ለውጥ በየቀኑ፣ በየሳምንቱ፣ በየወሩ፣ በየዓመቱ አዳዲስ ነገሮችን መፈፀም ነው። ለውጥ ሁሌም ቢሆን ራስን ከሁኔታዎች ጋር አዋዶ ወደፊት መራመድ ነው። ለውጥ ደረጃ በደረጃ በሁለንተናዊ መልኩ ራስን፣ ቤተሰብን፣ ጎረቤትን፣ ህብረተሰብን፣ ማህበረሰብና አገርን መቀየር ነው። ነገር ግን ሁሌም ቢሆን ለውጥ ከራስ ይጀምራል። ራሱን ያለወጠ ቤተሰቡን ሊለውጥ አይችልም። ራሱን ያለወጠ አካባቢውን ሊቀይር አይችልም። ራሱን ያለወጠ ማህበረሰቡን፣ ህብረተሰቡንና አገሩን በተለያየ መልኩ ሊያሻሽል አይችልም።
ምንም እንኳን ለውጥ ሂደት ቢሆንም በዚህ ዓለም ራሱን በፍጥነት መቀየር የማይፈልግ ሰው የለም። ሁሉም ፈጣን ለውጥ ፈላጊ ነው። በተለይ ጤናማ አይምሮ ያለውና ነገን አሻግሮ የሚያይ በህይወቱ ሁለንተናዊ ለውጥ በፍጥነት ማምጣት ይፈልጋል። ህይወት በራሱ የማያቋርጥ ኡደት በመሆኑ ማንም ሰው ከዚህ ኡደት ውጪ ሊሆን አይችልም። ለዛም ነው የሰው ልጅ በዚህ በማያቋርጥ የህይወት ኡደት ውስጥ ሁሌም ቢሆን ራሱን ለፈጣን ለውጥ ዝግጁ የሚያደርገው። ራስን በፍጥነት መቀየር ሲባል ግን ሁሌም ቢሆን መነሻው ውድቀት፣ እጦት፣ ችግር፣ ዝቅ ማለት ….ወዘተረፈ ነው።
ለመሆኑ በህይወታችን ፈጣን ለውጥ እንዴት ማምጣት እንችላለን ? እንዴትስ በፍጥነት መቀየር እንችላለን ? አይታችሁ እንደሆነ ብዙዎቻችን ቶሎ መቀየር እንፈልጋለን። አቋራጭ መንገድ እንፈልጋለን። የማራቶን ሩጫ ማየት የሚፈልግ እኮ የለም። የመቶ ሜትር ርቀት ሩጫ ውድድርን ግን ሁሉም ሰው ያየዋል። ለምን? ቶሎ ፉት ይላታል። ማራቶን ሩጫ እኮ ያደክማል። ኢትዮጵያውያን ራሱ ሲሮጡ አስር ሺ ሜትር ሩጫ ቁጭ ብዬ ላይ ነው እንዴ እንላለን። ለምን? ፈጣን ነገር እንወዳለን። በአጭር ግዜ ሀብታም የሚሆኑበት ስራ ሲባል ጆራችንን ጣል እናደርጋለን። በቀላሉ ትዳር ማግኘት የሚፈልጉ ከሆነ በዚህ ስልክ ቁጥር ይደውሉ ሲባል አሀ ! ትዳር በዚህ መንገድ ይገኛል ለካ ብለን ጆራችንን እንሰጣለን።
ዛሬም ድረስ ሚሊየኖች በአጭሩ ለመክበር ሎተሪ ይቆርጣሉ። ነገር ግን ጥቂቶች ብቻ እጣ ደርሷቸው ይከብራሉ። አያችሁ እንግዴ እኛ ሰዎች በህይወታችን ውስጥ ፈጣን ለውጥ እንፈልጋለን። የአይምሮ ሀኪሞችና የማህበራዊ ሳይንስ አጥኚዎች ግን በፍጥነት ወይም ቶሎ መቀየር የሚፈልግ ሰው አንድ ነገር ያድርግ ይላሉ። ይኸውም ራሱን ይቀይር/ይለውጥ ነው። ስለዚህ አንተ ካልተቀየርክ ትዳርህ አይቀየርም። ኑሮህ አይቀየርም። ስራህና ትምህርትህ አይቀየርም። አንተ ስትቀየር ግን በዙሪያህ ያሉ ሰዎች አንተን ማክበር ይጀምራሉ። ምን አግኝቶ ተለወጠ ይላሉ። ከዛ በኋላ እድሎች ወደህይወትህ ይመጣሉ። ስለዚህ ሰው ሆይ ህይወትህን በፍጥነት መቀየር ትፈልጋለህ ? እንግዲያውስ የሚከተሉትን ስድስት ነጥቦች አስተውል
1ኛ.መወሰን
ወዳጄ በህይወትህ ፈጣን ለውጥ ማምጣት ከፈለክ መወሰን አለብህ። መድሀኒቱን ካልዋጥከው መዳን የሚባል ነገር የለም። ስለዚህ መወሰን አለብህ። አየህ አንዳንድ ግዜ ህይወትና እድል እንደባቡር ናቸው ካመለጡህ አታገኛቸውም። ስለዚህ ወስን፤ ቁረጥ። ቁጭ ብለህ አስብ። የሆነ ግዜ ላይ ቆራጥ ሆነህ የወሰንካቸው ውሳኔዎች የሰጡህ ደስታ አለ። የሰጡህ ስሜት አለ። አየህ አሁንም ከወሰንክ በኋላ ህይወትህን ስትቀይር የሚገጥምህን አስብ። ሰዎች መጥተው በጆሮህ ምን እንደሚሉህ አስብ። እንዴት እንደሚያደንቁህ ተመልከት። አንተ እኮ ጀግና ነህ ሲሉህ፤ እኔ አንተን ነው መሆን የምፈልገው ብለው ሲመኙ፤ አንቺ እኮ በጣም ጀግና ነሸ፤ ሲሉሽ አንቺ ራስሽን ስታደንቂ አስቢ፤ ስትለወጪ፤ በህይወትሽ ውስጥ የሚኖርሽን ነገር በአይምሮሽ ሳይው። ምን አይነት የተረጋጋ ህይወት እንደሚኖርሽ ፤ በምን አይነት መንገድ መንፈሳዊ ህይወትሽ፣ የገንዘብ ህይወትሽ፣ የስራ ህይወትሽ፣ ትምህርትሽ እንደሚቀየር አስቢ። ስእሉን በአይምሮሽ ሳይው።
አንተም ስሜቱን እስኪ በህይወትህ አጣጥመው። ምን አይነት እርካታ እንደሚኖርህ፤ ስትለወጥ፣ ህይወትህን ስትቀይር የሚኖርህ ደስታ፣ በቃ ከሰዎች እኮ አላንስም። እኔም ወጥቼ እገባለሁ። ሰርቼ አገኛለሁ። የምፈልገውን እየኖርኩ ነው ስትል አስብ። ይህንን ሁሉ ካሰብክ በኋላ ጥሩ ስሜት ውስጥ ከገባህ ወስን፤ ቁረጥ። ልክ ስትቆርጥ ህይወትህን መቀየር ትችላለህ።
2ኛ.ወደኋላ የሚጎትትህን ነገር እወቅ
አንዳንዴ አቅሙና ልምዱ ይኖርሃል። ዝግጁነቱም እንደዛው። እኔ እኮ ለምንም ነገር አላንስም ልትል ትችላለህ። ግን የጎተተህ፤ ያስቀረህ የሆነ እንከን አለ። የሆነ ጉድለት ይኖራል። ያ ጉድለት መዝምዞ ብዙ ነገር ያሳጣሀል። አንድ ሰው ራሱን ሲይዝ ራሴን አመመኝ ይላል። አንገቱን ሲይዝ አንገቴን አመመኝ ይላል። ዝቅ ብሎ ደሞ ልቤን አመመኝ ይላል። ለካ ሰውዬው ምኑንም አይደለም የታመመው። እጁን ነው የታመመው። አየህ አንተም የሆነች ትንሽዬ ጉድለትህ ብዙ ነገርህን እያጠፋችብህ ይሆናል። አንዳንዴ አብረሀቸው የምትውላቸው ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ ህይወትህን እያበላሹት። መበጠስ ያለበት ጓደኝነት ካለ መበጠስ አለበት። ያንተ ጠላት ስልክህ ሊሆን ይችላል። ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተጥደህ መዋልህ ሊሆን ይችላል ካለህበት፣ ከምትደርስበት ያስቀረህ፤ የጎተተህ፤ እንዳትለወጥ ያደረገህ። እንቅልፍ መውደድህ፣ ገንዘብ አጥፊ መሆንህ ይሆናል የጎተተህ። በስራህም ቢዝነስህም እንዳትቀየር ያደረገህ ውሎህም ከሆነ ቀይር። ከሚጠቅሙህ ጋር ዋል። አንድ አይነት ቀለም ያላቸው ወፎች አብረው ይበራሉ እንደሚባለው ራስህን ለመቀየር የሚጎትቱ ነገሮችን በሙሉ በጥሳቸው። ቁጭ ብለህ አስበው። ምንድን ነው ወደኋላ ያስቀረኝ በል። ያኔ ራስህን መቀየር ትጀምራለህ። ያውም በፍጥነት።
3ኛ. በህይወትህ መስለህ ሳይሆን ሆነህ ተውን
በህይወትህ ውስጥ አንዳንድ ግዜ መስለህ ሳይሆን ሆነህ የምትተውንባቸው ግዚያቶች አሉ። ለምሳሌ አንተ የምትፈልገውን ስኬት ቀድሞ ያሳካ ሰው አለ። አንተ መኖር የምትፈልግበት ቤት ውስጥ አሁን እየኖረ ያለ ሰው አለ። አንተ ህልሜ ነው የምትለውን ስራ አሁን እየሰራ ያለ ሰው አለ። አንተ ህልሜ ነው የምትለውን ገንዘብ እያንቀሳቀሰ ያለ ሰው አለ። አንተ ፍላጎቴ ነው የምትለውን መኪና እየነዳ ያለ ሰው አለ። ያ ሰው ምን አድርጎ ነው እዛ የደረሰው ? እሱን ሰውዬ ሁነው። በቃ ኮርጀው። እንዴት ነው የሚያስበው ? እንዴት ነው የሚወስነው ? እንዴት ነው የሚለብሰው ? እንዴት ነው የሚራመደው? እንዴት ነው ቀኑን፣ ግዜውን የሚያሳልፈው? እንዴትስ ነው ገንዘቡን የሚያጠፋው የሚለውን ለማወቅ እሱን ሰው መሆን አለብህ። የምትፈልገውን አታገኝም። የሆንከውን ነው የምታገኘው። መምሰል አለብህ። በህይወትህ መተወን መቻል አለብህ።
በዓለም ላይ አንድ የተከበረ ሼፍ ፒዛ እንዴት እንደሚበስል መረጃ ቢሰጥህና አንተ ቤትህ ገብተህ እያንዳንዱን ነገር አሟልተህ ፒዛውን ብትሰራ ከሼፉ እኩል አሪፍ ፒዛ አልሰራህም? ሰርተሀል። አሁንም ቢሆን በህይወትህ ባለሞያ መሆን ከፈለክ አንተን የቀደመህ ሰው ሊኖር ይችላልና እርሱን ምሰለው። ራሱን ሁነው። ህይወትህን ትቀይራለህ። ከየት አግኝቼ ልንኮርጅ ? ያንን ሰው ከየት ላገኘው እችላለሁ ? ልትል ትችላለህ። ዝምብለህ ፊልም እይ። መፅሀፍ አንብብ። ስለምታደንቀው ሰው የተሰራ ዘጋቢ ፊልም ተመልከት። የእርሱን ቃለምልልስ ተመልከት። በምን አይነት መልኩ በህይወቱ ውሳኔዎችን እንዳሳለፈ፣ ምን እንደሚያስደስተው፣ ምን ሰርቶ እዛ እንደደረሰ እይ፤ ኮርጅ። ለመኮረጅ ቀላል ምክንያት ነው ካንተ የሚጠበቀው። እርሱም ራስህን ማዘጋጀት ነው።
4ኛ. እምነትህ ላይ ጠንክር
በፍጥነት ህይወትህን መቀየር ከፈለክ እምንተህ ላይ ጠንክር። ዓለምን የቀየሩ ሰዎች በሙሉ አማኞች ናቸው። በሁሉም ዘርፍ ስኬታማ የሆኑ ሰዎች አማኞች ናቸው። አንተም አማኝ መሆን አለብህ። ካላመንክማ እንዴት ትቀየራለህ። እንደምትለወጥ እርግጠኛ መሆን አለብህ። እኔ እርግጠኛ ነኝ እለወጣለሁ፤ አምናለሁ እንድትል አማኝ መሆን አለብህ። እምነት ደግሞ የሚገርምህ እንደቫይረስ ነው ይጋባል። የሚሰርቅ ነገር ነው። ታዲያ ምን ይሻልሃል ? መፅሀፍ ቅዱስ ወይም ቁርዐን በየቀኑ አንብብ። ክርስቲያን ከሆንክ ቢያንስ አንድ ምዕራፍ ከመፅሐፍ ቅዱስ ሙስሊም ከሆንክ ደግሞ አንድ ሱራ ከቁርዐን አንብብ። ለምን መሰለህ ባነበብክ ቁጥር በስነልቦናህ በመፅሀፍ ቅዱስ አልያም ደግሞ በቁርዐን ውስጥ ካሉት ጋር ትውላለህ። በዚህም ለካ መለውጥ ይቻላል ትላለህ። በህይወትህም እርግጠኛ ትሆናለህ። አማኝ ከሆንክ በፍጥነት ራስህን ትቀይራለህ። እምነትህ ጠንካራ ከሆነ ህይወት በጣም ቀላል ትሆናለች።
5ኛ.ለራሴ ያለሁት እኔ ነኝ በል
አንተ ካልተቀየርክ ማንም አይቀየርም። ሰበበኛውን ቅበረው። ፈጣን ለውጥ አይደል የምትፈልገው ? ሰበብ የሚሰጥህን ውስጥህ ያለውን መጥፎ ድምፅ አቁመው። አንተ እኮ ደሀ ሀገር ነው የተወለድከው። እንዴት ራስህን ትቀይራለህ። የሚረዳህ የለም። እውቀት የለህም። ገንዘብም የለህም። ልምድም ቢሆን የለህም። እንዴት አድርገህ ራስህን ትቀይራለህ የሚለውን ሰበበኛ እንዳታዳምጠው። ድፈረው፤ በቃ እኔ እቀይራለሁ። ለራሴ ያለሁት እኔ ነኝ። ማንም አይደለም ህይወቴን የሚቀይረው። ለራሴ እራሴ ኃላፊነት እወስዳለሁ። መቶ ከመቶ ራሴ ነው የምቀይረው። ለራሴ ያለሁት እኔ ነኝ። ማለት ጀምር። ትጠነክራለህ። ህይወትህ መቀየር ይጀምራል።
አይተህ ከሆነ ስትጠነክር ሁሉም ሰው ይፈልግሀል። እሱ እኮ ጎበዝ ነው። ጠንካራ ነው። ዓላማ አለው። ይሰራል። ይበረታል ይሉሀል። መንግስት እንኳን የሚያበድረው ለሚሰሩ ስዎች አይደል። ዝምብሎ ቢያበድርህማ ትጠፋለህ እኮ። የት ያምንሀል። የት የሰራኸውን፤ ምን ሰርተህ ታውቃለህ ከዚህ በፊት ይልሀል። ስለዚህ አያበድርህም። የምታሲዘው ነገር ያስፈልግሃል። አየህ ስትጠነክር ማንም ካንተ ጋር ያሽቃብጣል። ለራሴ ያለሁት እኔ ነኝ በል። ህይወትህን በፍጥነት ትቀይራለህ።
6ኛ. ምክንያታዊ ሁን
ለምሳሌ አንድ ሰው ደውሎልህ መቶ ሺ ብር እንድትሰጠኝ ፈልጌ ነው። በዚህ የባንክ አካውንት አስገባልኝ ቢልህ ይሄ ልጅ እንዴት ደልቶታል ይቀልዳል እንዴ ትላለህ። ግን ይወልህ አሁኑኑ መቶ ሺ ብር ካላስገባህ ቤተሰቦችህን አሁኑኑ ነው እዚሁ የምረሽናቸው ብትባል ትደነግጣለህ። መቶ ሺ ብሩን ከየትም ብለህ ታመጣዋለህ። ሌላ ግዜ መቶ ሺ ብር ስትባል የምትደነግጠው ሰው ቤተሰቦችህ ሊያልቁ ነው ስትባል ከየትም ታመጣዋለህ። አየህ በህይወትህ ውስጥ ምክንያት ነው ያጣኸው እንጂ አቅም አንሶህ አይደለም። ጉልበት አጥተህ አይደለም። ስለዚህ ምክንያት ያስፈልግሃል።
በነገራችን ላይ ህልም ሲኖርህ፤ ዓላማ ሲኖርህ አንተ ትቀየራለህ። ያንን ነገር ለማሳካት ስትል ትሰለፋለህ፤ ትለወጣለህ ሙሉ አቅምህን አንጠፍጥፈህ ትጠቀማለህ። ስለዚህ ምክንያት ያስፈልግሃል ማለት ነው። ፈጣን ለውጥ ማለት ነው። አንዳንድ ሰዎች ምን ይላሉ እኔ እኮ የምሰራው እንዲሁ ስሜ ሲጠራ እንዳይብጠለጠል ነው። ቢያንስ ባለሀብት እገሌ ብባል ጥሩ ነው ይላሉ። በጣም ጥሩ ነው። ዶክተር እከሌ ለመባል ነው የምማረው የሚልም ሰው አለ። ይህም በጣም ጥሩ ነው። ምክንያትህ ብቻ ምንም ይሁን የኔ ፍላጎት ትልቁ አስመጪና ላኪ መሆን ነው፤ ትልቁን ሆስፒታል፣ ትልቁን ሆቴል፣ ትልቁን ፀጉር ቤት መገንባት ነው ልትል ትችላለህ። ምክንያትህ ከሆነ ይህ በጣም ጥሩ ነው። እንድትሮጥ የሚያደርግህ ከሆነ ህይወትህን ትቀይራለህ።
አንድ ሰው ባንክ ቤት የሚቆጥሩባትን ማሽን ገዝቶ እቤቱ ያስቀምጣል። ሁል ግዜ ድምጿን ተረረረ ሲል ይሰማታል። እናም ይህ ማሽን እኮ የሚቆጥረው ገንዘብ ያስፈልገዋል። እርቦታል ይልና ፈጥኖና ወጥሮ ይሰራል። ራሱን ይቀይራል። ገንዘብ ያመጣና በማሽኑ ሲቆጥረው ያድራል። ከዛ ሁሌ ማሽኑን ይሰማዋል፤ ገንዘብ ያስፈልገኛል ይላል ይበረታል። በነገራችን ላይ ምክንያታችን ምንም ቢሆን ችግር የለውም። ነገር ግን ሰው ላይ ምቀኛ ሆነን፤ አሉታዊ አሳቢ ሆነን፣ መጥፎ አስበን ሰዎችን ጠልፈን ጥለን አይሁን ብቻ፤ ትልቁን ፎቅ የምትሰራው በሁለት መንገድ ነው። የመጀመሪያው ያሉትን ፎቆች ሁሉ ትደመስስና ያንተን ጂ ፕላስ ስሪ ረጅሙ ፎቅ ታስብላለህ። ሁለተኛው መንገድ ደግሞ በራስህ ጠንክረህ ረጅሙን ፎቅ ትሰራለህ። አየህ ምክንያት ሲኖርህ የኔ ረጅሙ ፎቅ ነው፤ እኔ ትልቅ ቦታ እደርሳለሁ ካልክ የሌላው አያገባህም። ለራስህ ትበረታለህ፤ ትጠነክራለህ። ምክንያት ያስፈልግሃል ወዳጄ።
ብዙውን ግዜ ለውጥ ሲጀምር በጣም ፈጣን ሊሆን ይችላል። አይተህ ከሆነ ስፖርት ስትጀምር እንዴት ጥሩ ስሜት ተሰማኝ ልትል ትችላለህ። አስራ አንድ ሰዓት በጥዋት የተነሳህ ሰሞን በጣም ደስ ይላል እኮ አንተ ትላለህ። ስትደጋግመው ግን ያ ስሜት ስለሚደጋገም ብዙም አታስተውሉም። ለውጡ አይታይህም። እናም ወዳጄ በፍጥነት ራስህን መቀየር ከፈለክ ምክንያታዊ ሁን።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2015