
አርቲስት ዘሪሁን ወዳጆ የአርት ሥራውን በብዛት በአፋን ኦሮሞ ቢያቀርብም ሥራዎቹ በሙሉ ገና በለጋ እድሜ ስለ ሰው ልጆች እኩልነት፣ ነፃነትና አንድነት የሚዘክሩ ናቸው፡፡ አርቲስቱ ሕዝቡን ሲያማርር የነበረውን በተለይ በጉቦ ዙሪያ «የጉቦ ጣጣ ከመንዲ ይውጣ» በማለት ገና በለጋ እድሜው በወቅቱ የነበረውን የጭቆና ሥርዓት በግልጽ የተቃወመ አርቲስት ነበር፡፡ አርቲስቱ የሰው ልጆች እኩልነትና ወንድማማችነት አቀንቃኝ መሆኑ ከመቃብር በላይ ያሉ ሥራዎቹ ምስክር ናቸው፡፡
ዘረኝነትን እንደ የማርያም ጠላት አጥብቆ ስለሚጠላ «እኔ የአንድ ወንዝና የአንድ ወገን ልጅ አይደለሁም» በሚል በጥበብ ሥራው የገለጸ አርቲስት ነው፡፡ የተለያዩ የውጭ አገራትን በመጎብኘቱ እዚያ የመኖር ዕድሉ ሰፊ የነበረ ቢሆንም ወደ አገር በመመለስ ከሕዝብ ጋር የመከራ ትግል በመምረጡ በሕዝብ ልብ ውስጥ የወርቅ ሐውልት መሥራት ችሏል፡፡
አርቲስት ዘሪሁን የፊውዳል ሥርዓትን በግንባር የተፋለመ፣ ደርግም ወደ ሥልጣን ሲመጣ «መሬት ለአራሹ» የሚለው መፈክርና አንዳንድ ለውጦቹን አስመልክቶ እንደታሰቡ ተስፋ የሚጣልባቸው ለውጦች አለመሆናቸውን ገና በጅምሩ ተገንዝቦ በጥበብ ሥራ እርቃናቸውን ያስቀረ ጥበበኛ አርቲስት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ናቸው፡፡
አርቲስቱ ከአንጋፋዎቹ የኦሮሞ አርቲስት እንደነ እልፍነሽ ቀኖ፣ ታደሰ ደበላ፣ አብተው ከበደ፣ ተርፋሳ ምትኩና ሰለሞን ደነቀ ጋር በመሆን የወለጋ ባህላዊ ኪነ ጥበብ ቡድን በማቋቋም «ኑ ከማሳችን አረም እናርም» በማለት ሕዝባዊ ትግል ዳር ያደረሰው ድንቅ አርቲስት እንደነበርም ገልጸዋል፡፡
መለያየት፣ ዘረኝነትና ክፋት ለሰው አንድነትና ወንድማዊ ሕብረት ጠንቅ በመሆናቸው በአርቲስቱ ዘንድ እጅግ የሚጠሉ አስነዋሪ ድርጊቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን አይደፈሬ በሚባሉት ዘመናት እንኳ ለእውነትና ለሕብረት ለአንዲት ሕይወቱ ሳይሰስት በመታገሉ አብዛኛውን የሕይወት ዘመኑን በእስር ያሳለፈ አርቲስት ነበር፡፡ በመሆኑም «በምንኖረው አጭር ዕድሜ ውስጥ መልካምና ዘላለማዊ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ከዘሪሁን እንማር» በማለት አቶ ቀጀላ ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡
አርቲስት ዘሪሁን አስቸጋሪ ውጣውረዶችን ያለፈ፣ ለራሱ ያልኖረና ሙሉ ጊዜውን ለሕዝብ ትግል መስዋእት ያደረገ አርቲስት ነው ያሉት ደግሞ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ሠዓዳ አብዱራሂማን ናቸው፡፡ አክለውም የነበረውን የጭቆና ሥርዓት ለመገርሰስ በመረዋ ድምጹ ትውልዱን ያስታጠቀ፣ በቅኔ በተሞሉ ግጥሞቹ ሕዝቡን ከዳር እስከ ዳር በማነሳሳት ዛሬ ለታየው ለውጥ የራሱን ትልቅ አሻራ ያስቀመጠ አርቲስት በመሆኑ በሥራው ሁሌ ይታወሳል ብለዋል፡፡
አርቲስቱ የታገለለትን ዓላማ ዳር ለማድረስ ዛሬ ከትውልዱ የሚጠበቀው በአንድነት፣ በእኩልነትና በወንድማማችነት መንፈስ ለውጡን ዳር ለማድረስ መትጋት ነው፡፡ የክልሉ መንግሥትም የሕይወት ዘመናቸውን ለሕዝብና ለአገር የቆሙና የሰሩ ባለውለታዎች እንዲሁ እንደማይተዉና ከሕዝቡ ጋር በመሆን ልጆቻቸውን ከማሳደግ በተጨማሪ መልካም ሥራቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ነው የተናገሩት፡፡ ለአገር መልካም ሥራ ሠርተው ግን ደግሞ ችግር ላይ ወድቀው ያሉ ባለውለታዎች ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመሆን ውለታ ከፋይ እንዲሆንም ወይዘሮ ሠዓዳ ጠይቀዋል፡፡
«አርቲስት ዘሪሁን ለሁሉም የሰው ልጅ ድምጽ የነበረውና ማንም ያልደፈረውን ጭቆና በጥበብ ሥራው የደፈረ ጀግና አርቲስት ነው፡፡ ዘሪሁን በሥራው ህያው ስለሆነ ሞቷል አይባልም፡፡ ወደ እረፍቱ የተደረገው የጀግና ሽኝት በሥራው ስለሆነ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ከዚህ ብዙ ነገር እንደሚማሩ ሙሉ እምነቴ ነው» ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳዊት ይፍሩ ናቸው፡፡
አርቲስት ዘሪሁን ለራሱና ለቤተሰቡ ያልኖረና ለምድራዊ ሀብት አንድም ቀን ያልተጨነቀ፤ ነገር ግን በዚያው ልክ ያልተደረገለት አርቲስት ነው ያሉት ደግሞ የአርቲስቱ ባለቤት ወይዘሮ ኦላንቱ ገመቹ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የኦሮሞ ሕዝብ በተለይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ለአርቲስቱ ያደረጉትን ድጋፍም ወይዘሮ ኦላንቱ አመስግነዋል፡፡
የአርቲስቱ ሥራዎች ከመቃብር በላይ ቢሆኑም እሱ ግን ባደረበት ሕመም በሕንድ አገር በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ሕመሙ ስለጠናበት ሚያዝያ 15 ቀን 2015 ዓ.ም በ63 ዓመቱ ለሞት እጅ ሰጥቶ ሚያዝያ 18 ቀን 2015 የፌዴራልና የክልል አመራሮች፣ ወዳጅ ዘመዶቹና የአርቲስቱ አድናቂዎች በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ካቴደራል ሥርዓተ ቀብሩ ተፈጽሟል፡፡
ዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2015