ግብርናውን ከእጅ ወደ አፍ ግብርና ወደ ኮሜርሻል ግብርና ለማሸጋገር፣ ከበሬ ጫንቃ በማውረድ ሜካናይዝድ ለማድረግ መሥራት ከተጀመረ አመታት ተቆጥረዋል። ለእዚህም በቅድሚያ አነስተኛ ይዞታ ባላቸው አርሶ አደሮች እጅ ያለውን ማሳ ወደ ኩታ ገጠም ሰፋፊ ማሳ ለመለወጥ እየተሠራ ነው።
በቀድሞው የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ በአሁኑ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በኩል እየተከናወነ በቆየው በዚህ ግብርናውን የማዘመን ሥራም ኩታ ገጠም እርሻ (ኮሜርሻል ክላስተር) እየተስፋፋ መጥቷል። ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የተገኘ መረጃ እንደሚጠቁመው፤ ሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ቤተሰቦችን በኩታ ገጠም ግብርና ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡትን የ2015 በጀት አመት የስድስት ወራት ሪፖርት ተክትሎ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳሉትም፤ በአሁኑ ወቅት የኩታ ገጠም እርሻ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር ደርሷል። ይህም በጣም ተስፋ ሰጪ ውጤት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ ገና ብዙ እንደሚቀርም ነው ያስገነዘቡት። ‹‹የዚህን እጥፍ ማድግ ብንችል በምርታማነት ላይም ከፍተኛ ለውጥ ይመጣል›› ሲሉ አስታውቀዋል።
የግብርና ሚነስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በቅርቡ ለኢቢሲ ሲገልጹ፤ ‹‹ግብርናችንን ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ የግብርና አመራረት ስልተ ምርት ወደ ኮሜርሻል ግብርና እንዲሻገር የማድረጊያው አንዱ መንገድ ኩታ ገጠም እርሻን ማስፋፋት ነው›› ብለዋል። ኩታ ገጠም እርሻ በተለይ ባለፉት አራት አመታት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንም ነው ያስታወቁት።
በዚህ በኩል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ተልዕኮው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማምጣት፣ እንዲሞከሩ ማድረግ ከዚያም ለግብርና ሥርዓቱ ማስረከብ መሆኑን ይናገራሉ። ኢንስቲትዩቱ ኩታ ገጠምን ለማስፋፋት ከዚያ ቀደም ብሎም ሞክሯል፤ የማስፋት ሂደቱ ግን በጣም በጣም ውስን ነበር ሲሉ ገልጸው፣ በአገሪቱ ከአራት አመት በፊት ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር ያልበለጠ የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር እንደነበር አስታውሰዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ በለውጡ አመራር ለግብርና በተሰጠው ትኩረት አንዱ የሰፋው ግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ነው። በእነዚህ አራት አመታት የኮሜርሻል ክላስተሩ ብዛት ከአንድ ሚሊዮን ወደ ስድስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ደርሷል። በእነዚህ አመታት ከእጅ ወደ አፍ ግብርና ወደ ገበያ ተኮር ግብርና የመሸጋገሩ ሁኔታ በጣም ፈጣን ነበር።
አሁን በኢትዮጵያ ከሚታረሰው መሬት 45 በመቶው በግብርና ኮሜርሻል ክላስተር እየታረሰ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ይህ በጣም ትልቅ እምርታ እንደሆነም ነው ያሉት ያስታወቁት። በኩታ ገጠም እርሻ አርሶ አደር አንድ ላይ ሲሆን ቴክኖሎጂ በመጠቀም፣ ምክር በመስጠት፣ ትርፍ ምርት በማግኘት በኩልም ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው አስታውቀዋል።
ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፤ መሬት ክላስተር ከተደረገ ቀጥሎ የሚመጣው ይህንን ሜካናይዝድ ማድረግ ነው። ለዚህም መንግሥት ባለፉት አራት አመታት የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል። ለግብርናው ኮሜርሻላይዜሽን የሚያስፈልጉ ከአምስት መቶ በላይ የሚሆኑ የሜካናይዜሽንና የመስኖ ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ አድርጓል፤ አርሶ አደሩ ቆጥቦ ከሃያ እስከ አርባ በመቶ ቆጥቦ እነዚህን የሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች (ትራክተሮች ኮምባይነሮች፣ የውሃ መሳቢያ ማሽኖች) በብድር እንዲወሰድ ተደርጓል።
ሊዝ ፋይናንስ አቅርቦት ለግብርናው ዘርፍ እንዲቀርብ በማድረግ ወደ ሁለት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በትራክተርና በሌሎች የሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች እንዲታረስ መደረጉንም ጠቅሰው፣ በዚህም ሜካናይዜሽን 22 በመቶ፣ ኮሜርሻል ክላስተር ደግሞ 45 በመቶ ደርሷል ይላሉ። አሁንም ለሜካናይዜሽን ሊውል የሚችል የተዘጋጀ መሬት እንዳለ ጠቁመዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር ወርቃለማሁ ጣሰው በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ መምህር ናቸው። ፒኤችዲያቸውን በአግሪካልቸራል ኢኮኖሚ እያጠናቀቁ ይገኛሉ። በግብርናው ዘርፍ በገጠር ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ላይም ሠርተዋል፤ ረዳት ፕሮፌሰሩ የኢትዮጵያ ግብርና የሚታወቀው የተበጣጠሰ እርሻ (ፍራግመንትድ) በሚለው ነው ይላሉ።
‹‹በአርሶ አደር ደረጃ ያለው መሬት አነስተኛ ነው፤ አነስተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የእኛ ገበሬ የእቅድ ችግርም አለበት። የሚያቅደው የልጆቹን የምግብ ፍላጎት ማሟላት ላይ ተመስርቶ ነው። ከጓሮው እሸቱንም ሁሉንም ነገር ራሱ አሟልቶ ኑሮውን ማሸነፍ ይፈልጋል። ይህን ማድረግ ሲያስብ ካለው መሬት ግማሹን ለበቆሎ፣ ግማሹን ለስንዴ አድርጎ ማሳውን ይበጣጥሳል። በዚህ የተነሳ በአገሪቱ ሰፋፊ እርሻ ሳይታይ ቆይቷል ሲሉ ያብራራሉ።
በቀደመው ዘመን በባሌና በአርሲ የሜካናይዜሽን ሙከራዎች እንዲሁም የመንግሥት እርሻም እንደነበር አስታውሰው፣ በተለይ የመንግሥት እርሻው አወቃቀሩ ጤናማ ስላልነበረ በተለያዩ ሞዳሊቲዎች አርሶ አደሩን ወደ ሜካናይዜሽን ለማስገባት ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን አመልክተዋል። ከዚያም ውጪ አርሶ አደሩ በራሱ እንዲሁም ባለሀብቶች አርሲና ባሌ ላይ ኮምባይነር ማሽነሪዎች ሥራ ላይ ማዋላቸውን ይጠቅሳሉ። ባለሀብቶቹ ለአርሶ አደሩ የኪራይ አገልግሎት ይሰጣሉ፤ ገበሬውም እየተከራየ ሜካናይዜሽን ለመተግበር ጥረት ያደርጋል ይላሉ።
መንግሥት ይህን ሥራ ማስፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በፖሊሲ መምጣቱ በጣም ጥሩ ሀሳብ መሆኑን ጠቅሰው፣ የተበጣጠሰ ማሳ ተግዳሮት ሆኖበት ለቆየው የሰፋፊ እርሻ ሥራ አንዱ መፍትሄ ይኸው የኩታ ገጠም እርሻ መሆኑን ይጠቅሳሉ። የግብርና ሜካናይዜሽን ሲታሰብ አንዱ አብሮ የሚታሰበው ጉዳይ አርሶ አደሩ ከቤተሰብ ፍጆታ ያለፈ የቢዝነስ ሀሳብ እንዲኖረው ማድረግ ነው የሚሉት አግሮ ኢኮኖሚስቱ፣ የኮሜርሻል ክላስተር ዋና ፋይዳ የግብርና ትራንስፎርሜሽን መሆኑን ይጠቁማሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ትራንስፎርም የሚደረገውም ከፍጆታ ወደ ገበያ (ኮሜርሻላይዜሽን) ነው። የትልልቅ አገሮችም አመጣጥ ይኸው ነው፤ ግብርናው ቢዝነስ ይሆናል። አርሶ አደሩ ከጠነከረ ባለሀብት ይሆናል፤ ካልጠነከረም ሌላ ባለሀብት ግብርና ውስጥ ገብቶ አግሪካልቸራል ኮሜርሻላይዜሽን ይመጣል። በትራንስፎርሜሽን ውስጥ የአመለካከት፣ የእውቀት፣ የሀብት፣ የቴክኖሎጂ፣ የብዙ ነገሮች ጥያቄዎች አብረውት አሉ።
‹‹ይህም ደረጃ በደረጃ የሚፈጸም ነው፤ ሥርዓት አለው፤ አንድ ጊዜ ሁሉንም ላድርግ ካልክ ይገለበጥብሃል፤ ምንም ነገር ላታደርግ ትችላለህ፤ ስለዚህ አላማው ግብርናን ደረጃ በደረጃ ወደ ኮሜርሻል ግብርና መቀየር ነው ሲሉ ያብራራሉ። ረዳት ፕሮፌሰሩ እንዳሉት፤ ግብርናው ወደ ኮሜርሻል ሲሄድ ዛሬ ብዙ ሕዝብ የያዘው ግብርና በጥቂት ሰዎች ብቻ ይካሄዳል፤ አብዛኛው ሰው ወደ ሚቀጥለው ዘርፍ (ኢንዱስትሪ) ይሄዳል።
በዚህም የግብርናው ምርት ወደ ሌላ መልክ ሲቀየር ኢንዱስትሪ ነው አብሮ የሚመጣው። የዱቄት፣ የዳቦ፣ የዘይት፣ የኬክ ኢንዱስትሪ እያሉ አግሮፕሮሰሲንግ እንዱስትሪዎች ይቋቋማሉ። ከግብርና የሚወጣው የሰው ኃይል ወደ ኢንዱስትሪው እየሄደ ግብርና ለቢዝነስ ነፃ እየሆነ ይመጣና በጥቂት ባለሀብቶች ከፍተኛ ምርት የሚመረትበት ሁኔታ ይፈጠራል። በዚህም ምርታማነቱም ውጤታማነቱም በዚያው ልክ እየጨመረ ግብርናው ሳይንቲፊክ እየሆነ ይመጣል ሲሉ ይጠቁማሉ።
አርሶ አደሮች በክላስተር ማረስ መቻላቸው ትላልቅ የግብርና ሜካናይዜሽን ማሽነሪዎችን ለመጠቀም እንደሚያስችላቸውም ረዳት ፕሮፌሰር ወርቅአለማሁ ጠቅሰው፣ ሜካናይዜሽኑም ክላስተሩም የተሰወኑ ችግሮችን እንደሚቀርፉ ይናገራሉ። ኩታ ገጠም እርሻ ማንም ሰው ሊደግፈው የሚገባ ሀሳብ ነው፤ እንዴት ነው የሚተገበረው፣ ውጤታማ ነው ወይ ዘላቂ (ሰስቴይንአበል) ነው ወይ የሚለው ግን ሊሠራበት ይገባል ሲሉም ያስገነዝባሉ።
ግብርናን እንደ ቢዝነስ ብንወስደው አንድ ቢዝነስ ሊያድግ፣ ዘላቂ ሆኖ ሊቀጥል የሚችለው ራሱን ችሎ መንቀሳቀስ ሲችል መሆኑንም አግሮ ኢኮኖሚስቱ ይጠቁማሉ፤ ሁልጊዜ ተሰጥቶት፣ በዘመቻ እየተከናወነ፣ በግፊት መቀጠል እንደሌለበትም ያሳስባሉ። አርሶ አደሩ ተጠቃሚ መሆኑን እየተረዳ ወደ ክላስተር ሥርዓቱ በፈቃደኝነት ገብቶ፣ ሕግ ኖሮት፣ የጥቅም ግጭት የሚፈታበት አሠራር እንዲኖር ከተደረገ፣ አርሶ አደሩም አዋጭነቱን ካረጋገጠ ቀጣይነት ይኖረዋል፤ በራሱ የሚሄድም ይሆናል ብዬ አስባለሁ ሲሉ ይጠቁማሉ።
አሁን በመንግሥት በኩል ማሽነሪ ማቅረብ፣ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ኤክስቴንሽኑ ላይ መሥራትን የመሳሰሉ ድጋፎች ያሉ ይመስለኛል። ይህን ማድረግ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል ያሉት አግሮ ኢኮኖሚስቱ፣ ከዚህ ይልቅ ለእኔ የሚመስለኝ፣ በሕግ መደገፍ ነው ይላሉ። ረዳት ፕሮፌሰሩ ማሽነሪ ከሚያስገቡ አስመጪና ላኪዎች ጋር አስተሳስሮ ተመጣጣኝ (ፌይር) በሆነ ዋጋ ገበሬውም ነጋዴውም ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሥርዓት መዘርጋት ይገባል።
ቢዝነስ ሁልጊዜ ሰንሰለት አለው፤ አንዱ ጋ የሚቆም አይደለም፤ አምራቾች አሉ፤ ግብአት ይፈልጋሉ፤ ለምርቱ የግብይት ሥርዓት አለ፤ እነዚህ ሥርዓቶች ጠንካራ መሆን አለባቸው ሲሉም ይመክራሉ። በግብአት፣ በማሽነሪ አቅርቦትም ሆነ መለዋወጫ በማቅረብ በኩል ጠንካራ ሆኖ መገኘት እንደሚገባም ያሳስባሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ዛሬ የገባ ማሽነሪ ነገ ሊበላሽ ይችላል። መለዋወጫ ያስፈልጋል፤ መለዋወጫው ሁሌም ገበያ ላይ መገኘት ይኖርበታል፤ መለዋወጫ እየጠፋ የሚቆሙ ማሽነሪዎች እየታዩ ናቸው፤ ይህ ችግር ሊፈታ የሚችለው የገበያ ሥርዓቱ ሲመሠረት ነው፤ መለዋወጫው በአገር ውስጥ በግል ተቋም መመረት አለበት፤ ጋራዦች በቅርብ መኖር አለባቸው፤ የሚያንቀሳቅሱትም እውቀቱና ክህሎቱ ሊኖራቸው ይገባል።
ሥራው ጅምር ላይ ስለሆነ መንግሥት ለማበረታታት ሲል ብዙ ነገር እየሸፈነ ይሆናል። ቀስ በቀስ ግን ብዙውን ሥራ ለግሉ ዘርፍ እየተወ መንግሥት እጁን ማውጣት አለበት የሚል እምነት አለኝ ይላሉ። መንግሥት ድጋፍ በማድረግ ይህን ጉዳይ ሊወጣው እንደማይችልም ጠቁመው፤ እሱ ስታብሊሽ ማድረግ እና ሲስተም ላይ ማተኮር እንዳለበት ይመክራሉ። ሁሉም ለጥቅሙ ሲል ቢዝነስ ሥርዓት ውስጥ ይገባል፤ ከዚያም ራሱን እየቻለ ይሄዳል ነው የሚሉት።
ድጎማ የሚያደርግባቸው ሁኔታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም አግሮ ኢኮኖሚስቱ አቶ ወርቃለማሁ ይጠቁማሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን የግብርና ምርቶች ይደጎማሉ። የምርቱ ዋጋ ወጪያቸውን የማይሸፍን ከሆነ፣ የማምረቻ ዋጋው በጣም ከፍተኛ ሆኖ ከተገኘ መንግሥት ፖሊሲ ቀርጾ ድጎማ ሊያደርግ ይችላል ሲሉ ገልጸው፣ የመንግሥት ድጋፍ በባለሙያ፣ በቴክኒክ፣ ጋራዦችን በማቋቋም የግንዛቤ ማሳደጊያ ስልጠናዎችን በመስጠት፣ የኤክስቴንሽን ሠራተኞች ክትትል እንዲያደርጉ በማድረግ ላይ ማተኮር እንዳለበት ያስገነዝባሉ።
ሜካናይዜሽን አሉታዊ ጎን እንዳለውም አግሮ ኢኮኖሚስቱ ያስገነዝባሉ። እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ‹‹ሜካናይዜሽን ካፒታል ኢንቴንሲቭ ነው፤ በእኛ አገር ከፍተኛ የሰው ኃይል አለ፤ አገሪቱ ውስጥ ካለው ሥራ አብዛኛው ያለው ገጠር ነው፤ ግብርናው ካፒታል ኢንቱሲቭ ከሆነ አንድን ኮምባይነር ሁለትና ሦስት ሰዎች ያንቀሳቅሱታል፤ በጣም ብዙ ሰው የሚውልበትን እርሻ እሱ በጥቂት ሰዎች ይሠራዋል፤ ይህ ሁኔታ የሥራ አጥ ቁጥርን ሊጨምር እንደሚችል መታሰብ ይኖርበታል።
ከግብርናው ዘርፍ ሥራ እያጣ የሚመጣው ኃይል ሌላ ሥራ ውስጥ እንዲገባ መደረግ እንደሚኖርበትም ጠቅሰው፣ ለእዚህ መፍትሄው አግሮ ፕሮሰሲንግ እኩል አብሮ እንዲሄድ ማድረግ መሆኑን ያመለክታሉ። የግብርና ምርቶች አግሮ ኢንዱስትሪዎች ገብተው ፕሮሰስ ሲደርጉ ብዙ የሰው ኃይል እንደሚፈልጉም ነው የጠቆሙት።
ማሽነሪ፣ መለዋወጫ፣ ነዳጅ ከውጭ ነው የሚመጣው፤ አገራችን የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ እጥረት አለባት ሲሉ ጠቅሰው፣ ትክክለኛው ወጪና ገቢ ተሰልቶ ቢዝነሱ በራሱ አዋጭ ነው ወይ የሚለው በጥናት መመለስ እንዳለበትም ይጠቁማሉ። እኔ አግሪካልቸራል ሜካናይዜሽን ባክግራውንዱ አለኝ እውቀቱ አለኝ። በግብርና ቴክኖሎጂ ላይ ከመልካስ ግብርና ጋር ሠርቻለሁ የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ከውጭ የሚገቡ አንዳንድ ማሽነሪዎችና መለዋወጫዎችም በአገር ውስጥ የሚመረቱበት ሁኔታ መመቻቸት ይኖርበታል፤ ይህን የሚደግፈውን የኢንዱስትሪውን ክፍል የሚያጠናክር ተቋምም ያስፈልጋል ሲሉ ያሳስባሉ።
ረዳት ፕሮፌሰሩ ኮሜርሻል እርሻ ለኢትዮጵያ እድገት ተስፋ አለው ብለው እንደሚያምኑ ጠቅሰው፣ ኅብረተሰቡ እንዲቀበለው ተደርጎ ማስለመድ ማስፋፋት ላይ መሥራት እንደሚገባ ይጠቁማሉ። ክላስተሩ አፈጻጸም ይጨምራል፤ በኮምባይነር ስትሰበስብና ስትወቃ በእጅ ስትሰበሰብና ስታወቃ ልዩነት አለው፤ ክላስተሩ የድህረ ምርት ብክነትን ይቀንሳል፤ ምርታማነትን ይጨምራል፤ አርሶ አደሮቹ በማህበር ስለሚሠሩ በግዥና ሽያጭ ወቅት የመደራደር አቅማቸውንም ይጨምራል፤ በዚህም የተሻለ ዋጋና ገበያ የማግኘት ዕድል ይፈጥርላቸዋል ሲሉ አብራርተው፣ ሥራው ግን ማኔጅመንት ይጠይቃል፤ ቴክኒካሊ በባለሙያ መደገፍ አለበት ብዬ አስባለሁ ሲሉም ያስገነዝባሉ።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም