በዓል በደረሰ ቁጥርና የበዓል ሰሞን የሬዲዮን እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የባህል ሙዚቃዎችን ሞቅ አድርገው ይከፍታሉ። የንግድ ድርጅቶችና ገበያ ማዕከላትም እነዚህኑ ሙዚቃዎች በመክፈት የበዓሉን ድባብ ከጎዳና ጎዳና፣ ከሰፈር ሰፈር እየተቀባበሉ ዙሪያ ገባውን ያሟሙቁታል። የአዘቦት ልብሷን ጥላ የክት እንደምትለብስ ኮረዳ፤ የበዓል ሰሞናትም የባህል ሙዚቃዎችን ከያሉበት አውጥተው ይደምቁበታል።
ለምሳሌ እንዲህ በፋሲካ በዓል ላይ የታደሰ ዓለሙን «ሚሻሚሾ» የማናልሞሽ ዲቦን እንዲሁም የአምሳለ ምትኬ «አውደዓመት» የተሰኙ ባህላዊ የበዓል ሙዚቃዎችን ወዘተ ሌሎች በርካቶች በብዛት ይደመጣሉ። ልክ የክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ በአዲስ ዓመት ማለዳ ስንሰማው ደስ እንደሚያሰኘው፤ «13 ወር ጸጋ» ጨምሮ እነዚህን ሙዚቃዎችን አንረሳም።
ለዛሬ በዚህ በባህል አምድ ላይ የታደሰ ዓለሙ «ሚሻ ሚሾ» የተሰኘውን ሙዚቃ እናንሳ። በዚህ ሙዚቃ ውስጥ ሁለት ትልልቅ ጉዳዮችን ማየት እንችላለን። አንደኛው ድምጻዊው የበዓሉን ሃይማኖታዊ መሰረት የሚያነሳበት ሲሆን፤ በሁለተኛው ደግሞ «ሚሻ ሚሾ» የተሰኘውን ባህላዊ ክዋኔ ይጠቁማል። ይህንን ሙዚቃ ያበረከተልንንና ስሙንና ሥራውን ትቶ ነገር ግን በሕይወት አብሮን የሌለውን ታደሰ ዓለሙን እያመሰገንንና እያሰብን፤ ብሎም ከሙዚቃው ሥራ አብረው ለነበሩት ሁሉ እጅ እየነሳን ወደጉዳያችን እንዝለቅ።
ሙዚቃው ሲጀምር ተከታዩን ስንኞች ከዜማ ጋር አዋህዷል፤
«በቀራንዮ ላይ ታየ፣
በጎለጎታ ላይ ታየ፣
የዓለም መድኃኒት የጌታ ትንሣኤ።
አርባ ቀን አርባ መዓልት ገዳመ ቆሮንጦስ ጌታ ተፈትኖ፣
በፈጠረው ፍጡር ተወግሮ ተሰቅሎ የዓለም ቤዛ ሆኖ።
ክርስቶስ ታጅቦ እየተበተኑለት የዘንባባ ለምለም፣
ሆሣዕና በአርአያም በአህያ ውርንጫላ ገባ ኢየሩሳሌም።
ከደቀመዝሙራት በሰላሳ ዲናር ይሁዳ ሸጦት፣
በእለተ ሀሙስ ስጋ ደሙን ሰጠን ለእኛ ድኅነት።
13ቱን ህማማት ግርፋት ስቃዩን በአምላክነት ችሎ፤
በጊዜ ስድስቱ አይሁድ ቸንክረውት ጌታችን ተሰቅሎ፤
ኤሎሄ ኤሎሄ አባት ሆይ አደራ እንካት ነፍሴን አለ፤
በጊዜ ተሰዓቱ አሳለፈ ራሱን በመስቀል ላይ ዋለ።
ዲያቢሎስ ታሰረ አዳም ነጻ ወጣ ከሰራው አበሳ፤
እንኳን ደስ አላችሁ ሞትን ድል አድርጎ ጌታችን ተነሳ።
እነዚህ ስንኞች ሙሉ ለሙሉ ስለፋሲካ በዓል ሃይማኖታዊ መሰረት የሚገልጹ ናቸው። ዐቢይ የሆነው ሁዳዴ ጾም ዐቢይ ለመሆኑ ምክንያቱ የኢየሱስ ክርስቶስ አርባ ቀን አርባ ሌሊት መጾም ነውና፤ ይህም ሙዚቃ በስንኞቹ ታሪኩን ከዛ በመጀመር አቅርቦታል። ቀጥሎም ሆሣዕናን አንስቷል፤ እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ራት የበላበትን፤ እንካችሁ ብሎም ስጋና ደሙን የሰጠበትን ሐሙስን አውስቷል። የፋሲካ ትርጉሙ አንድም መሻገር ነውና፤ ዲያቢሎስ መታሰሩ ብሎም አዳም ነጻ መውጣቱ በዚሁ የሙዚቃ ግጥም ተጠቅሷል።
ይህ በጥቅሉ የፋሲካ በዓል ወይም የትንሣኤ ጉዞ ነው። ይህም ሙዚቃ ምንም እንኳ በግጥሙ የትረካ ፍሰት ላይ ከጊዜና ቦታ አንጻር ወጣ ገባ ማለቶች ቢኖሩም፤ እርሱን ለገጣሚው መብት ሰጥተን የምናልፈው ነው። ታድያ ይህ ሙዚቃ ይህን ብሎ ብቻ አያበቃል። በፋሲካ በዓል ቀደም ብሎ ከሚከወኑ ክዋኔዎችና በዓሉን መሰረት ካደረጉት ባህላዊ ስርዓቶች መካከል አንዱን መርጦ አስገብቷል፤ «ሚሻሚሾ»ን
«ኦ ሚሻ ሚሾ ሚሻ ሚሾ
ከብረሽ ቆይኝ ከብረሽ በሰላሳ ጠምደሽ
የጌታዬ ሰቀላ ተሸልሟል በአለላ
የእመቤቴ አዳራሽ ተሸልሟል በሻሽ…» በማለት ይቀጥልና፤ የበዓሉን ድባብ ያሳያል። በዚህም ከስቅለት ጀምሮ በዓሉ በሚከበርበት ቤት ሁሉ የበዓሉ ድባብ ምን እንደሚመስል ይስልልናል። የአባወራውን ቤትና የእማወራዋን እንግዳ መቀበያም ያሳየናል። ከዛ ወደ «ሚሻ ሚሾ» ጨዋታ ይዘልቃል፤
«እምዬ ይነሱ ይንበሳበሱ፣
እማ ከድፎው ቢሰጡኝ ቆርሰው፣
እማ ከጉልባኑ ይዝገኑ ይዝገኑ፣
እማ ከዱቄቱ ትንሽ በወጭቱ…
ማጣፈጫ…መሰልቀጫ፣
ትንሽ ቅቤ…ለወገቤ፣
ትንሽ ጨው…ቆንጥረው፣
ከቅመሙም…ጣል አርገው፣
በርበሬውን…ቀላቅለው»
ደራሲና ገጣሚት ውድአላት ገዳሙ ለሕትምት ካዘጋጀሁት «ልጅነትና የጉዞ ማስታወሻ» የተሰኘ መጽሐፍ የቀነጨብኩት ነው ብላ ካስነበበችው፤ ስለ ሚሻሚሾ ተከታዩን ብላለች። «ዓርብ የስቅለት ዕለት፣ ለእኛ ለልጆች ሚሻሚሾ የምንለውና በጉጉት የምንጠብቀው የቂጣ በዓላችን ነበረ። እንግዲህ የጸሎተ ኀሙስ ዕለት፣በጉልባን ንፍሮ ሆዳችን ተሞልቶ የዋልን ጉብሎች ሁላ፣ በሚሻሚሾ ቂጣ ለማለሳለስ በየተገናኘንበት ጊዜ ሁሉ፣ ወሬያችን ነገ ስለምናከብረው የስቅለት በዓል ዝግጅት ብቻ ነበር።
በዚህም ስለምንይዘው የዱቄት ማከማቻ ቁና፣ ስለምንገጥመው ወስከምባይ፣ ከማን ቤት ዕቃ እንደምንለምን፣ ማን አቡክቶ ማን እንደሚጋግርልን፣ ማን የሚሻሚሾውን ዝማሬ እንደሚያቀነቅን ወይም እንደሚመራ፣ ሌሎች ልጆች ሳይቀድሙን እንዴት በጧት ተነስተን ልመናውን እንደምንጀምር ሁሉ… ስንነጋገር እናመሻለን።» ብላ ከራሷ የልጅነት ልምድ ታካፍላለች።
ከዚህ በኋላ ወጣቶቹና ልጆቹ በየቤቱ እየዞሩ
«ሚሻ ሚሾ »ሚሻ ሚሾ -ሚሻሚሾ
እመይቴ ይነሱ – ይንቦሳቦሱ
ካደረው ዱቄት – ትንሽ ይፈሱ፤
እመይቴ – በቁልቢጡ
ነጭ ከዳቦ – ዱቄቱን ያምጡ።
ተልባና ኑጉን – ሱፉን ጨምረው
እማማ አደራ – ይዝከሩኝ አብረው።
ለስግደቱ – ለወገቤ
እመይቴ – ትንሽ ቅቤ፤
እማ ሆይ ይነሱ – ይንቦሳቦሱ፤
ማባያ ‘ሚሆን – ከጨው ድቁሱ።
መዋጫ – መሰልቀጫ፤
ከቅመሙ – ማጣፈጫ፤
እመይቴ ይነሱ – ይንደፋደፉ፤
ዘመራ ጠላ – ወይ ከድፍድፉ።
እመይቴ ይነሱ – ሳንርቅ ከደጁ፤
ከማር ወለላው – ይስጡን ከጠጁ።…» እያሉ።
በዚህ መልክ የተሰበሰበው ዱቄትና ቅመማቅመም አንድ ላይ አድርገው ከጨፋሪዎቹ መካከል አንዳቸው ወላጅ ቤት እንዲቦካ ይሆናል። የተቦካውም ብዙዎች ሰብሰብ ባሉበት በአንድ ላይ ተጋግሮ ይቋደሱታል። ስለሚሻሚሾ ባህላዊ ስርዓት እዚህ ላይ ትተን፤ ሙዚቃው ግን ይህን ባህላዊ ስርዓትም ማካተቱን እንመልከት። የሙዚቃው ግጥም ስንኞችም እነዚህኑ ባህላዊ ክዋኔ መሰረት ያደረጉና ከዛም የተዋሱ ሆነው እናገኛቸዋለን።
በእርግጥ ይህ ክዋኔ ከፋሲካ በዓል ቀደም ብሎ የሚደረግ በመሆኑ የመጀመሪያው አንድ ሃሳብ የያዘው የሙዚቃው ግጥም አንጓ በስቅለቱ ጨርሶ፤ ወደ «ሚሻ ሚሾ» መለስ ማለቱን እንታዘባለን። ይህም ሆኖ ሙዚቃው ለፋሲካ በዓልና ለሰሞኑ ልዩ ድምቀት ነው። ሌሎችም ባህላዊ ሙዚቃዎች በተመሳሳይ በዓላቱን ከነሃይማኖታዊ መነሻቸው ብሎም ባህላዊ ክዋኔውን አያይዘው ሲያነሱ እንመለከታለን።
ነገር ግን ስለእነዚህ ባህላዊ ሙዚቃዎቻችን ይልቁንም በአውደ ዓመት ጊዜ በይበልጥ ስለሚሰሙት በቂ ጥናቶች አልተሠሩም። አልያም ደግሞ የተሠሩ ጥናቶች ካሉ ለብዙሀኑ እይታ ያልቀረቡ መሆናቸው ግልጽ ነው። ባለሙያዎች እዚህ ላይ ትኩረት ቢሰጡ እያልን እናብቃ። መልካም የትንሣኤ በዓል፤ ሰላም!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም
ሊድያ ተስፋዬ