ኢትዮጵያውያን በጠንካራ ማኅበራዊ ትስስር፣ የአብሮነትና የመደጋገፍ ባሕል ይታወቃሉ። ማሕበራዊ ትስስራቸው አገር በቀል እውቀትን፣ ባሕልና ማንነትን ማዕከል ያደርጋል። ይህ ጠንካራ ማሕበራዊ ውል በጋራ ከመኖር ያለፈ ትርጉም አለው። ተደጋግፎ የመኖር (የአንቺ ትብሽ አንተ ትብስ መባባል) ከጥንትም በኢትዮጵያውያን ዘንድ የነበረ ነው። ይህ ባሕላዊ መሰረት ያለው እሴት የዜጎች ማሕበራዊ መጠንከር አንዱ ምሳሌ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
በተለያየ ምክንያት የተቸገሩ ዜጎች፣ ግለሰቦችና የማሕበረሰቡን አባላት በተደራጀ መንገድ (በእቁብ፣ እድርና በሌሎች አደረጃጀቶች) የመደገፍና የማቋቋም ልምድ አለ። ይህ ስርዓት ከሌላው ዓለም በተለየ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በብዛት ይንጸባረቃል።
ለምሳሌ በጉራጌ ብሔረሰብ ቤተሰብ፣ ወዳጅ እና የልብ ጓደኛን በእቁብና በመዋጮ በመደገፍ የንግድ ስራ እንዲጀምር፤ ድጋፉን ያገኘው ግለሰብ ሰርቶና ተለውጦ እሱ ደግሞ በምላሹ ሌሎችን በተመሳሳይ እንዲያግዝ የሚያደርግ የቆየ ባሕል አለ። በኦሮሞ ብሔረሰብም እንዲሁ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋ ሀብት ንብረቱን ያጣ ግለሰብና ቤተሰብን ፈጥኖ በመድረስ የማገዝ ልምድ አለ። በሌሎች በርካታ ኢትዮጵያውያንና ብሔረሰቦች ዘንድ በልዩ ልዩ አደረጃጀቶች የመደጋገፍና የመተባበር እሴት ይታያል።
በኢትዮጵያ ከላይ ካነሳናቸው መንገዶች ሌላም የበጎ አድራጎት ተግባር በተለያየ መልኩ ይከወናል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማሕበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ የሚያውሉ (ጥቂት በመደጋገፍ ስም የሚነግዱ ወንጀለኞች ቢኖሩም) እየበረከቱ ነው። ከዚህ ባሻገር አገር በቀል የግብረ ሰናይ ድርጅት በመክፈት በጎ ፍቃደኞችን በማስተባበር በዘላቂነት ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ‹‹አለሁ›› የማለትና ለወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች የስራ እድል መፍጠር እየተለመደ ነው። ይህ መሰሉ ስርዓት ባሕላዊውን አደረጃጀት የሚያጠናክር የቆዩ እሴቶችን በዘላቂነት ለማስቀጠል የሚረዳ እንደሆነ ይታመናል።
በባሕላዊ መንገድና በተቋማዊ አደረጃጀት ከሚደረጉ የበጎ ስራ ተግባራት ባሻገር ግለሰብ ተፅእኖ ፈጣሪዎችም እንዲሁ በዚህ ተግባር ላይ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ይታመናል። በግል ጥረት፣ ሀብትና እውቀታቸው የበርካታ ዜጎችን ሕይወት ሲያሻሽሉ፣ ለተቸገሩት ፈጥነው ሲደርሱ እንመለከታለን። እነዚህ ግለሰቦች ሲያልፉ ደግሞ ተከታዮቻቸው ራዕያቸውን በመጋራት አልያም መልካም ስማቸውን በማስቀጠል በበጎ ምግባር ስራው ላይ ሲሳተፉ አስተውለናል።
ከዚህ በተጨማሪ በልዩ ልዩ ዘርፍ እውቅናን ያተረፉ፣ ለአገር፣ ለማኅበረሰብና ለተወለዱበት አካባቢ ባለውለታ የሆኑ ግለሰቦች መልካም ስማቸው በዘላቂነት እንዲታወስ በሚል ቤተሰቦቻቸው (ስማቸውን ተጠቅመው) ፋውንዴሽኖችን ያቋቁማሉ። በፋውንዴሽኑም ለወጣቶች የትምህርት እድል፣ የሙያ ስልጠና እንዲሁም ሌሎች እውቀቶች ማግኝት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ሲፈጥሩ እንመለከታለን።
ከላይ ያነሳናቸው ጉዳዮችን በምሳሌ ለማስረዳት እንችል ዘንድ የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው ሀገርኛ ዓምዱ ላይ በአንድ ፋውንዴሽን ላይ ትኩረቱን አድርጓል። በዳሰሳውም አገር በቀል ፋውንዴሽኑ የተቋቋመበትን ዓላማ፣ ራዕይውንና ከምስረታው አንስቶ እያከናወነ ስላለው ተግባር በዝርዝር እንቃኛለን። ይህ ተቋም ጉዲና ቱምሳ ፋውንዴሽን ይባላል።
ፋውንዴሽኑ የመካነ-እየሱስ ቤተክርስቲያን ዋና ጸሀፊ ሆነው ባገለገሉት፣ በ1966 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የሉተራን ጉባኤ ካውንስል መስራችና ፕሬዚዳንት እንዲሁም ወንጌልን በማስፋፋት ስራ ላይ ትልቅ ስራ በሰሩት ቄስ ጉዲና ቱምሳ ስም የተሰየመ ነው፡፡
ቄስ ጉዲና ዜጎች መንፈሳዊ ጥንካሬ እንዲላበሱ አጥብቀው ከመስራታቸው ጎን ለጎን የኑሮ ደረጃቸው እንዲሻሻል፣ ከተረጂነት የተላቀቀ አስተሳሰብ እንዲሰርፅ አጥብቀው ይሰሩም እንደነበርም ይገለጻል፡፡
ወጣት ቤተልሔም ንጉሴ ትባላለች። በጉዲና ቱምሳ ፋውንዴሽን የማርኬቲንግና ሚዲያ ማኔጅመንት ባለሙያ ነች። እሷ እንደምትለው፤ ፋውንዴሽኑ ከተቋቋመ ከ30 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ለእናቶች እንዲሁም ስራ አጥ ለሆኑ ወጣቶች በተለያየ የሙያ መስክ ስልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል። ይህንን ሰልጠና የሚወስዱ የተመረጡ ተሳታፊዎች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙና ስራ የሌላቸው ሲሆኑ፤ በፋውንዴሽኑ እድል ተሰጥቷቸው አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ በማሰብ ስልጠናው ይሰጣቸዋል።
እንደ ወጣት ቤተልሔም ገለፃ፤ ጉዲና ቱምሳ ፋውንዴሽን በእጅ ሙያ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ስልጠና ይሰጣል፤ በዋናነት በሸክላ፣ በጋርመንት፣ ሽመና እና የቀርከሃ ሰራ ላይ ሰልጣኞች ሙያዊ እውቀትን እንዲማሩ ያደርጋል። ይህን መሰል አካሄድ ለዓመታት ሲከተል መቆየቱን የምትናገረው የሚዲያና ማርኬቲንግ ባለሙያዋ፣ በሚፈለገው ልክ ግን የሰልጣኞቸን ኑሮ እንዳላሻሻለ ገልፃለች።
‹‹ሰልጣኞች ሙያዊ እውቀት ማግኘታቸው ብቻ በቂ አልነበረም›› የምትለው የሚዲያና ማርኬቲንግ ባለሙያዋ፤ ምከንያቱ ደግሞ ስልጠናውን ጨርሰው ወደ ተሰማሩበት የሙያ መስክ (በሽመና፣ ቀርከሃ ስራ) ላይ የሚያመርቷቸውን ቁሳቁስ ሸጠው ኢኮኖሚያቸውን ለማሻሻልና ስራቸውን ለማስቀጠል የሚያስችል ገበያ አለማግኘታቸው መሆኑን ታስረዳለች።
ፋውንዴሽኑ ሰልጣኞቹ ከነበሩበት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ እና ስራ አጥነት እንዲላቀቁና ውጤታማ እንዲሆኑ በማሰብ የተቋቋመ ከመሆኑ አኳያ የተፈጠረውን የገበያ ክፍተት ለመሙላት ይፈልጋል የምትለው ባለሙያዋ፤ በዚህ ምክንያት ዳግም ሌላ መላ መዘየድ እንዳለበት በማሰብ ጥናት ማድረግ እና አዲስ ስትራቴጂ መፈለግ መጀመሩን ታስረዳለች። በዚህ ምክንያት ከሙያዊ ስልጠናና የሕይወት ክህሎት ድጋፍ ባሻገር የገበያ ትስስር የሚፈጥር ስትራቴጂ መንደፉንና ተግባራዊ ማድረጉን ትገልፃለች።
‹‹ላሰለጠናቸው ባለሙያዎች የገበያ ትስስር ለመፍጠር በማሰብ ‹ኮኢሊም› የሚባል ሌላ ፕሮጀክት ጀምረናል›› የምትለው ወጣት ቤተልሔም ንጉሴ፤ ፋውንዴሽኑ ከሁለት ዓመት በፊት የራሱ ሰልጣኞች የሚያመርቷቸውን እቃዎች በመግዛትና ለገበያ በማውጣት ትስስር መፍጠር መጀመሩን ታስረዳለች። ሰልጣኞቹ በለገጣፎ ልዩ ስሙ ሲሲዲ በሚባል ቦታ ላይ ሙያዊ ትምህርቱን እንደሚወስዱ በመግለፅም በዚያው አካባቢ ከቀርከሀ የተሰራ የሽያጭ ሱቅ በመክፈት ሽያጭ መጀመራቸውንም ትናገራለች።
ወጣት ቤተልሄም እንደምትለው፤ ጉዲና ቱምሳ ፋውንዴሽን በበርካታ ፕሮጀክቶች ላይ እንደሚሳተፍ የምትናገረው፣ በተለያዩ አካባቢዎች በቡና ምርት፣ በወተት አቅርቦት፣ በተማሪዎች ምገባ፣ በትምህርት እና በሌሎችም መሰል የዜጎችን ኑሮ በሚያሻሽሉ መስኮች ላይ ተሰማርቶ ለዜጎች የእውቀትና ክህሎት ድጋፍ ያደርጋል።
ሰልጣኞቹ የሚመረጡት በጥንቃቄ ሲሆን፣ ፋውንዴሽኑ ከመንግስት ጋር በትብብር ይሰራል። ሰልጣኞቹ የሚመለመሉት መንግስታዊ መዋቅርን በመጠቀም ነው፤ የእጅ ሙያ ስልጠና እንዲወስዱ እድሉ እንደሚመቻችላቸው የምታስረዳው ወጣት ቤተልሔም፤ ይህም ትክክለኛውን ፍላጎት ለመድረስ እንደሚያስችላቸው ትናገራለች። ስልጠናውን የወሰዱ ዜጎች በማኅበረሰቡ ውስጥ እየፈጠሩ ያሉትን በጎ ተፅእኖና ውጤታማነት በአግባቡ ለመለየት ይህንን መሰል ትብብር አስፈላጊ እንደሆነም ትናገራለች።
ለስልጠናው የተመረጡት ነዋሪዎች ስልጠናውን ሲያጠናቅቁ በቀጥታ ወደ ስራው እንዲገቡ የሚያስችል የፋይናንስ አቅርቦት ፋውንዴሽኑ ከመንግስት ጋር በመተባበር እንደሚያመቻች ትናገራለች። በዚህም 20 በመቶ የሚሆነውን የጉዲና ቱምሳ ፋውንዴሽን ሲሰጥ ቀሪውን 80 በመቶ ደግሞ ሰልጣኞቹን ከመንግስት አበዳሪ ተቋማት ጋር በማገናኘት ብድር እንዲወስዱ እንደሚደረግ የማርኬቲንግና የሚዲያ ባለሙያዋ ትናገራለች።
ስልጠናውን እንዳጠናቀቁ የፋይናንስ አቅርቦት ወዲያው መመቻቸቱ ባለሙያዎቹ የቀሰሙትን ትምህርት ያለምንም ችግር ወደ ተግባር እንዲያውሉት እድል እንደሚፈጥርም ታስረዳለች። ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በኮኢሊም ፕሮጀክት በርካታ ዜጎች በፋውንዴሽኑ ስልጠናውን እንዲወስዱ መደረጉን ያስታወሰችው ባለሙያዋ፣ ብደሩን አግኝተው ውጤታማ የሆኑም መኖራቸውን ተናግራለች።
ጉዲና ቱምሳ ፋውንዴሽን በኮኢሊም ፕሮጀክት ሰልጣኞች የሙያ እውቀት እንዲያገኙ ለማስቻል ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር ይሰራል፤ ከእነዚህ ውስጥ ሚሊንዳ ጌት ፋውንዴሽን አንዱ ነው። ተጨማሪ የፋይናንስ ምንጭ ለማግኘት ሰልጣኞች የሚያመርቱትን ምርት በመግዛት እና ዳግም ወደ ገበያ በማውጣት የስልጠና ሂደቱ አንዲቀጥልና ሌሎች ዜጎችም የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግም ይሰራል፡፡
‹‹በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ እድል መስጠት ያስፈልጋል›› የምትለው የሚዲያና ማርኬቲንግ ባለሙያዋ፤ ይህንን ለማድረግ የገበያ ትስስር መፍጠሩ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ታስረዳለች። በዚህ ምክንያት በአገር ውስጥ ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ የእጅ ሙያ ውጤቶችን ለተጠቃሚዎች በቀላሉ ለማድረስ የኮኢሊም ፕሮጀክትን ዓላማ እያስተዋወቁ መሆኑን ታስረዳለች። ይህንን እውን ለማድረግም መንግስት በሚያዘጋጃቸው የገበያ ትስስር መድረኮች ላይ እንደሚሳተፉ ትናገራለች።
በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ በተካሄደው፤ የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት ላይ የሰልጣኞቹን ምርት ለማስተዋወቅ ተሳታፊ እንደሆኑ የምትናገረው ወጣት ቤተልሔም፤ በመድረኩም ማኅበረሰቡን ለመደገፍ እና የበጎ ዓላማው ተሳታፊ ለመሆን እድል የሚከፍት አጋጣሚ ማግኘታቸውን ትናገራለች። ስራዎቻቸውን ባስተዋወቁ ቁጥር ተሳታፊዎች ምርቶችን እንዲገዙ እድል እንደሚያገኙ ገልፃ፤ በምርቱ ተጠቃሚ ከመሆናቸውም ባሻገር ማሕበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚያስችል አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን ታነሳለች።
ጉዲና ቱምሳ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ሁሉም አካባቢዎች ላይ ለመድረስ ራእይ እንዳለው ወጣት ቤተልሔም ጠቅሳ፣ በለገጣፎና በየረር አካባቢ (አዲስ አበባ) ያላቸውን አይነት ሱቆች በክልሎች እና ሁሉም ከተሞች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሹ ታስረዳለች።
የፋውንዴሽኑ ራዕይ በዚህ የተገደበ አለመሆኑንም አንስታም፤ በሙያቸው ብቁ የሆኑ ዜጎች በመፍጠር ለወጪ ንግድ ብቁ የሆኑ አገራዊ ምርቶችን በመላክ በገበያው ላይ ድርሻቸውን ማሳደግ እንደሚፈልጉ ትናገራለች። ይህንን ማድረግ ሲችሉ የሚሰሩ ጠንካራ እጆች እንደሚፈጥሩ ጠቅሳ፣ ፋውንዴሽኑም በመተማመን ከተረጂነትና ከዝቅተኛ ኢኮኖሚ መላቀቅ ዓላማ ማድረጋቸውን ትናገራለች።
ፋውንዴሽኑ በቄስ ጉዲና ቱምሳ ስም የተሰየመበትን ምክንያት ወጣት ቤተልሔም ስታብራራ እኚሀ መንፈሳዊ አባት በደርግ መንግስት መገደላቸውን አስታውሳለች። በጊዜው ቄስ ጉዲና ቱምሳ ዜጎች ከመንፈሳዊ ጥንካሬያቸው ባሻገር የኑሮ ደረጃቸው እንዲሻሻል፣ ከተረጂነት የተላቀቀ አስተሳሰብ እንዲሰርፅ ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበራቸው ትገልፃለች።
ይህን ራዕያቸውን ለማሳካት በርካታ ጥረቶችን ያደርጉ እንደነበር በመግለፅም፣ ስኬታማ ተግባር አከናውነው ማለፋቸውን ታስረዳለች። የእርሳቸው ሕይወት ሲያልፍም ራዕያቸውን ለማስቀጠል የደርግ ስርዓት ሲያበቃ ልጆቻቸው፣ ዘመድ ቤተሰቦቻቸው እና ጓደኞቻቸው ተሰባስበው ‹‹ጉዲና ቱምሳ ፋውንዴሽን›› በሚል መጠሪያ በጎ ምግባራቸውን ማስቀጠላቸውን ገልፃለች።
እንደ መውጫ
በዓለማችን ታላላቅ የበጎ ምግባር ተቋማት እንዲመሰረቱና ሰብዓዊነት እንዲስፋፋ ግለሰቦች ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ለዚህ ማሳያነት የማሪያ ትሬዛ፣ አበበች ጎበናን፣ የሜቄዶኒያን መስራች ቢኒያምን እና ሌሎች ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎችን ተሻጋሪ ራዕይ መመልከት ይቻላል። በጉዲና ቱምሳ ፋውንዴሽንም ይህንን ራእይ ለመድገም ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዝግጅት ክፍላችን እንግዳ ያደረጋት ወጣት ቤተልሔም በዝርዝር አስረድታናለች።
ከግለሰብ ራዕይና ነገን አሻግሮ ከመመልከት ቅን ልብ የሚነሱ መሰል ተግባሮች አገርን ይሰራሉ። በበጎዎች ጥረት፣ በመተባበር፣ በአንድነት፣ አብሮ በመስራትና ማደግን የሚያምን ትውልድን ለመፍጠር ዛሬ አንድ እርምጃን እንደ ጉዲና ቱምሳ ፋውንዴሽን ያሉ አሳውን ሳይሆን አጠማመዱን የሚያሳዩ ፋውንዴሽኖች ያስፈልጉናል። ሰላም!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ዓርብ ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም