በአስደሳች ድሎች፣ አወዛጋቢ ውጤቶች እንዲሁም ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ያለፈው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ዛሬ ይጠናቀቃል። በዛምቢያ ናዶላ ከተማ አዘጋጅነት ይህ ቻምፒዮና ከ18 እና 20 ዓመት በታች የሚካፈሉበት ውድድር ሲሆን፤ በጥምረት መካሄድ ከጀመረ ዘንድሮ ሁለተኛ ጊዜው ነው። በየፊናቸው ይካሄዱ የነበሩት እነዚህ ውድድሮች ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮናው ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ፤ ከ18 ዓመት በታች ቻምፒዮናው ደግሞ ለ4ኛ ጊዜም ነው የተከናወነው።
የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን የሚመራው በዚህ ውድድር ላይ 50 ሃገራት አትሌቶቻቸውን ከ18 ዓመት በታች በ40 እንዲሁም ከ20 ዓመት በታች በ44 የውድድር ዓይነቶች አሳትፈዋል። ከእነዚህ መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን ብሄራዊ ቡድኗ እስከ ትናንት ቀትር ድረስ 6 የወርቅ፣ 4 የብር እና 3 የነሃስ በጥቅሉ 13ሜዳሊያዎች ተመዝግበዋል። አስደሳች ድሎችና አወዛጋቢ ውጤቶች በተመዘገቡበት ቻምፒዮና ፈታኝ ሁኔታዎችን ለማሳለፍ የተገደደው ወጣት ቡድኑ ለዚህ መድረሱም እጅግ የሚያስመሰግነው ሆኗል።
ሃገራቸውን ወክለው በውድድሩ የተካፈሉት የቡድኑ አባላት ከ30 ያላነሱ አትሌቶች ሲሆኑ፤ በሁለቱም ጾታ እና የዕድሜ እርከኖች ከ800 ሜትር ጀምሮ እስከ 10 ሺህ ሜትር ድረስ ባሉ የውድድር ርቀቶች ተካፋይ ነበሩ። በዚህም ከ18 ዓመት በታች በጥቅሉ 3 ሜዳሊያዎች ሲመዘገቡ፤ ከ20 ዓመት በታች ደግሞ 10 ሜዳሊያዎች ተመዝግበዋል። በመጀመሪያው ዕለት ከተካሄዱ ውድድሮች ኢትዮጵያዊያን የተካፈሉበት የፍጻሜ ውድድር ከ20 ዓመት በታች 3ሺ ሜትር ሴቶች ሩጫ ከወርቅ እስከ ነሃስ ያሉትን ሜዳሊያዎች ጠራርጎ በመውሰድ ነበር ውደድሩ የተጀመረው። የድሉ ባለቤቶችም አትሌት አስማረች አንለይ፣ የኔዋ ንብረት እና አይናዲስ መብራቱ ናቸው።
በውድድሩ የሁለተኛ ቀን ውሎም ከ20 ዓመት በታች የሴቶች 1ሺ500ሜትር በተመሳሳይ ውብርስት አስቻለ፣ ሳምራዊት ሙሉጌታ እና ምጥን እውነቴ ተከታትለው በመግባት ከአንድ እስከ ሶስት በመውጣት ድሉን አስመዝግበዋል። በወንዶች በኩል ደግሞ አሸናፊ ኢማና ሁለተኛ በመሆን ሲገባ፤ ሁለት ዲፕሎማዎች ተገኝተዋል። ከ18 ዓመት በታች በ3ሺ ሜትር ርቀት ማርታ ዓለማየሁ የብር ሜዳሊያ ባለቤት ስትሆን፤ በ2ሺ ሜትር መሰናክል ወንዶች ደግሞ ኦብሳ ፈይሳ የነሃስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።
በሶስተኛው ቀን በተካሄዱ የፍጻሜ ውድድሮችም ከ18ዓመት በታች 3ሺ ሜትር መሰናክል ሰውመሆን አንተነህ የወርቅ ባለቤት ሊሆን ችሏል። ከ20 ዓመት በታች የወንዶች 10ሺ ሜትር እርምጃ ውድድርም የወርቅ ሜዳሊያው በምስጋና ዋቁማ ተመዝግቧል። ከ20 ዓመት በታች ሴቶች 3ሺ ሜትር መሰናክል ደግሞ አለምናት ዋለ እና ፍሬህይወት ገሰሰ ተከታትለው በመግባት የወርቅና የነሃስ ሜዳሊያውን ወስደዋል። ይሁንና በዚህ ርቀት የተገኘው ሜዳሊያ የውዝግብ መንስኤ ሊሆን መቻሉን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በድረገጹ አስነብቧል።
ይኸውም ከ20 ዓመት በታች የ3ሺ ሜትር መሰናክል ሴቶች ውድድር ለኢትዮጵያ የተመዘገበው የወርቅና የብር መሜዳሊያ አሸናፊ የሆኑ አትሌቶች እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ሆኖ የተወዳደሩት ግን ከ20 ዓመት በታች ውድድር ላይ በመሆኑ ነው። የተነሳው የተገቢነት ጥያቄም ‹‹ከእድሜያቸው በላይ በሆነ ውድድር ገብተው መወዳደር አይችሉም›› የሚል ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በበኩሉ ‹‹ከታችኛው የእዕሜ ደረጃ ወደ ላይኛው ዕድሜ ጣራ መወዳደርን የዓለም አትሌቲክስ ስለሚፈቅድ መብታችን ነው›› የሚል አቋም ይዟል። በዚህም ምክንያት ዘገባው እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ውጤቱ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ውስጥ አለመካተቱን አዲስ ዘመን አረጋግጧል።
ብሄራዊ ቡድኑ ከቀናት በፊት በአትሌቶች ስነልቦና አሉታዊ ስሜት ሊያሳድር የሚችል አስቸጋሪ ሁኔታም ገጥሞት ነበር። ይኸውም ከውድድሩ የመክፈቻ ስነስርዓት በኋላ መኝታ ማጣቱን ተከትሎ ውድድሩ ከሚካሄድበት ከተማ እስከ 65 ኪሎ ሜትር ለመጓዝ ተገዷል። ሆኖም መኝታ ባለማግኘቱና አግባብ ያልሆነ ምላሽ በማግኘቱ የቡድኑ አባላት ለሊቱን በመሬት ላይ እንዲሁም በወንበር ላይ ተኝተው ለማሳለፍ ተገደዋል። ሆኖም አባላቱ ጽናታቸው በሚያስመሰክር መልኩ በነገታው በተካሄደው ውድድር ተከታትለው በመግባት ከወርቅ እስከ ነሃስ ያለውን ሜዳሊያ መውሰዱ በርካቶችን አስደንቋል። ዛሬ በሚካሄዱ የፍጻሜ ውድድሮችም ቻምፒዮናው የሚጠቃለል ይሆናል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25/2015