ሄዶ ከኮሪያ ዘማች ሲመለስ
ያወሳል ናፍቆቱን በክራሩ ድምጽ
ብሏል ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)። በዚህ ሳምንት ከምናስታውሳቸው የታሪክ ክስተቶች አንዱ የኮሪያ ዘማች ታሪክ ነው። የኮሪያ ዘማች ትውስታ ባለክራሩን የሙዚቃ አርበኛ ካሳ ተሰማን አስከትሎ ወደ ኮሪያ የሄደው የኢትዮጵያ አርበኞች ታሪክ ነው።
ክስተቱ ከሚያዚያ 8 ቀን ጀምሮ በ1943 ዓ.ም በዚህ ሳምንት ነው። 2 ሺህ 168 ወታደር ያሰለፈው የኢትዮጵያ የክቡር ዘበኛ ሠራዊት፣ ቃኘው የሻለቃ ጦር ወደ ኮርያ ዘመተ። ከዘማቾቹ መካከል አንዱ የነበረው ‹‹የክራሩ ጌታ›› 50 አለቃ ካሣ ተሰማ ይገኝበታል። ‹‹እልም አለ ባቡሩ›› በሚለው ዘፈኑም ክስተቱን ለታሪክ አስቀምጦታል።
የመጀመሪያው ዙር የኮሪያ ዘማቾች አንድ ሺህ 153 ሲሆኑ ቀኑ ግን በትክክል አልተገለጸም። አብዛኞቹ መረጃዎች የሚያሳዩት በመጋቢት ወር መጨረሻ አካባቢ መሆኑን ነው። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከአራት ዓመት በፊት በሰራው ዘገባ መጋቢት 30 የሚል አለው። ምናልባት እሱ የመጀመሪያው ከሆነ የሚያዚያ ስምንትና ዘጠኝ አካባቢ ያለው ሁለተኛው ዙር ይሆናል ማለት ነው። ያም ሆነ ይህ የኮሪያ ዘማቾች በዚህ ሳምንት ይታወሳል ማለት ነው።
የኮሪያ ዘማች እና ከኮሪያ ዘማቾች ማህበር መሥራች አንዱ የሆኑት የማህበሩ ፕሬዚደንት ኮሎኔል መለሰ ተሰማ በተመሳሳይ ከዘማቾች አንዱ የሆኑት አስር አለቃ ዘነበወርቅ በላይነህ የኮሪያ ዘማቾች 60ኛ ዓመት ሲከበር ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ቆይታ አድርገው ነበር።
ዘማቾቹ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ዘመቻው በአምስት ዙር ነበር። በአጠቃላይ ከስድስት ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች የዘመቱ ሲሆን 122 የሚሆኑት ተሰውተዋል። ከኢትዮጵያ ወታደሮች አንድም የተማረከ አልነበረም፤ ‹‹ሬሳ እንኳን አልተማረከብንም›› ይላሉ ዘማቾቹ።
በ2005 ዓ.ም የኮሪያ ጦርነት 60ኛ ዓመት ሲዘከር ቢቢሲ ዓለም አቀፍ ‹‹ኢትዮጵያዊው ጀግና በኮሪያ ጦርነት›› በሚል ርዕስ የኮሪያ ዘማች ስለነበሩት ሌተናል ጄነራል ማሞ ሀብተወልድ ሰፊ ሐተታ አስነብቧል። በዚህም የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት ለዓለም አሳውቋል። የቢቢሲ ዓለም አቀፍ ሐተታ የመግቢያው ጽሑፍ ደመቅ (Bold) ተደርጎ እንዲህ ተጽፏል። ‹‹ከ60 ዓመታት በፊት፤ ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ ነበረች። ጦርነቱ አፍሪካ ውስጥ እንዳይመስላችሁ! ይልቁንም በሺዎች የሚቆጠር ማይል ርቀት ላይ ኮሪያ ውስጥ ነው…›› እያለ ይቀጥላል።
ቢቢሲ በዚያው ሐተታው እንደገለጸው፤ ኢትዮጵያውያን በኮሪያ 253 ውጊያዎችን (battles) አድርገዋል። ‹‹በጦር ሜዳ እጅ አንሰጥም!›› የሚል መሪ ቃል ነበራቸው። መሪ ቃላቸውንም በተግባር አሳይተዋል። እነሆ ኢትዮጵያም በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለምም ሰላም በማስከበር እንድትታወቅ አደረጋት። እነዚህ የኮሪያ ዘማች ጀግኖችም ሲታወሱ ይኖራሉ።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2015