ገጣሚ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣ ደራሲ፣ ሃያሲ፣ ተርጓሚ፣ መምህር እና የስነ ጽሑፍ ተመራማሪ ደበበ ሰይፉ ያረፈው በዚሁ ሳምንት ከ23 ዓመታት በፊት ሚያዚያ 16 ቀን 1992 ዓ.ም ነው።
ደበበ ሰይፉ ሥራዎቹ በተደጋጋሚ የሚጠቀሱና በብዙ የስነ ጽሑፍ ወዳጆች የተመሰከረለት ገጣሚ ነው። የግጥም ትሩፋቶቹ በአንድ ላይ ተሰባስበው ‹‹የብርሐን ፍቅር›› በሚል ርዕስ ታትመዋል። በ1992 ዓ.ም ደግሞ በሜጋ አሳታሚ ድርጅት አማካኝነት ‹‹ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ›› በሚል ርዕስ ሁለተኛዋ የሥነ ግጥም መፅሐፉ ታትማ ለንባብ በቅታለች።
ደበበ ሰይፉ ከገጣሚነቱ ባሻገር ሐያሲም ነበር። ያለፈውን ከአሁኑ ጋር እያነፃፀረ የሚያስረዳና የሚተነትን ባለሙያ ነው። የሒስ ጥበብን ከታደሉትና በኢትዮጵያ የዘመናዊ ሂስ ጥበብ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት ሰዎች መካከል ደበበ ሰይፉ አንዱ ነበር።
ደበበ የትያትር ጥበብ መምህር ከመሆኑም በላይ በዘርፉ ውስጥ ግዙፍ የሚባል አስተዋፅኦ አበርክቶ አልፏል። ደበበ በመድረክ ላይ የሚሠሩ ቴአትሮችንና የቴአትር ጽሑፎችን የያዟቸውን ሐሳቦች በመተንተንና ሒስ በመስጠት ለዘርፉ ዕድገት የበኩሉን ሚና ተጫውቷል።
ደበበ የቃላት ፈጣሪም ነው ይባልለታል። ለአብነት ያህል በትያትርና በሥነ ጽሑፍ ዘርፎች ውስጥ በእንግሊዝኛ ቋንቋ መጠሪያ የሆኑ ሙያዊ ቃላትን ወደ አማርኛ በማምጣት አቻ የሆነ የአማርኛ ትርጉም በመስጠት ይታወቃል። በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ክፍለ ትምህርት ውስጥ እስከ አሁን ድረስ መጠሪያ የሆኑትንና ‹‹ገፀ ባህርይ››፣ ‹‹ሴራ››፣ ‹‹መቼት››፣ ‹‹ቃለ ተውኔት›› … እየተባሉ የሚገለፁትን መጠሪያዎች የፈጠረው ደበበ ሰይፉ ነው።
ደበበ ለትያትር ትምህርት ዘርፍ ካበረከታቸው አስተዋፅኦዎች መካከል ለትምህርቱ መጐልበት ይረዳ ዘንድ በ1973 ዓ.ም ‹‹የቴአትር ጥበብ ከጸሐፌ ተውኔቱ አንፃር›› የሚል ርዕስ ያላት መጽሐፍ ማሳተሙ የሚጠቀስ ነው።
ደበበ ጸሐፌ ተውኔትም ነው። በርካታ ተውኔቶችን ጽፎ ለመድረክ አብቅቷል። አንዳንዶቹ ደግሞ ለበርካታ ጊዜያት ያህል በቴሌቪዥን ታይተውለታል። ደበበ ከጻፋቸውና ከተረጐማቸው ተውኔቶች መካከል ‹‹ከባህር የወጣ ዓሳ››፣ ‹‹እናትና ልጆቹ››፣ ‹‹እነሱ እነሷ››፣ ‹‹ሳይቋጠር ሲተረተር››፣ ‹‹የሕፃን ሽማግሌ››፣ ‹‹ማክቤዝ››፣ ‹‹ክፍተት››፣ ‹‹እድምተኞቹ›› እና ‹‹ጋሊሊዮ ጋሊሊ›› ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ በነበረባቸው ዓመታት በርካታ የምርምር ስራዎችን አከናውኗል፤ ብዙ መጽሐፍትንም ጽፏል። በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ተቋም የጥናት መጽሔት አሳታሚ ኮሚቴ እና በኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊ በመሆን ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ መስፋፋት ሰፊ እገዛ አድርጓል። እነሆ በሥራዎቹም ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22/2015