ኢትዮጵያ የባሕል፣ የቋንቋና የማኅበረሰብ እሴት ብዝኃነት ያላት አገር ነች። ሕዝቦች ዘመናትን ተሻግረው አብሮ የመኖር ጠንካራ ሥነ ልቦናዊ ማንነት የገነቡት በእነዚህ ኢትዮጵያዊ እሴቶች ነው። ማንነቶችን አክብሮ፣ በደስታና በመከራ ጊዜ አብሮ ለመኖር የሚያስችል ጠንካራ ሥርዓት የገነቡት ባሕላዊና ሃይማኖታዊ መልክ ባላቸው አገር በቀል አደረጃጀቶች ነው። እነዚህ አደረጃጀቶች ኅብረተሰቡን የሚያስተሳስሩ፣ ዜጎችን ሰብዓዊነት የሚያላብሱ፣ ግብረ ገብነትና መከባበርን የሚያስተምሩ ናቸው።
ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባሉባት ኢትዮጵያ ከየባሕሎቹና ሃይማኖቶቹ የተቀዱ ሀገርኛ ሥነ ሥርዓቶች (ማኅበራዊ አደረጃጀቶች) በርካታ ናቸው። አለመግባባት ሲኖር፣ ሉዓላዊነት ሲደፈርና ልዩ ልዩ ኅብረትና አንድነትን የሚጠይቁ ጉዳዮች ሲገጥሙ እነዚህ አደረጃጀቶች ጥቅም ላይ ውለው ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረክታሉ።
የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው “ሀገርኛ” አምድ ላይ ከእነዚህ ባሕላዊ አደረጃጀቶች መካከል አንዱ የሆነውንና የሐረሪ ብሔሄረሰብ መገለጫን “አፎቻ” ሥርዓት ሊያስቃኛችሁ ወዷል። መረጃውን የሰጡን የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት የባሕል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወልዳ አብዶሽ ናቸው። መልካም ቆይታ።
አፎቻ ምንድን ነው?
እንደ ባሕል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮው ኃላፊ አቶ ተወልዳ አብዶሽ ገለፃ፣ አፎቻ በአንዳንድ የብሔረሰቡ አባላት ዘንድ እድር በሚል ስያሜ ይታወቃል። “ሜሺያ” በተባለ የክልሉ መዝገበ ቃላት ውስጥ ደግሞ ማኅበር የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል። አፎቻ በሐረሪ ብሔረሰብ በተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ መደጋገፍንና መተባበርን መሠረት አድርጎ የሚመሠረት ወይም የሚቋቋም ማኅበራዊ ተቋም በመሆኑ ለማኅበረሰቡ አባላት ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ይሰጣል። በብሔረሰቡ ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥም ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ ሐረሪዎች ማንነታቸውን ጠብቀው ለዘመናት እንዲዘልቁ ካደረጉ መሠረቶች ውስጥ አንዱ ነው።
ከዚህ በመነሳትም አፎቻ የሐረሪ ብሔረሰብ መለያና ዋነኛ መገለጫ ነው ማለት ይቻላል። አፎቻ የሚለው ቃል ‹‹ጋር አፎቻ›› ከሚለው ቃል የተገኘ ሲሆን፣ ትርጉሙም ጎረቤት ማለት ነው። አንድ አካባቢ በጉርብትና የሚኖሩ ሰዎች በባሕላዊ መልኩ ተደራጅተው የሚያቋቁሙት ማኅበራዊ ተቋም ነው።
የአፎቻ አመሠራረት
“በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ አፎቻ መቼና እንዴት እንደ ተጀመረ ባይታወቅም በቃል እየተነገረ ከመጣው ትውፊት መረዳት የሚቻለው ተቋሙ ጥንታዊ መሆኑና እያንዳንዱ ትውልድ የራሱን አሻራ እያከለበት በቅብብሎሽ መዝለቅ የቻለ ማኅበራዊ ተቋም እንደሆነ ነው” የሚሉት የቢሮ ኃላፊው፤ የአፎቻ አመሠራረት ጾታን መሠረት ያደረገ መሆኑንም ይገልጻሉ። በዋናነት የሚታወቁት የአፎቻ አይነቶችም አቦች አፎቻ (የወንድ አፎቻ) እና ኢንዶች አፎቻ (የሴት አፎቻ) መሆናቸውን ይናገራሉ።
ከዚህ በተጨማሪ አህሊ አፎቻ (የዘመድ)፣ ጋር አፎቻ (የመንደር)፣ ቶያ አፎቻ( የሰፈር)፣ ሀርሺ አፎቻ (የእርሻ)፣ ጊዲር አፎቻ (ትልቁ) እና ላቂ አፎቻ (የአፎቻዎች ጉባዔ) ተብለው የሚጠሩ የአፎቻ አይነቶች መኖራቸውንም ያብራራሉ። እነዚህ የአፎቻ አይነቶች እንደተቋቋሙበት ዓላማ በሐረሪዎች ዘንድ የተለያየ ሚና እና ተግባር አላቸው።
አፎቻ የተደራጀ መዋቅር ያለው ተቋም በመሆኑ ቋሚ አባላት፣ አመራሮች፣ መተዳደሪያ ደንብ (የተጻፈ ወይም ያልተጻፈ)፣ መብቶች እና ግዴታዎች እንዲሁም የቅጣት መርሆች አሉት።እንደ እሳቸው ገለጻ፤ አሁንም ያ ነው የቀጠለው።ያም ሆኖ አሁን ላይ ጊዜው እየተሻሻለ መጥቶ የተጻፈ ሕግ አለ። ለተጻፈውም ሆነ ላልተጻፈው ሕግ የአፎቻ አባላት ተገዢዎች ናቸው። የአፎቻ አመራሮች ማኅበሩን በጥንቃቄ እና በብስለት የመምራት ኃላፊነት ያለባቸው ሲሆን፣ አዲስ አባል የማስገባት፣ አባላት ማኅበራዊ ኃላፊነቶቻቸውን በተገቢው ሁኔታ መፈጸማቸውን፣ ባሕሉ በሚፈቅደው ሥነ-ምግባር መጓዛቸውን እና ከሥነ-ምግባር ውጭ የሆኑት ደግሞ ተገቢውን ቅጣት ማግኘታቸውን ሁሉ ይቆጣጠራሉ።
ከዚህ በተጨማሪ መዋቅሩ በአባላቱ መካከል የሥራ ክፍፍል ያለው ሲሆን፣ ለምሳሌ እንደ ገንዘብ ያዥ፣ ንብረት አስተዳዳሪ፣ ሂሳብ ሠራተኛ፣ ለቀብር ቁፋሮ አስተባባሪ፣ አሙታ ጋር ወይም የኃዘን ቤት ሥርዓት አስተባባሪ እና የፊርዛል ወይም የስብሰባ ጥሪ አስተላላፊ የመሳሰሉት የሥራ ክፍፍሎች አሉት።
“በሴቶቹም ሆነ በወንዶቹ አፎቻን የሚመሩት በእድሜ የበሰሉ፣ በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸውና ባሕልና ወጉን በሚገባ የሚያውቁ አባቶች እና እናቶች ናቸው” የሚሉት የቢሮ ኃላፊው፤ በአመራር ላይ የሚቀመጠውን ቡድን የሚሾመው ደግሞ በአባላቱ ተሳትፎ በሚከናወን ምርጫ እንደሆነ ይገልፃሉ። በአፎቻው ለአመራርነት የተቀመጠ ሰው ጥፋት እስካልተገኘበት ወይም በቃኝ እስካላለ ድረስ በቦታው ይቆያል። በማንኛውም ወቅት ከአባላቱ የመተማመኛ ድጋፍ ካጣ ወይም ድምጽ ከተነፈገ ግን ጥፋት ባይገኝበትም እንኳን ከኃላፊነቱ ይነሳል ይላሉ።
የአፎቻ አስፈላጊነት
እንደ ቢሮ ኃላፊው ማብራሪያ፤ አፎቻ በሐረሪ ማኅበረሰብ ዘንድ በጣም አስፈላጊ ማኅበራዊ ተቋም ነው፤ ለሐረሪ ብሔረሰብ ማኅበራዊ ጉዳዮች መሠረታዊና ቁልፍ ጉዳይ ነው፤ እንደተቋም ከግለሰብ አቅም በላይ የሆኑ ማኅበራዊ ችግሮችን በጋራ ለመወጣትና ማኅበራዊ ግንኙነትን በማጠናከር ረገድ የማኅበረሰቡ ዋስትና ነው ማለት ይቻላል። በሐረር ያለ ዘመድ መኖር ይቻላል፤ ያለ አፎቻ ግን መኖር አይቻልም። በመሆኑም እያንዳንዱ የሐረሪ ማኅበረሰብ የግድ የአፎቻ አባል መሆን ይጠበቅበታል።
በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ አንድ ግለሰብ ትዳር ከመሠረተ በኋላ ከወላጆቹ ተለይቶ የራሱን ሕይወት መኖር የሚጀምር በመሆኑ የወላጆቹ አፎቻ ለእርሱ አገልግሎት ስለማይሰጥ ራሱን ችሎ የአፎቻ አባል መሆን ይኖርበታል። በብሔረሰቡ አንድ ሰው ጌይ ኡሱእ የአፎቻ አባል የሚሆነው ወይም የምትሆነው ካገባ ወይም ካገባች በኋላ ቢሆንም ዕድሜው ለአቅመ አዳም ከደረሰ ባያገባም እንኳ የአፎቻ አባል መሆን ይጠበቅበታል።
አቦቻች አፎቻ (የወንዶች አፎቻ) በትዳር ዓለም ያሉ ጌይ ኡሱኦችን ወይም አባ ወራ (አቦች) በአባልነት የሚያቅፍ ነው። እማ ወራዋም በኢንዶቻች አፎቻ (የሴቶች አፎቻ) ውስጥ ትሳተፋለች። አፎቻ በደስታና በኃዘን እንዲሁም በችግሮች ዙሪያ መደጋገፍን ዋነኛ ዓላማው አድርጎ የሚመሠረት እንደ መሆኑ በብሔረሰቡ የባሕል ሕግ ሥርዓት ውስጥ የዳኝነት ሥራ በመሥራትም ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረክታል።
የአፎቻ ዓይነቶች
አቶ ተወልዳ አብዶሽ ሲናገሩ፤ በብሔረሰቡ አፎቻ ጾታን መሠረት ባደረገ መልኩ አቦች (የወንዶች) እና ኢንዶች (የሴቶች) በሚል እንደሚመሠረት ይገልፃሉ።በዚሁ መሠረት የተለያዩ የአፎቻ ዓይነቶች ይመሠረታሉ። አፎቻዎች በዕለት ተዕለት የማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የየራሳቸው ሚና አላቸው። የሴቶችም ሆነ የወንዶች አፎቻ የሚያከናውኑት ተግባር እርስ በርስ የሚደጋገፍ ቢሆንም እስላማዊ ባሕሉን በጠበቀ መልኩ ሁለቱም አፎቻዎች የየራሳቸው ድርሻና ኃላፊነት አላቸው።እነዚህ የአፎቻ ዓይነቶች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
አቦች አፎቻ (የወንዶች አፎቻ)
“ይህ የአፎቻ አይነት በተለምዶ ዋናው አፎቻ በመባል ይታወቃል፤ በወንዶች ብቻ የሚመሠረት ነው” የሚሉት አቶ ተወልዳ አብዶሽ፤ በሐረሪዎች አንድ ወንድ ትዳር ሲመሠርት የአፎቻ አባል መሆን ይጠበቅበታል። የአፎቻ አባልነት በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ቢሆንም፣ የቤተሰብ ጥሪ ወይም ግብዣም አለበት።በመሆኑም ወንድ ልጅ የአባቱ አፎቻ አባል እንዲሆን ይጋበዛል። ይህ በአባት አፎቻ ተጋብዞ አባል የመሆን ሥርዓት አንድን ቤተሰብ በአፎቻ አባልነቱ ትውልዱ እስከቀጠለ ድረስ እንዲቆይ ያደርገዋል።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ የወንዶች አፎቻ በሐዘን ወቅት የመቃብር ቁፋሮ እና የቀብር ሁኔታ በትክክል መከናወኑን የሚከታተል እንዲሁም በሟች ቤት የሚደረግን ቁርዓን የመቅራት፣ ለሟች ተገቢውን ጸሎት መደረጉን የሚከታተል እና እነዚህን ተግባራት በተገቢው ሁኔታ የሚከውኑ አካላት አሉት። በሠርግ ወቅትም ቢሆን የወንዶች አፎቻ ኃላፊነት የመውሉድ እና ዚክሪ ሥርዓቶችን በመፈጸም ላይ ያተኮረ ነው። በወንዶች አፎቻ ውስጥ ሴቶች በአባልነት የሚሳተፉባቸው ሁኔታዎች አሉ። በተለይም የአፎቻ አባል የሆነ የቤቱ አባወራ በሞት ከተለየና በቤቱ ሌላ ወንድ ከሌለ ሚስት ወይም እናት አባልነቱን በመቀጠል የገንዘብ መዋጮ እና ሌሎች ኃላፊነቶችን መወጣት ትቀጥላለች። የወንድ አባላት የሚሠሯቸውን ሥራዎች ማከናወን ግን አይጠበቅባትም።
አህሊ አፎቻ
አህሊ የሥጋ ዝምድና ማለት ሲሆን አህሊ አፎቻ በዝምድና ትስስር የሚመሠረት ማኅበራዊ ተቋም መሆኑን የቢሮ ኃላፊው ይገልፃሉ። አህሊ አፎቻን የዘመድ ወይም የዘመዳሞች አፎቻ ልንለው እንችላለን። የአህሊ አፎቻ ማኅበራዊ ተቋም በአደረጃጀትና ተግባራቸው ከወንዶች፣ ከሴቶች እንዲሁም ከጊዲር (ትልቁ) አፎቻ የተለየ አይደለም። ይህ የአፎቻ ዓይነት ከተጠቀሱት የአፎቻ ዓይነቶች የሚለይበት ዋና ምክንያት አወቃቀሩ በዝምድና ትስስር ላይ የተመሠረተ መሆኑ ላይ ነው።
ጋር አፎቻ
“ጋር አፎቻ ማለት አንድ አካባቢ በጉርብትና የሚኖሩ ሰዎች በባሕላዊ መልኩ ተደራጅተው የሚያቋቁሙት ማኅበራዊ ተቋም ነው” የሚሉት አቶ ተወልዳ አብዶሽ፤ ጋር አፎቻ የመንደር ማኅበር ማለት እንደሆነ ይገልፃሉ። ይህ ማኅበራዊ ተቋም በሕመም ጊዜ፣ በለቅሶ ወቅት፣ በወሊድ ጊዜ፣ በጥቅሉ በመንደሩ የተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ሲፈጠሩ ቅድሚያ ደራሽና ተሳታፊ በመሆን የሚያገለግል ነው። ለምሳሌ በመንደሩ ሰው ሲሞት ቀድመው ለአፎቻው የሚነግሩ፣ በሩቅ ያሉ ዘመድ አዝማዶችን የሚጠሩ፣ በአጠቃላይ በደስታውም ሆነ በሀዘኑ በቅርብ ሆነው የሚተጋገዙና ችግሮቻቸውን የሚፈቱት የጋር-አፎቻ አባላት ናቸው፡
ቶያ አፎቻ
የቢሮው ኃላፊ ካነሱልን የአፎቻ አይነቶች የመጨረሻው “ቶያ አፎቻ” ነው። ይህም በአባላቱ ነጻ ፍላጎት ላይ ተመሥርቶ በሰፈር ደረጃ የሚመሠረት ማኅበር ነው። ቶያ አፎቻ ትልቁ (ጊዲር) አፎቻ መግባት የማይችሉ ሰዎች የሚመሠርቱት ሲሆን፣ እንደሰፈሩ ስፋትና እንደሰፈርተኛው የአሰፋፈር ሁኔታ አመቺነት ላይ ተመሥርቶ ሀያ ወይም ሰላሳ አባላት ሊኖሩት ይችላሉ። በዚህ ላይ ጥናት ያካሄዱትና መጽሐፍም የጻፉት አብዱላሂ ኢድሪስ ያሉትን ጠቅሰው እንደተናገሩት በአካባቢው አንዲት ሴት አግብታ ሁለትና ሦስት ልጆችን ብትወልድም ትልቁ አፎቻ ወዲያውኑ አትገባም።
በመጀመሪያ በቅርበት በሰፈር ደረጃ ቶያ አፎቻ ትገባለች። ደረጃ በደረጃ ደግሞ ልጆቿ ለአካለ መጠን ሲደርሱ ወደትልቁ አፎቻ ትገባለች። ትልቁ አፎቻ እስክትገባ ድረስ ግን ከቶያ አፎቻ አስፈላጊውን ድጋፍ ታገኛለች። ትልቁ አፎቻ በዋናነት የሚመሠረተው ለደስታና ለኃዘን በመሆኑ ልጆቿ ሲደርሱ ወደ ትልቁ አፎቻ በመቀላቀል አገልግሎቱን በዚህ ደረጃ ታገኛለች። እስከዚያው ግን ኃዘንም ሆነ ደስታ ቢገጥማት በቶያ አፎቻው ተሳትፎዋ ትታገዛለች››።
ቶያ አፎቻን የሚመሩት ከላይ እንደተገለጸው በሰፈርተኛው ነጻ ፍላጎት ላይ ተመሥርቶ በምግባራቸው የተመሰከረላቸው፣ በሃይማኖት እውቀታቸው የላቁ፣ በባህሪያቸው፣ በችሎታቸው፣ ሰፈርተኛውን በማስተባበር ልምድና አቅማቸው የተሻሉ አባቶች እና እናቶች ናቸው። በዚህ መልኩ የተመረጡ አባቶች እና እናቶች በሰፈር ደረጃ በሚከሰቱ የተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ግንባር ቀደም ደራሽና ተሳታፊ በመሆን የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ይሠራሉ። ለምሳሌ በሰፈር ደረጃ ለሚከሰቱ የደስታና የኃዘን ጉዳዮች መተጋገዝን በሚጠይቁ ሥራዎች ላይ ይሳተፋሉ።
የቶያ-አፎቻ አባላት የአካባቢው ኗሪ በሆኑ ግለሰቦች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በመፍታትና ዕርቅ በማውረድ የአካባቢው ማኅበረሰብ ወደቀደመ ሰላሙ እንዲመለስ በከፍተኛ ሁኔታ ይሠራሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘ ከቶያ-አፎቻ ጋር የሚሠሩ ቶያ ራጋች ወይም የሰፈር ሽማግሌዎች ይኖራሉ። እነርሱም ማዕረጉን የሚያገኙት ባላቸው ዕድሜ፣ ችሎታና የሰፈሩን ችግሮች ለመፍታት ባደረጉት ተሳትፎና ባሳዩት የውጤት ደረጃ ተገምግመው ነው። የቶያ-ራጋች ቁጥር ገደብ የለውም። የቶያ ራጋች ማዕረግ የሚገኘው ሰፈርተኛው በሚሰጠው ዕውቅና ነው። አንዳንድ ጉዳዮች ወደቶያ አፎቻ ወይም ቶያ ራጋች የሚመጡት በባት ወይም አባት ራጋች ያልተፈቱ ጉዳዮች በይግባኝ መልክ ወይም ሰፈሩን በሙሉ የሚመለከቱ ጉዳዮች ሲሆኑ የሚቀርቡበት ነው።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20/2015