የሚገኙ ፖለቲከኛ ነን ባዮች ግን አገራችንን ለማፍረስ ከመጋጋጥ ውጭ ለአገራቸው አንድም ጠብ የሚል ነገር ሲሰሩ አልተስተዋለም።
በእኔ እይታ ለዚህ ሶስት ዋና ዋና ምክንያቶች ያሉ ይመስለኛል። አንደኛ ከእነ ማርክስ ምንም ሳያላምጡ የወሰዱትን ንድፈ ሃሳብ አብዛኛውን በቅጡ አልተረዱትም። ለምሳሌ ብሔርን በተመለከተ በእነ ማርክስ የፍልስፍና የተሰጠው ትንታኔ እና የእኛ አገር ፖለቲከኛች የተረጎሙበት ሂደት ፈጽሞ የጠራራቀ ነው። እነ ማርክስ አንድ ማህበረ ሰብእ ብሔር ሊባል የሚችለው ስድስት ነገሮችን ሲያሟላ መሆኑን ይናገራሉ። ከስድስቱ አንድ እንኳን ቢጎድል ብሄር ሊባል እንደማይችል ትንታኔ ይሰጣሉ። የእኛ አገር ፖለቲከኞች ደግሞ አንድን ማህበረሰብ ብሔር የሚሉት እነ ማርክስ ከጠቀሷቸው ስድስት ቅድመ ሁኔታዎች አንዱን የሆነውን ቋንቋን ብቻ መሰረት አደርገው ነው። የእኛ አገር ፖለቲከኞች ዋነኛ ችግር የፖለቲካ ፍልስፍና መነሻቸው አገር በቀል ካለመሆኑም ባለፈ ከሌሎች የቀዱትን እንኳን በቅጡ መገንዘብ አለመቻላቸው ነው። በዚህም አሁን ላይ በቆሞ ቀሮች ከ1960ዎቹ እስካሁን ድረስ አገራችንን እያስከፈሏት ያለው ዋጋ ምን እንድሚመስል የአደባባይ ምስጢር ነው።
ሁለተኛው ምክንያት ቆሞ ቀሮቹ የእነ ማርክስን ፍልስፍና ሲቀዱ የፍልስፍናውን ሙሉ ሀሳብ አልወሰዱም። የወሰዱት ለራሳቸው የትግል ስልት ይጠቅመናል ያሏቸውን ንድፈ ሃሳቦች እና በራሳቸው ልክ አጣመው መስፋት የሚችሉትን ብቻ ንድፈ ሃሳቦች ነው። ለምሳሌ የፓርቲ አመሰራት፤ የብሄር ብሄረሰቦች መብት ፣ ፊደራሊዝም ፣ ወዘተ ናቸው።
ሶስተኛ የእኛ ፖለቲከኛች የወሰዱትን ንድፈ ሃሳብ መሬት ላይ መተግባበር አልቻሉም። ለዚህ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረወው የማርክሲዝምን ጽንሰ ሀሳብ በቅጡ ካለመረዳት የመነጨ ነው።
ዝናብ ለሰጠ ጌታ ውሃ ነፈጉት እንዲሉ ኢትዮጵያ ላይ ግፍ እያደረሱ ያሉት እነዚህ ኃይሎች ኢትዮጵያ የምትበላው ሳይኖራት ለምና እና ተበድራ ያስተማረቻቸው ናቸው። ብድሯን መክፈል ሲገባቸው ጽንፍ ረግጠው ህዝቦቿን እርስ በርስ እያባሉ ይገኛሉ። መማር እንደዚህ ከሆነ ልጆቻችሁን ትምህርት ቤት አትላኩ! ይቅርባችሁ።
ንድፈ ሃሰቦችን በቅጡ ካለመረዳት ጋር ተያይዞ ሁሌም የማልረሳው አንድ የደርግ ባለስልጣን አለ። ስለሱ ትንሽ ልበላችሁ። በአንድ ወቅት ይህ የደርግ ባለስልጣን አብዮተኛ ነን ባይ በመንግስት እያመጹ ያስቸገሩ ተማሪዎችን ለማወያየት በሰፈራችን ከሚገኘው የትምህርት ቤት አዳራሽ ይሰበስባቸዋል። ተማሪዎቹም በማርክሲዝም ፍልስፍና ያበዱ ነበሩ። ለቡና መጠጫ የሚወሩ ቀልዶችን እንኳን ሲያወሩ የማርክሲዝምን ፍልስፍናዎች ቀላቅለው ካላወሩ የሚጨቃንቸው አይነት ናቸው ።
ተማሪዎችን የሰበሰበው የደርጉ ባለስልጣን ደግሞ ከውትድርና ቤት እንዲሁ አፈ ቀላጤ ስለሆነ ባለስልጣን የሆነ እንጂ እብዛም ቀለም የዘለቀው አልነበረም ። ነገር ግን እሱም እንደተማሪዎች የእነ ማርክስን ስም ካልጠራ ህዝብን ማስተዳደር እና አብዮቱን ማስቀጠል የሚችል አይመስለውም ። የሚገርመው ሚስቱም ባሏን እየሰማች ማርክስ እና ሌኒን ማን መሆናቸውን እንኳን ሳታውቅ ማርክስዬን ፤ ከማርክስዬ ይነጥለኝ ፤ የሌኒንዬን ስጋ ያስበላኝ እያለች ስለምትምል የሰፈሩ ሴቶች የማርክስ እናት እያሉ ይጠሯት ነበር ።
ወደ ጀመርኩት የተማሪዎች ስብሰባ ልመልሳችሁ። ስብሰባውም አብዮታዊት ኢትዮጵያ የማርክስ እና ሌኒን ሃሳቦች በመተግበር ወደፊት በሚል መፈክር ተጀመረ። በመፈክሩም ሁሉም ተማሪዎች የግራ እጃቸውን ከፍ አድርገው መፈክሩን አሰሙ። ስብሰባውን የሚመራው ሰው ግን የቀኝ እጁን ነበር ለመፈክር ከፍ ያደረገው። ይህን የተመለከተው አንድ አብዮተኛ ነኝ ባይ ተማሪ ‹‹ጌታዬ! የእነ ማርክስን መፈክር ለማሰማት እንዴት የቀኝ እጅዎት ከፍ ያደርጋሉ !? ይህ የአብዮቱን አካሄድ የሚጻረር ነው» ብሎ አፈጠጠባቸው ። ሰብሳቢውም አለማወቃቸውን ለመደበቅ «በደንብ ጠላትን መቀጥቀጥ የሚችለውን እጅ የማውቀው እኔ ነኝ!» ሲሉ መለሱ።
የሆነው ሆኖ ስብሰባው ተጀመረ፤ ባለስልጣኑ ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ነገሮችን ሳያበዛ ከተናገረ በኋላ ተማሪዎች እንዲናገሩ እድል ሰጠ። አብዮተኛ ተማሪዎችም እየተነሱ የደርጉ ባለስልጣን ሊገነዛባቸው የማይችላቸውን የማርክሲዝም እና የሌሎች ሶሻሊስት ፈላስፋዎችን ንድፈ ሃሳቦች በማንሳት ማርክስ ‘እንዳለው’ ፣ ሌኒን ‘እንዳለው’ እከሌ ‘እንዳለው’ እያሉ ፖለቲካዊ ትንታኔ ሰጡ።
ይህን የተመለከተው የደርጉ ጥራዝ ነጠቅ ባለስልጣን ተማሪዎች ማርከስ፣ ሄንግልስ ፣ሌኒን እንዳለው እያሉ ሲናገሩ አቶ እንዳለው የሚባሉ ሰው እነ ማርከስን ፣ሄንግልስንና ሌኒን የወለዳቸው መስሎት ምን ቢል ጥሩ ነው! ‹‹አብዮቱ እዲፋጠን እና ፍሬ እንዲያፈራ እነኝህን የመሰሉ ብርቅዬ ልጆች የወለዱትን አቶ እዳለውን መሸለም አለብን›› ብሎ አረፈው።
ይህ ፖለቲካን በቅጡ ሳይረዱ መተንተን ዛሬም ላይ እንደክፉ በሽታ ተጣብቶን ይገኛል። አሁን ላይ በእኛ አገር በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ ቧልቶችን እየሰበሰቡ እና እየቃረሙ ራሳቸውን እንደፖለቲካ በመቁጠር አገር የሚያተራምሱ ኃይሎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።
የሚገርመው እነኝህ አካላት አገር አፍራሽ እንቅስቃሴ እያደረጉ እያለ በአገረ መንግስት ግንባታው ሂደት ራሳቸውን እንደሁነኛ አካል አድርገው መቁጠራቸው ነው።
ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ይህን ንግግር እያደረገ እያለ ሁሉም የሰፈራችን ሰዎች ጸጥ እረጭ ብለው እያዳመጡ ነበር ። ነገር ግን ሁሌም ሳይፈቀድለት የሚናገረው አብሿሙ ክንፈ ጉደታ፣ በይልቃል አዲሴ ንግግር ላይ ተደርቦ የይልቃል አዲሴን ንግግር አቋረጠው ።
ባለፈው እንደነገርኳችሁ የሰፈራችን ሰዎች ክንፈ ጉደታን አብሿም ይበሉት እንጂ ክንፈ ጉደታ የእውነት አብሾ መጠጣቱን በእርግጠኝነት መናገር የሚችል ሰው የለም።
የይልቃል አዲሴን ንግግር ያቋረጠው አብሿሙ ከንፈ ጉደታ «ይልቃል አዲሴ ያደረጋቸው ንግግሮች በሙሉ እውነታ አላቸው ። እኔም ከሱ ሃሳብ ላይ የምጨምረው ነገር አለኝ» አለና ንግግሩን እንዲህ ሲል ጀመረ ….‹‹ቆሞ ቀሮች እውቀት የሌላቸው እና ወና ስለሆኑ ለውጥ የሚባል ነገርን አብዝተው ይፈሩታል። ምክንያቱም ለውጥ የአዋቂዎች ነውና ። በነገራችን ላይ ተፈጥሮ በራሷ ለውጥን ስለምትፈልግ ወናነትን አብዝታ ትጠየፋለች ። ስለሆነም ተፈጥሮ የምትፈልገው ከጊዜው ጋር አብሮ የሚዘምንን እና የሚለወጥን ነው ።
አብሿሙ ከንፈ ጉደታ ንግግሩን ቀጠለ ….አዋቂ ማለት ንድፈ ሃሳብን ሸምድዶ የሚያነበንብ አይደለም ። ንድፈ ሃሳብን በተግባር ላይ የሚያውልን እንጂ። ለውጥ ለማምጣት ከተፈለገ ንድፈ ሃቦችን ብቻ ማውራት ተገቢነት የለውም። ለዚያ ነው ፍሬድሪክ ኤንግልስ «ከአንድ ቶን ንድፈ ሃሳብ አንድ ወቂት ተግባር የበለጠ ዋጋ አለው !» ያለው። ይሄን አስተሳሰብ የሚደግፈው ሎይድ ጆንስ «ምንም ነገር ለመስራት ሳይሞክሩ ከተሳካላቸው ይልቅ አንድ ነገር ለማድረግ ሞክረው ያልተሳካላቸው ሰዎች ያለጥርጥር የተሻሉ ናቸው ! »ያለው ።
የቆሞ ቀሮች ዋነኛ መታወቂያ ንደፈ ሃሳብን ከማንም በላይ መናገር መቻላቸው ነው ። ነገር ግን ተግባር ላይ ይህ ነው የተባለ ስራ መስራት የሚችሉ አይደሉም ። ከሚያውቁት ንድፈ ሃሳብ አንድም ነገር በተግባር መሬት ላይ ማውረድ የማይችሉ ናቸው ።
በዓለም ላይ ብሄር የሚባለው ነገር የተመሰረተው ከፊውዳሊዝም መጥፋት እና ከካፒታሊዝም መመስረት ጋር ተያይዞ ነው። ፊውዳሊዝምን አጥፍቶ ካፒታሊዝምን የማዳበር ሂደት በሌላ አነጋገር ህዝቦችን በብሄር የመመስረት ሂደት ነው ። ይሁን እንጂ በምዕራብ አውሮፓ እና በምስራቅ አውሮፓ ብሄር የተመሰረተበት ሁኔታ እጅጉን ይለያያል። በምዕራብ አውሮፓ የተለያዩ ግዛቶች የተለያዩ ብሄሮች ሲሆኑ ፤ በምስራቅ አውሮፓ ግን የተለያዩ ብሄሮች የተለያዩ ግዛቶችን እደፈጠሩ ፖለቲከኞች እና የታሪክ ምሁራን ያስረዳሉ። ይሁን እንጂ አንድ ማህበረ ሰብእ ብሔር ለመባል ማሟላት የሚገባቸውን ነገሮች ያሟሉ ናቸው ።
በእኛ አገር ያሉ ብሄርን የፖለቲካ መጫወቻ ካርድ ያደረጉ ኃይላት ግን በእኛ አገር የተፈጠሩ ብሄሮች የየትኛውን አገር የብሄር አመሰራረት መሰረት ያደረጉ ናቸው ? ተብሎ ቢጠየቁ ለጥያቄው መልስ አይኖራቸውም።›› ብሎ ወደመቀመጫው ተመለሰ ። የሰፈራችን ሰዎች አብሿሙ ከንፈ ጉደታ ንግግር ተገርመው ሞቅ አድርገው አጨበጨቡለት ።
አብሿሙ ክንፈ ጉደታ ንግግሩን ሲጨርስ ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ንግግሩን ከአቆመበት ቀጠለ …. እንደእነዚህ አይነት ሰዎችን አድሃሪ (Reactionary) የለውጥ ተቃዋሚ የሚለው የፖለቲካ ቋንቋ በትክክል ይገልጻቸዋል። አድሃሪ የሚለው ቃል ድኅሮት፣ ድኂር ከተሰኙ የግዕዝ ቋንቋ የተወሰደ ሲሆን፣ ትርጉሙም ወደኋላ መቅረት፣ መጨረሻ መሆን፣ ባሉበት መቆየት ማለት ነው። ማርክሲስቶች አድሃሪ የሚለውን ቃል በአንድ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ የሚገኝን ማህብረሰብ ጊዜው የሚፈልገውን አይነት እርምጃ ወይም ለውጥ ደግፎ ወደፊት መጓዝ ሲገባው በቀደመ አስተሳሰብ ተቸንክሮ ጊዜው የሚፈልገውን ለውጥ ወደኋላ ጎትቶ ለማስቀረት የሚሞክር ነው። ይህን የሚያደርጉትም በዋናነት ከኋላቸው በገንዘብ እና በሌሎች ጥቅም የሚጋልቧቸውን አለቆቻቸውን ለማስደሰት ሲሉ ነው።
ከቀደመው ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ የምናያቸው አብዛኛው በአገራችን ፖለቲካ ተዋናኝ ፖለቲከኞች አገራችን ወደፊት ማራመድ እንዳትችል ትናንትም ዛሬም አንድ አይነት ሃሳብ እንደ ፀሎት መጽሐፍ እየደጋገሙ እዚያው ባሉበት አሉ።
የሚገርመው እነኝህ ግትር ፖለቲከኞች ራሳቸውን የማርክሲስት ፍልስፍናዎችን አንብብው ራሳቸውን በፖለቲካው መድረክ ተዋናይ ያደረጉ ቢሆንም ማርክሲዝም ከሚታወቅባቸው አንዱ እና ዋንኛው የሆነውን ዲያሌክታዊ (DIALECTICS) አስተሳሰብን እናራምዳለን የሚሉ ሜታ ፊዚክሰን የሚተቹ ቢሆንም በተግባር ግን ዲያሌክታዊ (DIALECTICS) አስተሳሰብን የረሱ ሜታ ፊዚክሰን የሚደግፉ አይነት ሰዎች ናቸው ።
እነኝህ አካላት ራሳቸውን የማርክሲዝም ፍልስፍና ፈትፋች አጉራሽ ያድርጉ እንጂ በተፈጥሮ ያሉ ክስተቶች ሁሉ በማያቋርጥ እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን እና የማያቋርጥ ለውጥም እንደሚያደርጉ የሚያስተምረውን የማርክሲዝም ፍልስፍና የሆነውን ዲያሌክታዊ (DIALECTICS) አስተሳሰብ በፍጹም የዘነጉ ናቸው። ስለሆነም ለኢትዮጵያ ሰላም እነኝህን ቆሞ ቀሮች አጥበቀን ልንፋለማቸው ይገባል ! ብሎ ንግሩን ሲጨርስ የሰፈራችን ሰዎች በጭብጨባ አጀቡት። ስብሰባውም በዚሁ ተቋጨ።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 26/2015