እንኳን ለትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሰን፤ አደረሳችሁ። በክርስትና እምነት ዐቢይ የተባለው የሁዳዴ ጾም ዛሬ በትንሣኤው ተቋጭቷል። ጾም ከምግብ መታቀብ ብቻ እንዳይደለና በውስጡ በርካታ መንፈሳዊ ጸጋዎች እንዳሉት የሃይማኖት አባቶች ደጋግመው ይናገራሉ። ይህን አቆይተን ነገር ግን የፋሲካ በዓል በድምቀት በሚከበርባቸው አገራት ለጾም መፍቻና ለበዓሉ ድምቀት ገበታ ላይ የሚቀርቡ ምግቦችን እናነሳለን።
በአገራችን ዐቢይ ጾም ከሌሎቹ በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከሚጾሙ አጽዋማት ሁሉ ረጅሙ ነው። ምዕመናንም እንደ አቅም፣ እንደችሎታ እንዲሁም እንደጤና ሁኔታቸው ከተለያዩ የእንስሳት ተዋጽኦ ካላቸው የምግብ ዓይነቶች ታቅበው የሚቆዩት ለ55 ቀናት ነው። ከዚህም ባሻገር ከስቅለት ማለትም ከአርብ ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ድረስ በጠቅላላ ከምግብ ታቅበው የሚቆዩ ወይም «የሚያከፍሉ» ደግሞ አሉ።
ታድያ እዚህ ላይ «ታሞ ከመማቀቅ…» የሚለውን ብሂል እያስታወስን በአንድ በኩል ጥንቃቄ ማድረግ ላይ ማተኮር እንደሚገባ ላወሳ እወዳለሁ። የህክምና ባለሙያዎችም በዓል በደረሰ ቁጥር ደጋግመው እዚህ ላይ ሃሳባቸውን ያካፍላሉ፤ ምክርም ይሰጣሉ። ይህን ካልን ዘንዳ ገበታችንን እንመልከት፤ ከዶሮ ወጥ ጀምሮ የበግ ወጥ፣ ክትፎ፣ ጥብስ፣ አይብ ወዘተ ይገኛል።
የበርካታ ባህሎች ባለቤት በሆነች አገራችን፤ ገበታ ላይ እነዚህ የምግብ ዓይነቶች ብቻ እንደማይቀርቡ እናውቃለን። እንደምንኖርበት የባህል ስርዓትም በአንድ አገር ላይ ሆነንም ገበታችን የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን ሲያስተናግድ እናያለን። እንዲህ ለፋሲካ ሲሆን ግን ብዙውን ጊዜ የተለመደው ዶሮ ወጥ ነው። ከዛ በተረፈ ድፎ ዳቦና ህብስት ወይም የውሃ ዳቦ ይቀርባል። አንዳንዴም ዳቦው በውስጡ የተቀቀለ እንቁላል ይከተታል፤ ገሚሱን የዳቦ ክፍልም ቀይ በማድረግ ይቀርባል።
በሌሎች አገራትስ? ሌሎች የዓለማችን አገራት እንጀራን አያዘወትሩምና ዶሮ ወጥ አይሠሩም። ነገር ግን ዶሮንም ቢሆን እንዴት አድርገው መብላት
እንደሚችሉ የኖሩበት ባህልን ሠርተዋል። ይሁንና በተለይ በፋሲካ በዓል ላይ አብዛኞቹ ኬኮችን ወይም ጣፋጭ ዳቦዎችን ከገበታቸው አይነጥሉም። ይህም ደግሞ በፋሲካ በዓል በተለየ ሁኔታ የሚታይ ነው።
በዚህ መሰረት አንዷ ሩስያ ናት። በሩስያ ረጅምና የተድቦለቦለ ኬክ ለበዓሉ ይቀርባል። ይህም አንዳንዴ የሦስት ማዕዘን /ፒራሚድ/ ቅርጽ ያለው ነው። መጋገሪያውም ቢሆን ከመደበኛው ለየት ያለ፤ ክብ ሆኖ ቁመቱም ዘለግ ይላል። ታድያ ይህን ኬክ የሩስያ ክርስትያኖች በቅርጫት አስቀምጠውና ዙሪያውን በጣፋጮች አሰማምረው ያስባርኩታል። እስካላለቀ ድረስም ከቁርስ በፊት የሚመገቡት ሲሆን ትራፊ የሚባል ነገር አይታሰብም።
ሌላዋ አገር ጣልያን ስትሆን በጣልያን «ጉባና» የሚባል ጣፋጭ ዳቦ ይቀርባል። ይህም ጣፋጭ ጠንካራ ሲሆን በውስጡ ቸኮላት አለው። አንዳንዴም በላዩ ላይ አልኮል ፈሰስ ያደርጉበታል። በፈረንሳይ ግን ከዚህ የተለየ ምግብ ነው ለፋሲካ ገበታው ላይ የሚቀርበው፤ የበግ እግር። ይህም ስጋ በነጭ ሽንኩርት፣ ጨው፣ ቃርያ እና የወይራ ዘይት የሚጠበስ ሲሆን፤ ለፋሲካ በዓል ይህን መብላት በፈረንሳይ የተለመደ ነው።
ሜክሲኮ እንመልከት፤ ሜክሲኳዊ ቢሆኑ በለውዝና በፍራፍሬ የተሠራ ጣፋጭ ዳቦን ለፋሲካ ይመገባሉ። ይህን የምግብ ዓይነት ለበዓል ብቻ አይደለም፤ የስቅለት ቀን እንዲሁም በሰሞነ ጾሙም ሜክሲኳውያን ይመገቡታል። ከዚህም ውጪ በቀረፋና በቅርንፉድም ጣፋጭ ዳቦን ለፋሲካ ይጋግራሉ። እንደውም ይህኛው ምሳሌም ያለው ሲሆን በሚጋገረው ዳቦ ላይ ቀረፋው የክርስቶስ መስቀል፣ ቅርንፉዱ ደግሞ የተቸነከረበትን ምስማር የሚያመላክት እንደሆነ ይነገራል።
ወዲህ መለስ ብለን ደግሞ ጃማይካን እናገኛለን። በጃማይካ ስሙ የገነነና በተለይ ለፋሲካ በዓል የሚመገቡት የኬክ ዓይነት አለ። ይህም መደበኛውን ተቆራጭ ኬክ ቢመስልም በተለያዩ ቅመማት የሚዘጋጅ ወይም የሚጋገር ነው። በላዩም ላይ ቺዝ ተደርጎበት የፋሲካ እለት በማለዳ ይቀርባል።
በግሪክ ለፋሲካ የሚጋገረው ዳቦ ቀይ የምግብ ቀለም የተቀቡና የተቀቀሉ እንቁላሎች የሚከተቱበት ሲሆን፤ ጣፋጩ ዳቦ በሹሩባ መልክ የተሠራና የተገመደ ነው። እንቁላሉን ቀይ የምግብ ቀለም መቀባታቸው የክርስቶስን ደም በማሰብ ነው ይባላል። የበለጠ ደግሞ ምግቡን ለየት የሚያደርገው በአገሩ ባህላዊ የሚባሉትን «ማስቲክ» እና «ማህላብ» የተሰኙ ቅመማ ቅመሞች የሚደረግበት መሆኑ ነው።
ሳይፕረስ በሜዲትራንያን ባህር ምስራቅ ክፍል የምትገኝ ደሴት ናት። ታድያ በዚህች ደሴት የፋሲካን በዓል የሚያከብሩ ክርስቲያኖች «ፍላውንስ» ብለው የሚጠሩትን ጣፋጭ ዳቦ ይጋግራሉ። ይህ ጣፋጭ ዳቦ አነስ ባለ መጠንና እንደ ኩኪስ በብዛት የሚቀርብ ሲሆን፤ የሚዘጋጀው የስቅለት ቀን ነው። ውስጡም በአይብና በዘቢብ የተሞላ ነው።
በብራዚልም ፋሲካን ሊያከብሩ ሰብሰብ ሲሉ «ማፍን» እንደሚባለው ዓይነት ያለ ጣፋጭ ዳቦን ያቀርባሉ፤ ይመገባሉ። ይህም ከኦቾሎኒ፣ በስኳርና በጨው የሚጋገር ጣፋጭ ነው። በፖላንድ ግን እንዲህ ያለ ጣፋጭ ዳቦ ሳይሆን ሾርባ ነው የሚቀርበው። ይህም የበዓሉ ቀን ለቁርስ የሚቀርብ ሲሆን ሾርባው ድንች፣ እንቁላል፣ አይብ እና ስጋ የተቀላቀለበት ነው።
በእንግሊዝ ፋሲካ ሲከበር እንደ ሌሎቹ ሁሉ መጠናቸው አነስ ያለ ጣፋጭ ዳቦዎች ናቸው የሚጋገሩት። እነዚህም በቅመማ ቅመም የተዋዙ ሲሆኑ በላያቸው ላይ የመስቀል ቅርፅ ይሠራባቸዋል። በውስጣቸው በቁጥር 12 ዘቢቦች የሚከተቱ ሲሆን፤ ይህም ተምሳሌትነቱ የሐዋርያት ነው። ከዚህ በቀር ዴንማርክን ስናነሳ፤ በዴንማርክ እንደቀደሙት ጣፋጭ ዳቦ ወይም ኬክ አይደለም በፋሲካ በዓል ማድመቂያነት የሚታወቀው፤ መጠጥ ነው። ለፋሲካ በዓል ከምግቡ ይልቅ ማወራረጃ ቢራው የበለጠው ትኩረት ይሰጠዋል።
እንግዲህ እነዚህን ከ«ላይፍ በዝ» የተሰኘ ገጽ ላይ ያገኘናቸው ጥቂት አገራት ናቸው። በዓለማችን ላይ የክርስትና እምነት ተከታዮች ባሉበት ሁሉ ጾም ይኖራልና የበዓል አከባበርና የጾም ፍቺውም እንደ ስርዓትና ልምዱ ይለያያል። ብቻ ግን ሁሉም በልክ ሲሆን ነውና መልካም የሚሆነው፤ አበላል ላይ መጠንቀቅ ነው እንላለን። ይህ ሁሉ ዛሬ የፋሲካ በዓል ሲከበር እየተበላ እንደሆነ ልብ ይሏል። መልካም ፋሲካ!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም
ሊድያ ተስፋዬ